Tuesday, February 27, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፒኤስኤስ ከ1.7 ሚሊዮን በላይ የገንዘብ ዝውውር መልዕክቶችን አስተላለፈ

ተዛማጅ ፅሁፎች

–  አዳዲስ የክፍያ ካርድ አገልግሎቶችን ሊጀምር ነው

ዘመናዊ የባንክ አገልግሎቶችን ለመስጠት የተቋቋመውና ስድስት ባንኮችን በአባልነት የያዘው ፕሪሚየም ስዊች ሶሉሽንስ (ፒኤስኤስ) አክሲዮን ማኅበር፣ በ2007 በጀት ዓመት ከ1.7 ሚሊዮን የኤቲኤም ትራንዛክሽን መልዕክቶችን ለአባል ባንኮቹ ያስተላለፈና ያቀነባበረ መሆኑን አስታወቀ፡፡ የብድር፣ የቅድሚያ ክፍያና ከወለድ ነፃ የካርድ አገልግሎቶችን ለመጀመር እየተዘጋጀ ነው፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ ባለፈው ሐሙስ ይፋ እንዳደረገው፣ እስከ 2007 በጀት ዓመት መጨረሻ ድረስ ከ250 ሺሕ በላይ የፒኤስኤስ ካርዶችን፣ ከ230 በላይ ኤቲኤሞችንና ከ300 በላይ ፖይንት ኦፍ ሴል ተርሚናሎችን ወደ ክፍያ መረቡ ማገናኘት ችሏል፡፡

በዚህም ተግባሩ በኤቲኤም የክፍያ ካርድ አገልግሎቱ ከተስተናገዱ 1.7 ሚሊዮን የገንዘብ ዝውውሮች በተጨማሪ፣ 3,600 የፖስ ትራንዛክሽን መልዕክቶችን ለአባል ባንኮች ማስተላለፍ መቻሉን የአክሲዮን ማኅበሩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ጌታነህ ገልጸዋል፡፡

በበጀት ዓመቱ የደረሰበት ደረጃ አክሲዮን ማኅበሩ ሥራ ከጀመረበት ጊዜ ወዲህ ያስተላለፋቸውን የትራንዛክሽን መልዕክቶች ቁጥር ከ2.3 ሚሊዮን በላይ ማድረሱን፣ በዚህም 2.2 ቢሊዮን ብር ማዘዋወር ችሏል ተብሏል፡፡

አገልግሎቱ በአንድ የክፍያ ካርድ ስድስቱም አባል ባንኮች በተከሉዋቸው የኤቲኤም ማሽኖች አንዱ በሌላኛው መገልገል የሚያስችል ነው፡፡ የአንዱ ባንክ ደንበኛ በሌላኛው ባንክ የክፍያ ማሽን የመገልገሉ ልምድ እያደገ እንደመጣና ለዚህም በበጀት ዓመቱ 34 በመቶ የሚሆነው አገልግሎት የተሰጠው የአንዱ ባንክ ደንበኛ በሌላኛው ባንክ የክፍያ ማሽኖች ላይ የተጠቀሙ ለመሆናቸው በአስረጅነት ቀርቧል፡፡ ይህም አክሲዮን ማኅበሩ የተመሠረተበትን ዓላማ እያሳካ መሄዱን ያመለከተ ነውም ተብሏል፡፡

ፒኤስኤስ ሁሉን አቀፍ የሆነና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ሲስተም በመዘርጋት የተለያዩ አገልግሎቶችን ለአባል ባንኮች በማቅረብ ቀልጣፋና አስተማማኝ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛልም ተብሏል፡፡ በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ ባንኮቹ ይህን ሲስተም ተጠቅመው የክፍያ ካርዶችን ለደንበኞቻቸው እያሰራጩና የገንዘብ መክፈያና የክፍያ መቀበያ ማሽኖችን በተለያዩ ቦታዎች እየተከሉ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

ኩባንያው ከአገር ውስጥ ካርዶች በተጨማሪ ባንኮች የውጭ አገር ካርዶችን ተቀብለው እንዲያስተናግዱ የሚያደርግ መሆኑን አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡ ባለፈው በጀት ዓመት ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ሥራ ከጀመረው የማስተር ካርድ መረብ በተጨማሪ፣ ፒኤስኤስን ከቪዛ መረብ ጋር የማገናኘቱ ሥራ በ2007 ዓ.ም. ተጠናቆ ከቪዛ የአባልነት ማረጋገጫ ያገኙት ባንኮች የቪዛ ካርድን በኤቲኤሞቻቸው ላይ እንዲቀበሉ አስችሏል፡፡

በተጨማሪም ከዩኒየን ፔይ ኢንተርናሽናል ጋር በገባው ውል መሠረት የሲስተም ማገናኘቱን ሥራ በማጠናቀቅ ላይ መሆኑም ተመልክቷል፡፡ ይህም ተጠናቆ ሲያልቅ አባል ባንኮች ለክፍያ የሚቀበሏቸውን የውጭ አገር ካርድ ዓይነቶች ሦስት ያደርሰዋል፡፡ ፒኤስኤስ ከሌሎች የውጭ የካርድ ድርጅቶች ጋር ግንኙነት የመፍጠሩንም ሥራ የሚቀጥል መሆኑን አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ፒኤስኤስ አሁን አባል ባንኮችን እየጠቀሙባቸው ካሉት የአገልግሎት ዓይነቶች በተጨማሪ የቅድሚያ ክፍያ ካርድ፣ የብድር ካርድና ከወለድ ነፃ ካርድ አገልግሎቶችን ዝግጁ እያደረገ መሆኑ ተገልጿል፡፡ በቀጣዩ በጀት ዓመትም በመረጃ መረብ ግብይት፣ በሞባይል ክፍያ፣ በውጭ ሐዋላና ለተወሰኑ አገልግሎቶች ብቻ የሚውሉ እንደ ፔትሮሊየም ካርድ ያሉ የካርድ ዓይነቶች ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር ለመጀመር ዝግጅቱን እንዳጠናቀቀም የአቶ ብርሃኑ ማብራሪያ ያስረዳል፡፡

ፕሪሚየር ስዊች ሶሉሽንስ በ2007 ዓ.ም. አሳክቼዋለው ብሎ ካቀረባቸው ክንውኖች መካከል ዋነኛው የውጭ ካርዶችን መረጃ ለማስተላለፍ፣ ለማቀናበርና ለማጠራቀም እንደ ቅድመ ሁኔታ የሚቀመጠውን ማረጋገጫ ማግኘቱ ነው፡፡ የፒሲአይዲኤስኤስ (Payment Card Industry Data Security Standard) ወይም የክፍያ ካርድ መረጃ ደኅንነት ሰርቲፊኬሽን በመጀመር ከፍተኛ የሆነ ሲስተም ፍተሻ ሲያደርግ ቆይቶ፣ ሒደቱን በብቃት በመወጣት ዓለም አቀፍ የደኅንነት ማረጋገጫ ሰርቲፊኬቱን ማግኘቱም ተገልጿል፡፡

ይህም ፒኤስኤስ በቪዛ የካርድ መረጃ ደኅንነት ማረጋገጫ ባገኙ የክፍያ አስተላላፊዎች ዝርዝር መሠረት ከኢትዮጵያ አንደኛ፣ ከምሥራቅ አፍሪካ ደግሞ ሦስተኛው ኩባንያ መሆን እንዳስቻለው አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል፡፡

ማረጋገጫው የፕሪሚየር ስዊች ሶሉሽንስ አባል ባንኮችን ከዘመናዊ የክፍያ ሥርዓት ጋር ተያይዘው ከሚነሱ የደኅንነት ሥጋቶች ነፃ እንዲያደርጋቸው፣ የተለያዩ አዳዲስ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አገልግሎቶችን ለደንበኞቻቸው በነፃነት እንዲያቀርቡ የሚረዳቸው መሆኑን አቶ ብርሃኑ ገልጸዋል፡፡

አክሲዮን ማኅበሩ ከአምስት ዓመት በፊት ሲቋቋም መሥራች ባለአክሲዮን በመሆን ያቋቋሙት አዋሽ፣ ኅብረትና ንብ ባንኮች መሆናቸው ይታወሳል፡፡ ብርሃን፣ አዲስና የኦሮሚያ ኅብረት ሥራ ባንኮች አክሲዮን ማኅበሩን የተቀላቀሉት ሦስቱ ባንኮች በጥምረት ሆነው ሥራ ከጀመሩ በኋላ ነው፡፡

ስድስቱ ባንኮች በጥቅሉ ከአምስት ሚሊዮን ያላነሱ ደንበኞች አሉዋቸው፡፡ በ2008 በጀት ዓመት ስድስቱም ባንኮች ተጨማሪ ኤቲኤም ማሽኖችን ለመትከል የተዘጋጁና በጀት የያዙ ሲሆን፣ በበጀት ዓመቱ ይጨምራሉ ተብሎ በሚጠበቀው ኤቲኤም ምክንያት ደንበኞቻቸው የሚገለገሉባቸውን ኤቲኤሞች ቁጥር ከ600 በላይ ያደርሰዋል፡፡ አሁን ሁሉም 250 ኤቲኤም ማሽኖች አሉዋቸው፡፡

 

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች