Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

መንግሥት ለአዲስ አበባ ባቡር ትራንስፖርት 1.5 ቢሊዮን ብር ለመደጐም ተስማማ

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ስህተት የታየባቸው የአካባቢ ስሞች በፍጥነት ይስተካከላሉ ተብሏል

ባለፈው እሑድ መስከረም 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ረፋድ ላይ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት ከተሳፋሪዎች አቅም ጋር የተጣጣመ አገልግሎት መስጠት እንዲችል፣ የፌዴራል መንግሥት በዓመት 1.5 ቢሊዮን ብር  እንደሚደጉመው ተገለጸ፡፡

የትራንስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ገበየሁ በዕለቱ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፣ መንግሥት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ፕሮጀክትን ዕውን ለማድረግ ከቻይና መንግሥት የተበደረውን 475 ሚሊዮን ዶላር፣ ከሌሎች አማራጮች ለአብነትም ከአዲስ አበባ ውጪ ካሉ የባቡር መስመሮች እንደሚከፍል ገልጸዋል፡፡

የአዲስ አበባ ባቡር እንደየትኛውም ዓለም የዋና ከተማ ትራንስፖርት የአገልግሎት ዋጋው ርካሽ ሊሆን የሚገባ በመሆኑ፣ መንግሥት ለግንባታው ያወጣውን ወጪ ከአገልግሎቱ እንደማይጠብቅ ከዚህ አልፎም በዓመት 1.5 ቢሊዮን ብር ለመደጐም መወሰኑን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ትራንስፖርት መጀመር በርካታ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ያስደሰተ መሆኑን፣ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ሲጀመር በሥፍራው  ደስታቸውን ሲገልጹ ከነበሩ ነዋሪዎች መረዳት ተችሏል፡፡

የተለያዩ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም ከፍተኛ የዘገባ ሽፋን በመስጠት አዲስ አበባ ዘመናዊ የባቡር ትራንስፖርት ባለቤት መሆኗን ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ የትራንስፖርት አገልግሎቱ ሲጀመር በባቡሩ መተላለፊያ ዝግ መስመር ውስጥ የሚገቡ እግረኞችና እንስሳት (ባለቤት አልባ ውሾችና አህዮች) ከፍተኛ ሥጋት ፈጥረዋል፡፡

በጉዳዩ ላይ የተጠየቁት ሚኒስትሩ አቶ ወርቅነህ ይህ የእሳቸውም ከፍተኛ ሥጋት መሆኑን የገጠማቸውን በማውሳት ተናግረዋል፡፡ የባቡር ትራንስፖርቱ ከመጀመሩ አንድ ቀን በፊት በባቡር ተሳፍረው መሠረተ ልማቱን እየጐበኙ ባለበት ወቅት፣ አንድ ልጅ ዘሎ ወደ ባቡሩ መስመር መግባቱንና አደጋ ሊደርስ እንደነበር ገልጸው፣ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በግንባታው ወቅት ከፍተኛ ትብብር እንዳደረጉ ሁሉ በጥንቃቄም ከፍተኛ ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

‹‹የተሻለ የትራንስፖርት አገልግሎት ማቅረብ እንጂ አንድም ሰው በባቡር እንዲሞት አንፈልግም፤›› ብለዋል፡፡

መመስከረም 7 ቀን 2008 ዓ.ም. የሚኒስትሮች ምክር ቤት የባቡር ደኅንነት ደንብ ማውጣቱን የተናገሩት ሚኒስትሩ፣ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች የባቡሩን ደኅንነት የመጠበቅ ግዴታቸውን ይወጣሉ ብለዋል፡፡

የባቡር ደኅንነትን ከማረጋገጥ አኳያ የኢትዮጵያ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት፣ የፌዴራል ፖሊስ፣ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የተካተቱበት ቡድን መዋቀሩን መዘገባችን ይታወሳል፡፡

የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚዎች የትራንስፖርት ደኅንነቱን ለማረጋገጥ ኃላፊነታቸውን ይወጣሉ ያሉት ሚኒስትሩ፣ አሽከርካሪዎችና እግረኞች ከፍተኛ ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል፡፡

‹‹ባቡሩ በተወሰነ ቦታ ብቻ ነው የሚሄደው፡፡ ከመስመሩ ወጥቶ ጉዳት አያደርስም ስለዚህ አሽከርካሪዎችና እግረኞች ወደ መስመሩ ላለመግባት መጠንቀቅ አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡

የትራንስፖርት አገልግሎቱን ከሚሰጠው ከሼንዛን ሜትሮ ጋር የተደረገው ስምምነት በየ15 ደቂቃው በየፌርማታው ማድረስ እንደሆነ፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ምክትል ሥራ አስፈጻሚ አቶ ጥላሁን ሻርካ ገልጸዋል፡፡

ባቡሩ በፌርማታ ላይ የሚቆየው ለሁለት ደቂቃዎች በመሆኑ ተሳፋሪዎች በፍጥነት መውጣትና መውረድን መልመድ እንደሚገባቸውም ገልጸዋል፡፡ አንድ ባቡር ቢያመልጥ በአሁኑ ወቅት በ15 ደቂቃ ውስጥ የሚመጣ መሆኑን፣ ወደፊት ደግሞ በየስድስት ደቂቃው እንዲደርስ የሚደረግ በመሆኑ የሚያሳስብ ነገር አለመኖሩን አቶ ጥላሁን አስረድተዋል፡፡

በዕቅዱ መሠረት በሰዓት 60 ሺሕ ነዋሪዎችን በሁለቱም የባቡር መስመሮች ለማጓጓዝ መታሰቡን የገለጹት አቶ ጥላሁን፣ በአሁኑ ወቅት ግን ይህንን ያህል ተሳፋሪዎች እንደሚይኖሩ ለዚህም አንደኛ የባቡር አገልግሎቱ አዲስ መሆን፣ ሁለተኛ ኅብረተሰቡ የራሱ የሆነ አመለካከት ስላለው ነው ብለዋል፡፡

ባቡሩ ከንጋቱ 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽቱ አራት ሰዓት አገልግሎት እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡

የባቡር ፌርማታዎች መጠቆሚያ ጽሑፎች የአማርኛ መጠሪያ ላይ የተስተዋሉ ስህተቶች ለምሳሌ ሃያ ሁለት ማዞሪያ ለማለት (አያ ሁለት ማዞሪያ)፣ ጉርድ ሾላ ለማለት (ጉርድ ሸላ) የመሳሰሉት ስህተቶች የተፈጸሙት በቻይናዎቹ ኮንትራክተሮች መሆኑን ገልጸው፣ በፍጥነት እንዲተካኩ መታዘዙም የኮርፖሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ደረጀ ተፈራ ገልጸዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች