[ክቡር ሚኒስትሩ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ጅማሬ ሥነ ሥርዓት ላይ ተገኝተው ከተጋባዥ እንግዶች መካከል ከአንደኛው ጋር እያወሩ ናቸው]
- አንተ ለመሆኑ እዚህ አገር አለህ እንዴ?
- አለሁ ክቡር ሚኒስትር፣ የት እሄዳለሁ ብለው ነው?
- እኔማ አይቼህ ስለማላውቅ ከአገር የወጣህ መስሎኝ ነው፡፡
- አገሬን ጥዬማ የትም አልሄድም፡፡
- አዎ አገራችን እያደገች ስለሆነ ጥሎ መሄድማ ጥሩ አይደለም፡፡
- ከአገር ጥፉ ጥፉ የሚያሰኙ በርካታ ችግሮችማ አሉ፡፡ ግን…
- ግን ምን?
- እየታየ ባለው የልማት ጅማሬ ባንፅናና ኖሮ መጥፋታችንማ አያስገርምም፡፡
- ምን ችግር ኖሮ ነው እንዲህ የተመረርከው?
- ራሳችሁ በግልጽ ያመናችሁዋቸው ችግሮች ምን ሊባሉ ነው?
- በእርግጥ ችግሮች ቢኖሩም እነሱን በቆራጥነት ለመፍታት ወስነናል፡፡
- ቆራጥነቱ እኮ ከወሬ አላልፍ እያለ ነው፡፡
- ይኼው ባቡሩን ሥራ እንዳስጀመርነው ሌላውንም እናቀላጥፈዋለን፡፡
- የዘገየው ባቡር ሥራ መጀመሩ ደስ ቢልም፣ የእናንተ ቆራጥነት ግን ያሳስበኛል፡፡
- ለምን ያሳስብሃል?
- ከስብሰባ የመግለጫ ጋጋታ በስተቀር ተግባራዊነቱ ላይ ታጠራጥራላችሁ፡፡
- ስብሰባዎቻችን እኮ የስትራቴጂዎቻችን መቀመሪያ ናቸው፡፡
- ብዙዎቹ ስብሰባዎቻችሁ ደግሞ ዴሞክራሲና ፍትሕን ማዳፈኛ እየሆኑ ነው፡፡
- ምሳሌ አቅርብልኝ፡፡
- ለምሳሌ ከመቐለው ጉባዔ በኋላ ቴሌቪዥኑን ሳየው ወሬው ሁሉ ዴሞክራሲ አይሸትም፡፡
- ምንድነው የሚሸተው?
- የተለመደው የጎረና ፕሮፓጋንዳ፡፡
- የአንተ አፍንጫ ታሞ ቢሆንስ?
- ይኼ እኮ ነው ችግራችሁ፡፡
- ምኑ?
- ተቃውሞ ሲቀርብ ለማረም ከመሞከር ይልቅ ማጣጣል፡፡
- ስለዚህ?
- ስለዚህማ ዛሬ በደስታ የተጀመረው የባቡር ትራንስፖርት ዓይነት በሕዝብ ተቀባይነት ያለው ሥራ አሳዩ፡፡
- ተቃዋሚ ትመስላለህ፡፡
- መደገፍም መቃወምም መብት መሰለኝ፡፡
- አንዴ እንኳ ምሥጋና ከአፍህ አይወጣም?
- ምሥጋና ለሚገባው ይቀርባል፡፡ የሚወቀሰው ደግሞ በደንብ ይቀጠቀጣል፡፡
- ምን ይሻልሃል?
- ወቀሳ ማቅረብ፡፡
- ወቀሳ ምን ያደርግልናል?
- በአድርባዮች ሽንገላ የሞቀ ልባችሁን ቀዝቀዝ ያደርገዋል፡፡
- እንዲያው ምን ቢደረግ ይጥማችኋል?
- ልባችንን ማሸነፍ ከቻላችሁ በቂ ነው፡፡
- አሁንስ?
