አቶ ሰለሞን አፈወርቅ፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት
የአገሪቱን የግል ዘርፍ የሚወክሉ የከተማ፣ የክልልና የአገር አቀፍ የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች አለመጠናከራቸው በተደጋጋሚ ይነገራል፡፡ በተለይ የንግድ ምክር ቤቶችን እንደ አዲስ ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 341/95 ተግባራዊ ከተደረገ በኋላ፣ የበለጠ ድክመት እየታየባቸው መሆኑ በተደጋጋሚ ተገልጿል፡፡ በአዲሱ አዋጅ አደረጃጀት መሠረት ንግድ ለብቻ ዘርፍ ለብቻ የሚለው አደረጃጀት ራሱ ችግር ፈጥሯል መባሉም አዲስ ነገር አይደለም፡፡ አሁንም ይህ የአደረጃጀት ጉዳይ ለንግድ ምክር ቤቶች ጥንካሬ ማጣት ሰበብ ሆኖ ይቀርባል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ዳዊት ታዬ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅን አነጋግሯል፡፡
ሪፖርተር፡- የግሉ ዘርፍና የመንግሥት ግንኙነት ምን ደረጃ ላይ ይገኛል? እንዴትስ ይመዘናል?
አቶ ሰለሞን፡- የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ ግንኙነት ጥሩ ደረጃ ላይ ነው ማለት ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- ጥሩ ነው ሲባል እንዴት? መገለጫው ምንድነው?
አቶ ሰለሞን፡- ከመገለጫዎቹ አንዱ የግል ዘርፉ መደመጥ መቻሉ ነው፡፡ የእሪታውን ስሜት ማስቀረት ተችሏል፡፡ አንዱ በሌላው ላይ ይታይ የነበረውን መገፋፋት አስቀርቶ መንግሥትም ከግሉ ዘርፍ የሚቀርቡለትን ጥቆማዎች እየተቀበለ ነው፡፡ ማድመጥ ጀምሯል፡፡ እኛም የግሉ ዘርፍ የሚያጋጥሙትን ችግሮች አስጠንተን እያቀረብን መነጋገር ችለናል፡፡ እኛ የተነገረውን መረጃ ሁሉ ይዘን አይደለም የምንቀርበው፡፡ የግል ዘርፉ ዘንድ ምን ችግር አለ? መንግሥትስ ጋ ምን ችግር አለ? ብለን ነው የምናየው፡፡ የሚከሰቱትን ነገሮች ሁሉ ወደ አንዱ የምትጥለው አይደለም፡፡ በአሁኑ ወቅት በንግድ ምክር ቤቱ ውስጥ ያለውንና ካለመጠንከር ጋር የሚፈጠሩ ነገሮችንም ማየት ተችሏል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ ራሱን ወደ ውስጥ ማየት ጀምሯል፡፡ ነጋዴው ራሱን ወደ ውስጥ ማየት ችሏል፡፡ መንግሥትም ራሱን መፈተሽ ችሏል፡፡ ማድመጥና መደማመጥ በመፈጠሩ ግንኙነቱ ጥሩ እንደሆነ ያሳያል፡፡
ሪፖርተር፡- በዚህን ያህል ደረጃ የሚገለጽ መቀራረብና መደማመጥ መጥቷል ከተባለ፣ የንግድ ኅብረተሰቡ አሉብኝ ያላቸውን ችግሮች መፍታት ተችሏል ብለው ያምናሉ? የንግድ ኅብረተሰቡ አሁንም ችግሮች አሉብኝ እያለ ነው እኮ?
አቶ ሰለሞን፡- ችግሮቻቻን አይፈቱም፡፡ እስከ መጨረሻው ይፈታሉ ተብሎ አይጠበቅም፡፡ የግል ዘርፉ እያደገ በሄደ ቁጥር ያደገ ችግር ይመጣል፡፡ በአንድ ወቅት የተከሰተ ችግር ሊፈታ ይችል ይሆናል፡፡ በየዘመኑ ከሚመጣው ዕድገት ጋር ተያይዘው የሚመጡ ችግሮች በዚያው ዘመን የሚፈቱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በአሁኑ ወቅት መንግሥት ወደ ማኑፋክቸሪንግ ግቡ እያለና ይህም እንዲተገበር እያሳሰበ ነው፡፡ ወዲህ እንዴት እንገባለን የሚለው ጉዳይም እንደ ችግር ይታያል፡፡ ከዚህ ቀደም ግን ችግሩ ከታክስ ጋር የተያያዘ ነበር፡፡
አሁን ግን ወደ ማኑፋክቸሪንግ ግቡ ከሚለው ጋር መያያዙ በራሱ ለውጥ መምጣቱን ያሳያል፡፡ ለኢንቨስትመንት ማነቆ የሆነባችሁን ጉዳይ አጋልጡ፡፡ ግብራችሁን በሰዓቱ ክፈሉ የሚል ነው፡፡ አሁን እኮ ግብር በሰዓቱ መከፈል ተጀምሯል፡፡ መዝገብ ያዙ መባል ተጀመረ፡፡ መዝገብ ሲይዝ ደግሞ ይህንን አልቀበልም የሚል ነገር መጣ፡፡ የለም መቀበል አለብህ መባባል ተጀመረ፡፡ ስለዚህ እንዲህ እንዲህ ያሉ በየደረጃው የሚመጡ ችግሮችን እየፈታን ነው የምንሄደው፡፡ ለዚህ ነው ሁለቱም አካላት እስካሉ ድረስ ችግሮች አያልቁም የምንለው፡፡ ነገም ያልተጠበቀ ነገር ሊፈጠር እንደሚችል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ የሚመሩት ብሔራዊ ንግድ ምክር ቤትም ሆነ ሌሎች የክልልና የዘርፍ ምክር ቤቶች አቅም አናሳ መሆኑ ይነገራል፡፡ ዕድገት የማይታይባቸው ተቋማት ናቸው የሚልም እምነት አለ፡፡ ማደግ በሚገባቸው ደረጃ አላደጉም ይባላል፡፡ እርስዎ አድገዋል ይላሉ?
አቶ ሰለሞን፡- አላደጉም፡፡ ላለማደጋቸው የተለያዩ ምክንያቶች አሉ፡፡ በሚፈለገው ደረጃ ላለማደጋቸው አንዱ ምክንያት ከአደረጃጀት ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ከአሥር ዓመት በፊት የግል ዘርፍ በነበረበት ደረጃ የታሰበ አደረጃጀት ነው ያለው፡፡ ይህንን ጉዳይ መንግሥት ሊያስብበት ይገባል፡፡ አሁን ያለው የግል ዘርፍ ከአሥር ዓመት በፊት ከነበረበት ደረጃ በተለየ ነው፡፡ በንግድ ምክር ቤቶቹ ውስጥ ብዙዎቹ የግሉ ዘርፍ አካላት አልታቀፉም፡፡ ያልታቀፉበት ምክንያት ንግድ ምክር ቤት ጥርስ የለውም በሚል ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ አደረጃጀቱ ችግር ያለበት በመሆኑ ምክንያት አቅም ሊፈጥር ባለመቻሉ ደካማ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ ይህንን ለመለወጥ የተለየ አደረጃጀት ያስፈልገዋል፡፡ የተለየ አደረጃጀት ኖሮት እንዲሠራ ማድረግ ይገባል፡፡ ወደ ማኑፋክቸሪንግ እንዲገባ ተቋሙ ሥልጠና መስጠት፣ ማሳየት የሚችልበት አቅም ሊኖረው ይገባል፡፡ ሁልጊዜ ለሙግት የተዘጋጀ ተቋም መሆን የለበትም፡፤ መፍትሔ ሰጪ ተቋም መሆን አለበት፡፡ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል አደረጃጀት መኖር አለበትው እያልን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ቀደም ብለው እንዳነሱልኝ ንግድ ምክር ቤቶች ደካማ ናቸው ሲባል የአደረጃጀት ጉዳይን እንደ ምክንያት ታቀርባላችሁ፡፡ አደረጃጀትን በተመለከተ የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ያለበት ችግር ምንድነው?
