የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) የትምህርት ቤት የወጣቶች የኤችአይቪ መከላከል ፕሮግራምን ለትምህርት ሚኒስቴር አስተላለፈ፡፡ ኤምባሲው በላከው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በትምህርት ሥርዓቱ ውስጥ ለሚገኙ ወጣቶች ኤችአይቪን ለመከላከል የሚያስችሉ ሥራዎችን አስመልክቶ ከፍተኛ ፍላጎት ያለ በመሆኑ፣ የትምህርት ሚኒስቴርና የክልል ቢሮዎች ፕሮግራሙ ባልተካሄደባቸው በሌሎች ትምህርት ቤቶች ተግባራዊ የሚያደርጉት ይሆናል፡፡
የኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ለኤችአይቪ ተጋላጭ የሆኑ ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ያቀፈ ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት ወጣቱ ላይ ትኩረት አድርገው ሲካሄዱ የነበሩ የኤችአይቪ መከላከል ሥራዎችን ማቀናጀት የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ኤጀንሲ ፕሮግራም ሲቀረጽ ግምት ውስጥ እንዲገባ ተደርጓል፡፡ ከአሜሪካው ፕሬዚዳንት የአስቸኳይ ጊዜ የኤድስ ዕቅድ (ፔፕፋር) ድጋፍ የተደረገለት ይህ ፕሮግራም፣ በየትምህርት ዓይነቶቹ ውስጥ ክህሎትን መሠረት ያደረገ የኤችአይቪ መከላከል ሥራዎችን ያካተተ፣ የተጠኑ የመካላከል መልዕክቶችን ያዘለና፣ ተማሪዎችን ከኤችአይቪኤድስና ከሥነ ተዋልዶ ጤና አገልግሎት ጋር ያቆራኘ ነው፡፡
በኤፍኤችአይ 360 (FHI 360) ተግባራዊ የተደረገው የዚህ የሁለት ዓመት ፕሮግራም ዋና ዓላማ፣ በሁለተኛ ደረጃና በኮሌጆች የወጣቶችን የባሕሪ ለውጥ ተግባቦት ችሎታን ማሳደግና ከፍተኛ ተፅዕኖ የሚፈጥሩ የባሕሪ ለውጥ መሣሪያዎችንና አቀራረቦችን ማሰራጨት፤ እንዲሁም መንግሥት ፕሮግራሙን የማስፈጸም አቅም እንዲኖረው ለማስቻል የትምህርት ሥርዓቱን መደገፍ ናቸው፡፡
መግለጫው እንዳመለከተው፣ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ተግባራዊ የተደረገው የተቀናጀ የኤችአይቪ የመከላከል ፕሮግራም በ62 ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ውጤታማ ሆኗል፡፡ በተጨማሪም 9,000 የአቻ ለአቻ አስተማሪዎች የክህሎት ተኮር የማስተማሪያ ማንዋል አጠቃቀምን የተመለከተ ሥልጠና ወስደዋል፡፡
ከዚህ ቀደም በነበረው ሥራ፣ 40 ዩኒቨርሲቲዎችና ኮሌጆች ፕሮግራሙን ተግባራዊ አድርገዋል፡፡ ከ210,000 በላይ የአቻ ለአቻ አስተማሪዎችና ተማሪዎች የባሕሪ ለውጥ ተግባቦት መልዕክቶች እንዲደርሳቸው ተደርጓል፡፡ ከ67,000 በላይ የሁለተኛ ደረጃ፣ የኮሌጅና ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች በኤችአይቪ ሥጋት ግምገማ በኤችአይቪ የምርመራና ምክርና ቀይ ካርድ አገልግሎት በመሳሰሉ ማኅበረሰብ አቀፍ ሁነቶች ላይ ተሳትፈዋል፡፡