ሁለተኛው የዓለም ጦርነት በጃፓናውያን ታሪክ ውስጥ ጥቁር ጠባሳ ጥሎ አልፏል፡፡ ሂሮሺማና ናጋሳኪ የሚኖሩ ጃፓናውያን በአሜሪካ አቶሚክ ቦምብ ሰለባ የሆኑትም በዚሁ ጊዜ ነው፡፡ ጃፓን በጦርነቱ ወቅት ከደረሰባት ጉዳት አንፃር ራሷን ለመከላከል ካልሆነ በስተቀር፣ ጦሯን ወደ ሌሎች አገሮች እንዳታዘምትና ጦርነት ውስጥ እንዳትገባም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማክተም ጀምሮ ስምምነት ፈርማለች፡፡
ጃፓናውያን ያለፉትን 70 ዓመታት ያሳለፉትም ስለሰላም ሲዘምሩ ነበር፡፡ በጦርነት አይሳተፉም፣ የጦር መሣሪያም ሆነ የወታደር ቁጥራቸው የተወሰነ ነበር፡፡ የጦር መሣሪያ አምርተው አይሸጡም፣ ከውጭም አያስገቡም ነበር፡፡ ካሳለፍነው ሳምንት ጀምሮ ግን በጃፓን ለ70 ዓመታት ተዘግቶ የነበረው የጦርነት በር ተከፍቷል፡፡ ጃፓን የወታደር ቁጥሯን፣ የጦር መሣሪያዎችና ቁሳቁሶቿን እንዲሁም የጦር ሠፈሮቿን ታስፋፋለች፡፡ ላለፉት 70 ዓመታት ራሷን ለመከላከል ብቻ ዘብ ቆሞ የነበረው መከላከያ ኃይሏ፣ ከዚህ በኋላ ድንበር ተሻግሮ ለመዋጋት ምክንያት ካገኘ ይሳተፋል፡፡ በአጋር አገሮች ጥምር ጦር ውስጥም ለመካተት በር ተከፍቶለታል፡፡ የሁለተኛው ዓለም ጦርነት አክትሞ 70ኛ ዓመቱ በተከበረ ማግሥትም ጃፓን “ጠንካራ የመከላከያ ኃይል ያስፈልገኛል” ስትል ብዙ ክርክር፣ ውዝግብና ድብድብ ያስነሳውን ሕግ አፅድቃለች፡፡ ከዚህ በኋላም የጃፓን ጦር በሌሎች አገሮች ለመዝመት ይችላል፡፡
በጃፓን ፓርላማ በብጥብጥና በድብድብ ታጅቦ ሕጉ ቢፀድቅም፣ ጃፓናውያን ተቃውሟቸውን እየገለጹ ነው፡፡ የሕጉ ደጋፊዎች የሰሜን ኮሪያ የሚሳይል ሙከራ፣ እንዲሁም ቻይና በጃፓን ደሴቶች ላይ ጥቃት በማድረስ የጃፓንን ሉዓላዊነት የምትደፍረውን ለመግታት ሕጉ ያስፈልጋል ሲሉ፣ ተቃዋሚዎች ደግሞ የሰሜን ኮሪያም ሆነ የቻይና ጃፓንን የማጥቃት ወሬ አከራካሪ እንደሆነ፣ ሕጉ የወጣበት ምክንያትም ግልጽ እንዳልሆነና መንግሥት ሕጉን ለማፅደቅ የቸኮለበት ሁኔታ በራሱ አወዛጋቢ መሆኑን እየገለጹ ነው፡፡
አልጄዚራ እንደዘገበው፣ የጃፓን አዲሱ የደኅንነት ሕግ በጃፓንና በጎረቤት አገሮች ላይ ባለፉት 70 ዓመታት ከነበረው ሰላም ተቃርኖን ይዞ ይመጣል፡፡ ሕጉ በአሜሪካና በአጋሮቿ ይሁንታ ሲቸረው፣ ቻይና ግን ሕጉን አጣጥላ አካባቢው የጦርነት ቀጣና እንዳይሆን ሥጋት አለኝ ስትል አስጠንቅቃለች፡፡ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣናትን ጨምሮ የሕጉ ደጋፊዎች፣ ‹‹ጃፓን የመከላከያ ኃይሏን ኃላፊነት ማስፋፋት ያስፈልጋታል፡፡ ይህም ከሰሜን ኮሪያና ከቻይና ሊቃጣ የሚችለውን ጥቃት ለመቆጣጠር ያስችላል፡፡ በተለይ ሰሜን ኮሪያና ቻይና የመከላከያ ኃይላቸውንም ሆነ የኑክሌር ፕሮግራማቸውን እያስፋፉ መምጣት፣ ጃፓን ሕጉን እንድታፀድቅ ያስገድዳታል፤›› ብለዋል፡፡
ባለፈው ወር የሁለተኛው ዓለም ጦርነት ማክተምን 70ኛ ዓመት አስመልክቶ በቻይና በነበረው ክብረ በዓል፣ ቻይና ግዙፉን የመከላከያ ኃይሏን በግልጽ አሳይታለች፡፡ ሰሜን ኮሪያ ደግሞ አሜሪካና ግብረ አበሮቿ በሰሜን ኮሪያ ላይ ጣልቃ ገብነታቸውን ካልተው የኑክሌር መሣሪያዎቿን በማንኛውም ጊዜ ልትጠቀም እንደምትችል አስጠንቅቃለች፡፡ ረዥም ርቀት ሊጓዝ የሚችል ሮኬት የሚጠቀም አዲስ ሳተላይት በቅርቡ እንደምታመጥቅም ተናግራለች፡፡ ይህም ለአሜሪካ ራስ ምታት ሆኗል፡፡ በመሆኑም አሜሪካና ታማኝ አጋሮቿ ጃፓን የአሜሪካን ፍላጎት እንድታስጠብቅ ግፊት ሲያደርጉባት ቆይተዋል፡፡
እ.ኤ.አ. በ1960 ጃፓንን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከል ስምምነት የተፈራረመችው አሜሪካ፣ ጃፓን የጦር ኃይሏን ሚና እንድታስፋፋ ስትወተውት ከርማለች፡፡ በመሆኑም ጃፓን በፓርላማዋ ብጥብጥና ድብድብ ያስነሳውን ሕግ አፅድቃለች፡፡
በጃፓን ቶኪዩ መቀመጫውን ያደረገው የስትራቴጂ አማካሪ ድርጅት ሕጉን ከደገፉት አንዱ ነው፡፡ በእስያ በመንግሥት ፖሊሲዎች ላይ ትንተና በመስጠት የሚታወቀው ድርጅት ስትራቴጂስት ኬት ሄንሪ፣ “ጃፓን በአሜሪካ ጥበቃ እየተደረገላት የምትኖር የ42 ዓመት ሕፃን ናት፤” ሲሉ ከዚህ ጥገኝነት የሚገላግላትን ሕግ ማፅደቋን እንደሚደግፉት ተናግረዋል፡፡ ሄንሪ ሕጉን የገለጹት፣ “ጃፓን አደገች” በማለትም ነው፡፡ ሰላምና ዴሞክራሲ የሚሉት ቃላት አከራካሪ፣ አሻሚና በተግባር በማይታዩባት ዓለም ፖለቲካውና መልክዓ ምድራዊው አቀማመጥ ከጊዜ ወደጊዜ እየተቀየረ ባለበት ሁኔታ፣ ጃፓን የራሷ መከላከያ ኃይል ቀጣና ማስፋቷ ወሳኝ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ይህ የራሱ አደጋ አለው፡፡
የጃፓናውያን ተቃውሞ ሠልፍ በቶኪዮ
በጃፓን የተቃውሞ ሠልፍ ማድረግ የተለመደ አይደለም፡፡ ሆኖም ጃፓን በጦርነት እንድትሳተፍ የሚያስችለው ሕግ መፅደቅን ተከትሎ ጃፓናውያን ለተቃውሞ ሠልፍ በቶኪዮ ጎዳናዎች ወጥተዋል፡፡ ይህም አንዱ በጃፓን ላይ የተጋረጠ አደጋ ነው፡፡ ሰላምን በመስበክ የሚታወቁት ጃፓናውያን መንግሥታቸውን በመቃወም እምብዛም አይታወቁም፡፡ ዛሬ ግን አድርገውታል፡፡ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ጃፓናውያን፣ “ጦርነት አንፈልግም” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡ ሲኤንኤን እንደዘገበው፣ አንዳንዶች የትምህርት ቤት ዩኒፎርም ለብሰው፣ አንዳንዶች “ጦርነት አያስፈልግም” የሚል ፖስተሮች ይዘው፣ ብዙዎች ደግሞ “ኖ ዋር” (ጦርነት አንፈልግም) “ኖ አቤ” (ጠቅላይ ሚኒስትር አቤን) አንፈልግም የሚሉ ቲሸርቶችን ለብሰው ለተቃውሞ ወጥተዋል፡፡
በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ጃፓናውያን በፓርላማ ፊት ለፊት ሆነው ሕጉን መቃወማቸውን ሲገልጹ፣ እንዲህ ዓይነት ተቃውሞ ካለፉት 50 ዓመታት ወዲህ በጃፓን ምድር ተስተውሎ እንደማያውቅ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ዘግበዋል፡፡ ሕፃናት፣ ተማሪዎች፣ መምህራን ጡረተኞችና አዛውንቶችም በተቃውሞው ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ‹‹ሕዝቡ ሳይወያይበትና ሳይመክርበት በጃፓን ለ70 ዓመት የነበረውን ሰላም በዋዛ የሚንድ የጦርነት አዋጅ›› ሲሉም አዲሱን የደኅንነት ሕግ ነቅፈውታል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሺንዞ አቤ ፎቶም እንደ ናዚው ሂትለር ዓይነት ሪዝ ተደርጎለት፣ የናዚ ዓርማ ተለጥፎበት በትልቅ ፖስተር ተደርጎ በተቃውሞው ሠልፍ ታይቷል፡፡ በጃፓን የሕጉ መረቀቅ ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ተቀባይነት እያሽቆለቆለም መጥቷል፡፡ ይህንንም ለማሳየት ጃፓናውያን ከዚህ ቀደም ደፍረው የማያደርጉትን ጠቅላይ ሚኒስትራቸውን በአደባባይ እስከመቃወምና ‹‹ናዚ›› ብለው እስከመግለጽ አድርሷቸዋል፡፡
የ65 ዓመቱ የአይቲ ኢንጂነር ሂድኖሪ ሺዳ፣ “ጃፓን ደግሞ ጦርነት ውስጥ ላትገባ ቃል የገባች አገር ነች፡፡ ባለፉት 79 ዓመታት የጃፓን መሣሪያዎች ሰው ገድለው አያውቁም፡፡ አሁን ግን መግደል ይጀምራሉ፡፡ ሕጉ ይቅርታ የማይደረግለት ነው፤” ብለዋል፡፡
የጃፓን መንግሥት በሥልጣን መቆየት
የጃፓን መንግሥት በሥልጣን ይቆያል ወይ? የሚለው ሌላው ሥጋት ነው፡፡ ጃፓናውያን፣ ‹‹አዲሱ የደኅንነት ሕግ ሕዝቡና ፓርላማው በቂ ጊዜ ወስዶ ሳይወያይበት የፀደቀ ነው›› ይላሉ፡፡ በጥድፊያ በመሆኑም ጃፓናውያን ስለሕጉ ጥልቅ መረጃም ሆነ ግንዛቤ የላቸውም፡፡ አዲሱ ሕግ ጃፓን ከአሜሪካና ከአጋሮቿ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር የሚያግዝ ቢሆንም፣ በሌላ በኩል የጃፓናውያንን ፍላጎት የጠበቀ አይደለም ተብሏል፡፡ ምክንያቱም ሕጉ በጦርነት ጊዜ አገሮች ለሚፈጥሩት ጥምረት ጃፓን የቁሳቁስን ጨምሮ ወታደራዊ ድጋፍ እንድታደርግ ይፈቅዳል፡፡ በሶፊያ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የሆኑት ኮቺ ናካኖ የሚሉትም፣ ሕጉ የመንግሥትን በሥልጣን የመቆየት አቅም እንደሚያሳጣ ነው፡፡
የጠቅላይ ሚኒስትር አቤ ተቃዋሚዎች ሥልጣን ሊረከቡ እንደሚችሉም በቅርቡ በደኅንነት ሕጉ ላይ የተደረገ የሕዝብ አስተያየት አሳይቷል፡፡ የጃፓን ጋዜጣ የሆነው አሳሂ ሺምቡን ይዞት የወጣው ዘገባም፣ በአዲሱ ሕግ ዙሪያ በተሠራ የሕዝብ አስተያየት ከተሳተፉት 54 በመቶ ያህል ሕጉን ሲቃወሙ፣ 29 በመቶው ደግፈዋል፡፡ ሦስት አራተኛ ያህሉ ደግሞ በፓርላማ የተደረገው ክርክር በቂ አልነበረም ብለዋል፡፡
የመከላከያ በጀት
አዲሱ የደኅንነት ሕግ ጃፓን ለመከላከያ ኃይሏ የምታወጣውን በጀት ያሳድገዋል፡፡ ይህም ከበጀት እጥረት ጋር ተያይዞ በትግል ለሚኖረው ዜጋ ተጨማሪ ሥቃይ ነው፡፡ የጃፓን መከላከያ ሚኒስቴር እ.ኤ.አ. ለ2016 በጀት ዓመት 5.09 ትሪሊየን የን (የጃፓን ገንዘብ) ወይም 41.7 ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር የበጀት ጥያቄ ለመንግሥት አቅርቧል፡፡ ይህም እ.ኤ.አ. በ2015 ከነበረው የ2.2 በመቶ ጭማሪ አለው፡፡ በሌላ በኩል ከ1960ዎቹ ወዲህ የጦር መሣሪያና የውትድርና ቁሳቁስ ወደ ውጭ ለመላክ ገደብ ተጥሎበት የነበረው የጃፓን የመከላከያ ኢንዱስትሪ ያድጋል፡፡ ይህም ጃፓን ወደ አዲሱ ገበያ እንድትገባ ያደርጋታል፡፡ አሜሪካ ይህንን የምትቀበለው ሲሆን፣ የአቤ ተቃዋሚዎችና ሕዝቡ ግን አጣጥለውታል፡፡
የወጣቶች ድምፅ በጃፓን
አዲሱን የደኅንነት ሕግ በመቃወም 45 ሺሕ ያህል ጃፓናውያን ሠልፍ ወጥተዋል፡፡ የጃፓን ወጣቶች ደግሞ ሠልፎችን በማቀነባበር ተሳክቶላቸዋል፡፡ የ22 ዓመቷ አንትሮፖሎጂስት ማና ሺባታ፣ ብዙ ወጣቶች ለአቤና ለሕግ አውጭዎች መንግሥት እየተከተለ ያለው መንገድ አደገኛ መሆኑን ገልጸው መልዕክት ማስተላለፋቸውን ገልጻለች፡፡ ‹‹ዝም በማለታቸው ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ አምባገነን እየሆኑ ነው፤›› ብላለች፡፡
የጃፓን መንግሥት ያፀደቀውን የደኅንነት ሕግ ተከትሎ የተቃውሞ ሠልፍ ብቻ አይደለም መንግሥትን የገጠመው፡፡ ማኅበራዊ ድረ ገጾችም አቤን በመቃወም በዘመቻው ከፍተኛ ሚና እየተጫወቱ ነው፡፡ ሺባታ እንደምትለው፣ በሁሉም የዕድሜ ክልል ያሉ ጃፓናውያን በትዊተርና በፌስቡክ እያንዳንዷን መረጃ እየተከታተሉ መልዕክት እየተለዋወጡ ነው፡፡ ተቃውሞውም የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ጃፓናውያን ቤታቸው ገብተው እንቅልፍ እንደማይወስዳቸውና መንግሥት የናደውን የሰላም ግንብ መልሰው ለመገንባትም ነቅተው እንደሚሠሩ እየተናገሩ ነው፡፡