Monday, April 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዓለም ባንክ የፈቀደው የ600 ሚሊዮን ዶላር ፋይናንስና ከአራት ዓመት በኋላ የሚጠበቀው ውጤት

ተዛማጅ ፅሁፎች

የዓለም ባንክ መንግሥት ላቀዳቸው የልማት ፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ ብድርና ዕርዳታ ሲሰጥባቸው የቆዩ በርካታ ፕሮጀክቶች ይጠቀሳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅትም በርካታ ፕሮጀክቶችን ፋይናንስ እያደረገ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ መካከል  በመሠረታዊ መንግሥታዊ አገልግሎቶች አሰጣጥ ላይ መንግሥት ማሻሻያ ብቻም ሳይሆን መሠረታዊና መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ ያስችላል ያለውን ፕሮግራም ሲደግፍ የቆየው ባንኩ እስከ 2011 ዓ.ም. ለሚቆየው የመሠረታዊ አገልግሎት ፕሮግራም ማስፈጸሚያ የ600 ሚሊዮን ዶላር ወይም የ12 ቢሊዮን ብር የፋይናንስ ድጋፍ ማፅደቁን አሜሪካ ከሚገኘው ዋና መሥሪያ ቤቱ የወጣው መግለጫ አመልክቷል፡፡

የዓለም ባንክ ኃላፊዎችም ባንኩ ያፀደቀውን ፋይናንስ በማስመልከት በሰጡት አስተያየት ባለፉት አሥርት ውስጥ በአገልግሎት አሰጣጥ መስክ የተመዘገቡትን ለውጦች እያመሳከረ በጥናት አቅርቧል፡፡ በመጪዎቹ አራት ዓመታት ውስጥ መንግሥት በአገልግሎት አሰጣጡ ብቻም ሳይሆን በሚያቅዳቸው የልማት ሥራዎች፣ በፋይናንስና ግዥ በመሳሰሉት ተግባሮቹ ሕዝብን በግልጽነት እንዲያሳትፍ ይጠበቃል፡፡ መንግሥት እንዲህ ያለውን ሥራ ለማከናወን ድጋፍ የሚደረግለት የታዩት ለውጦች ድሃውን ሕዝብ ተጠቃሚ እያደረጉ እንዲቀጥሉ በማሰብ እንደሆነ የገለጸው ባንኩ፣ ከወራት በፊት ይፋ ያደረገው የድህነት ዳሰሳ ጥናት በአገሪቱ ድህነት ቅነሳ ላይ የታዩትን ለውጦች ታሳቢ መደረጋቸውን ያብራራል፡፡

ለ12 ቢሊዮን ብር መነሻ ታሪኮች

የዓለም ባንክ በድህነት ቅነሳ ረገድ በአገሪቱ ለውጥ ታይቷል ቢልም፣ ታችኛው የድህነት መስመር ላይ የሚገኘው ሕዝብ ግን ወደባሰ ድህነት መውረዱን የገለጸበት ሪፖርቱ፣ በአገሪቱ የሚታው እኩልነት ከሌሎች አገሮች የተሻለ እንደሆነም ይተነትናል፡፡ ይህም ቢባል ግን ድሆች ሕይወት ላይ ተገቢው ለውጥ ካልመጣባቸው ምክንያቶች አንዱ በዝቅተኛ ደረጃ የሚገኙት የታክስ ከፋይ መሆናቸው አንዱ ነው፡፡ ምንም እንኳ ሁሉም ሰው በሠራው መጠን ካገኘው ገቢ ላይ ለመንግሥት ማካፈል እንዳለበት በሕግ ቢደነገግም መሠረታዊው ታክስ የመሰብሰብ መርኅ ግን ከፍተኛ ከሚያገኘው ሰው ወደ ዝቅተኛው በማምጣት የገቢ መመጣጠንን ወይም የገቢ እኩልነት ለመፍጠር ሲባል የሚተገበር እንደሆነ የኢኮኖሚክስ ባለሙያዎች ይገልጻሉ፡፡ በአጭሩ በሀብታምና በድሃው መካከል ያለውን የገቢና የሀብት ልዩነት ለማጥበብ  መሣሪያ ሆነው ከሚያገለግሉት አንዱ ታክስና ግብር ማስከፈል ነው፡፡

እርግጥ መንግሥት የሚከተለው ከታች ወደ ላይ እየጨመረ የሚመጣ የታክስ ስሌትን ነው፡፡ ይህም ሆኖ በከተማም ሆነ በገጠር የሚገኘው ድሃው ሕዝብ ቫትን ጨምሮ፣ ከደመወዙ፣ ከመሬት ግብር፣ ከሚሰጠው አገልግሎት የሚቆረጥበት ‹‹ዊዝ ሆልዲንግ ታክስ›› ጨምሮ ቀላል የማይባል ጫና ውስጥ ይገኛል፡፡ ይህንን የሚያጠናክረው የዓለም ባንክ የድህነት መጠን ትንታኔ፣ ምንም እንኳ የታችኛው የኅብረተሰብ ክፍል የሚከፍለው ግብርና ታክስ አነስተኛ ነው ቢባልም መንግሥት ታክስ በማስከፈል የፈጠረው ጫና ሳይጠቀስ አላለፈም፡፡ በመሆኑም በድሃውና በሀብታሙ መካከል በንጽጽር በአገሪቱ መመጣጠን እንዲታይ ለማስቻሉ የዚህ ዓይነቱ ጫናም አስተዋጽኦ ማድረጉን ባንኩ አብራርቷል፡፡

ከዚህ ባሻገር ግን መንግሥት በመሠረታዊ አገልግሎት መስኮች ማለትም በትህምርትና ጤና መስኮች ላይ ኢንቨስት በማድረግ ያስመዘገባቸው ለውጦች ድሃውን ለመካስ አስችለዋል ያለው ባንኩ፣ ከ1997 እስከ 2005 ዓ.ም. ባለው ጊዜው ውስጥ የጤና ኬላዎች ቁጥር በ159 ከመቶ መጠን ጨምሯል ብሏል፡፡ የጤና ማዕከሎች ቁጥር በ386 ከመቶ በመጨመር የአገሪቱን የጤና አገልግሎት ሽፋን ከከተማ እስከ ገጠር ለማዳረስ አስችሏል ያለው ባንኩ፣ በትምህርት መስክም ብዙ ውጤት መገኘቱን ሳይጠቁም አላለፈም፡፡ ዕድሜያቸው ለትህምርት የደረሱ ታዳጊዎች ከ1997 እስከ 2005 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ ከ42 ከመቶ ወደ 62 ከመቶ ማደጉን የዓምናው የባንኩ ሪፖርት ይዳስሳል፡፡

በአሁኑ ወቅት አገሪቱ በሚሊኒየሙ የልማት ግቦች መለኪያ አብዛኞቹን ግቦች በማሳካት በዓለም ከሚጠቀሱ ጥቂት አገሮች መካከል መሆኗም የባንኩን ድጋፎች ለማግኘት ካስቻሏት ውስጥ አንኳር ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በጾታ ድርሻ የተመጣጠነ የአንደኛ ደረጃ ትምህርትን ለሁሉም ማዳረስ በሚለው ግብ ስትመዘን ውጤታማ ተብላለች፡፡ ከዚህም ባሻገር የሕፃናትን ሞትን በመቀነስ፣ ኤችአይቪ/ኤድስን በመዋጋትና የወባ በሽታን በመቀነስ ሒደት ለአገሪቱ የለውጥ ስኬቶች ጎልተው የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ይሁንና የሁለተኛ ደረጃ ትህምርትን በማስፋፋትና የእናቶች ሞትን በመቀነስ ረገድ አገሪቱ ያሳየችው ለውጥ ብዙ የሚባልለት አልሆነም፡፡ መንግሥት ባለፈው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መሠረት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ከ60 ከመቶ በላይ የማስፋፋት ዓላማ ቢኖረውም፣ በአምስት ዓመት ውስጥ ያሳየው ለውጥ ከ37 ከመቶ በላይ ሊጓዝ አልቻለም፡፡ የኑሮ ውድነትም በየጊዜው እየተባባሰ መምጣቱን መንግሥት እንደሚገነዘብ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ በተዋረድ ያሉት ባለሥልጣናት ሲገልጹ ይደመጣል፡፡ ለማሻሻል የተወሰዱ ዕርምጃዎችና የመጡ ለውጦች ግን አጥጋቢ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡ ይልቁንም በየጊዜው እየጨመረ የሚገኘው የዋጋ ንረት ከነጠላ አሃዝ ወደ ባለሁለት አሃዝነት እያሻቀበ መጥቷል፡፡ የቤት ኪራይና ሌሎች የኪራይ አገልግሎቶች ዋጋን ጨምሮ ምግብ ነክ የሆኑና ያልሆኑ ሸቀጦች ላይ የሚታየው የዋጋ ለውጥ ከባድ እየሆነ ይገኛል፡፡ 

እንዲህ ያሉ ጉራማይሌዎችን ያለፈው የአገሪቱ ኢኮኖሚ፣ ላለፉት አሥር ዓመታት በተጓዘበት የዕድገት መጠን ልክ እንዲያቀና የዓለም ባንክ ለመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የአቅም ግንባታ፣ የደመወዝና የሥልጠናና ክህሎት ድጋፎች በመስጠት የሚሰጡትን መሠረታዊ የጤና፣ የትምህርትና መሰል አገልግሎቶች እያደጉ እንዲቀጥሉ ለማስቻል 12 ቢሊዮን ብር ፋይናንስ ለመንግሥት እንዲሰጥ ወስኗል፡፡ በግርድፍ ትርጉሙ ‹‹እኩል አገልግሎትን በመስጠት ብልጽግናን መምጣት፤›› ተብሎ የሚጠራ አዲስ የአራት ዓመት ፕሮግራም ይፋ ያደረገው የዓለም ባንክ፣ ከዚህ ቀደም በባንኩ ውጤት ተኮር ፕሮግራም በማለት በመሠረታዊ አገልግሎቶች አቅርቦት ዘርፍ ላይ ሲያደርገው በቆየው ፕሮግራም ሥር የሚመደብ መሆኑን አስታውሷል፡፡ ከፌደራል መንግሥት ጀምሮ በተዋረድ ከክልል እስከ ታችኛው ወረዳ እርከን ላይ ለሚገኙ መንግሥታዊ ተቋማት የሥራ አፈጻጸም መሻሻል ብቻም ሳይሆን ሥራቸው፣ የሚያወጡት ወጪና የሚበጅቱት በጀት ላይ ግልጽነት እንዲሰፍን፣ ሕዝብ እንዲሳተፍ፣ ተጠያቂነት እንዲጎለብት ለማድረግ የታለመበት ፕሮግራም፣ የአገሪቱ ልማት መዋቅራዊ ለውጥ እንዲያመጣ ለማስቻል ጭምር ተስፋ የተጣለበት ነው፡፡

ከዚህ ቀደም ሲተገበር በቆየው የመሠረታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ፕሮግራም ሁለቱን የከተማ አስተዳደሮችና የፌደራል መንግሥት መሥሪያ ቤቶችን ጨምሮ 11 ክልሎች፣ 700 ወረዳዎችና 17 ሺሕ የገበሬ ማኅበር አስተዳደሮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡

የመሠረታዊ አገልግሎት አሰጣጥ ፕሮግራም ዋና ፈተና በአገሪቱ የታቀዱ የማኅበራዊና የኢኮኖሚ ግቦችን ለማስፈጸም የሰውና የተቋማዊ ብቃት ችግሮች ጋሬጣ ሆነው መገኘታቸውን የገመገመው ባንኩ፣ ዋቢ የሚያደርጋቸው አገሪቱ በየዘርፉ የምትተገብራቸው ያፈጁ ሕጎች፣ አድካሚ የሥራ ሒደቶችና ሥርዓቶች፣ መዋቅራዊ መዘበራረቆች፣ እንዲሁም በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሚታየው መሠረታዊ የክህሎት ችግሮች ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህን ክፍተቶች ለመሙላት የመንግሥትን የሰው ኃይል በክህሎት በማሻሻልና በኢንፎርሜሽን በቴክኖሎጂ የተደገፈ አግልግሎት እንዲሰጥ በማስቻል ችግሮች ተብለው የተለዩትን ለመቅረፍ ታቅዶ ነበር፡፡ የተወሰነ ለውጥ መታየቱንም ባንኩ አስታውሷል፡፡ ከአቅም ግንባታ፣ ከሲቪል ሰርቪስ ማሻሻያ ፕሮግራም አሁን እስከተደረሰበት ጊዜ ድረስ ባሉት ሒደቶች በአገሪቱ የተደረጉ ለውጦችና መዋቅራዊ የተቋማት ለውጦችን በዝርዝር የገመገመው የዓለም ባንክ፣ እስከታችኛው የመንግሥት አስተዳደራዊ መዋቅር ድረስ ባሉት ተቋማት ዘንድ ያልተማከለ አሠራር እንዲዘረጋ የማድረግ ተግባር ቅድሚያ የሚሰጠው በመሆኑ የ12 ቢሊዮን ብር ፋይናንስ መፍቀዱን አስታውቋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአገሪቱ ለመጪዎቹ 15 ዓመታት የሚተገበሩትን ዘላቂ የልማት ግቦች ለመተግበርና ለማስፈጸም የሚችል ተቋምና የሰው ኃይል በአገሪቲ እንዲፈጠር ለማገዝ ድጋፍ መደረጉን የባንኩ ኃላፊዎች በመግለጫቸው አስታውሰዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች