Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊ‹‹በአረጋውያን ላይ የሚደርሰው ችግር አስከፊ ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው››

‹‹በአረጋውያን ላይ የሚደርሰው ችግር አስከፊ ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው››

ቀን:

ዶ/ር ፈለቀ ታደለ፣ የኸልፕኤጅ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ፕሮግራም ተጠሪ

ከኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል 4.8 ሚሊዮን ያህሉ አረጋውያን ሲሆኑ፣ ከእነዚህ ውስጥ የጡረታ ዋስትና የሚያገኙት ከ700 ሺሕ አይበልጡም፡፡ አማካይ ገቢያቸውም በወር 555 ብር በመሆኑ ከተለያዩ ተጨማሪ አገልግሎቶች ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረግ መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን የኸልፕኤጅ ኢንተርናሽናል የኢትዮጵያ ፕሮግራም ተጠሪ ዶ/ር ፈለቀ ታደለ ይናገራሉ፡፡

ከሪፖርተር ጋር ቆይታ ባደረጉት ዶ/ር ፈለቀ ገለጻ፣ የጡረታ ባለመብት ከሆኑት ከእነዚሁ አረጋውያን በስተቀር የቀሩት አረጋውያን የጡረታ ዋስትና የላቸውም፡፡ ይህም በመሆኑ በዘመዶቻቸውና በቤተሰቦቻቸው ድጋፍ እንዲሁም በየዕምነት ተቋማቱ አጥር ሥር ተጠልለው በምፅዋት ይኖራሉ፡፡

‹‹በአረጋውያን ላይ የሚደርሰው ችግር አስከፊ ደረጃ ላይ እየደረሰ ነው፤›› በሚሉት ዶ/ር ፈለቀ አነጋገር፣ በብሔራዊ የማኅበራዊ ደኅንነት ፖሊሲ መሠረት የከተማና የገጠር የማኅበራዊ ልማት ሽፋን ተግባራዊ ከሆነ አረጋውያኑ ቢያንስ ከድህነት ወለል በታች እንዳይኖሩ ለማድረግ የሚያስችል ድጎማ ይኖራል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህም ቢሆን ለችግሩ አፋጣኝ መፍትሔ ያስፈልጋል፡፡

ዶ/ር ፈለቀ እንደሚሉት፣ አረጋውያን በመሆናቸውና ገቢያቸውም አነስተኛ በመሆኑ ብቻ በመንግሥት ሕክምና ተቋማት በነፃ የሕክምና አገልግሎት እንዲያገኙ የተደረገ ቢሆንም የሕፃናት ሐኪም እንዳለ ሁሉ በአረጋውያን ሕይወት ላይ ያተኮረና ለጤንነታቸው ጉድለት ምላሽ ሊሰጥ የሚችል በቂ የሕክምና ባለሙያ ያስፈልጋል፡፡

ዶ/ር ፈለቀ ድርጅታቸው ከሁለት ዓመት በፊት በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ በአማራ፣ በኦሮሚያና በትግራይ ክልሎች እንዲሁም በአዲስ አበባ ያካሄደውን ጥናት ዋቢ አድርገው እንዳመለከቱት፣ አረጋውያኑ ሐኪም ቤቱን በነፃ ያገኙ እንጂ በሆስፒታሉ ለማይገኙ የላቦራቶሪ ምርመራዎች የሚጠየቁትና ከውጭ እንዲገዙ የሚደረገው መድኃኒት ከአቅማቸው በላይ ነው፡፡ በዚህም የተነሳ ብዙዎቹ ወደ ፀበል ወይም ወደ ባህል ሕክምና ይሄዳሉ፡፡

ከዚህ አንፃር ለአረጋውያን በአዋጁና በፖሊሲው መሠረት የጤና ዋስትና የሚያገኙበት ሁኔታ ሊመቻችላቸው፣ የሕክምና ምርመራ፣ የመድኃኒትና ሌሎች ተጓዳኝ ወጪዎቻቸው ሊሸፈንላቸው ይገባል የሚሉት ዶክተሩ፣ በጥናቱ ከተካተቱ ናሙናዎች ውስጥ 30 ከመቶ ያህሉ ቢያንስ አንድ ተላላፊ ያልሆነ በሽታ እንዳለባቸው ከእነዚህም የዓይን፣ የመተንፈሻ አካል፣ የልብ ሕመም በዋነኛነት እንደሚጠቀሱ ገልጸዋል፡፡

በዚህ በኩል አገሪቱ በራዕይ ሃያ፣ ሃያ ፕሮግራም አይነስውርነትን ለመቀነስ ጥረት እያደረገች ነው፡፡

የአረጋውያን መብቶችን ለማስከበር በማኅበር ተደራጅተው መንቀሳቀስ ከጀመሩ 16 ዓመት ሆኗቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ የራሳቸው ገቢ ስለሌላቸው እንቅስቃሴያቸው ተጓትቷል፡፡ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶችም (መያድ) ዕርዳታ አሰባስበው ተገቢውን እገዛና ድጋፍ ሊያደርጉላቸው አይችሉም፡፡ ይህም ሊሆን የቻለው መንግሥት ለመያዶች የአስተዳደር ወጪን ለመወሰን ያወጣው የአሠራር ደንብ ስለሚያግዳቸው ነው፡፡

የአፍሪካ ኅብረት የአህጉሩን አረጋውያን መብት ለማስከበር የሚያስችል ፕሮቶኮል እያረቀቀ ሲሆን፣ በአገራችን ደግሞ የማድሪድ የድርጊት ፕሮግራም ተግባራዊ እየሆነ ነው፡፡ ይህንንም ለመተግበር 24 የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች እየተንቀሳቀሱ ቢሆንም ከእነዚህ መካከል ብዙዎቹ መሥሪያ ቤቶች ሪፖርት የማይጠየቁበትና ተጠያቂነታቸውም እየላላ ያለበት ሁኔታ መኖሩንም ተናግረዋል፡፡

ትራንስፖርት ሚኒስቴር የአረጋውያንን ከመደገፍ አኳያ በመንግሥት የከተማ አውቶቡስ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው ምን ዕርምጃ ወስዷል? ምንስ ማስፈጸሚያና ማስገደጃ ዘዴ አለው? አሁን ደግሞ ከቀላል ባቡር ጋር በተያያዘ ምን ዝግጅት አድርጓል? የሚሉት ሲዳስሱ ምንም ዓይነት ዕርምጃ እንዳልተወሰደ ይታያል፡፡

በኮንስትራክሽን ሚኒስቴር በኩልም የከተማ ፕላን ሲወጣና ሕንፃዎች ሲገነቡ ለአረጋውያንና ለአካል ጉዳተኞች የተመቸ ነው ተብሎ ይዘጋጃል ወይስ? የሚለውም ጉዳይ ምላሽ ይሻል፡፡

በሌሎች አገሮች አረጋውያን ቤት፣ ትራንስፖርትና ሌሎች አገልግሎቶችን  በቅድሚያ የማግኘት መብተ አላቸው፡፡ ጎረቤቶቻቸውን ለማየት ወደ ሁለተኛ፣ ሦስተኛ፣ አራተኛና ከዚያም ከፍ ወደሚል ፎቅ የሚሄዱበት ሁኔታ የተመቻቸ ነው፡፡ ለአገራችን አረጋውያንና አካል ጉዳተኞች ግን ይህ ዓይነቱ ሁኔታ አለ ለማለት አይቻልም፡፡ ለወደፊት በሚሠሩት የጋራ መኖሪያ ቤቶች ላይ ግን ይህ ጉዳይ ትኩረት ሊቸረው ይገባል፡፡

በኮከብ ደረጃ የሚገኙ ትላልቅ ሆቴሎችም የስብሰባ ማዕከሎቻቸውና አገልግሎቶቻቸው ለአረጋውያንና ለአካል ጉዳተኞች ተደራሽ ሆነው አይታዩም፡፡ አረጋውያን ለወጣቱ ትውልድ ጥሩ ባህልንና በዕድሜ ዘመናቸው ያካበቱትን ልምድና ተሞክሮ ሊያስተላልፉባቸው የሚችሉ መድረኮችን የሚያመቻች፣ እንዲሁም ዕድሜ ጠገብ ለሆኑና ብዙ ለሠሩ አረጋውያን ሽልማትና አድናቆት ለመስጠት የሚያስችሉ ሁኔታዎችን የሚያቀናጁ ተቋሞች በብዛት አለመኖርም እንደ ችግር የሚታይ ነው፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ አረጋውያንን በተመለከተ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርት ውስጥ ያካተተውን የአፍሪካ አረጋውያን ገጽታ ለመመርመር፣ አዲስ አበባ ውስጥ በተካሄደው ምክክር ከተገኙት አንዱ አምባሳደር ኦላዋሊ ሚያጉን የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የማኅበራዊ ጉዳይ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ አነጋገር፣ የአፍሪካ አረጋውያንን መብት በማስከበር ረገድ የጎላ ሚና ይጫወታል ተብሎ የታመነበት ፕሮቶኮል የማርቀቁ ሥራ ወደ መጠናቀቁ ተቃርቧል፡፡ የፊታችን ታኅሣሥ አዲስ አበባ ላይ በሚካሄደው ስብሰባ ረቂቁ ቀርቦ ከተገመገመና በስብሰባው ተቀባይነት ከተቸረው የሚፀድቅ ይሆናል፡፡

ረቂቁ ሊጠበቁና ሊከበሩ የሚገባቸው በርካታ የአረጋውያን መብቶችን አካትቷል፡፡ ከእነዚህም መካከል የጡረታ አበል፣ የጤና፣ የማኅበራዊ ዋስትና፣ ከጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች የመጠበቅ መብቶች የመሳሰሉና ሌሎችም እንደሚገኙበት አምባሳደሩ ተናግረዋል፡፡

ኸልፕኤጅ ኢንተርናሽናል ባዘጋጀው ሪፖርት፣ የአፍሪካ አገሮች አረጋውያን እንቅስቃሴ ተካትቷል፡፡ የኢትዮጵያ እንቅስቃሴ በሪፖርቱ ውስጥ ባይካተትም መንግሥት ለአረጋውያኑ አቅም በፈቀደ መጠን የሚያደርገው ድጋፍና እገዛ አበረታች መሆኑን ዶ/ር ፕራፉላ ሚሸራ የኸልፕኤጅ ኢንተርናሽናል የምሥራቅ፣ የምዕራብና የመካከለኛው አፍሪካ ሬጂን ዳይሬክተር ተናግረዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት በራዲሰን ብሉ ሆቴል የስብሰባ አዳራሽ በተከናወነው ውይይት ላይ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሹማምንትና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...