አቶ ሰለሞን፡- ለምሳሌ በአንድ ከተማ ብዙ ማኅበራት አሉ፡፡ ዘርፍ ለብቻ፣ ንግድ ለብቻ ይደራጃሉ፡፡ እንደገና ሁለቱ አንድ ላይ እንዲደራጁ ይደረጋል፡፡ ይህ ትልቅ ችግር ነው፡፡ እንደገና ደግሞ አባልነት በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህ ብዙ አባላትን እንዳታፈራ ያደርጋል፡፡ መንግሥት ይህንን ሥሩና ለእኛ ይህንን አድርጉልን ብሎ ለይቶ የሰጠን ሥራም የለም፡፡
ሪፖርተር፡- ከመንግሥት ምን ዓይነት ሥራ እንዲያከናውን ይጠበቅበት ነበር?
አቶ ሰለሞን፡- ለምሳሌ የንግድ ፈቃድ ማደስ ሥራን ልጠቅስ እችላለሁ፡፡ በተለያዩ አገሮች የንግድ ፈቃድ ማደስና ከዚያ የሚገኘውን ገቢ የሚጠቀሙት የንግድ ምክር ቤቶች ናቸው፡፡ የሌሎች አገሮች ንግድ ምክር ቤቶች ከመንግሥት የተለያዩ ድጎማዎችም ያገኛሉ፡፡ እነዚህ በሌሉበት ሁኔታ ጠንክሮ ለመውጣት ከባድ ነው፡፡ አባል ለመሆን የሚፈልግ የትኛው ውስጥ መሳተፍ እንዳለበት እንኳን የማያውቅ ብዙ አለ፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በንግድ ኅብረተሰቡ ላይ ጫና አሳደረ የተባለ ችግር ከመንግሥት ጋር ተደራድሮ እንዲፈታ ሲደረግ፣ የተፈታው ችግር የሚጠቅመው አባል ሆኖ የአባልነት መዋጮ የከፈለውንም ያልከፈለውንም ነው፡፡ በዚህ ምክንያት አባልም ባይሆን ችግሩ ስለሚፈታለት ተሳትፎው እምብዛም ስለሚሆን የአባልነት ቁጥሩ ያንሳል፡፡ ስለዚህም ችግሩ መደገፍ አለበት፡፡ አደረጃጀቱም መለወጥ አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- በሥራ ላይ ያለው የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅና አደረጃጀቱ እያሠራ አይደለም ከተባለ፣ ይህንን ችግር ለመቅረፍ እናንተ ምን እያደረጋችሁ ነው?
አቶ ሰለሞን፡- አዋጁና በአዋጁ ውስጥ ያሉት የአደረጃጀት አንቀጾች እንዲለወጡ አሳውቀን ለመንግሥት አቅርበናል፡፡ ለንግድ ሚኒስቴርና ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ሳይቀር አቅርበናል፡፡ ለፕሬዚዳንቱና ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ችግሩን አስረድተናል፡፡ እየጮህን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- ይህንን ጥናትና ጥያቄ ካቀረባችሁ ከሦስትና ከአራት ዓመታት በላይ ሆኖታል፡፡ እስካሁን ምላሽ አላገኛችሁም? ለምን?
አቶ ሰለሞን፡- በሒደት የሚሆነው ከሚመለከተው አካል ጋር እንዲመከርበት ነው፡፡ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩም ያሉት ከሚመለከተው አካል ጋር ሁናችሁ አጥንታችሁ ለሚመለከተው አካል ይቅረብ የሚል ነው፡፡ ይህንን ግን ማብሰል አለብን፡፡ በጥሬው ማቅረብ ሳይሆን ሦስት አራት ጊዜ አዋጅ ቀይሩ ከምንል አንድ ጊዜ መሠረት የያዘ አዋጅ እንዲሆን እየሠራን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በመጀመሪያው የዕቅድ ዘመን እንደታየውና መንግሥትም እንደገለጸው፣ የግሉ ዘርፍ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲገባ ለማድረግ የተደረገው ሙከራ የተፈለገውን ያህል አልሰመረም፡፡ በንግድ ምክር ቤታችሁ የግል ዘርፉ ወደዚህ እንዲገባ ምን ሠርታችኋል?
አቶ ሰለሞን፡- እሱን ነው እየሠራልን ያለው፡፡
ሪፖርተር፡- እስካሁንስ ምን ሠርታችኋል? ተጨባጭ ምሳሌ አለዎት?
አቶ ሰለሞን፡- እስካሁን እኮ መንግሥት ምንም አላደረገም፡፡ እኛ ብቻ ሳንሆን መንግሥትም ብዙም ያደረገው ነገር የለም፡፡ ብዙ አድርጎ ቢሆን ኖሮ ብዙ ለውጥ ይመጣል፡፡ ስለዚህ ንግግራችንን ወደ መሬት ማውረድ አለብን፡፡ ለምሳሌ አሁን እየፈጠራቸው ያሉትን የኢንዱስትሪ ዞኖች የግል ዘርፉ እንዲያውቃቸው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ እኛም የግል ዘርፉ እዚህ ውስጥ ገብቶ እንዲሠራ ማድረግ የሚገባንን ሁሉ ማድረግ አለብን፡፡ በሚገባ ማሳወቅ ይጠይቃል፡፡ አትራፊ እንደሆነና ጠቃሚነቱንም በሚገባ ማስገንዘብ አለብን፡፡ ነገር ግን አንዳንዴ ዘርፉ ምን ያህል አትራፊ መሆኑን ለማወቅ እንኳን ተቸግሯል፡፡
ሪፖርተር፡- ለንግድ ምክር ቤቶች ጠንካራ ሆኖ አለመገኘት የሚቀርበው ምክንያት ከንግድ ምክር ቤቶች መመሥረቻ አዋጅ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ደጋግማችሁ የአደረጃጀት ችግር አለብን እያላችሁ ነውና እንደ ምሳሌ የሚቀርቡ ዋና ዋና ችግሮች የትኞቹ ናቸው?
አቶ ሰለሞን፡- አባልነት በፈቃደኝነት መሆኑም ሊጠቀስ የሚችል ችግር ነው፡፡ ለመሰባሰብ ትንሽ አስቸጋሪ ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ይህም የአባላት ቁጥር በተፈለገው ደረጃ እንዳያድግ አድርጓል፡፡ በአንድ ማኅበር ውስጥ የሚሰባሰቡት ሰዎች ጥቂት ስለሆኑ ከእነርሱ የሚገኘው አስተዋጽኦ ምክር ቤቱን ከፍ ወዳለ ደረጃ ለመውሰድ አላስቻለውም፡፡ ኅብረተሰቡ በማኅበር ተደራጅቶ የራሱን መብት የማስከበር ልምድ ያለመኖር ችግርም አለ፡፡ ቀደም ሲል በደርግ ጊዜ የነበረው አደረጃጀት ለመንግሥት አገልግሎት ለመስጠት እንዲመች ከመደረጉ ውጪ ለግል ዘርፉ የተሠራ ሥራ ባለመኖሩና ይህንን ልምድ ለማጥፋት ያለመቻል ሁኔታዎች አሉ፡፡ አሁንም ያለው ቻምበር ምን ይጠቅማል የሚል ነገር መፍጠሩም እንደ ችግር የሚታይ ነው፡፡ እንዲህ ያሉትን ነገሮች ለመለወጥ ብዙ መሠራት አለበት፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ የአቅም ውስንነት አለ፡፡ ምክንያቱም አባላት በብዛት ስለሌሉን ሀብት የለንም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ እንዲህ እንዲህ ያሉ ነገሮች ስላሉ ነው አደረጃጀቱ ለየት ያለ መልክ ሊኖረው ይገባል የምንለው፡፡ በዚህ አዋጅ አደረጃጀቱ ወረዳ ላይ፣ ከተማ ላይ፣ ክልል ላይ እያለ ሁሉ አለ፡፡ እንደገና በወረዳም በክልልም ንግድ ለብቻ፣ ዘርፍ ለብቻ ሆኖ እንዲደራጅ ይደረጋል፡፡ ይህ ነገሮችን አወሳስቧል፡፡
ሪፖርተር፡- በሐሙሱ [መስከረም 6 ቀን 2008 ዓ.ም.] በጠቅላላ ጉባዔያችሁ ላይም ከአባል ምክር ቤቶቻችሁ ሳይቀር ንግድ ምክር ቤቱ ጠንካራ ሊሆን አልቻለም የሚል ሐሳብ ተሰንዝሯል፡፡ እየሠራ አይደለም የሚሉ አስተያየቶች ጭምር ቀርበው ነበር፡፡ እንዲህ ያሉትን አስተያየቶች እንዴት ይገነዘቡዋቸዋል?
አቶ ሰለሞን፡- ንግድ ምክር ቤቱ ጠንካራ አይደለም ስንል መመዘኛውንም ማስቀመጥ አለብን፡፡ አንድ ምክር ቤት ራሱን የተደራጀውን አካል ነው የሚመስለው፡፡ ከዚህ የተለየና መለኮታዊ አይደለም፡፡ ከአየር ላይ አይመጣም፡፡ ከራሱ ውስጥ ነው የሚወጣው፡፡ ጠንካራ የግል ዘርፍ ከሌለ ጠንካራ ተቋም ወይም ንግድ ምክር ቤት አይኖረውም፡፡ ይህ ግልጽ ነው፡፡ ወጣም ወረደ ግን የጥንካሬው መለኪያም ምንድነው? ጠንካራ አይደለም ስንል ብዙ በመናገር፣ ወይም ብዙ አደባባይ በመውጣት ሲመዘን ይታያል፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ዋናው የጥንካሬ መለኪያ የግል ዘርፉን ከፍ ወዳለ ደረጃ እንዲሄድ መንገድ ማሳየት ነው፡፡ አመራር መስጠት ነው፡፡
ሁለተኛው ደግሞ የንግድ ምክር ቤቶች ዓላማ ንግድና ኢንቨስትመንትን ማስተዋወቅ፣ እንደ ድልድይ ሆኖ ከመንግሥት ጋር ማገናኘትና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እንዲህ ያሉ ነገሮችን እየሠራን ነው? ወይስ እየሠራን አይደለም? የሚለውን ማየት ያስፈልጋል፡፡ ሁልጊዜ በመጯጯህ የሚገኝ ውጤት ሳይሆን፣ በተጠናና በዕውቀት በተሞላ ሁኔታ የግል ዘርፉ የሚጠቀምበት ዕድሎች መፍጠር ነው፡፡ ለዚህ እንግዲህ ከግል ዘርፉ ውስጥ የሚወጣውን አካል ከሌላ የመጣ መለኮታዊ አካል ተደርጎ መወሰድ የለበትም፡፡ በጥቅሉ ንግድ ምክር ቤቱ ጠንካራ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ነገር ግን እያደገ እንደሄደ፣ ለውጥ እንዲመጣ ለግል ዘርፉ ቋሚ አገልግሎት እየሰጠ እየተጓዘ እንደሆነ፣ ከመንግሥትም ተቀባይነት እያገኘ መምጣቱም መታወቅ አለበት፡፡ አሁን እኮ አሉ የሚባሉ ችግሮች እየተቀረፉ ነው፡፡ ቀድመህ ሄደህ ነገሮችን ታሳያለህ፣ ወደፊትም ችግሩ እንዳይፈጠር መከላከል ትችላለህና እንዲህ ዓይነት የተለያዩ ሥራዎች ተሠርቷል፡፡
ከመንግሥት ጋር ባለን ግንኙነት ለችግሮች መፍትሔ እንዲፈለግ የምናደርገው በጥናት ላይ ተመሥርተን ነው፡፡ እንዲያው በዕለት ደራሽ ችግሮች እየተነሳን ይኼ ነው ማለት እንችልም፡፡ በሌላ በኩልም እነዚህ ችግሮች በትክክል የማን ናቸው ብለህ ማሰብ አለብህ፡፡ መፍትሔአቸው ምንድነው ብለን አብረን በመሥራትም ነው ችግሮቹን መቅረፍ የምንችለው፡፡ እኛም ዘዘንድ ችግር እንዳለ ማወቅ መቻል አለብን፡፡ ሁልጊዜ ከሳሽ ብቻ ሆኖ የመቅረብ ሳይሆን ራሳችንንም ማጥራትና በጠራ ጎዳና ላይ መሄድ ያስፈልጋል፡፡ በዲሲፕሊንና በንግድ ሥነ ምግባር መሥራትንም ይጠይቃል፡፡ በምናደርገውም እንቅስቃሴ እኛም ላይ ችግር እንዳይፈጥር እየተጠነቀቅን የምንሠራ እስካልሆን ድረስ፣ ወደ አንድ አቅጣጫ ብቻ መወርወር የለብንም፡፡
ሪፖርተር፡- እንደ ጠቀሱልኝ ከመንግሥት ጋር ጥሩ ግንኙነት እየፈጠራችሁ በመግባባትና በመደማመጥ እየተሠራ ከሆነ፣ ለንግድ ምክር ቤቶች እንቅስቃሴ ማነቆ ነው ያላችሁትን አዋጅና አደረጃጀት በመለወጥ ረገድ አንድ ድምዳሜ ላይ ሳይደረስ ሦስትና አራት ዓመት መፍጀቱ ለምን ይሆን?
አቶ ሰለሞን፡- በዚህ ላይ መንግሥት አዎንታዊ አመለካከት አለው፡፡ መጀመሪያም ቢሆን አዋጁን ያወጣው መንግሥት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ደግሞ አዋጁ የሚያሠራ አይደለም፡፡ በአዋጁ ምክንያት የግል ዘርፉን መንግሥትም በሚፈልገው ደረጃ እያሳደገው አይደለም፡፡ መንግሥትም እኮ ጠንካራ የግል ዘርፍ እንዲኖር ይፈልጋል፡፡ የውጭውን የግል ዘርፍ ግቡ ብሎ ይጠይቃል፡፡ የአገር ውስጥ ባለሀብቱም ወደ ማኑፋክቸሪንግ እንዲገባ ይፈልጋል፡፡ ግን እኛ ደግሞ እነዚህ ነገሮችን አጥንተን ቁልጭ ያለው መልክ ይኼ ነው ብለን ጥናቶች በተደጋጋሚ ቀርበው ተከልሰዋል፡፡ አንድ ጥናት ላይ ስትደርስ የአገሪቱ ሁኔታዎች ፈጠን ብለው ይኼዱና እኛ ያጠናነው ወደ ኋላ ይቀርብናል፡፡ እንዲህ እንዲህ ያሉ ችግሮች ናቸው እንጂ የመንግሥት ፍላጎት አለ፡፡
ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ አጥኑና ከነመፍትሔው አቅርቡ ተብሏል፡፡ አሁን እኮ መብቱን ለእኛ ሰጥተዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ወደሚመለከተው የሕግና መሰል አካል ይሄዳልና በጋራ በፍጥነት እናጥና ነው፡፡ መንግሥት እንቢ ብሎ የተወው ጉዳይ አይደለም፡፡ እኛ በውጭ አማካሪ አስጠንተናል፡፡ ንግዱ እንዲህ ቢሆን ዘርፉ ደግሞ እንዲህ ቢሆን ብለን አይተናል፡፡ አሁን መንግሥት ትኩረት ያደረገው ወደ ኢንዱስትሪ ነው፡፡ ይህንን ሳናካትት በበፊቱ መንገድ ብንሄድ አግባብ አይሆንም፡፡ ስለዚህ አሁን የመጨረሻውን ጥናት ካለቀ በኋላ ተገምግሞ በቅርቡ እናቀርባለን፡፡ ያቀረብነውን መፍትሔ ይሆናል የተባለ ሰነድ በአጭር ጊዜ መንግሥት ተመልክቶ ሕግ ሊያደርገው ይችላል ብለን እንገምታለን፡፡
ሪፖርተር፡- ስለዚህ እስካሁን ያቀረባችሁትን ጥናትና የመፍትሔ ሐሳብ ልትከልሱት ማለት ነው?
አቶ ሰለሞን፡- አሁን አይከለስም፡፡ አሁን የሠራነው የመጨረሻውን ነው፡፡ ንግድ፣ ኢንዱስትሪና ቱሪዝም አንድ ላይ እንዲተሳሰሩ አድርገናል፡፡ ከአሁን በፊት ቱሪዝም ትኩረት አይሰጠውም ነበር፡፡ አሁን ግን መንግሥት ራሱ ለዘርፉ ትኩረት ሰጥቷል፡፡ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ የሚያስገኝ ኢንቨስትመንት በመሆኑ እንዲሻሻል በቀረበው ሰነዱ ላይ አካትተናል፡፡
ሪፖርተር፡- የንግድ ምክር ቤታችሁ የመተዳደሪያ ደንብ ብዙ ማሻሻያዎች ተደርጎበት በጠቅላላ ጉባዔአችሁ እንዲፀድቅ ተደርጓል፡፡ ይህ ማሻሻያ ምን ለውጥ ያመጣል?
አቶ ሰለሞን፡- በአዲሱ በንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ መሠረት ንግድ ምክር ቤቱ ሲቋቋም፣ የመተዳደሪያ ደንቡ ብዙ ትኩረት የተሰጠው አልነበረም፡፡ በፍጥነት የተዘጋጀ ስለነበር ክፍተቶች ነበሩት፡፡ መተዳደሪያ ደንብ ማለት ገዢ ነው፡፡ አዋጁን ለማስፈጸም አስፈላጊ ነገር ነው፡፡ ስለዚህ ማሻሻሉ ግድ ነበር፡፡ ለምሳሌ በአዲሱ ማሻሻያ ውስጥ እስካሁን ለአባል ምክር ቤቶች መዋጮ በቋሚነት የተመደበ ነገር አልነበረውም፡፡ አሁን ግን ይህ እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ ደካማ ነው ከሚባልበት ምክንያቶች አንዱ የፋይናንስ አቅም ስለሌለው ነው፡፡ በፋይናንስ ከደከምክ ደግሞ ጠንካራ ሠራተኞች ልትቀጥር አትችልም፡፡ ስለዚህ እያንዳንዱ አባል በዓመት የተቆረጠ ክፍያ መክፈል አለበት፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ከአባላቱ ከሚሰበሰበው አሥር በመቶ ለብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱ ፈሰስ ማድረግ ይኖርበታል የሚል አንቀጽ ተካትቷል፡፡ ይህ የንግድ ምክር ቤቱን የፋይናንስ አቅም ከፍ ሊያደርገው ይችላል፡፡
በዚህ ማሻሻያ የተካተተው ሌላው ጉዳይ ደግሞ የአመራር ምርጫንና የጊዜ ገደብን የሚመለከት ነው፡፡ ልክ መንግሥት እየሄደበት እንዳለው አመራሩ በቅብብሎሽ መተካካት እንዲፈጥር ያስፈልጋል፡፡ ወጣቶች ወደ ላይ መምጣት አለባቸው፡፡ ስለዚህ በዚህ ማሻሻያ አዳዲስ ጉልበትና ወጣቶች ወደ አመራር የሚመጡበት ደንብ ስለሚያስፈልግ ይህንን ለማሳካት የሚያስችል አንቀጽ እንዲካተት ተደርጓል፡፡ ከዚህም ሌላ በመንጠባጠብ የሚደረጉ ጠቅላላ ጉባዔዎችን በማስቆም የጊዜ ገደብ ተበጅቶ እንዲካሄዱ የሚያደርግ አንቀጽ እንዲቀመጥ ተደርጓል፡፡ እንዲህ ያሉ ለውጦች ወደ ጥንካሬ ይወስዱሃል፡፡ አባላትህንም በአግባቡ ታገለግላለህ፡፡ በአጠቃላይ ማሻሻያዎቹ ወደ ተሻለ ጥንካሬ ለመሄድ የሚያገለግሉ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- በአንዳንድ የተሻሻሉ አንቀጾች ላይ ግን ተቃውሞም ቀርቧል፡፡
አቶ ሰለሞን፡- ነገሩ ተቃውሞ አይደለም፡፡ ማዳበሪያ ነው የቀረበው፡፡ በማሻሻያዎቹ ሁሉም ደስ ብሎአቸዋል፡፡ ማሻሻያው ከራሳቸው የመጣ ነው፡፡ ለእያንዳንዱ ንግድ ምክር ቤት ተልዕኮ አንዳንዶቹ ተወያይተውበታል፡፡ በችኮላም አይቶ የመጣም ይኖራል፡፡ ጉዳዩን በደንብ ያላየውም ይኖራል፡፡ በጥቅሉ የሚያውቁት ነገር ነው፡፡ ነገር ግን ነገሩ ትንሽ ስለቆየ እንደ አዲስ ታየ እንጂ ማሻሻያው የሚጎዳ ነገር የለውም፡፡ ነገር ግን ማሻሻያውን እናቆየው የሚል ነገር ነበር፡፡ በአንዳንድ ምክር ቤቶች ማሻሻያው ከእኛ መተዳደሪያ ደንብ ጋር ይጋጫል የሚል ሐሳብ ቀርቧል፡፡ እንዲህ ዓይነት ነገሮች የቀረቡ ቢሆንም፣ የተሻለው ማሻሻያ ማፅደቅ የግድ በመሆኑ ፀድቋል፡፡