Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

‹‹የመንግሥት አመራር በሙሉ ሙስና ስለፈጸመ ስብስብ አድርጋችሁ የምታደርጉትን አድርጉ የሚል መልዕክት አልደረሰኝም››

ተዛማጅ ፅሁፎች

አቶ ዓሊ ሱሌይማን፣  የፌዴራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽነር

የፌደራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን የሙስና መፈልፈያ ወይም የሥጋት ቀጣና በሚባሉት የመሬት አስተዳደር፣ የግብርና ታክስ አስተዳደር፣ የመንግሥት ግዥና ሽያጮች ላይ ክትትል በማድረግ የሙስና መከላከልና ሙስና ከተፈጸመም ምርመራ በማድረግ ክስ ሲመሠርት መቆየቱን ይናገራል፡፡ በተለይ በ2007 ዓ.ም. በተጠረጠሩ ጉዳዮች ምክንያት በርካታ ንብረቶችን ያሳገደ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ 87.7 ሚሊዮን ዶላር፣ 27.7 ሚሊዮን የሱዳን ፓውንድ፣ ስምንት ንግድ ድርጅቶች፣ አንድ ፋብሪካ፣ 37 መኖሪያ ቤቶች፣ 15 የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች፣ 55 ተሽከርካሪዎችና አራት ሕንፃዎች ይገኙበታል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የተመዘበረ የመንግሥትና የሕዝብ ንብረት በማስመለስ በኩል ደግሞ 74.8 ሚሊዮን ብር፣ አራት ተሽከርካሪዎች፣ ሦስት መኖሪያ ቤቶች፣ አራት ሕንፃዎች፣ 26,244.4 ካሬ ሜትር መሬት እና 81,422.76 ግራም ወርቅ ለመንግሥት ተመላሽ ማድረጉን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡ የፌደራል የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዓሊ ሱሌይማን በ2007 በጀት ዓመት የተከናወኑ ተግባራትንና በተያዘው በጀት ዓመት ስለሚከናወኑ ተግባራት አስመልክቶ ለጋዜጠኞች ባለፈው ዓርብ መስከረም 7 ቀን 2008 ዓ.ም. መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ኮሚሽነር ዓሊ ተጠይቀው ምላሽ ከሰጡባቸው ጉዳዮች መካከል፣ ኢሕአዴግ በቅርቡ ባካሄደው ጉባዔ ሙስና የሥርዓቱ አደጋ መሆኑንና ከፍተኛ ባለሥልጣናትም ተሳታፊ መሆናቸውን ቢገልጽም፣ ኮሚሽኑ ግን አሁንም በአነስተኛ የሙስና ወንጀሎች ላይ ማተኮሩ፣ አገሪቱ ሜጋ ፕሮጀክቶችን እያካሄደች ቢሆንም ኮሚሽኑ በዚህ ዘርፍ ተሳታፊ ያልሆነበት ምክንያትና በቀጣዩ ዓመት የኮሚሽኑ የትኩረት አቅጣጫዎች ይገኙባቸዋል፡፡ አቶ ዓሊ የሰጡትን ጋዜጣዊ መግለጫ የተከታተለው ውድነህ ዘነበ በዋና ዋና ጉዳዮች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚከተለው አጠናቅሯል፡፡

ጥያቄ፡- በቅርቡ በተካሄደው የኢሕአዴግ ጉባዔ ላይ የሥርዓቱ አደጋ ከተባሉት መካከል ከፍተኛ (ግራንድ) ሙስና ነው ተብሏል፡፡ ፀረ ሙስና ኮሚሽን እስካሁን እየተዋጋ ያለው አነስተኛ የሙስና ወንጀሎችን ነው፡፡ ከዚህም በላይ ዕርምጃ እየወሰደ የሚገኘው ከፖለቲካው ቅኝት በመነሳት ነው የሚሉ አሉ፡፡ ሥርዓቱ ራሱ ሙስና ውስጥ ተዘፍቄያለሁ በሚልበት ወቅት የእርስዎ መሥሪያ ቤት መናኛ ጉዳዮች ላይ መጠመዱ ለምንድነው?

