Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንግድ ምክር ቤቱ ለአምስት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ዕውቅና ሰጠ

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  አከራካሪውን መተዳደሪያ ደንብ አፀደቀ

የኢትዮጵያ ንግድ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ለግሉ ዘርፍ ዕድገትና መጐልበት እገዛ አድርገዋል ላላቸው አምስት ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ዕውቅና ሰጥቷል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ በተለያየ ደረጃ ለግል ዘርፉና ለንግድ ምክር ቤቱ ከፍተኛ ድጋፍ አድርገዋል ብሎ በቀዳሚነት ዕውቅና የሰጣቸው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ተሾመን ነው፡፡ ከፕሬዚዳንቱ ሌላ ለግል ዘርፍ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ነበራቸው፤ ለንግድ ምክር ቤቱና ለግል ዘርፉ ጥያቄዎች በራቸውን ከፍተው አስተናግደውናል ተብለው የተሸለሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ናቸው፡፡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሌላኛው ተሸላሚ ሆነው የቀረቡት  ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ዳዋኖ ከድር ናቸው፡፡

በጉባዔው ዕለት ለግል ዘርፉ ከፍተኛ ደጋፍ በማድረግ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ተብለው ለሽልማት የበቁት ሦስተኛው ተሸላሚ ደግሞ ከግሉ ዘርፍ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከ20 ዓመታት በላይ ሲሠሩ የቆዩት የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ታደሰ ኃይሌ ናቸው፡፡ የንግድ ሚኒስትሩ አቶ ከበደ ጫኔም በተመሳሳይ የንግድ ምክር ቤቱ ተሸላሚ ሆነዋል፡፡

ንግድ ምክር ቤቱ ከሌሎች በተሻለ ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክተዋል ላላቸው ለነዚህ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በወርቅ የተሠራ የደረት ፒን እና ያበረከቱትን አስተዋጽኦ የሚያመላክት መልዕክት የያዘ የምስክር ወረቀት በመስጠት ዕውቅና ሰጥቷቸዋል፡፡

በንግድ ምክር ቤቱ ቀዳሚ ተሸላሚ ለሆኑት ዶ/ር ፕሬዚዳንት ሙላቱ የደረት ፒኑን ያኖሩላቸው የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አፈወርቅ ሲሆኑ፣ ለቀሪዎቹ ተሸላሚዎች ደግሞ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ የደረት ፒኑንና የምስክር ወረቀቱን ሰጥተዋቸዋል፡፡

ዶ/ር ሙላቱ ከሽልማቱ ሌላ በዕለቱ የጉባዔው የክብር እንግዳ በመሆናቸው ጭምር ለጠቅላላ ጉባዔው አባላት ንግግር አድርገዋል፡፡ በፕሬዚዳንቱ ንግግር ትኩረት ተሰጥቶት የተብራራው መንግሥት የግል ዘርፉን ለማሳደግ እየሠራ ያለውን ሥራ በማጉላት ነው፡፡ የግል ዘርፉም ለአገር ዕድገት የሚያበረክተውን አስተዋጽኦ በማስታወስ ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲገባም አሳስበዋል፡፡

የንግድ ምክር ቤቱ በዕለቱ ለከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ዕውቅና ከመስጠት ጎን ለጎን ለኩላሊት እጥበትና ሕመምተኞች ማኅበር 100 ሺሕ ብር መለገሱን አስታውቋል፡፡ በዕለቱም የ100 ሺሕ ብር ቼክ የሚሰጥ ስለመሆኑና ቼኩንም ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሙላቱ ለማኅበሩ ተወካዮች እንዲሰጡላቸው ከጋበዙ በኋላ፣ ሊሰጥ የታሰበው ቼክ ሳይቀርብ ቀርቷል፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ቼኩ የተዘጋጀ መስሎዋቸው በፕሬዚዳንቱ በኩል እንዲሰጥ ያደረጉት ግብዣ ባለመሳካቱም፣ ይቅርታ ጠይቀው ቼኩ ተጽፎ የማኅበሩ ተወካዮች ከፕሬዚዳንቱ እጅ እንዲቀበሉ እናደርጋለን በማለት ተናግረዋል፡፡

 እንዲህ ካለውና ሁሉንም ካስደመመ አጋጣሚ በኋላ የዕለቱን የክብር እንግዶች በመሸኘት ጠቅላላ ጉባዔው ወደ ውይይት ገብቷል፡፡ ጠቅላላ ጉባዔው በንግድ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ቀርቦ የነበረው የሁለት ዓመት ሪፖርት ላይ በመወያየት የተጀመረ ነበር፡፡ እንደተጠበቀውም የአብዛኛዎቹ አባላት አስተያየት ጠቅላላ ጉባዔውን ጊዜውን ጠብቆ ያለመካሄዱ አግባብ ያለመሆንን በመተቸት ተጀምሯል፡፡ በዕለቱ ዕድሉን ያገኙ ተናጋሪዎችም ይህን ጉዳይ እንዲብራራላቸውና እንዳይደገም ማሰሪያ ሊበጅለት እንደሚገባ ጭምር አሳስበዋል፡፡ አቶ ሰለሞን አፈወርቅ በበኩላቸው ጠቅላላ ጉባዔው የሚደረግበት ወቅት መፋለሱ አሁን የተፈጠረ ያለመሆኑንና ሲወራረስ የመጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ እርሳቸው የሚመሩት ቦርድ ግን ስብሰባውን በወቅቱ ላለመደረጉ ምክንያቶች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡ ንግድ ምክር ቤቱ አሁንም ጠንካራ ያለመሆኑ የሚገልጽ አስተያየትም ከጠቅላላ ጉባዔው ተሳትፊዎች የቀረበ ሲሆን፣ በተለይ የግል ዘርፉን ወደ ማኑፋክቸሪንግ ለማስገባት የሠራው ሥራ እጅግ ደካማ እንደነበር የሚገልጹ አስተያየቶችም ተንፀባርቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ አልባሳት ማኅበርና ፕሬዚዳንት አቶ ፋሲል ታደሰ ንግድ ምክር ቤቱ በአድቮኬሲ ሥራ ላይ ብቻ ማተኮሩን በመግለጽ፣ አባላት ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እንዲገቡ የሠራው ሥራ የለም በማለት ተችተዋል፡፡

አቶ ሰለሞን ወደ ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ የግሉ ዘርፍ ያለመግባቱ የመንግሥትም ችግር መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡ በዚህ ጉባዔ ላይ የቀረበው ሌላው አስተያየት ደግሞ የውጭ ጉዞን የሚመለከት ነው፡፡ አንዳንድ የጠቅላላ ጉባዔው አባላት እንደገለጹት፣ ንግድ ምክር ቤቱ ከማኅበራትና ከተለያዩ አገሮች ነጋዴዎች ጋር የሚፈጠር ውይይት ጎልብቶ የንግድ ትስስር አላመጣም ተብሏል፡፡ መነጋገሩ ብቻ በቂ ባለመሆኑ ምክር ቤቱ ይህንን የሚከታተል ዘርፍ ሊኖረው ይገባል ተብሏል፡፡ አቶ ሰለሞን ባቀረቡት ሪፖርት ላይ በሁለት ዓመት ውስጥ ከ36 በላይ አገሮች ከመጡ ልዑካን ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡

ነጋዴ ያልሆኑ ሰዎች በውጭ ጉዞው እንደሚሳተፉ ተደርጓል የሚልም አስተያየት ቢሰጥም፣ አቶ ሰለሞን ግን ይህ መሆን የማይችል ቢሆንም ወደ ፊት ከተገኘ እናጣራለን በማለት ተናግረዋል፡፡ ነጋዴውን ኅብረተሰብ የሚያረካ አገልግሎት አለመሰጠቱንም የተናገሩ አስተያየት ሰጪዎች ነበሩ፡፡

ከንግድ ምክር ቤቱ አቅምጋር ተያይዞ የተሰጡ አስተያየቶች እንደሚያመለክቱትም ብሔራዊ ንግድ ምክር ቤቱም ሆነ ሌሎች ንግድ ምክር ቤቶች የፋይናንስ እጥረትና የአቅም እጦት ያለባቸው መሆኑን ነው፡፡

ሌላው ቀርቶ የግሉን ዘርፍ ስብሰባ ለማካሄድ ለአባል የሚከፈለውን ወጪ ለመሸፈን ያለው ችግር በምሳሌነት ተነስቷል፡፡ በንግድ ምክር ቤቱ በዕለቱ ትልቅ ግምት የተሰጠው ሌላው ጉዳይ የንግድና ምክር ቤቱን የመተዳደሪያ ደንብ ለማሻሻል የቀረበው ሐሳብ ነው፡፡ በቦርዱ ቀርቦ የነረበው የማሻሻያ ሐሳብ ብዙ ያከራከረ ነበር፡፡ ማሻሻያው ጊዜ ተሰጥቶት ይመከርበት ያሉም ነበሩ፡፡ ነገር ግን ማሻሻያው ጠቃሚ ነው የሚለው ሐሳብ ድጋፍ አግኝቶ እንዲፀድቅ ተደርጓል፡፡

ማሻሻያው የንግድ ምክር ቤቱን የምርጫ ሥርዓት፣ የሥራ ዘመንና የመሳሰሉትን የቀድሞ አንቀጾች በአዲስ የተካ ነው፡፡ የተሻሻለው መተዳደሪያ ደንብ በተደጋጋሚ ወደ ምክር ቤቱ አመራር ለማውጣት ያለውን ፍላጎትና ከዚሁ ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ውዝግቦችንም የሚያስቀር ነው ተብሏል፡፡ በተለይ የምክር ቤቱን የምርጫ ሒደት፣ የክልል ምክር ቤቶች የጉባዔ አካሄድና የሚመረጡ አመራሮች የምርጫ ጊዜ ላይ ገደብ ያደርጋል፡፡

አንድ የቦርድ አባል በስብሰባዎች ላይ ካልተገኘ ሊወሰድበት የሚገቡ ዕርምጃዎችንም በየደረጃው ያስቀመጠ ነው ተብሏል፡፡ ከዚህ በፊት በነበረ አሠራር አንድ የቦርድ አባል ከስብሰባዎች ሲቀር ምንም ዓይነት ዕርምጃ አይወሰድበትም ነበር፡፡ በተሻሻለው አንቀጽ ግን ሊወሰድ የሚገባውን ዕርምጃ አስፍሯል፡፡ የንግድ ምክር ቤቱ ጽሕፈት ቤትም ተጨማሪ የኃላፊነቶችን እንዲወስድ የሚያደርግ አንቀጽ ተካቷል፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች