በአሜሪካ ኤምባሲ በተካሄደ ሥነ ሥርዓት 62 አሜሪካ የሰላም ጓድ አባላት በኢትዮጵያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች የእንግሊዝኛ ቋንቋን ለማስተማርና ሌሎች ኅብረሰተብ አቀፍ ድጋፎችን ለመስጠት ቃለ መሃላ ፈጸሙ፡፡
የአሜሪካ ኤምባሲ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ መሠረት መስከረም 7 ቀን 2007 ዓ.ም. በተካሄደው የቃለ መሃላ ሥነ ሥርዓት የሰላም ጓድ አባላቱ በትግራይ፣ በአማራ፣ በአሮሚያና በደቡብ ክልሎች ውስጥ በሚገኙ የሁለተኛ ደረጃ ትምርህርት ቤቶች እንግሊዝኛ ቋንቋን ከማስተማር ባሻገር፣ በበጎ ፈቃደኛነት የተለያዩ ማኅበረሰብ ተኮር ፕሮጀክቶችን ለማስፈጸም ቃለ መሃላ ፈጽመዋል፡፡
የእንግሊዝኛ ቋንቋን በኢትዮጵያ ትህምርት ተቋማት የማስፋፋት ዓላማ ይዞ የተነሳው ፕሮጀክት አካል የሆኑት የበጎ ፈቃድ የሰላም ጓዶች፣ ከዘጠነኛ እስከ 11ኛ ባሉት ክፍሎች እየተመደቡ እንደሚያስተምሩ ታውቋል፡፡ ለሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ከሚሰጠው የቋንቋ ትምህርት በተጨማሪ ለመምህራን ሥልጠናዎችን እንደሚሰጡም ይጠበቃል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም በማኅበረሰብ አቀፍ ፕሮጀክቶች በኩል ከሕዝብ ጋር በመተባበር የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ እንዲሰባሰብ በማስተባበር፣ ለማኅበረሰቡ በፆታ እኩልነት ላይ ያተኮሩና ሌሎች ከትምህርት ክፍለ ጊዜ ውጪ ባሉ ተግባራት ላይ ተሳትፎ እንደሚያደርጉ ኤምባሲው አስታውቋል፡፡
የሰላም ጓዶቹ የሦስት ወራት የቅደመ ማስተማር ሥልጠናዎችን ጨምሮ የማስተማሪያ ሥልቶችን፣ የትምህርት ሥነ ዘዴዎችንና የአራት ቀናት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ተግባራዊ የማስተማር ልምምድ ማድረጋቸውን የአሜሪካ ኤምባሲ ገልጾ፣ በሆለታና አካባቢው ለሚገኙ አንድ ሺሕ ያህል ተማሪዎች የክረምት ወራት የእንግሊዝኛ ቋንቋ ሥልጠና ሲሰጡ መቆየታቸውን አስታውቋል፡፡
የሰላም ጓዶች በየተመደቡባቸው ክልሎች ተሰማርተው በሕዝቡ መካከል ሲኖሩ በቀላሉ ለመግባባት እንዲያስችላቸው ሲባል የአማርኛ፣ የትግርኛና የኦሮምኛ ቋንቋ ሥልጠና መከታተላቸውም ታውቋል፡፡