አቶ ዓሊ፡- የፖለቲካና የሕግ ቋንቋ የተለያየ ነው፡፡ መንግሥት እንደ ፖለቲካ አቋም እንዲህ ብሏል፡፡ ድርጅቱ ራሱን ገምግሞ እንዲህ ብሏልና እኛ ከዚህ ተነስተን ወደ ዕርምጃ አንገባም፡፡ በማስረጃ ላይ የተመሠረተ ዕርምጃ ነው የምንወስደው፡፡ ድርጅቱ በፖለቲካ ቁርጠኝነት አልመራንም፣ ለሙስና መንሰራፋት ተጠያቂዎቹ እኛ ነን፣ የሚገባንን አላደረግንም፣ ከዚህ የላቀ ቁርጠኝነት ያስፈልገናል፣ እኛ የሥርዓቱ መሪዎች ሆነን ሙስናን አልታገልንም ነው የተባለው፡፡ በዚያ ኮንግረስ እከሌ ሙሰኛ ነው ተብሎ መረጃ አልቀረበም፡፡ እኛ ደግሞ በማስረጃ ተመሥርተን ነው ክስ የምንመሠርተው፡፡ ወደ ሕግ ለመውሰድ መረጃ ያስፈልጋል፡፡ መረጃ ይዘን ነው ፍርድ ቤት የምንሄደው፡፡ ይህን ለማድረግ በሚያስችል ደረጃ የተገለጸ ነገር የለም፡፡

ነገር ግን መንግሥት ሙስናን ለመዋጋት ቁርጠኛ ነው፡፡ ሙስናን ለመዋጋት ማንኛውንም ነገር አደርጋለሁ ብሏል፡፡ ይኼ ኮሚሽንም ቢሆን ሥራውን ለመሥራት በሚያደርገው እንቅስቃሴ ሙሉ ድጋፍ እሰጠዋለሁ በሚል ነው [የኮንግረሱን] ሐሳብ የወሰድኩት፡፡ የመንግሥት አመራር በሙሉ ሙስና ስለፈጸመ ስብስብ አድርጋችሁ የምታደርጉትን አድርጉ የሚል መልዕክት አልደረሰኝም፡፡

ጥያቄ፡- በአገሪቱ ውስጥ ከፍተኛ ሙስና እየተንሰራፋ እየመጣ ነው፡፡ ነገር ግን ኮሚሽኑ አነስተኛ ሙስና ወንጀል ላይ ያተኩራል፡፡ ከፍተኛ ሙስና የሚፈጸመው በከፍተኛ ባለሥልጣናትና ባለሀብቶች በመሆኑ ፍርኃት አለባችሁ? ለዚያ ነው ደፍራችሁ የማትገቡት?

አቶ ዓሊ፡- የምንፈራበትም፣ የማንፈራበትም ጉዳይ አለ፡፡ ትልቁ ነገር ግን ፍርኃቱ የግል ጉዳይ አይደለም፡፡ ልማት እንዳይደናቀፍ በመሥጋት ነው፡፡ ልማቱን ላለማደናቀፍ በማለት ትንሹን ነገር አስበን ትልቁ ነገር እንዳይሰናከል ከማድረግ አኳያ የምናደርገው ሊኖር ይችላል፡፡ በተረፈ ግን በራሳችን እንዲህ ብናደርግ እንዲህ ይመጣብናል የምንለው ነገር የለም፡፡ ከዚህ አንፃር ፍርኃት የለብንም፡፡      

ጥያቄ፡- በተጠናቀቀው በጀት ዓመት መንግሥታዊ ተቋማት ባካሄዷቸው ግምገማዎች ሙሰኝነት መንሰራፋቱን ያመለክታሉ፡፡ ፀረ ሙስና ኮሚሽን አምና ያከናወነው ሥራ እንዳለ ሆኖ ዘንድሮ ምን ዓይነት ተግባራትን ለማከናወን አቅዷል?

አቶ ዓሊ፡- ከሁሉም በላይ እያንዳንዱ ተቋም፣ እያንዳንዱ የመንግሥት የልማት ድርጅት ከሙስናና ከብልሹ አሠራር የፀዳ መሆኑን፣ እያንዳንዱ አመራር ማረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ የፀረ ሙስና ኮሚሽን ከዚህ ያለፈ ሥራ ነው የሚኖረው፡፡ ነገር ግን እኔ የምመራው መሥሪያ ቤት ሙስና ሲፈጸም እደነግጣለሁ ወይ? ያሳስበኛል ወይ? በእኔ የአመራር ዘመንና ጥላ ሥር የሚፈጸም ሙስና ያሳስበኛል? ያስደነግጠኛል ወይ? አስተዳደራዊ ተጠያቂነትና ፖለቲካዊ ተጠያቂነት አለ፡፡ በሌሎች አገሮች አንድ ባለሥልጣን በሚመራው መሥሪያ ቤት ውስጥ አንድ ወንጀል ወይም ችግር ሲፈጸም ባለሥልጣኑ በይፋ ሥራ ይለቃል፡፡

የፖለቲካ ተጠያቂነት ስለሚያስጨንቅ ኃላፊው ሥራውን ይለቃል፡፡ ይህ አሠራር በእኛ አገር መለመድ አለበት፡፡ እያንዳንዱ አመራር አስፈቅዶ የሚወስደውን በጀት በትክክል ለሕዝብ አገልግሎት መዋሉን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ስለዚህ ዘንድሮ በሚጀመረው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ትግበራ ትኩረት ሰጥተን የምንሠራው ይህ ተግባር፣ በሁሉ መሥሪያ ቤት ኃላፊዎች እንዲከናወን ነው፡፡ ኃላፊዎቹ ትኩረት ሰጥተዋል ወይ? እያንዳንዱ ተቋም አስፈቅዶ የሚወስደው የሕዝብና የመንግሥት በጀት አለ፡፡ ይህ በጀት ለተባለው ተግባር መዋሉን የማረጋገጥ ኃላፊነት መሥሪያ ቤቱን የሚመራው አመራር ኃላፊነት ነው፡፡

ይኼን ካላደረግን ውድቀት ነው፡፡ የእኛም ሥራ ይህንን መከታተል ይሆናል፡፡ የተዘጋጁ ሰነዶች አሉ፡፡ በሰነዱ ላይ እያንዳንዱ መሥሪያ ቤት በየወቅቱ የተገልጋዩን ሁኔታ ላይ የገመገመ በስድስት ወራት ውስጥ ሙስና አለ ወይ? በየትኛው አካባቢ ነው ሙስና ያለው? ኃላፊው ምን ባደርግ እየተፈጠረ ያለውን ሙስና ላጠፋው እችላለሁ? በማለት መሥራት አለበት፡፡ ኅብረተሰቡም ሊተባበር ይገባል፡፡ ከአሉባልታና ከሐሜት አልፎ ለሚቀርቡ ጥያቄዎችና መጠይቆች ትክክለኛ ምላሽ መስጠት አለበት፡፡ ኃላፊው ከዚህ ተነሥቶ መሥሪያ ቤቱን እንዲያስተካክል ጠቀሜታ አለው፡፡ ይህ ትብብር ከሌለ ኃላፊው ብቻውን ምንም ሊያደርግ አይችልም፡፡ ለውጥ የምናመጣው በመደጋገፍ ነው፡፡       

ጥያቄ፡- ኮሚሽኑ የባለሥልጣናት የሀብት ምዝገባ ቢያካሂድም ለሕዝብ አላቀረበም፡፡ ይህ በፀረ ሙስና ትግሉ ላይ ሳንካ አይፈጥርም ወይ?

አቶ ዓሊ፡- አዋጁ ኅብረተሰቡ ባለሥልጣናት፣ ተመራጮች ወይም የመመዝገብ ግዴታ ያለባቸው ሰዎች ያስመዘገቡትን ሀብት የማወቅ መብት አለው ይላል፡፡ ይህን መብት ግን የሚያገኘው በጽሑፍ ጥያቄ ሲያቀርብ እንደሆነ በአዋጁ ተደንግጓል፡፡ በሪፖርታችን ላይ እንደተመለከታችሁት አንድ ሺሕ የሚሆኑ ሰዎች ሀብታቸውን ያስመዘገቡ ባለሥልጣናትን ሀብት ለማወቅ በጽሑፍ ጥያቄ አቅርበው ምላሽ ተሰጥቷቸዋል፡፡ የእከሌ ሀብት ምንድነው የሚለውን ጠይቀው ምላሽ አግኝተዋል፡፡ ዛሬ (ዓርብ) ራሱ ሁለት ሰዎች ጥያቄ አቅርበው ምላሽ ሰጥተናል፡፡

