Friday, September 29, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየአበራ ለማ ቅንጣት

የአበራ ለማ ቅንጣት

ቀን:

‹‹ሞገደኛው ነውጤ›› በአበራ ለማ የተጻፈ አጭር ልብ ወለድ ነው፡፡ በ‹‹ሞገደኛው ነውጤ›› የተሳለው ነውጤ የተሰኘ ገፀ ባህሪ ታሪኩን ካነበቡ ሰዎች ህሊና የሚጠፋ አይደለም፡፡ አርቲስት ፍቃዱ ተክለማርያም በኢትዮጵያ ሬዲዮ ላይ በተረከበት ወቅትም የብዙዎችን ቀልብ ስቦ ነበር፡፡ ሰው በመግደል ወንጀል ተጠርጥሮ ፍርድ ቤት የቀረበው ነውጤ የሚያሳየው ገራገር ባህሪና ጉዳዩን ከያዙት ዳኛ ጋር በንግግር አለመግባባታቸው ጽሑፉን ተወዳጅ ካደረጉት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡

‹‹ሞገደኛው ነውጤ››ን ጨምሮ አራት ኖቭሌቶች የያዘ መጽሐፉን በቅርቡ ያሳተመው ደራሲና ጋዜጠኛ አበራ መጽሐፉን መስከረም 8 ቀን 2007 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ (ወመዘክር) አስመርቋል፡፡ ‹‹ቅንጣት፤ የኔዎቹ ኖቭሌቶች›› የተሰኘው መጽሐፉ አራት ኖቭሌቶች ተካተውበታል፡፡

ቀድሞ በተለያዩ ሥራዎቹ የሚታወቀው አበራ መጽሐፉን ባስመረቀበት ዕለት ሐያሲ አብደላ አዝራ በመጽሐፉ ስለተካቱ ጽሑፎች ሒስ አቅርቧል፡፡ ስለ ጽሑፎቹ ይዘት ያወሳ ሲሆን፣ በዕለቱ መነጋገሪያ ከሆኑ ርእሰ ጉዳዮች ዋነኛ የሆነው ‹‹ሞገደኛው ነውጤ›› እና ሌሎችም ሦስት የአበራ ጽሑፎች በኖርዌይ ቋንቋ (ኖርዌጂያን) መተርጎማቸው ነው፡፡

የታሪኮቹ አማርኛ አገለላጾች ወደ ኖርዌጂያን ሲተረጎሙ ምን ያህል ትርጉም ይሰጣሉ? በሚለው ጉዳይ ላይ ረዘም ያለ ውይይት ተደርጓል፡፡ አበራ በበኩሉ ተርጓሚዎቹ የጽሑፎቹን ይዘት ተገንዝበው የአገሪቱ ቋንቋ ተናጋሪዎች በሚረዱት መልኩ መቅረቡን ገልጿል፡፡ አብዛኞቹን ጽሑፎቹ መቼታቸውን በትውልድ አካባቢው ያደረጉና በገሀዱ ዓለም የሚያስተውላቸውን ተመርኩዞ እንደሚያዘጋጃቸውም ተናግሯል፡፡

አበራ የተወለደው በ1943 ዓ.ም. በሰላሌ መራቤቴ አውራጃ ነው፡፡ በወቅቱ ትምህርት የማግኘት እድል ስላልነበረው ልጅነቱን ያሳለፈው ከብት በመጠበቅ ነበር፡፡ ትምህርት ከጀመረ በኋላ ለክረምት ትምህርት ቤት ሲዘጋ አዲስ አበባ የሚኖሩት አጎቱ ጋር ይመጣ ነበር፡፡ ለሥነ ጽሑፍ ከፍተኛ ፍቅር የነበራቸው አጎቱ ይገዙለት የነበሩት መጻሕፍት በሥነ ጽሑፍ ሕይወቱ የራሳቸውን አስተዋፅኦ አበርክተዋል፡፡

የመጀመርያ ደረጃ ትምህርቱን በጎሐጽዮን የተከታተለ ሲሆን፣ ተማሪ ሳለ የሚጽፋቸው ጽሑፎች በመምህራኑ ተወዳጅ ነበረ፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን በተከታተለበት ወሊሶም የሥነ ጽሑፍ ሥራዎቹን አጠናክሮ ቀጥሎ ነበር፡፡ በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ ይማር በነበረበት ወቅት የተቋሙ መጽሔት አዘጋጅ ነበር፡፡ ከኮሌጁ ከተመረቀ በኋላ በሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መምህርነት ሠርቷል፡፡

በመቀጠል በማስታወቂያ ሚኒስቴር የሥነ ጽሑፍ ክፍል ውስጥ የሠራው አበራ፣ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ የባህል ዐምድ አዘጋጅም ነበር፡፡ ለዓመታት በዘለቁትና ትኩረታቸውን ባህል ላይ ባደረጉ ጽሑፎቹ ይታወቃል፡፡

ከመሥሪያ ቤቱ ከለቀቀ በኋላ በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበርና በአንበሳ አውቶቡስ ድርጅት በሕዝብ ግንኙነት ኃላፊነት ሠርቷል፡፡ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ ክፍል የመጀመርያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡ በኢትዮጵያ ደራስያን ማኅበር ውስጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማበርከቱም ይነገርለታል፡፡ ደበበ ሰይፉ የማኅበሩ ሊቀ መንበር በነበረበት ወቅት ‹‹ብሌን›› በተሰኘው የማኅበሩ መጽሔት በዋና አዘጋጅነት ሠርቷል፡፡

ወደ ኖርዌይ አቅንቶ ኑሮውን በዛው ካደረገ በኋላ በኖርዌይ በአፍ መፍቻ ቋንቋው የሚጽፍ ብቸኛ ጥቁር ለመሆን በቅቷል፡፡ ከሥራዎቹ መካከል ‹‹የማለዳ ስንቅ››፣ ‹‹አውጣጪኝ››፣ ‹‹መቆያ››፣ ‹‹ጥሎ ማለፍ›› እና ‹‹ሽፈራው ሞሪንጋ›› የተሰኙት ይጠቀሳሉ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...