በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መንግሥት በመላ አገሪቱ በሚገኙ አርሶ አደሮች ዘንድ የበቆሎ ምርትን በእጥፍ ለመጨመር መታቀዱ ተገለጸ፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ፈንታሁን መንግሥቱ ይህን ያስታወቁት፣ ላለፉት ስምንት ዓመታት ሲሠራበት የቆየውን “ድርቅን ተቋቋሚ በቆሎ ለአፍሪካ” የተሰኘው ፕሮጀክት መጠናቀቁን አስመልክቶ ከመስከረም 3 ቀን እስከ 6 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ከ13 የአፍሪካ አገሮች የተውጣጡ ከፍተኛ የግብርና ባለሙያዎች፣ ምሁራንና የመንግሥት ኃላፊዎች የተገኙበትን ዓውደ ጥናት በከፈቱበት ወቅት ነው፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ፣ “የበቆሎ ምርት በእጥፍ እንዲጨምር ይሠራል፡፡ አሁን የሚመረተው በአማካይ በሔክታር 34 ኩንታል ነው፡፡ ነገር ግን ካለው የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና በስፋት የመመረት አቅም አንፃር በሁለተኛው የዕቅድ ዘመን መጨረሻ በአማካይ 70 ኩንታል በሔክታር ይጠበቃል፡፡ በእርግጥም ደግሞ ይህንን ማድረግ ይቻላል፤” ብለዋል፡፡
በአሁኑ ወቅት የተከሰተው የአየር ንብረት ለውጥና የዝናብ መዛባት በአገሪቱ የበቆሎ ምርት ላይ ያስከተለው ችግር ምን እንደሆነ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ፣ “የአየር መዛባቱ ይህን ያህል ጉዳት የሚያስከትል አይመስለኝም፤” ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ “ለምሳሌ ወደ ወለጋና ጎጃም አካባቢ በቆሎ እንደ ዘንድሮ በቅሎ አያውቅም፡፡ ሌሎች የምሥራቅ አካባቢዎች ድርቅ የሚቋቋሙ ዝርያዎች ያላቸው የተሻለ ምርት ይሰጣሉ፡፡ አንዳንድ ቦታ ደግሞ ከአበቃቀል ጋር ተያይዞ ችግር ሊፈጠር ይችላል፡፡ ዞሮ ዞሮ በአጠቃላይ ሲታይ ግን በቆሎ የሚበቅልበት ሥነ ምኅዳር የምዕራብ፣ የደቡብ ምዕራብና የሰሜን ምዕራብ አካባቢ ስለሆነ በቆሎ ላይ ያን ያህል ጉዳት አይኖርም ብዬ አስባለሁ፤” በማለት አስረድተዋል፡፡
ለአራት ቀናት ያህል በካፒታል ሆቴል ሲካሄድ የሰነበተው ዓውደ ጥናት አጠቃላይ ዓላማም የኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ከዓለም አቀፍ የበቆሎ ምርምር ኢንስቲትዩት ጋር በጋራ ሲያከናውኑት የቆየውን ድርቅ ተቋቋሚ በቆሎን የተመለከተ ሥራ፣ ውጤቱን መገምገምና ቀጣይ አቅጣጫዎችን ማስቀመጥ እንደሆነ በወቅቱ ተገልጿል፡፡
ይህ “ድርቅን ተቋቋሚ በቆሎ ለአፍሪካ” የተሰኘው ፕሮጀክት በዋነኛነት ዓላማው የተለያዩ ዝርያ ያላቸውን የበቆሎ ዝርያዎችን ለገበያ ማቅረብ ሲሆን፣ ባለፉት ስምንት ዓመታት እንቅስቃሴውም የኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች 13 የአፍሪካ አገር አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ ማድረጉም ተገልጿል፡፡
ከዚህ አንፃር “አፍሪካ ውስጥ አንድ ዝርያ ለ27 ዓመታት ያህል ይመረታል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ደግሞ ዲቃላ ዘሮችን ጨምሮ ከ15 እስከ 20 ዓመታት ድረስ ይመረታሉ፡፡ ይህ ግን ምርታማነትን የሚቀንስ በመሆኑ አዋጭ አይደለም፡፡ ስለዚህ የዚህ ፕሮጀክት ጠቀሜታ ዘሮችን በፍጥነት በማቅረብና በመተካት ምርታማነትን መጨመር ነው፤” በማለትም የፕሮጀክቱን አጠቃላይ ጠቀሜታ ዶ/ር ፈንታሁን አስረድተዋል፡፡ ምንም እንኳ ፕሮጀክቱ በአጠቃላይ ዝርያዎች ላይ እመርታ ቢያስመዘግብም፣ ፕሮጀክቱ ራሱ ባካሄደው የዳሰሳ ጥናት ኢትዮጵያ ውስጥ የዘር አቅርቦት እንደ ልብ አለመገኘት ትልቅ ፈተና እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
“ያሉት የዘር አምራቾች በቂ አይደሉም፡፡ የመነሻ ዘሩ በስፋት አይገኝም፡፡ የተወሰኑ ዝርያዎች ላይ ብቻ የማተኮር ነገር አለ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አምስት ዝርያዎች ላይ ነው አትኩሮት የሚደረገው፡፡ እነዚህ አምስት ዝርያዎች ደግሞ እስከ 65 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናሉ፡፡ ይህ መቀየር አለበት፡፡ ይህ በራሱ ፈተና ነው፤” በማለት አክለዋል፡፡
“ድርቅን ተቋቋሚ በቆሎ ለአፍሪካ” በተሰኘው ፕሮጀክት አማካይነት በ13 የአፍሪካ አገሮች ለሚገኙ አርሶ አደሮች ከ200 ዓይነት በላይ የበቆሎ ዝርያዎችን ባለፉት ስምንት ዓመታት ማቅረብ የተቻለ መሆኑን፣ ዝርያዎቹም ድርቅን የመቋቋም አቅማቸው ከፍተኛነቱ የተረጋገጠና ለበርካታ አርሶ አደሮችም የምግብ ምንጭ በመሆን በማገልገል ላይ ይገኛሉ ተብሏል፡፡ ይህ ፕሮጀክት በቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን በገንዘብ የሚረዳ ሲሆን፣ ሌሎች ለጋሽ አገሮችና ተቋማትም እንደሚሳተፉበት በዓውደ ጥናቱ ላይ ተገልጿል፡፡