- አሁንማ ሩብ መንገድ አልደረሳችሁም፡፡
- ተሳስተሃል፡፡
- አንድ ነገር ልንገርዎት?
- ምን?
- ከውዳሴ ይልቅ ለወቀሳ ትኩረት ስጡ፡፡
- እስቲ ይሁና!
[ክቡር ሚኒስትሩ ከሾፌራቸው ጋር ወደ ቤት እየተመለሱ ነው]
- የባቡሩን ሥራ መጀመር እንዴት አገኘኸው?
- ደስ ይላል… ግን…
- ግን ምን?
- በቻይና የሚነዳ ባቡር ማየት ይገርማል፡፡
- የእኛዎቹ እኮ እስከሚሠለጥኑ ነው፡፡
- ቻይና ለወራት ሠልጥነው ተመለሱ ተብሎ እኮ በቴሌቪዥን ሲታዩ ነበር፡፡
- ቢሆንም የሥራ ላይ ልምምድ ማድረግ ይገባቸዋል፡፡
- የሚገርመው የፌርማታዎቹን ስያሜ አየተንተባተበች የምትጠራው ሴት መንገደኞችን ታሳስታለች፡፡
- ምን ብላ ጠራች?
- ስለ ምትኮላተፍ አይሰማም፡፡
- ለጊዜው መቻል ነው፡፡
- ክቡር ሚኒስትር በአማርኛ ባይነገረን እኮ ሁላችንም ቃሊቲ ገብተን ነበር፡፡
- ምን ልትሆኑ?
- ሳንዘጋጅ እስረኞችን ልንጠይቅ፡፡
- አሹፈህ ሞተሃል፡፡
- እውነቴን ነው እኮ?
- ሌላስ?
- ለዘመናት አንበሳ አውቶቡስ በኢትዮጵያውያን እንዳልተነዳ ለባቡራችን ቻይና መሆኑ አናዶኛል፡፡
- ለጊዜው ነው ሲባል አልሰማህም እንዴ?
- ለጊዜው ነው እየተባለ ስንቱ ዘለዓለማዊ ለመሆን ሲታገል እያየን?
- ማነው እሱ?
- እሱን ሆድ ይፍጀው፡፡
- ከማን ጋር ነው የምትውለው?
- ከጓደኞቼ ጋር፡፡
- ስንተዋወቅ?
- ምኑን?
- ውሎህን ነዋ፡፡
- ሆሆሆ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- አይዞህ ለጨዋታ ያህል ነው፡፡
- አዎ ቻይናም በሰፊው እየተጫወች ነው፡፡
- ምን ዓይነት ጨዋታ?
- በባቡር ፌርማታዎች ላይ የተጻፉትን አይተዋል?
- ምን ተጻፉ?
- ቻይንኛ ይሁኑ አማርኛ የማይገቡ ነገሮች በሽ ናቸው፡፡
- ወሬኛ!
[ክቡር ሚኒስትሩ ቤታቸው ገብተው ከባለቤታቸው ጋር ምሣ ለመብላት ገበታ ቀርበዋል]
- የባቡሩን ሥራ መጀመር በአካል ተገኝተሽ ብታይው ጥሩ ነበር፡፡
- ሥራ አላጣሁም እባክህ፡፡
- ምነው?
- ቴሌቪዥኑ እየደጋገመ ካሳየኝ በቂ ነው፡፡
- ምን ምን አየሽ?
- ሕዝቡ ተሳፍሮ ሲጓዝና በየፌርማታው ሲወርድ አየሁ፡፡
- ምን ተሰማሽ?
- ከእኔ ይልቅ ወይዘሮ ስርጉት ያሉት ይሻላል፡፡
- እሳቸው ደግሞ ምን አሉ?
- ለዚህ ትውልድ ነው እንጂ ለእኛ ብርቅ አይደለም አሉ፡፡
- ምን አልሻቸው?
- እኔ ምን እላለሁ? እሳቸው ከአዲስ አበባ ድሬዳዋ የተንፈላሰሱበትን ዘመን እያስታወሱ ብዙ አወሩ፡፡
- ምንድነው የሚሉት?
- ለትውልዱ ዘመናዊ ባቡር ሥራ መጀመሩ ጥሩ ነው፡፡ ነገር ግን የበለጠ መሥራት እንጂ በአንድ ጅምር መኩራራት አይገባም ነው ያሉት፡፡
- ይኼው ከአዲስ አበባ – አዋሽ – ጂቡቲ፣ ከመቐለ – ወልዲያ – አዋሽ – ጂቡቲ ሥራው ቀጥሏል፡፡ ወደ ደቡብና ምዕራብ ኢትዮጵያም እንዲሁ ይቀጥላል፡፡
- እሳቸው ይኼንን አላጡትም፡፡
- ታዲያ ምን እያሉ ነው?
- አንድ ነገር ከያዘ የማይለቀው ቴሌቪዥን በወሬ እንዳያደነቁረን ነው የሚሉት፡፡
- ተደጋግሞ ቢወራ ምን ይላል?
- እጅ እጅ ይላል ነው የሚሉት፡፡
- ምኑ ነው እጅ እጅ የሚለው?
- ድግግሞሹ፡፡
- ወይ ጣጣ?
[ክቡር ሚኒስትሩ በጠዋት ቢሮአቸው ገብተው ጸሐፊያቸው አማካሪያቸውን እንድትጠራ ባዘዙዋት መሠረት መጣ]
- እንዴት አደሩ ክቡር ሚኒስትር?
- ምን ሰላም አለ ብለህ ነው?
- ምን ሆኑ?
- ትናንት ባቡሩ ሥራ ከጀመረ ጊዜ ጀምሮ ጨቅጫቂዎች በዝተውብኝ ስናደድ ነው ያደርኩት፡፡
- አይ ክቡር ሚኒስትር ምድረ ኪራይ ሰብሳቢ የፈለገውን ቢያወራ ለምን ይናደዳሉ?
- እንደሱ ነው ብለህ ነው?
- አልገባኝም?
- ዙሪያችንን ያሉ ሰዎች እኮ ናቸው በነገር የሚሸነቁጡን፡፡
- እነሱ ያውሩ እኛ ሥራ ላይ ነን፡፡
- ይኼም አባባል እያስተቸን ነው፡፡
- ለምን?
- ተቃውሞ መስማት አትፈልጉም እየተባለ፡፡
- ክቡር ሚኒስትር ምድረ ኪራይ ሰብሳቢን ዝም በሉዋቸው፡፡
- ሥራ ላይ ነን እያላችሁ አበዛችሁት እያሉን ነው እኮ?
- ምን እንበል ታዲያ ክቡር ሚኒስትር?
- እኔም ግራ ገብቶኛል እባክህ፡፡
- ምኑ?
- ይህ ሕዝብ ምን እንደሚፈልግ?
- መንጌም ያለው ይኸንን ነበር እኮ?
- የእሱን ስም አታንሳብኝ፡፡
- ለምን ክቡር ሚኒስትር?
- ያቅለሸልሸኛል፡፡
- እውነት ነው ክቡር ሚኒስትር ወደ ጉዳያችን እንግባ፡፡
- የእነዚያን ሰዎች ፕሮፖዛል አየኸው?
- ክቡር ሚኒስትር የየትኞቹን?
- የአርቲስቶቻችንን ነዋ?
- የሚገርሙ ፕሮፖዛሎችን ነው ያቀረቡት፡፡
- ጠቅለል አድርገህ ንገረኝ እስቲ፡፡
- ሲጀምሩ “እኛ ልማታዊ አርቲስቶች …” ነው ያሉት፡፡
- እሺ?
- የፕሮጀክቶቹ ጨረታዎች “ውስን ይሁኑልን” ብለዋል፡፡
- ምን ማለት ነው?
- ግልጽ ጨረታ እንዳይሆን፡፡
- በጄ?
- በ“ውስን” ጨረታዎች መሳተፍ ያለባቸውን የልማታዊ አርቲስቶችን ስም ዝርዝሮችም አቅርበዋል፡፡
- እነ ማንን?
- “ልማታዊ” የሚባሉትን ዋነኞቹን ነዋ፡፡
- ከዚያስ?
- እንደየፍላጎታቸው ፕሮጀክቱ ከተሰጣቸው በኋላ የድጋፍ ደብዳቤ እንዲጻፍላቸው፡፡
- ለማን?
- የድጋፍ ደብዳቤው ለየመንግሥታዊ መሥሪያ ቤቶች ተልኮ ስፖንሰርሺፕ እንዲጠይቅላቸውም ይፈልጋሉ፡፡
- ይህንን ሁሉ ትብብር ምን ስለሆኑ ነው የሚጠይቁት?
- “ልማታዊ አርቲስቶች በመሆናችን ነው” ብለዋል፡፡
- የእኛ ጥቅም ምንድነው?
- ክቡር ሚኒስትር መደራደር ነዋ፡፡
- እኛው የራሳችንን ፕሮጀክትና የድጋፍ ደብዳቤ እየሰጠን እንደራደር?
- ክቡር ሚኒስትር ዘመኑ እኮ የጥበብ ነው፡፡
- የምን ጥበብ?
- “ልማታዊ አርቲስቶች” የሚተውኑት ነዋ፡፡
- እኛም ከእነሱ ጋር እንተውን እንዴ?
- የግድ ይላል ክቡር ሚኒስትር፡፡
- እኛ የምንተውነው ለምንድነው?
- በዚህ ዘመን ማንም በድፍረት መተወን ስለሚችል፡፡
- ያለ ሙያችን?
- ክቡር ሚኒስትር ማን ሙያ ኖሮት ነው የሚተውነው? ለምሳሌ ልማታዊ የሚባሉት አርቲስቶቹም በጨበጣ እኮ ነው የሚተውኑት፡፡
- እነሱ እኮ መድረኩን፣ ቴሌቪዥኑን፣ ሬዲዮኑን፣ ፊልሙን ሳይቀር በሙያቸው ተቆጣጥረውታል፡፡
- ክቡር ሚኒስትር አይመኗቸው፡፡ በጨበጣ መተወን ስለቻሉ እኮ ነው እኛንም…
- እኛንም ምን?
- በቁጥጥር ሥር ያዋሉን፡፡
- በል ዝም በል!
[የክቡር ሚኒስትሩ አማካሪ ከወጣ በኋላ ጸሐፊያቸው የዳያስፖራ እንግዳ እንዳለ ነግራቸው እንዲገባ ተደረገ]
- እስካሁን ወደ አሜሪካህ አልተመለስክም እንዴ?
- አለሁ ክቡር ሚኒስትር፡፡
- ምነው እዚህ ቆየህ እባክህ?
- አዲሱን ዓመት ከቤተሰብና ከወዳጆቼ ጋር አክብሬ ልመለስ ብዬ ነው፡፡
- በዓል አገር ቤት ማክበር ደስ ይላል አይደል?
- በጣም እንጂ፡፡ ባቡሩን ባየንበት ዓይን ሌላው ግን…
- ሌላው ምን?
- አንዳንድ የማያቸውና የምሰማቸው ነገሮች ግን እርምት ያስፈልጋቸዋል፡፡
- ለምሳሌ?
- በአዲሱ ዓመት ዋዜማ የሰማሁት አናዶኛል፡፡
- ምን አናደደህ?
- ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት በተገኙበት ሥነ ሥርዓት ላይ የሰማሁት ነገር አበሳጭቶኛል፡፡
- እስኪ ንገረኝ፡፡
- መድረኩን የሚመሩት አስገራሚ ጉዶች አዲሱ ዓመት የሚጀምረው ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ነው ብለው አረፉት፡፡
- እነማን ናቸው?
- “ልማታዊ አርቲስቶች” የምትሉዋቸው፡፡
- ዘመኑ የሚቀየረው መቼ ነበር?
- አገሪቱ በራሷ ካላንዴር መሠረት ቀኗ የሚቀያየረው ሁሌም ከንጋቱ አሥራ ሁለት ሰዓት ነው፡፡
- ነው እንዴ?
- አዎን፡፡
- ማረጋገጫ አለው?
- መንግሥት ለበዓላት መድፍ የሚተኩሰው በዚያ ሰዓት መሆኑ እኮ የአገሪቱ ልዩ መታወቂያ በሆነው ካሌንደር ምክንያት ነው፡፡
- ልማታዊ አርቲስቶቹ ከየት አመጡት ታዲያ?
- የዘንድሮ ‘ዕውቀት’ እኮ እንትን ሆኗል፡፡
- ምን ሆነ?
- ኮንትሮባንድ፡፡
- ማለት?
- ከየትም እየቃረሙ ማውራት የአዋቂነት ምልክት ከሆነ ከኮንትሮባንድ ዕቃ ተለይቶ አይታይም፡፡
- ይኼ ነው ያበሳጨህ?
- ሌላም አለ፡፡
- ምንድነው እሱ?
- እነዚህ “ልማታዊ …” የምትሉዋቸው ሰዎች በጣም አብዝተውታል፡፡
- ምንድነው ያበዙት?
- ጨረታ በውስን እየተባለ ያለ ውድድር ይሰጣቸዋል፡፡ በመንግሥት ስፖንሰርሺፕና በመሳሰሉት ሁሉንም ነገር መቆጣጠራቸው ብዙዎችን ቅር አሰኝቷል፡፡
- እነሱ በትጋት ሲንቀሳቀሱ መደገፍ ተገቢ አይደለም ነው የምትለው?
- ድጋፍ ሁሉንም አሳታፊ፣ ትክክለኛ፣ ፍትሐዊና ከሙስና የፀዳ ሲሆን ጥሩ ነው፡፡
- አሁንስ?
- አሁንማ የሚታየው አድልኦና መጥፎ መንፈስ የከበበው ድርጊት ነው፡፡
- መጥፎ መንፈስ ስትል አልገባኝም?
- ይኼንንማ እርስዎም ያውቁታል፡፡
- ምኑን ነው የማውቀው?
- በልማት ስም ከሚያጭበረብረውና ከሚያወናብደው ጋር አብሮ እፍ ማለቱን፡፡
- ለመሆኑ ልማታዊ ማለት ምን እንደሆን ታውቃለህ?
- ልማታዊ ማለት በሚገባ ይገባኛል፡፡ አልገባህ ያለኝ ሌላው ነው፡፡
- ምኑ ነው የማይገባህ ታዲያ?
- “ልማታዊ አርቲስት፣ ጋዜጠኛ፣ መሐንዲስ፣ ነጋዴ…” ብሎ ነገር ግን አይገባኝም፡፡
- ለምን አይገባህም?
- “ልማታዊ እስስት” ማለት ስለሚመስለኝ፡፡
- እንዴት እባክህ?
- እስስት በየደረሰበት አይደል ቀለሙን የሚቀያይረው?
- እና?
- እነዚህም ልማታዊ የምትሏቸው አካላቸው ከእናንተ ጋር ይምሰል እንጂ ልባቸው ሌላ ጋ ነው፡፡
- የት?
- ልባችን እያወቀው?
- ልብህ ካወቀው ንገረኛ?
- ሞቅ ሲላቸው ምን እንደሚሉዋችሁ ማየት ይፈልጋሉ?
- የት?
- ቺቺኒያ!
- የባሰ አታምጣ!