Tuesday, February 27, 2024

ያለፉት ሦስት ዓመታት በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም አመራር ሥር

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

የዛሬ ሦስት ዓመት ነሐሴ 14 ቀን 2004 ዓ.ም. ጐህ ሲቀድ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን በርካታ ኢትዮጵያውያንን ያስደነገጠ የሐዘን ዜና አስደመጠ፡፡ ለወራት ስለአቶ መለስ ዜናዊ መሰወር ሲጠበቡ የነበሩ ኢትዮጵያውያን በተለያዩ የአገሪቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የመሪያቸው መጥፋት እውነት ዘግይቶ ቢነገራቸውም፣ አሁንም ከጥርጣሬና መላ ምቶችን ከመሰንዘር አልቦዘኑም፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ስለአገሪቱ መሪ ይሰጡ የነበረው መረጃ በርካቶችን በተስፋና ግራ መጋባት ውሰጥ የከተተ ነበር፡፡ ‹‹የአገሪቱ መሪ እያገገሙ ነው፡፡ በቅርቡ ወደ ኃላፊነታቸው ይመለሳሉ›› የሚል መልዕክት ያዘሉ መረጃዎች ተስፋ ቢሰጡም፣ የእርሳቸው በምንም አጋጣሚ አለመታየት ወይም አለመሰማት ግን ግራ መጋባትን ፈጥሮ ነበር፡፡ ለዚህም ነው የነሐሴ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. የንጋቱ 12 ሰዓት ዜና በበርካቶች ዘንድ ድንጋጤን ፈጥሮ የነበረው፡፡ በሕዝብ ትራንስፖርቶች ውስጥ ዝምታ ሰፈነ፡፡ የሚግባቡ ሐዘናቸውን ይለዋወጣሉ፡፡ የተለያዩ የውጭ መገናኛ ብዙኃን ቀጣይ የኢትዮጵያን ዕጣ ፈንታ ይተነብያሉ፡፡ ከ20 በላይ ዓመታት ኢትዮጵያን ሲያስተዳድሩ የነበሩት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትርን ሊተካ የሚችል መሪ አለመዘጋጀቱን በመጥቀስ መላ ምቶች በየቦታው ይሰነዘራሉ፡፡ እርግጠኛ አለመሆን፣ ፍርኃት፣ ስለወደፊቱ መጨነቅ ወቅቱ የፈጠረው ግዴታ ነበር፡፡

እንደዚህ ዓይነት ድንገተኛ ሞት በአገሪቱ መሪ ላይ ቢከሰት የአገሪቱን ሥልጣን ማን ይረከባል የሚለው በሕገ መንግሥቱ በግልጽ አለመቀመጡ የወቅቱ ውዥንብር ሌላኛው መነሻ ነበር፡፡ የሥልጣን ክፍተቱ ለአለመረጋጋት መንስዔ ሊሆን ይችላል፣ ገዥው ፓርቲ ራሱ እርስ በእርሱ ይከፋፈላል የመሳሰሉት ይሰነዘሩ ነበር፡፡ ግብፅ ይህንን የሥልጣን ክፍተት በመጠቀም የታላቁ ኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን ለማስቆም የራሷን ጥረት ታደርጋለች፣ ኤርትራም ተወስዶብኛል የምትለውን መሬቷን ለማስመለስና የቀደመ ሽንፈቷ ማገገሚያ ታደርገዋለችና የመሳሰሉ ትንታኔዎች ይሰጡ ነበር፡፡ ከእነዚህ ተንታኞች መካከል ደግሞ መቀመጫውን በብራሰልስ ያደረገው ታዋቂው ኢንተርናሽናል ክራይስስ ግሩፕ ይገኝበታል፡፡

በዚሁ መኸል ደግሞ በወቅቱ የአገሪቱ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የሥልጣን ክፍተቱን እንዲሸፍኑ ይደረጋል በሚል ስማቸው ተያይዞ ይነሳ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ እርሳቸው ኢሕአዴግን ከመሠረቱት አባል ድርጅቶች መካከል በዕድሜ ገና ወጣት ከሆነው ደኢሕዴን መምጣታቸውና በትግሉ ወቅት ተሳታፊ አለመሆናቸው፣ በዚህ ፈታኝ ወቅት የዚህ ሥልጣን ኃላፊነት ሊወድቅባቸው አይችልም የሚሉት መላምቶችና በሕይወት የተለዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ከመጀመሪያውም ለዚህ ሥልጣን አጭተዋቸዋል የሚለው ያለየለት መከራከሪያ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ዘጠነኛ ጉባዔውን በባህር ዳር ያደረገው ገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ አቶ ኃይለ ማርያምን የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጐ መረጠ፡፡ በመሆኑም በፓርቲው ልማዳዊ አሠራር መሠረት ማለትም የፓርቲው ሊቀመንበር ከዚህ ቀደም ለነበሩት በርካታ ዓመታት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረ በመሆኑ፣ አቶ ኃይለ ማርያምም ይህንን ኃላፊነት እንደሚረከቡ ፍንጭ ሰጠ፡፡

በ2005 ዓ.ም. በመስከረም ወር መጨረሻ ላይ ሥራውን የጀመረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በመጀመሪያ ውሎው ይህንን የሥልጣን ክፍተት ለመመለስ አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝን ለቀሪዎቹ ሦስት ዓመታት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጐ በሙሉ ድምፅ ሾመ፡፡ ከዚህ ሹመት በፊት ሲነሱ የነበሩ የፖለቲካ አለመረጋጋት መላ ምቶች ግን ከሥልጣን በኋላም ቀጥለዋል፡፡ በመሆኑም አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር እነዚህ ፈተናዎችን በአግባቡ ማለፍ ነበረባቸው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ካለፉባቸው ፈተናዎች መካከል ዋና ዋናዎቹ እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች

በመጀመሪያዎቹ ወቅቶች ከገጠሙ ፈተናዎች መካከል አንዱ ኢኮኖሚውን የገጠመው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ነው፡፡ በወቅቱ የውጭ ምንዛሪ ክምችት በበቂ ሁኔታ መኖር አለመኖርን በመረጃ ለማስቀመጥ አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ባንኮች የአገሪቱን ነጋዴዎችና ኢንቨስተሮች የውጭ ምንዛሪ ጥያቄን መመለስ አልቻሉም ነበር፡፡ በኋላ ላይ የውጭ ምንዛሪው እጥረት አርቲፊሻል መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ለፓርላማው ይፋ አደረጉ፡፡ በወቅቱ በነበረው የሥልጣን ሽግግር የተነሳ በርካታ ባለሀብቶች ከዚህ ቀደም ሲጠይቁት ከነበረው የውጭ ምንዛሪ ብዙ እጥፍ ጥያቄ በማቅረባቸው እንጂ፣ የምንዛሪ እጥረት አለመከሰቱን ይፋ አደረጉ፡፡ ባለሀብቶቹ ይህንን የተጋነነ ጥያቄ ለማቅረብ ምክንያት የሆናቸው አገሪቱ አትረጋጋም ከሚል እምነታቸው መሆኑን ገለጹ፡፡

ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ይህ የመጀመሪያ ፈተና ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ባለፉት ሦስት ዓመታት አቶ ኃይለ ማርያምም ምናልባትም ከአቶ መለስ የተሻሉ አፈጻጸሞችን በኢኮኖሚው ዘርፍ አስመዝግበዋል፡፡ ከእነዚህ ውስጥ በወቅቱም ሆነ ከዚያ በፊት በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ እንደ ካንሰር ይቆጠር የነበረው የዋጋ ንረት አንዱ ነው፡፡ እርሳቸው ወደ ጠቅላይ ሚኒስትርነት በመጡበት ወራት አጠቃላይ የአገሪቱ የዋጋ ግሽበት 40 በመቶ ተጠግቶ ነበር፡፡ ምንም እንኳን የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር አጠቃላይ የሞኒተሪ (የገንዘብ) ፖሊሲ አፈጻጸም ውጤት በመሆኑ ሙሉ በሙሉ የውጤቱን ዕውቅና ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም መስጠት ባይቻልም፣ እስከ 2007 ዓ.ም. ሐምሌ ወር ድረስ አጠቃላይ የዋጋ ግሸበቱ ከአሥር በመቶ በታች ወይም ወደነጠላ አኃዝ መውረድ ችሏል፡፡

በተመሳሳይ አገሪቱ በአለመረጋጋት ቀውስ ውስጥ ትወድቃለች ተብሎ በተሰጋበት ጊዜ ከፍተኛ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በጥራት ጭምር ወደ አገሪቱ መግባት ችሏል፡፡ ከእነዚህም መካከል የቻይናው ጆርጅ ሹዝ፣ የስዊድኑ ኤችኤንድኤም፣ የእንግሊዙ ዩኒሊቨርና ቴስኮ ጥቂቶቹ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት 1.5 ቢሊዮን ዶላር በመሆን ከአፍሪካ ከቀዳሚዎቹ  ተርታ ተመዝግቧል፡፡ በዚሁ በኢኮኖሚ ዘርፍ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ በታሪኳ ከፈጸመቻቸው ተግባራት መካከል አንዱ የሆነው፣ የአገሪቱን የውጭ ብድር የመሸከምና የመክፈል አቅምን ማስመዘንና ለመጀመሪያ ጊዜ ለዓለም አቀፍ ገበያ ቦንድ ሽያጭ የተከናወነውም፣ በዚሁ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም የሦስት ዓመታት የሥልጣን ዘመን ነበር፡፡ በመሆኑም የአገሪቱ ብድር የመሸከምና የመክፈል አቅም በዓለም አቀፍ ደረጃ በታወቁት ሦስት ኩባንያዎች ተመዝኖ ‹‹ቢ›› ደረጃን ከዓመት በፊት ማግኘቱ ይታወሳል፡፡ ይህንን መነሻ አድርጐ የተከናወነው የቦንድ ሽያጭም በሦስት ቀናት ውስጥ አንድ ቢሊዮን ዶላር በማግኘት ተጠናቋል፡፡

አመጽ

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በሙሉ ድምፅ በፓርላማው ከተመረጡ ከቀናት በኋላ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የእስልምና እምነት ተከታዮች ወደ ጐዳና ወጥተዋል፡፡ ጥያቄያቸው ደግሞ መንግሥት በሃይማኖታቸው ውስጥ እየገባ እንደሆነ የሚገልጽ ነበር፡፡ ይኸው ተቃውሞ በተለይም የእምነቱ ተከታዮች የፀሎት ቀን በሆነው ዓርብ ዕለት በየጊዜው ይቀሰቀስ ነበር፡፡ በእርግጥ ይህ የእስልምና ተከታዮች ተቃውሞ ማቆጥቆጥ የጀመረው በአቶ መለስ ዜናዊ የሥልጣን ዘመን ነበር፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ የመጨረሻ የፓርላማ ንግግራቸውን ባደረጉበት ወቅት ካነሷቸው ሐሳቦች መካከልም አንዱ ይኸው ጉዳይ ነበር፡፡ አቶ መለስ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑት በሺዎች የሚቆጠሩ ተቃውሞ አቅራቢዎች እንደሚሉት መንግሥት ጣልቃ አልገባም ማለታቸው ይታወሳል፡፡

አቶ መለስ ችግሩን የገለጹበት መንገድም እንደሚከተለው ነበር ‹‹በአርሲና በባሌ የአልቃይዳ ሴሎችን አግኝተናል፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ የሰለፊ አስተምህሮን ማስፋፋት ይፈለጋል፡፡ በእርግጥም ሁሉም የሰለፊ አስተምህሮ ተከታዮች የአልቃይዳ አባል አይደሉም፡፡ ነገር ግን ሁሉም የአልቃይዳ አባሎች ሰለፊዎች ናቸው፤›› በማለት በኢትዮጵያ ውስጥ የሰለፊ እምነትን መከተል መብት ቢሆንም፣ ከጀርባ ለመፍጠር እየተፈለገ ነው ያሉትን ሃይማኖታዊ መንግሥት ይፋ አድርገዋል፡፡

በመሆኑም ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ከዚህ አስቸጋሪ ጉዳይ ጋር መጋፈጥ ሌላኛው ፈተና ነበር፡፡ ከዚህ የእስልምና እምነት ጥያቄና እንቅስቃሴ በስተጀርባ ለሌላ ተልዕኮ ሲንቀሳቀሱ ነበሩ የተባሉ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በሽብር ተከሰሱ፡፡ ረጅም ጊዜን ከፈጀ የፍርድ ሒደት በኋላም ተከሳሾቹ ከሰባት ዓመት እስከ 22 ዓመታት በቅርቡ እንደተፈረደባቸው ይታወሳል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በሦስት ዓመት ቆይታቸው ሌላው የተፈተኑበት ጉዳይ የ11 ሰዎችን ሕይወት የቀጠፈው፣ በኦሮሚያ ክልል በሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥና በአካባቢው ነዋሪዎች የአዲስ አበባና የኦሮሚያ የተቀናጀ ማስተር ፕላንን በመቃወም የተቀሰቀሰው ተቃውሞ ነበር፡፡

ተማሪዎቹና የአካባቢው ነዋሪዎች የማስተር ፕላኑ ድብቅ ዓላማ የአዲስ አበባን ግዛት ወደ ኦሮሚያ ልዩ ዞን ማስፋት ነው የሚል ነበር፡፡ ይህ አስተሳሰብ አመራር ላይ በነበሩ አንዳንድ የክልሉ ፓርቲና የመንግሥት አመራሮች ጭምር በመታየቱ ሥጋቱ ከፍተኛ ነበር፡፡

ማስተር ፕላኑን ለመተግበር ከመንቀሳቀሱ በፊት በቂ የሕዝብ ውይይት አለመደረጉ የመንግሥት ስህተት ነው በማለት በዚህ ረገድ ተጠያቂነቱን መንግሥት ወስዷል፡፡ በመሆኑም ክልሉን የሚወክለው የኢሕአዴግ መሥራች ድርጅት ኦሕዴድ ከፍተኛ አመራሮች የኦሮሞ ሕዝብን የማወያየት ሥራ አከናውነዋል፡፡

የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በዚህ ተቃውሞ ሕይወታቸውን ላጡ 11 ዜጐች ማዘናቸውን ቢገልጹም፣ የሞታቸው ምክንያት እንዲጣራና እንዲገለጽ አልተደረገም፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝም በጉዳዩ ላይ ይፋዊ መግለጫ ሲሰጡ አልተስተዋሉም፡፡ ይህ የጋራ ማስተር ፕላን በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በኩል የፀደቀ ሲሆን፣ በጨፌ ኦሮሚያ በኩል እንደሚፀድቅ ይጠበቃል፡፡

ሙስና

አቶ ኃይለ ማርያም የጠቅላይ ሚኒስትርነት ሹመትን ካገኙ ከሰባት ወራት በኋላ የወሰኑበት ጉዳይ ደግሞ፣ የአገሪቱ ከፍተኛ የታክስ ባለሥልጣናትና ተፅዕኖ መፍጠር የሚችሉ የንግድ ማኅበረሰቡ አካል የሆኑ ግለሰቦች በሙስና እንዲጠየቁ ማድረግ ነበር፡፡

የካቢኔ አባል የሆነ ባለሥልጣን ለመጀመሪያ ጊዜ በሙስና የተጠየቀው በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዘመን እነ አቶ ታምራት ላይኔ ላይ ነበር፡፡ ከዚህ በኋላ የተከሰተው የገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተርና የካቢኔ አባል አቶ መላኩ ፈንታና ምክትላቸው አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ ከሌሎች 60 በሚሆኑ የንግዱ ማኅበረሰብ አባላትና ሌሎች ሠራተኞች ላይ የቀረበው ሁለተኛው ክስተት ነው፡፡

ይህንን ውሳኔ ከመወሰናቸው በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ  ማርያምም የሚገጥማቸውን ተፅዕኖ መገምገምና መመዘን አንዱ ፖለቲካዊ ፈተናቸው መሆኑ ግልጽ ነው፡፡

ዕርምጃው ከተወሰደና ለሕዝብ ይፋ ከሆነ በኋላ ያገኙት ግብረ መልስ ግን ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚጠይቅ ነው፡፡ ምንም እንኳን ከዚህ በኋላ በተመሳሳይ ሁኔታ ከፍተኛ ባለሥልጣናት በሙስና ሲጠየቁ ባይታይም፡፡

ግብፅ

በዓባይ ወንዝ ጉዳይ ኢትዮጵያና ግብፅ ላለፈው ምዕተ ዓመት ተግባብተው አያውቁም፡፡ ግብፅ በቅኝ ግዛት ዘመን የፈረመችው የውኃ አጠቃቀም ውል 85 በመቶ የውኃውን የመጠቀም መብት ይፈቅድላታል፡፡ የላይኛው ተፋሰስ አገሮች በዓባይ ወንዝ ላይ ማንኛውንም ግንባታ ከማካሄዳቸው በፊት የግብፅን ይሁንታ እንዲጠይቁ ይገደዳሉ፡፡ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለሰ ዜናዊ ሌሎች የተፋሰሱ አገሮችን በማስተባበር ከ12 ዓመታት በላይ ከግብፅ ጋር ያደረጉት ውይይት የቅኝ ግዛቶቹን ውሎች በመሻር እንዲጠናቀቅ ሆኗል፡፡

ይሁን እንጂ ግብፅ ታሪካዊ የሆነው የውኃ መጠቀም መብቷ እንዲከበርላት የማትፈነቅለው ድንጋይ የለም፡፡ ነገር ግን ኢትዮጵያ ከአራት ዓመታት በፊት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን መጀመሯ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል አዲስ ውጥረት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል፡፡ የጦርነት ቃላት በግብፅ በኩል መሰንዘር መጀመራቸውና የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ተመሳሳይ ምላሾች በርካቶችን አስደንግጠዋል፡፡ አቶ መለስ በተደጋጋሚ ጊዜ ‹‹ግብፅ ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት አትገጥምም፡፡ ቀጥታ ባልሆነ መልኩ ከዚህ ቀደም ኢትዮጵያን ለመበጥበጥ የሄደችባቸው መንገዶችም ቢሆኑ እንደከዚህ ቀደሙ ውጤታማ አይሆኑም፤›› ብለው ነበር፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ይበሉ እንጂ በኢትዮጵያና በግብፅ በኩል መሆን ያለበት የሠለጠነ ውይይትና ለጋራ ጥቅም መሥራት ብቸኛው አማራጭ እንደሆነ መጠቆማቸው የተለመደ ነው፡፡ ይህ ጥረት በተወሰነ መልኩ ሁለቱን መንግሥታት ቢያቀራርብም አለመተማመን በፈጠረው አለመግባባት በተደጋጋሚ ሲቋረጥ ተስተውሏል፡፡

ከአቶ መለስ ሕልፈት አንድ ዓመት በኋላ የዓባይ ውኃ ተፈጥሯዊ መስመር ለግንባታ ሲባል ተቀየረ፡፡ ይህ ዕርምጃ ግብፆችን አስቆጣ፡፡ በወቅቱ የነበሩት ፕሬዚዳንት መሐመድ ሙርሲ የአገሪቱን ፖለቲከኞች በመሰብሰብ በቀጥታ ቴሌቪዥን አወያዩ፡፡ እናም እስከ ጦርነት በመሄድ የኢትዮጵያን ግድብ ግንባታ ማስቆም እንደሚገባ መከሩ፡፡

የዓለም የሚዲያዎች ይህንን እየተቀባበሉ ቢዘግቡትም ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ለዚህ ምላሽ ባለመስጠት በሰከነ መንገድ እንዲያልፍ አደረጉ፡፡ የግብፅ አብዮት ማብቃትን ተከትሎ ወደ ሥልጣን የመጡት አብዱልፈታህ አልሲሲ ላይ እምነት የጣሉት አቶ ኃይለ ማርያም፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው በኩል የውይይት ጥያቄ አቀረቡ፡፡ ይህንን ጥያቄ ተከትሎም ሁለቱ መሪዎች በኢኳቶሪያል ጊኒ ከተማ ማላቡ በአፍሪካ ኅብረት የመሪዎች ጉባዔ ላይ ተገናኙ፡፡

በወቅቱ ባደረጉት የጐንዮሽ ውይይት ባለ ሰባት ነጥቦች የመግባቢያ ስምምነት ላይ ደረሱ፡፡ የዚህ ስምምነት ማጠንጠኛ የዓባይ ወንዝን ለጋራ ጥቅም ማዋልን ይመለከታል፡፡ ከጥቂት ወራት በኋላ በመጋቢት ወር 2007 ዓ.ም. ኢትዮጵያ፣ ግብፅና ሱዳን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ‹‹ዲክላሬሽን ኦፍ ፕሪንሲፕል›› (የመርህ መገለጫ ሰነድ) ተፈራረሙ፡፡ በመጨረሻም የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ኢትዮጵያን በመጐብኘት በፓርላማ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ወንድማማችነትንና መተባበርን የሚጠይቅ ንግግር አደረጉ፡፡

በማንኛውም መልኩ ቢታይ ግብፅ የፈረመችው ‹‹ዴክላሬሽን ኦፍ ፕሪንሲፕል›› (የመርህ መገለጫ ሰነድ) በዓባይ ፖለቲካ ውስጥ ታሪካዊ ነው፡፡ ይህም ግብፅ ለመጀመሪያ ጊዜ በፊርማዋ ኢትዮጵያ የዓባይ ውኃን የመጠቀም ሕጋዊ መብት እንዳላት እንዳረጋገጠች ተወስዷል፡፡

የውጭ ግንኙነት

ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት (አይሲሲ) አፍሪካውያን መሪዎችን እያሳደደ ነው በማለት፣ በመጀመሪያ ያወገዙት የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስ ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በሦስት ዓመታት ቆይታቸው የመጀመሪያ ዓመት የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበርነታቸውን በመጠቀም፣ ዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤትን ‹‹ዘረኛና ጥቁር መሪዎችን ብቻ እያሳደደ ፍትሕ አስፋኝ ለመሆን የሚጥር›› በማለት አወገዙት፡፡ በመሆኑም በወቅቱ በፍርድ ቤቱ ይፈለጉ ለነበሩት የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡህሩ ኬንያታና ምክትላቸው ዊሊያም ሩቶ፣ እንዲሁም ለሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሐሰን አል በሽር አጋርነታቸውን አሳዩ፡፡ የአፍሪካ ኅብረትን በመጠቀምም የአፍሪካ አገሮች ከዓለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት አባልነት እንዲወጡ ጠየቁ፡፡ አቶ ኃይለ ማርያም በዚህ ረገድ ተሰሚነትን ቢያገኙም፣ ኢትዮጵያ ያዋለደቻት ደቡብ ሱዳን ገና እንደ አገር ሳትቆም ከገባችበት የእርስ በእርስ አዘቅት ውስጥ የማውጣት ኃላፊነትን እንደ ጐረቤት አገር መሪና እንደ ኢጋድ ኃላፊነቱን ቢወስዱም፣ እሰከዛሬ የለወጡት ነገር የለም፡፡      

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -