Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
- Advertisement -

ፌርማታ ፅሁፎች

የ80 ዓመቱ ባለ ፔዳሉ የፀጉር ማስተካከያ ለከተሜዎች

ትኩስ ፅሁፎች

የ80 ዓመቱ ባለ ፔዳሉ የፀጉር ማስተካከያ ለከተሜዎች- (1927 ዓ.ም.) በአዲስ አበባ አራዳ/ፒያሳ /Straßenszene beim Friseur in Addis-Abeba 1935 (Privatsammlung)/

**********

ፍሬ ውስጥ ብንገባም- ፍሬዎቻችንን ግን እያጣን ነው
                                               በሔኖክ ያሬድ

     “ኢዮሃ አበባዬ . . . መስከረም ጠባዬ

ኢዮሃ አበባዬ . . . መስከረም ጠባዬ”

ዘመን በተሞሸረ ዓመት በተቀመረ ቁጥር መልካም ምኞት የምንለዋወጥበት ሐረግ ነው፡፡ ድምፃውያንም ያቀነቅኑታል፡፡ እንግዲህ ኃያሉ ክረምት ሊያበቃ፣ መሰስ እያለ ወጥቶ ለከርሞ ሊመለስ ከመስቀል በኋላ አንድ ሳምንት ቢቀረው ነው፡፡ ግን ኢዮሃ እያልን የመዘመራችን፣ የማቀንቀናችን ምስጢር ምንድን ነው? ኢዮሃስ ምን ማለት ነው? ታላቁ ሊቅ አለቃ ደስታ ተክለወልድ (ዘብሔረ ወግዳ)፣ በታላቁ ‹‹አዲስ ያማርኛ መዝገበ ቃላት›› ሥራቸው ያወሱትን እዚህ ላይ እናስታውስ፡፡ ሥርወ ቃሉ (የቃሉ ሥር መገኛ) ‹‹ኢዩ››- እይ፣ ‹‹ሃ››- ውሃ ማለት ሲሆን፣ ሲናበብ ደግሞ ‹‹ውሃ ያደረገውን እይ ተመልከት›› የሚል ፍች ይኖረዋል፡፡ ኢዮሃ አበባዬ የደስታ ቃል ነው፡፡ ወንዶች የደመራ ለት እየዘፈኑ ድምሩን የሚዞሩበት ያበባ ዘፈን ነው፡፡
     ሰኔ ግም ብሎ፣ ያምሌን ጨለማ አልፎ፣ በእኝኝ ተሻግሮና የነሐሴን ጎርፍ ሙላት ተንተርሶ በጠንካራው ዝናብ (ውሃ) ምክንያት ብቅ የምትለዋ ያደይ አበባ ናትና፤ ውሃ ያደረገውን ታምር፣ ያስበቀለውን አበባ አደያዊን ተመልከት ለማለት ‹‹ኢዮሃ አበባዬ መስከረም ጠባዬ›› እንላለን፡፡ የስድስተኛው ምታመት መዝሙረኛው፣ ዜማ ቀማሪው፣ የነገረ መለኮት ሊቁ (ቲኦሎጊያን) ቅዱስ ያሬድም በመጽሐፈ ድጓው፣ ‹‹ኀለፈ ክረምቱ ጸገዩ ጽጌያት ቆመ በረከት!›› – ክረምቱ አለፈ አበቦችም ፈኩ፣ በረከትም ቆመ ይለናል፡፡ አሁን የምንገኝበት ወቅት ክረምት ነው፡፡ መስከረም 1 በክረምት ውስጥ የምትገኝ ያመት መነሻ ናት፡፡ ክረምቱ ሰኔ 26 ቀን ገብቶ የሚወጣው መስከረም 25 ቀን ላይ ነው፡፡ እንደ ቅዱስ ያሬድ አመዳደብ፣ በውስጡም ልዩ ልዩ ንኡሳን ክፍሎች አሉት፡፡ ከነሱም መካከል የነሐሴ መጨረሻና የጳጉሜን ሳምንት ‹‹ጎሕ፣ ጽባሕ››- ወጋገን፣ ንጋት ይለዋል፡፡ ይህም ያዲስ ዘመን መስከረም የሚጠባበት ጊዜ መድረሱን አመላካች ነው፡፡

ሌላው ንኡስ ክፍል ከዓመት አውራ መነሻ (ርእሰ ዐውደ ዓመት) መስከረም 1 ቀን እስከ መስከረም 7 (8) ቀን ያለው ‹‹ዮሐንስ›› ሲባል፣ ከመስከረም 9 እስከ 15 ዘመነ ፍሬ ይባላል፡፡ ‹‹ዮሐንስ›› የሚለው ቃል የተወሰደው በመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ከምናገኘው ኢየሱስ ክርስቶስን ካጠመቀው የዘካርያስ ልጅ ዮሐንስ ነው፡፡ መስከረም 1 ቀን ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዕለተ ዮሐንስ መባሉ በተምሳሌታዊ ፍች የመጣ ነው፡፡ ከአሮጌው ብሉይ ኪዳን ወደ ሐዲስ ኪዳን፣ ወደ ዓመተ ምሕረት መሸጋገሪያ ላይ የመጣው መንገድ ጠራጊው ዮሐንስ ስለሆነ፤ ባህላችን/ ትውፊታችን ካሮጌው ዓመት ወዳዲሱ መሸጋገሪያዋን ዕለት፣ መስከረም 1 ቀንን በዘይቤ ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ›› እያለ ይጠራዋል፡፡ ከጥንት እስከ ዛሬ እየተጠቀምንበት እንገኛለን፡፡

እንዳለመታደል፣ ምስጢሩን ባለመረዳት የኢትዮጵያ መንግሥት ሚዲያዎች በመናገሻ ከተማችንም ሆነ በየክልሉ የሚገኙት ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ›› የሚለውን የመስከረም 1 ቀን ልዩ መጠርያ ላለመጥራት ተማምለዋል፣ ምለዋል፡፡ ሃይማኖታዊ ብሎ በመደምደም፡፡ ዩኔስኮ ልዩ ስለሆነው የኢትዮጵያ ዘመን አቈጣጠር (ካሌንደር/ ቀለንቶን)፣ አዲሱ ዓመት ዘመኑ የሚለወጥበት ንጋት 12 ሰዓት ላይ እንጂ እንደ ምዕራባውያን እኩለ ሌሊት (6 ሰዓት) ስላለመሆኑ፣ ያመቱ መነሻ መስከረም 1- ቅዱስ ዮሐንስ- ዕለተ ዮሐንስ መባሉንና ሌሎች የቀመር ጓዞችን የያዘውን ጥንታዊ የባሕረ ሐሳብ ብራናን (መጽሐፍ) በ2015 ዓመት የኢትዮጵያ 13ኛው የዓለም ቅርስ አድርጎ ለመመዝገብ ባጨበት ጊዜ ላይ ደርሰን፣ ሚዲያዎቻችንና የሚመለከታቸው አካላት ያለዕውቀት ቅርሱንና ውርሱን እየጣሉት ይገኛሉ፡፡

ከኢትዮጵያ ባሕረ ሐሳብ (መርሐ ዕዉር) ጋር የማይተዋወቁት፣ አላዋቂዎቹ ‹‹አርቲስቶች›› እኩለ ሌሊት ላይ አዲሱ ዓመት ገባ እያሉ ማደናገራቸውን፣ ዓመት ዓመት መቀጠላቸውንም ሃይ የሚልም ጠፍቷል፡፡ ወይ አለመተዋወቅ! ዓይን እቅርቡ ቅንድብ እያለለት አያይም መባሉ፣ ለካ የኛን ጉዶች ይገልጻቸዋል፡፡ ለነገሩ የዘመን መለወጫ እንቁጣጣሽ ዜማዎቻችን ውስጥ፣ ክብር ለድምፃውያኑ ይሁንና ቅዱስ ዮሐንስን ፈጽሞ አልረሱትም፡፡ (ሁለት የዘመን መለወጫ በዓል የሚከበርባት ኤርትራ መስከረም 1 ቀንን ‹‹ቅዱስ ዮሐንስ›› እያለች ዳር እስከ ዳር እያከበረችው መሆኑን ልብ ይሏል፡፡)

ዩኔስኮ የባሕረ ሐሳባችሁን ቅዱስ ዮሐንስ አውቄዋለሁ፣ አክብሬዋለሁ ሲል እኛ ግን እየጣልነው ነው፡፡ ባለቤቱ የናቀውን ባለዕዳው ሲቀበለው እያየን ነው፡፡ ሁለተኛው የዕድገትና የውላጤ (ትራንስፎርሜሽን) ዕቅድ ለባህላችንና ለቅርሳችን፣ ለውርሳችንም ካለፈው የመጀመሪያው ዕቅድ ክፍተት ይልቅ በተሻለ የሚቃኝበት እንዲሆን ምኞታችን ብቻ ሳይሆን ጸሎታችንም ነው፡፡ በነገራችን ላይ ‹‹ትራንስፎርሜሽን›› ለሚለው ቃል፣ አቻ አማርኛ ሳይጠፋለት “ሳይቸግር ጤፍ ብድር” ሆኖ በባዕድ አፍ መጠቀሙን ቀጥለናል፡፡ ሕዳሴን፣ ውዳሴን፣ ቅዳሴን እየተጠቀምን እያለን በነሱ ቅጥ አለመሄዳችን ምነው! ከዛሬ አምስት ዓመት በፊት ጀምረን ኧረ ‹‹ውላጤ›› የሚል አቻ ቃል አለን እያልን ብንጮህም ሰሚ አጥተናል፡፡ ለነገሩ የቋንቋ ፖሊሲ መቼ አለንና!

ገዢው ፓርቲ ባህልና ቅርስ፣ ቱሪዝምንም እንደ ውጭ ጉዳይ፣ ትምህርት፣ ግብርና ወዘተ. ጉዳዬ የሚልበት የዕድገትና ውላጤ ዘመን ይሆንልናል ብለን ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ሊቁ ዶክተር እጓለ ገብረ ዮሐንስ፣ የዛሬ 53 ዓመት በአዲስ አበባ ራዲዮ ጣቢያ የዘመን መለወጫ በዓል ዋዜማ ላይ፣ ባደረጉት ንግግር ማሰሪያቸውን እንዲህ የገለጹበትን ፍኖት እዚች ላይ ማንሣት ወደድን፡፡ ‹‹በዘመን መለወጫ በዓል አሮጌው አልፎ አዲስ ሲተካ የክረምት ጭለማ አልፎ ብርሃን ሲመጣ ሁሉም ‹በተውሳከ መብልዕ ወመስቴ› [ምግብና መጠጥን በመጨመር] እየተደሰተ፣ ከአንዱ ዘመን ወደ ሌላው መሻገሩን በሚያከብርበት ዕለት ትንሽ ጊዜ አስተርፎ ስለጠቅላላው የሕይወት ጉዞ ለሚያስበው ረድኤት ይሆን ዘንድ፣ ለማያስበው ደግሞ እንዲያስብ ምክንያት ይሆን ዘንድ፣ እሊህን ሐሳቦች ለማቅረብ ደፈርን፡፡››

እኛስ ይህን የሊቁን እጓለ መርሐ ሐሳብ ለምን አንሰንቅም? በተለይ የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎቻችን መንግሥታዊዎቹም ሆኑ ግሎቹ ይህ ኃይለ ቃል ሳይጠቅማቸው አይቀርም፡፡ የዘንድሮውን እንቁጣጣሽ፣ ቅዱስ ዮሐንስ፣ ዘመን መለወጫ በቲቪና በሬዲዮ ለተከታተለ እንደታዘበው፣ ‹‹ዘመኑ ከምንትስ ቢራ ወደ ምንትስ ቢራ›› የተለወጠ ይመስል፣ ከቢራዎች ማስታወቂያ ባለፈ (ስፖንሰርነቱ መኖሩ አስፈላጊነቱ ባያጠያይቅም) ስለኢትዮጵያ ዘመንና ክብረ በዓል ጥንተ ተፈጥሮ ባህላዊና ትውፊታዊ፣ ፎክሎራዊ መገለጫዎችን መግለጹ ተትቶ፣ የቢራዎች ጥንተ ተፈጥሮ አንቀጽ ከነጓዙ በሰፊ ያየር ሽፋን መጥለቅለቁ እንዴት ነው ነገሩ ያሰኛል፡፡

ሚዲያዎቻችን፣ ሁሉም የአዳምና የሔዋን ልጅ ስለጠቅላላው የሕይወት ጉዞ ለሚያስበው፣ ረዳት የሚሆንለትን መሠረት ከማንነቱና ከባህሉ የሚመነጩ እየጠለፉለት ማቅረብ ላፍታም ችላ ሊሉት የማይገባ ነው፡፡ አሊያ የሰሞኑ የቢራዎች የማስታወቂያ ከልክ ያለፈ ጋጋታ ማትረፍ የማይቻልበት ለመሆኑ አንዱ ማሳያ፣ አንድ ብላቴና ተናገረ የተባለው ነው፡፡ ‹‹ማሙሽ ስታድግ ምን ማድረግ ትፈልጋለህ? ሲሉት፣ ‹‹ቢራ መጠጣት!›› ብሎ እርፍ፡፡ ከሀገረ ዱባይ ለእንቁጣጣሽ፣ ቅዱስ ዮሐንስ ክብረ በዓል የመጣች የወንዜ ልጅ፣ ‹‹ያገራችሁ የቴሌቪዥን ጣቢያ የቢራዎች ጣቢያ ነው እንዴ?›› ብለው የባሕር ማዶ ሰዎች የነገሯትን የነገረችኝ በመቆጨት ነበር፡፡ ጆሮ ያለው ይስማ!

እንደ ነፍስ ኄር እጓለ ገብረ ዮሐንስ (የገሞራው/ ኃይሉ ገብረ ዮሐንስ ወንድም) አገላለጽም፣ የዚያ ሰው ይበለን እንጂ ለከርሞ በተሻለ ለማቅረብ እያሰብን ለሰሚዎቻችን [ላንባቢዎቻችን] መልካም በዓል እንመኛለን፡፡ የዘመን ጉዞአችንን እንቀጥል፡፡ መስከረም 9 ቀን 2008 ዓ.ም. ከዮሐንስ ወደ ፍሬ የተሸጋገርንበት ዘመን ፍሬዎቻችንን የምናውቅበትና የምናከብርበት ይሁንልን፡፡

**********

የቷ ነሽ?
                                                   በደመቀ ከበደ – መሀል ሸገር

ከትናንት በስቲያ
እሆነው እስካጣ – ጢቢ ልቤ እስክትፈርጥ – እያሳቅሽኝ ቆየን
በሳቅ ተለያየን፤

ትናንት
ለንቦጭሽ ተልቆ – ከመጫኛ ልቆ – በኩርፊያ ጥለሽው
ሰላሜን አመስሽው፤

ማታ
በጎረቤት ሀዘን – ቅስምሽ ስብር ብሎ – አይሎብሽ ራሮት
ተለያየን ባምሮት፤

ጠዋት
ጥድፍድፍ ጥድፍድፍ – በሚል የሴት ጉዞ – ያውም በቁም ጫማ
ቻው ሳትይኝ ወጣሽ – ወርቅ እንደተቀማ፤

ምሳ ላይ
በጉርሻ ላጠግብሽ – ጣትሽ ወጥ ላይነካ – በጉጉት ስዘጋጅ
መጣች ያንቺ ወዳጅ
እህሉን ረግጠሽ – ሄድሽብኝ በ‹ግዳጅ›፤

አመሻሽ
እምባ አዝለው ዓይኖችሽ – እንደሽንኩርት ቀልተው – ከበርበሬ ልቀው
በዚያ ላይ ተልቀው
‹‹ምን ሆንሽ?›› ከማለቴ – ቃል ካፌ ሲወጣ – ሳጅል ንግግሬን
‹‹ናፍቀኸኝ ነው›› ብለሽ – ጎረስሽው ከንፈሬን፤

ይህን እንቆቅልሽ – ይህን ያንችን ቅኔ
ልፈታው ብጥርም – አልቻልኩትም እኔ፤

በሞቴ….
ትወጅኛለሽ ወይ – ብዬ አልጠይቅሽም – ምን አጠያየቀኝ
ይልቅ የቸገረኝ – ይልቅ የጨነቀኝ
በቀን ለዕልፍ ጊዜ – ትለዋወጫለሽ
በሰዓት ሽህ ጊዜ – ትቀያየሪያለሽ
የምሬን እኮ ነው – አንቺ ግን የቷ ነሽ?

**********

“ምስኪን ብችል ይህቺን ጨረቃ እመርቅልህ ነበር”

አንድ የዜን መምህር ከተራራ ሥር በሚገኝ ትንሽ ቤታቸው ውስጥ ለረዥም ዓመታት እጅግ በጣም ቀላል የሆነ ሕይወት በመምራት ይኖሩ ነበር:: አንድ ምሽት ከቤታቸው ርቀው እግራቸውን እያፍታቱ ሳለ ሌባ እቤታቸው ገብቶ መበርበር ይጀምራል፡፡ ይሁንና በቤት ውስጥ አንዳች የሚሰረቅ ጠቃሚ ነገር ሳያገኝ ሲንጎዳጎድ ቆይቶ ባዶ እጁን ሊወጣ ወደበሩ ሲያመራ መምህሩ ተመልሰው ከቤት ይደርሳሉ፡፡ የዜኑ መምህር ሌባውን ከቤታቸው ሲወጣ ሲመለከቱ ወዳጄ ሆይ ልትጎበኘኝ ከሩቅ ሥፍራ እዚህ ድረስ ተጉዘህ መጥተህማ ባዶ እጅህን አትመለስም በማለት የለበሱትን ልብስ አውልቀው ከእጁ ላይ ያስቀምጡታል:: በዚህ ጊዜ ሌባው ሀፍረትም ንዴትም እየተሰማው የዜኑ ልብስ ይዞ መሮጥ ይጀምራል፡፡ የዜኑ መምህር ሌባውን ተከትለው በመውጣት ከደጃፍ ተቀመጡና ዓይናቸውን ወደ ምሽት ጨረቃ በመላክ “ምስኪን ብችል ይህቺን ጨረቃ እመርቅልህ ነበር፤” አሉ:: ዜኖች ሲናገሩ በእጁ ባለው ነገር እንደማይደሰት ሰው አሳዛኝ ፍጡር የለም ይላሉ፡፡ ዛሬ ፈጣሪ የሰጠህ ማንኛውን ነገር ለሕይወትህ በቂ መሆኑን አምነህ ተቀበል፤ ስግብግብነት ስስት እንዲሁም ምሬት ምንጫቸው በሕይወት ውስጥ በያዝነው ነገር አለመርካት እንጂ ሌላ አይደለም፡፡ የዜኑ መምህር ሌባውን የእሱ ንብረት ያልሆነውን በመስረቅ ሊፈፅመው ከነበረው ሀጢያት የዜኑ መምህር በመስጠት አዳኑት፤ ሌባውም ባለመስረቁ ዜኑም ያላቸውን በማካፈል ሁለቱም በእኩል ደረጃ መልካም ሆኑ።

  •  (ዜን ቡድሂዝም)
- Advertisement -
- Advertisement -

ተጨማሪ ለማንበብ

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች