Friday, January 27, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአይሲቲ ፈጠራ አመንጪዎች ሁዋዌ በሰጣቸው የሥልጠና ዕድል ወደ ቻይና አቀኑ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ መስክ የአዲስ አበባ አስተዳደር የተሻለ የፈጠራ ውጤት አቅርበዋል ያላቸውን ወጣቶች ለሥልጠናና ለልምድ ልውውጥ ወደ ቻይና እንዲሄዱ አደረገ፡፡ በቻይና የሁዋዌ ኩባንያ በሰጠው ዕድል ለመጠቀም ባለፈው ዓመትም ሌሎች የአይሲቲ ፈጠራ አፍላቂዎች ወደ ቻይና ማቅናታቸው ይታወሳል፡፡

መስከረም 5 ቀን 2008 ዓ.ም. አምስት ኪሎ በሚገኘው በስፖርት ኮሚሽን ሕንፃ ላይ በተደረገ የሽኝት ሥነ ሥርዓት ላይ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከንቲባ የሕዝብ ግንኙነት አማካሪ አቶ ተወልደ ገብረፃድቃን እንዳስታወቁት፣ በዚህ ዓመት ተካሂዶ በነበረው አዲስ አበባ አይሲቲ ዓውደ ርዕይና ኮንፈረንስ ላይ በመሳተፍ ልዩ ልዩ የአይሲቲ ፈጠራ ውጤቶችን ያስተዋወቁ 11 ወጣቶች ወደ ቻይና በመጓዝ ሥልጠናና ልምድ ቀስመው እንዲመጡ ተመቻችቷል፡፡ በመሆኑም የሁዋዌ ኩባንያ በሰጠው ነፃ የሥልጠና ዕድል ወደ ቻይና ያቀኑት ወጣቶች፣ የኩባንያውን ዋና መሥሪያ ቤት ከመጎብኘት ባሻገር በሁዋዌ ባለሙያዎች አማካይነት ሥልጠና እንደሚከታተሉ ገልጸዋል፡፡

የሁዋዌ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ ሲሊያ ሁዋንግ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ ባለፈው ዓመትም 11 ወጣቶች የሁዋዌን የሥልጠና ዕድል በማግኘት ወደ ቻይና አቅንተው ተመልሰዋል፡፡ በቻይና ጓንዶንግ ግዛት ውስጥ ዋና መሥሪያ ቤቱን ያደረገው ሁዋዌ፣ ለወጣቶቹ በራሱ አስተማሪዎች ከሚሰጠው ሥልጠና ባሻገር ባለሦስት ኮከብ በሆነው በራሱ ሆቴል በማሳረፍ ሥልጠናውን ጨምሮ ለ11 ቀናት የሚቆይ የጉብኝት መርሐ ግብር ለአዲስ አበባ አይሲቲ ፈጣሪ ወጣቶች አሰናድቷል፡፡

አቶ መብራቱ ኪዳነ ማርያም በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአይሲቲ ልማት ኤጀንሲ የሶፍት ዌር ቡድን ኃላፊና በየዓመቱ በኤጀንሲው ለሚካሄደው ዓውደ ርዕይ አስተባባሪ ናቸው፡፡ አቶ መብራቱ ለሪፖርተር እንዳብራሩት፣ ከኢንፎርሜሽንና ከመገናኛ ቴክኖሎጂ ዓውደ ርዕይ ተሳታፊዎች አራት የፈጠራ አመንጪዎች፣ አምስት ከአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ የተውጣጡትን ጨምሮ 11 ወጣቶች በሞባይል ቴክኖሎጂ፣ በሶፍት ዌርና በሃርድዌር እንዲሁም ከኢንፎርሜሽንና ከመገናኛ ቴክኖሎጂ ውጭ የሆኑ በራሪ መሣሪዎችን፣ በርቀት መቆጣጠሪያ የሚሠሩ የመጋረጃ መክፈቻና መዝጊያዎች እንዲሁም የመብራት ማብራሪያ ማጥፊያ በመሥራታቸው ለቻይና ጉዞ አብቅቷቸዋል፡፡ ከተጓዦቹ መካከል መስማት የተሳነው ወጣትም በፈጠራ ውጤቱ ሳቢያ ተሳታፊ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከ60 አገሮች ለሚውጣጡ ወጣቶች በየዓመቱ የአይሲቲ ሥልጠና የሚሰጠው ሁዋዌ፣ በምርምርና ልማት መስኮች ከ4.5 ቢሊዮን ዶላር በላይ በየዓመቱ ወጪ እንደሚያደርግም የኩባንያው ኃላፊዎች ይናገራሉ፡፡

በቅርቡ በአፍሪካ ኅብረት በኮሙዩኒኬሽንና በኢንፎርሜሸን ቴክኖሎጂዎች ላይ ሲመክር የሰነበተው ልዩ የቴክኒክ ኮሚቴ ስብሰባ ላይ የተገኙት የሁዋዌ ቴክኖሎጂስ ምክትል ፕሬዚዳንት ቻርልስ ዲንግ ናቸው፡፡ ምክትል ፕሬዚዳንቱ በተለይ ከሪፖርተር ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳብራሩት፣ ገና በሙከራ ደረጃ ላይ የሚገኘው ‹‹5G›› የሞባይል ኔትወርክ ቴክኖሎጂ በፍጥነቱ እስካሁን ከተዘረጉት ሁሉ ከፍተኛው ነው፡፡ በቻይና ከተሞች መሞከር የጀመረው ይኼ ቴክኖሎጂ በአሁኑ ወቅት ከቤተ ሙከራ ወጥቶ በመስክ ፍተሻ እየተደረገበት ሲሆን፣ በቅርቡም ተግባራዊ እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡ 

ይህንን ቴክኖሎጂ ወደ አፍሪካ ከማምጣት ባሻገር ኩባንያው ለአፍሪካ ወጣቶች የሥልጠናና የሥራ ዕድሎችን እያመቻቸ እንደሚገኝም ዲንግ ገልጸዋል፡፡ ሁዋዌ በአፍሪካ በከፈታቸው ሰባት የሥልጠና ማዕከላት እስካሁን ለ15 ሺሕ የአፍሪካ መሐንዲሶች ሥልጠና መስጠቱን ያስታወቁት ዲንግ፣ ‹‹ሲድስ ኦፍ ዘ ፊውቸር›› በተሰኘው የሥልጠናና የሥራ ዕድል ፕሮግራምም ለ1,000 አፍሪካውያን ወጣቶች ቻይና በሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤቱ ሥራ ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ አስረድተዋል፡፡ 

በኢትዮጵያ ከቴሌኮም መሠረተ ልማትና ዝርጋታ በተጨማሪ የስማርት ስልኮች ገበያ ላይ እየጎላ የመጣው ሁዋዌ፣ በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለውን የኔትወርክ መቆራረጥ ችግር በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመቅረፍ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል ብለዋል፡፡ ኩባንያው በአሁኑ ወቅት በአዲስ አበባ የ‹‹4G›› ኔትወርክ በመዘርጋት ለአገልግሎት ማብቃቱ ይታወቃል፡፡ 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች