እነሆ መንገድ። ከኦሎምፒያ ወደ ጎተራ ልንጓዝ ነው። በራሪ ጃጉዋር ከፊታችን መጥታ ድቅን… “ሂያጅ ናችሁ?” ሾፌሩ በጋቢናው መስተዋት በኩል አስግጎ ይጠይቃል። “በስመ አብ ወወልድ ወ መንፈስ ቅዱስ! ምን አልክ አንተ?” ካፖርታቸው ላይ ፎጣ፣ ፎጣው ላይ ጋቢ የደራረቡ አዛውንት ነገር ሲያያይዙ ወያላና ቀለም አልባዋ ታክሲ ሞልታለች። “ምነው አባባ?” ሾፌሩ ግራ ይገባዋል። አንዴ እኛን አንዴ እሳቸውን ያማትራል። “ደግሞ ብላችሁ ብላችሁ በጅምላ ታባልጉን?” አዛውንቱ አከረሩ። “ምን አጠፋሁ?” ሾፌሩ ጋቢና ወደተሰየመው ወጣት ዘወር ብሎ ሲጠይቅ ዓይኑን ጨፍኖ፣ ጆሮውን በ‘ኤርፎን’ ደፍኖ ይወዛወዛል። “ና ውረድ እንዲያውም። ሕግ ፊት ባላቆምህ?” ይገለገሉ ይጀምራሉ። “ንሱ ፊቱን ያሳዩኝማ አባት! እኔ ደግሞ ጀርባው ሰልችቶኝ የሕግ ነገር በቅቶኝ ነበር፤” ሲል ከኋላ፣ “ምን ብሎዎት ነው ጋሼ?” ከሾፌሩ ጀርባ ጥጉን ይዞ የተደላደለ ጎልማሳ አጠገቡ የተቀመጠችን ቀዘባ ጭን ተደግፎ እየተንጠራራ ይጠይቃቸዋል። “ኧረ እጅህን አንሳልኝ። ተጭኖ ገደለኝ እኮ!” ትላለች ቆንጂት። የክርኑን መቆርቆር ብቻ አይመስልም የምታወራው። እሷና እሷ ብቻ የሚያውቁት ደዌዋን ጭምር የደባለቀችው ይመስላል።
ከጀርባ ደግሞ ቁንጅናዋና የአነጋገሯ ዘዬ አልጣጣም ያለው ልጅ እግር ወደኔ እያየ፣ “ወይ አዲስ አበባ! ልማቱን በ‘ሞኖፖል’ ተቆጣጥራው እኮ ‘ሚክሱ’ በዛ፤” ይለኛል። አዛውንቱ ደግሞ፣“ሂያጅ ናችሁ ወይ?’ ይላል እንዴ? ነጥለህ አታሸሙርም? እኔ የሰውዬው ልጅ ነኝ ሽንጥና ዳሌ አድናቂ አብዮተኞች መሀል የምሠለፈው? ዘመን የሚዋጅና በዘመን የሚዋጅ ሰው አትለይም?” ብለው ያፈርጡታል። ነገሩ ወዲያው ገባን። ሾፌሩ፣ “ይቅር በሉኝ አባት! ኑሮና አማራጩ ሲጠብ ሰው እንኳን በቋንቋው በነፍሱ ይገኛል እኮ። በጣም ይቅርታ! ኑ እንዲያውም አጠገቤ ነው የሚቀመጡት አላስከፍልዎትም፤” አላቸው። ክሱ ተረሳ። የአፍ ወለምታውም ታለፈ። ባለ ‘ኤርፎኑ’ ወጣት በቁሙ ከተኛበት ተነቅንቆ ተቀስቅሶ ወደ መጨረሻ ወንበር እንዲሸጋሸግ ሲደረግ ተሳፋሪዎች ቁጭት ታየባቸው። የአፍ ወለምታው፣ አንድምታው ሰፊ የሆነ ቋንቋ አጠቃቀም ባጥለቀለቀን በዚህ ጊዜ እንደ አዛውንቱ ቆመው ቢሟገቱ ካሳውን እያሰቡ ሳይሆን አይቀርም። ካሳው ቀርቶብኝ ኮሶው ባሻረኝ አትሉም!
ጉዟችን ተጀምሯል። “ወያላ የለውም እንዴ ታክሲው?” ትላለች ብር የያዙ እጆቿን አንከርፍፋ ሦስተኛው ረድፍ ላይ የተሰየመች ወይዘሮ። ሾፌሩ የቴፑን ድምፅ እየቀነሰ፣ “ወያላዬ እኮ ዘመተ!” ከማለቱ ከጎኔ የተቀመጠው ስልኩን አወጣና የፌስቡክ ግድግዳው ላይ ‘ኢትዮጵያና ኤርትራ ጦርነት ጀመሩ’ ብሎ ሲጽፍ አየሁት። አቤት ችኮላ? ስንቱ ባልተጣራ ወሬ ስንት ነገር ደርሶበት ይሆን? “የት ነው የዘመተው?” አዛውንቱ ገና ኩርፊያቸው አልቀቃቸውም። “ወደ ባቡሩ! ‘አሰናብተኝ በቃ። እዚህ ባቡር ላይ የሆነ ነገር ታይቶኛል። ወይ ያልፍልኛል ካልሆነም ኮረንቲውን ጨብጬ አልፋለሁ’ አለኝ፤” ሲላቸው አዛውንቱ ከተቀመጡበት ለመነሳት ሞከሩ። አብን፣ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን ሥልት ባለው አጠራር መንገድ ካስተያየን ለሁለተኛ ጊዜ ጎላ አርገው ጠርተው አማተቡ።
ወደ ሾፌሩ መለስ ብለው፣ “ምን ዓይነት ክፉ ሰው ነህ? እና ሰደድከው?” ዓይን ዓይኑን እያዩ። “ታዲያ ምን ምርጫ አለኝ? ምርጫ ሲኖር እኮ ነው። ይኼንንም እሱ ሆኖ ነው። ማን ነው በዚህ ሕግ አሰናብቱኝ ብሎ ተሰናብቶ የሚሄድ ሠራተኛ?” አላቸው ተራውን ትኩር ብሎ እያጠናቸው። “ለነገሩ ሸኝውስ ምን ጤና አለው?! ጥፋ እንጂ ልማ ብሎ ማን ይሸኛል? እንዲያው አደራህን ሄዶ እንዳለው ኮረንቲውን ቢጨብጠውስ?” ሲሉ ከጎናቸው ያለው ተሳፋሪ፣ “አንቱ ደግሞ! እንኳን ተጨብጦ የሚጨብጥ የበራድ ውኃ የሚያፈላ የኤሌትሪክ ኃይል አለ እንዴ? ይኼው እኔ ለእራት የምበላውን ወጥ እኮ ጠዋት ነው ጥጄው የምወጣው። መብራቱ ሲመጣ ሲሄድ ይውልና ማታ ስገባ አሙቆት ይጠብቀኛል፤” ቢላቸው፣ “የባሰ አለ አገርህን አትልቀቅ!” ብለው ዝም አሉ። አያስችለንም እንጂ ዝምታ ‘ቢዝነስ’ ቢሆን ትርፍ በትርፍ እንዳትሉ ደግሞ። ህም!
“ሒሳብ ለማን ነው የምንሰጠው? ነው በነፃ ነው? ሾፌር?” ወይዘሮዋ ለክፍያ ቸኩላለች። ሾፌሩ መንገድ መንገዱን እያየ ፈገግ ብሎ፣ “እንኳን የምድሩ የፅድቁ ጎዳና ‘ገንዘብ’ ሆኖ እያየሽ አላሳዝንሽም?” አላት በግንባር መስተዋቱ የኋሊት በዓይኑ እየፈለጋት። “አምጡ እኔ እሰበስባለሁ” ብሎ ከመቅፅበት ያ በገዛ ገንዘቡ፣ በቴክኖሎጂ ዕርዳታ መስሚያውን ደፍኖ የነበረው ወጣት ተነሳ። ይኼን ጊዜ መጨረሻ ወንበር ከተቀመጡት ወጣቶች አንዱ፣ “የዛሬን አያርገውና ትምህርት ቤት እያለሁ ደብተር ሰብሳቢ እኔ ነበርኩ። ዛሬ ገንዘብ ሲሆን የሚቀድመኝ በዛ። ኋለኞች ወደፊት፣ ፊተኞች ወደኋላ፤” እያለ አጠገቡ ያሉትን ለወሬ ይቀሰቅሳል። “አይዞህ! ቢያንስ ተሰብስቦ የሚታረም ደብተር የነበራቸው ተማሪዎች መሀል ተምረሃል። አታያቸውም የዛሬዎቹን? መቼ የሚሰበሰብ ቀልብ አላቸው?” አለች ወይዘሮዋ ተሽቀዳድማ።
“ምን ያድርጉ እነሱ? ወላጅ ዘመን ተገልብጦበት ግራ ገባው። መንግሥት የትውልዱን ሥነ ምግባር ከማነፅ ይልቅ የፖለቲካ አቋሙን የሚደግፍ አልያም ስለምንም ነገር ደንታ የማይሰጠው ትውልድ በማነፅ ተጋ። ጎረቤት የጎረቤቱን ልጅ መግረፍ ቀርቶ በሙሉ ዓይኑ ቀና ብሎ አይቶ የመገሰፅ መብቱን ተነፈገ። ‘ማን ባማጠ ማን ይቆነጥጣል?!’ ይባልልኛል። ይኼ ይኼ ድሮ ቢኖር ኖሮ እኛ እንዲህ እንሆን ነበር?” አለ አንዳች የሚያህል ጥቁር መነጽር ዓይኑ ላይ የሰካ ተሳፋሪ። “አንድም ዓይናችን ነው እባክህ። ምንም ሳይሆን ደህና እያየ የማይመጥነንን የአስተሳሰብ መነጽር ስንቀያየር አይመስልህም ነገሩ ሁሉ ብልሽትሽት ያለው?” የሚለኝ ከጎኔ የተሰየመው ነው። ከፊታችን ደግሞ ቆንጂት ጎልማሳውን፣ “አንተዬ ይኼ ሁላ ዩኒቨርሲቲ ተከፍቶ አስተምሮ እያስመረቀ ‘የዘንድሮ ተማሪ እንኳን ደብተር መቼ ቀልብ አለው?’ ይባላል?” ስትለው፣ “ዝም አትያቸውም? አሉ አይደል እነሱስ ዕውቀት ሳይኖራቸው ዕውቀት ሸማቾችን የሚያሙ?” ብሎ መልሶላት አዳሩን ሊያመቻች አዋዋሉን የሚያሽሞነሙን መሰለ። የነቆራና የሽሙጡ መብዛት ሲገርመን ለከፋና ጠበሳ ተደርቦ አረፈው? እንዲያ ነው!
ጉዟችን ቀጥሏል። ወይዘሮዋና ከጎኗ ተቀምጦ የነበረው ወርደው በምትካቸው የደራ ጨዋታ ይዘው ሁለት ጓደኛማቾች ገብተዋል። “አንተ ግን ያን ያህል ሰዓት ስታስጠብቀኝ ትንሽ ቅም አይልህም?” ይላል አንደኛው። “ምን ማለት ነው ቅም ደግሞ?” ይጠይቃል ያኛው። “ዘንድሮስ አማርኛ ማስጠናት ልጀምር መሰል። ሳያዋጣኝ አይቀርም፤” አንዴ ወደኋላ አንዴ ወደፊት እየተዟዟረ ምክር ጠየቀ። “አማርኛ ለራሱ ‘አሳይለም’ የሚጠይቅበት አገር እየፈለገ ጨንቆታል አንተ ማስጠናት ያምርሃል?” ጎልማሳው ይመልሳል። “ለማንኛውም ያስረፈደኝ ሠልፍ ነው፤” አርፋጁ የወዳጁን ነገር ማነካካት የወደደው አይመስልም። “በባቡር መስሎኝ የመጣኸው? የምን ሠልፍ ነው የምታወራው?” ያኛው ንጭንጩ እንደበረታ ነው። “ቲኬት ለመግዛት ነዋ ሠልፉ። ሠልፍ ትተንማ ምኑን ተለወጥነው? ያለ ተራውና ያለ ሕግ ያደገ አገር አይተሃል? ሁሉም ይሠለፋል፤” ይላል የወዳጁን ንዴት እንደ ማብረድ እያባባሰ።
“በቃ! በቃ! ዝም ካልኩህ ገና ‘በባቡር ስሄድ ‘ትራንስፎርሜሽን’ ተሰማኝ ትለኛለህ እኮ አንተ አታፍርም፤” ሲለው የወዲኛው ቀበል አደረገና “አቦ የታክሲህን አመል እዚያው!” አለው። ሳቅ በሳቅ። ይኼኔ ደግሞ፣ “እኔን የናፈቀኝ ባቡራችን ልክ እንደ ታክሲዎቻችን በሸንቋጭ ጥቅሶች ተሸልሞ ማየት ነው፤” አለች ከመጨረሻ ወንበር። “እስኪ ለምሳሌ? አንድ ጣል አርጊልና፤” ከማለቱ ከጎኔ የተቀመጠው “ለምሳሌ . . . ‘ብድር ባይኖር ኖሮ ይኼኔ አዳሜ ተሠልፈሽ ነበር’ . . . እ . . . ‘ሾፌሩን ማናገር የሚቻለው መብራት ሲጠፋ ብቻ ነው!!’ ወዘተ፤” ስትል ማጨብጨብ የቃጣው ሁሉ ይታያል፡፡ መንገድ ያዋዛል ያልነው ጥቅስ ጥል እንዳይጎትት ፈራን መሰል ተውነው። የባቡሩ ነገር ሲነሳ በየፌርማታው የታዩ የተጣመሙ ጽሑፎች ጉዳይ በለሆሳስ ታለፈ፡፡ በስንቱ እያሳቁ ይቻላል? እየቃጡ መተው ብርቅ ነው?
ወደ መዳረሻችን ነን። “እናንተ…” ይላል ጎልማሳው። “ሰሞኑን የምናየው ነገር አይገርምም?” “ምኑ?” አዛውንቱ ተቀበሉት። “የክረምቱ ዝናብ መዛባት ባስከተለው ችግር፣ መንግሥት ከ4.5 ሚሊዮን ሕዝብ በላይ የሚሆነውን የተፈናቃይ ወገን ለመድረስ እጅ ያጥራል። ያሰብኩትን ያህል ዕርዳታም አላገኘሁም’ ማለቱ?” ብሎ በግርምት ሲናገር፣ “ማየትና መስማት አይለይም እንዴ ይኼ ሰውዬ? ነው ጆሮው ‘ጃም’ ተደርጓል?” ይላል ከኋላ አንዱ ፌዘኛ። “እና ምኑ ገረመህ?” አዛውንቱ አልገባቸውም። “የገረመኝማ ያልጠበቅኩት የመንግሥት ግልጽነት ነው፤” ሲል ጎልማሳው፣ “ምን ይላል ይኼ ሰው? ዕድሜ ለዚህ ለዚህ ካልረዳማ ምን ዋጋ አለው? ‘ጎሽ!’ ነው የሚባል ይኼኔ! አንድ ያለን አንዱ መንግሥታችን ነው፤” ብለው አፋቸውን በጋቢያቸው ሲጠራርጉ፣ “ድሮስ ሁለት ፀሐይ ያበራል እንዴ ባንድ ሰማይ? እስካሁን ደህና ነበሩ እኚህ ሰው፤” ይለኛል ከጎኔ። ተሳፋሪው የግልጽነትና ተጠያቂነት ባህል የበለጠ እንዲዳብር ከአንጀቱ ሐሳብ ማዋጣቱን ቀጠለ።
“እኔን ያማረኝ…” ይላል ወዲያ ማዶ። “… ‘የእንትን የእንትን አንዳንድ ወረዳ ነዋሪዎች ልማቱ አስተማማኝና ፈጣን እንደሆነ ገለጹ’ ዓይነቱ ዜና ቀርቶ፣ ‘የቀላል የከተማ ባቡር ሥራ ተጠናቆ አገልግሎት መስጠት ቢጀምርም መንግሥት የክልል ከተሞች ዕድገትና ልማት ጠበቅ ተደርጎ እስካልተያዘ ድረስ ሁሉም አዲስ አበባ አዲስ አበባ እያለ የትራንስፖርት ችግሩ ሊቀረፍ እንደማይችል ገለጸ’ በሚለው ሲተካ ማየት ነው፤” ሲል ሌላው ተቀብሎ፣ “ከኢኮኖሚው ዕድገት ጋር ተያይዞ የመጣው የኑሮ ውድነት በወርኃዊ ገቢ ብቻ ለሚተዳደሩ ዜጎች ሸክሙ ከባድ በመሆኑ፣ አስቸኳይ መፍትሔ ለመሻት መንግሥት ርብርብ ማድረግ እንዳለበት አመነ’ ሲባል መስማት ናፍቆኛል፤” ይላል። ተሳፋሪዎች በጠቅላላ እኔን የማረኝ እያሉ ስለፍትሕ፣ ዴሞክራሲ፣ መልካም አስተዳደር የናፈቁትን ፍርጥርጥ ያለ ዜና ሲያነቡ ሾፌሩ ደንግጦ፣ “እርጉዝ ብቻ ነው እንዴ የጫንኩት?” እያለ ታክሲዋን ዳር አስያዛት። “ማርገዝ ብቻ ምን ዋጋ አለው በሰላም ካልተገላገሉት?” ብለውት አዛውንቱ አመስግነው ወረዱ። ‘የአዋላጅ ያለህ?’ እያለ ሁሉም ወርዶ በየፊናው ሲተም በሐዘንና በቁጣ የተሞሉ ልቦች በይቅርታ መብረድ እንዳለባቸው አመላካች ነበር፡፡ ለማንኛውም ይቅርታ ማለትና መቀበል ቢለምድብንስ? መልካም ጉዞ!