የሀብት ምዝገባ የፕሮፓጋንዳ መሣሪያ አይደለም፡፡ የሀብት ምዝገባ ሙስናን ለመዋጋት እንዲረዳ ታስቦ የተዘጋጀ ነው፡፡ ሰዎች ሀብታቸውን አስመዝግበዋል፡፡ ሙሉ ሀብታቸውን አስመዝግበዋል? አላስመዘገቡም? አቶ እከሌ ሀብታቸውን ያስመዘገቡት የትኛውን ነው? ሁሉንም አስመዝግበዋል ወይ? ይህ ነው ብለን ምላሽ እንሰጣለን፡፡ አቶ እከሌ ባስመዘገበው ሀብት በተጨማሪ ሌላ ሀብት ካለው ጥያቄ አቅራቢው አጣርቶ ያመጣል፡፡ በዚህ ቦታ በዚህ ሥፍራ በዚህ አገር ይህ ሀብት አለው ብሎ መረጃ ያቀብላል፡፡

ዓላማውም ተልዕኮውም ይኸው ነው፡፡ ሰዎች በጋዜጣ ታትመ የሚወጣ ይመስላቸዋል፡፡ ይኸ አዋጅ ማመቻመች (ኮምፕሮማይዝ) ነው፡፡ በግላዊነትና በሕዝብ ጥቅም መካከል ማለት ነው፡፡

ነገር ግን ይህ አዋጅ ሲወጣ ‘አቶሜሽንን’ ከግምት አላስገባም፡፡ ነገር ግን ‘አቶሜሽን’ አሠራር ቢኖር ሰዎች እዚህ (ፀረ ሙስና ኮሚሽን) ድረስ ከመምጣት ይልቅ፣ በዌብ ሳይት መጠየቅ ይችሉ ነበር፡፡ በየትኛውም ዓለም የግለሰቦች፣ የኩባንያዎች ሀብት በጋዜጣ ላይ አይወጣም፡፡ በዝርዝር የሰው ሀብት አይወጣም፡፡

ለኮሚሽኑ የሀብት ምዝገባው ታላቅ እሴት ነው፡፡ ከዚህ በመነሳት በሚደርሰን ጥቆማ ተመሥርተን ምርመራ አካሂደን ክስ እየመሠረትን ነው፡፡ ገቢ የሆኑ በርካታ ሀብቶችም አሉ፡፡

አንድ የገጠመን ችግር አለ፡፡ አዋጁ በየሁለት ዓመቱ ምዝገባውን እንድናድስ ይጠይቃል፡፡ ይህን ማከናወን አልቻልንም፡፡ ምክንያቱም እንመዘግባለን ብለን ያሰብነው ከ30 ሺሕ አይበልጥም ነበር፡፡ ከፍ ቢል እንኳ 45 ሺሕ ነው የገመትነው፡፡ ነገር ግን ከ95 ሺሕ በላይ ነው የመዘገብነው፡፡ እንዲያውም ምዝገባውን ሳንጨርስ ሁለተኛው መመዝገቢያ ጊዜ መጥቷል፡፡ ይህን ለማድረግ የአዋጅ ማሻሻያ ይጠይቅ አይጠይቅ እያጠናን ነው፡፡

አንዳንድ አገሮች የሀብት ምዝገባ እድሳት የሚያደርጉት ከፓርላማ ሥራ ዘመን ጋር በተገናኘ ነው፡፡ እኛ ግን ከዕውቀት ማነስ በየሁለት ዓመት የምናከናውን መስሎን ነበር፡፡ አስቸጋሪ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ መመዝገቢያ ቅጹም አስቸጋሪ ነው፡፡ የወደፊቱን አስበን ያዘጋጀነው በመሆኑ ሰፋ ይላል፡፡ አንዳንድ ባለሥልጣናት ቅጽ ላይ የተቀመጡትን መጠይቆች አይተው ፈገግ ይላሉ፡፡ መርከብ አለህ ወይ

211

? አውሮፕላን አለህ ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች አሉ፡፡ ወደፊት የተሻለ ሁኔታ ሲፈጠር ሊመጣ ይችላል፡፡ ብዙዎቹ መጠይቆች የሚሠሩት ለሌሎች አገሮች ነው፡፡ ከሀብት በኋላ ወደ ፖለቲካ ለሚመጡ አገሮች ተግባራዊ የሚሆን ቅጽ ነው፡፡ እኛ አገር ከሀብት በኋላ አይደለም ወደ ፖለቲካ የምንመጣው፡፡ ከሀብት ቀድመን ነው ወደ ፖለቲካ የምንገባው፡፡        

 

ጥያቄ፡- መንግሥት ትላልቅ ሜጋ ፕሮጀክቶችን እየገነባ ይገኛል፡፡ ለእነዚህ ፕሮጀክቶች የተለያዩ ሰፋፊ ግዥዎች ይፈጽማሉ፡፡ ግዥዎቹ ምናልባት ቆይቶ ከጥራት አንፃር አገሪቱን ዋጋ ሊያስከፍሏት ይችላሉ፡፡ ነገር ግን ፀረ ሙስና ኮሚሽን በእነዚህ ፕሮጀክት አልገባም?

አቶ ዓሊ፡- ትላልቅ ፕሮጀክቶችን አትቆጣጠሩም፣ አነስተኞቹ ላይ ብቻ ነው የምታዩት የተባለው እኔ እንደ አነስተኛ አላያቸውም፡፡ በእርግጥ የኮሚሽኑ አቅም ውስን ነው፡፡ አንዳንድ ትላልቅ ግዥዎች በከፍተኛ ደረጃ የሚከናወኑ ለምሳሌ እንደ ህዳሴ ግድብ ያሉት ከጨረታ ሒደት ያለፉ ሌሎች ታሳቢ የሚደረጉ ጉዳዮች አሉ፡፡ አንዳንዶቹ ግንባታውን የማያከናውኑ አካላት በሚሰጡት ብድር የሚገዙ ናቸው፡፡ የብድሩና የግንባታው ውል አብሮ የሚፈጸም ነው፡፡ ከመደበኛ የግዥ ሥርዓት ወጣ ያሉ ናቸው፡፡ እነዚያ ውስጥ ብዙም አልገባንም፡፡ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን በመደበኛ የግዥ ሥርዓት መከናወን ያለባቸው ግዥዎች መደበኛ የግዥ ሥርዓት መከናወን አለባቸው፡፡ ግዥዎቻቸው እንዲስተካከሉ እየገፋን ነው፡፡ ከመደበኛ ሥርዓት ወጣ ያሉ ግዥዎችን እንቃወማለን፡፡ ወደ መደበኛ ግዥ እንዲገቡ ግፊት እናደርጋለን፡፡     

ጥያቄ፡- በግሉ ዘርፍ የሚፈጸም የሙስና ወንጀል ላይ የሚያስገባችሁን የሕግ ማዕቀፍ አፀድቃችኋል፡፡ በዚህ መስክ ዘንድሮ ለማከናወን ያቀዳችሁት ምንድነው?

አቶ ዓሊ፡- አደረጃጀታችንን እያየን ነው፡፡ አዲስ አበባ ላይ ብቻ አተኩሮ የሚሠራ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አቋቁመናል፡፡ አዲስ ሕንፃ ውስጥ በቅርቡ ራሱን አደራጅቶ ሥራ ይጀምራል፡፡ በሁለተኛ ደረጃም የግሉን ዘርፍ እንዴት እናስተዳድረው? ኃላፊነታችን እንዴት እንወጣ? የሚለውን እያየን ነው፡፡ ከወዲሁ አቤቱታዎችና ቅሬታዎች ቀርበው እየተመለከትንም እንገኛለን፡፡ በግሉ ዘርፍ በሁሉም ጉዳዮች ላይ ሳይሆን፣ ከፍተኛ የሕዝብ ጥቅም በሚያስጠብቁ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡ የባለድርሻ አካላትን የሚጎዳ ሲሆን እንገባለን፡፡  

ጥያቄ፡- በአዲስ አበባ አስተዳደር ከቤት ሥራ ጋር ተያይዞ በርካታ ማኅበራት በእግድ ላይ ይገኛሉ፡፡ በዚህም ዋነኛ ጥፋተኞች የሚባሉት በተለያዩ መንገዶች የተገነቡትን ቤቶችና መሬቶች ለሦስተኛ ወገን አስተላልፈዋል፡፡ ነገር ግን ሦስተኛ ወገኖች ንብረቶቹን መሸጥ መለወጥ ባለመቻላቸው እንዲሁም የባለቤትነት ዋስትናቸውም ባለመረጋገጡ ችግር ውስጥ ናቸው፡፡ ይህንን ችግር ለመፍታት ቁልፉ ያለው በኮሚሽኑ እጅ በመሆኑ ችግሩን ለመፍታት ምን አስባችኋል?

አቶ ዓሊ፡- ፀረ ሙስና ኮሚሽን ማኅበራቱ በሕገወጥ መንገድ የተቋቋሙ መሆናቸውን በሕግ አረጋግጧል፡፡ በዚህ መሀል ሦስተኛ ወገኖች በቅንነት የገቡ ይኖራሉ፡፡ ይኼ በምን መንገድ ሊስተናገድ ይገባዋል የሚለው ሐሳብ ቀርቦ ውይይት እየተደረገበት ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉንም ባማከለ መንገድ መፍትሔ ይሰጣል፡፡ ይኼ የኮሚሽኑ ብቻ ሥራ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ቁልፉ እኛ ጋ አይደለም፡፡ ቁልፉን አስረክበናል፡፡ እኛ ጥፋተኛ ማሰኘት ነው፡፡ ሕገወጥ መሆናቸውን ማረጋገጥ ነው፡፡ ፖለቲካና ማኅበራዊ ሁኔታዎችን አይቶ ውሳኔ የሚሰጠው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትም መመርያ ተሰጥቶበታል፡፡ የጊዜ ጉዳይ እንጂ ምላሽ ይሰጣል፡፡

ጥያቄ፡- ዋና ኦዲተር በተለያዩ ጊዜያት በሚያቀርባቸው ሪፖርቶች የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከግዥ ጋር በተገናኘ ከፍተኛ ሙስና ውስጥ መዘፈቃቸው ይገለጻል፡፡ ምን ዕርምጃ ተወሰደ?

አቶ ዓሊ፡- ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ቁጥራቸው እየጨመረ፣ መንግሥት የሚመድበው በጀትም እያደገ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ደግሞ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ያለው አመራሮች በአብዛኛው ልምድና ብቃት ያላቸው እንዳልሆኑ በጥናት አረጋግጠናል፡፡ አንዱ ብዙዎቹ የአካዳሚ ሰዎች ናቸው፡፡ ቀጥታ ከትምህርት ቤት ነው ወደዚህ አመራርነት የሚመጡት፡፡ በዚህ ምክንያት ሕግና መመርያ ከመጠበቅ አኳያ ክፍተት እንዳለ ተረድተናል፡፡ ይህ ከልምድ ማነስና ከአመራር ብቃት ማነስ ጋር ተያይዞ የተከሰተ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በተለይ ከአመራሩ ሥር ያሉ ባለሙያዎች የተወሰነ ልምድ ያላቸው በመሆናቸው፣ የአመራሩን አለማወቅ የመጠቀም አዝማሚያ ያላቸው አሉ፡፡ ይህ ጉዳይ በዋና ኦዲተርም በተደጋጋሚ ይነሳል፡፡ ከዚህ በመነሳትም የመሠረትናቸው ክሶች አሉ፡፡

ሙስና ከመፈጸሙ በፊት ደርሰን ያተረፍነውም አለ፡፡ ለዚህ አንዱ ምክንያት የልምድ ችግር ነው፡፡ መንግሥት አመራር በሚመድብበት ወቅት ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ተቋማቱ አዲስ እንደ መሆናቸው ሥርዓቱን አለማወቅና አለመለማመድ በመኖሩ ሥልጠና እየሰጠን ነው፡፡ ተቋማቱ ከፍተኛ ወይም በቢሊዮን የሚቆጠር በጀት የሚመደብላቸው በመሆኑ፣ በጀቱ በበዛ ቁጥር ችግሩ ስለሚሰፋ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፡፡      

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች