ዴቪድ ኬኔዲ፣ በአሜሪካ ኤምባሲ የፐብሊክ አፌርስ ኃላፊ
እየተገባደደ ባለው የ2015 ዓመት (እ.ኤ.አ.) የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ላለፉት 75 ዓመታት አሜሪካ በመላው ዓለም ስትተገብራቸው የቆዩትን የልምድ ልውውጥ ፕሮግራሞች በመዘከር ላይ ይገኛል፡፡ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በየዓመቱ ከ50 ሺሕ በላይ ተሳታፊዎችን ጉዳይ ይከታተላል፡፡ አሜሪካ የልምድ ልውውጥ ፕሮግራሞችን ማስፋፋት የጀመረችው የሁለተኛው የዓለም ጦርነት ከተገባደደ በኋላ ነው፡፡ አሜሪካ የሐሳብና የመረጃ ልውውጦች ትልቅ ተፅዕኖ እንደሚኖራቸው በመገንዘብ፣ ዓለም አቀፍ ግንኙነቶች እንዲጠናከሩ የተለያዩ አገር ሰዎችን ወደ አሜሪካ በመውሰድ የልምድ ልውውጥ ማካሄድ ጀመረች፡፡ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የባህል ግንኙነት የተባለ ክፍል በማቋቋም ከተለያዩ መስኮች የተውጣጡ መሪዎች ወደ አሜሪካ እንዲያቀኑ የጉዞ ዕድሎችን ማመቻችት ጀመረ፡፡ ይህም ‹‹ኢንተርናሽናል ቪዚተር ሊደርሺፕ ፕሮግራም›› እየተባለ የሚጠራውን የልምድ ልውውጥ መድረክ ፈጠረ፡፡ በሒደትም ፉልብራይትና ማንዴላ ዋሽንግተን የተባሉ ፕሮግራሞች ለውጭ ዜጎች መሰጠት ተጀመሩ፡፡ ብሩህ ይሁንበላይ በአሜሪካ ኤምባሲ የፐብሊክ አፌርስ ኃላፊ የሆኑትን ዴቪድ ኬኔዲን በ75 ዓመት የልምድ ልውውጥ ፕሮግራሞች አልማዝ ኢዮቤልዩ አከባበር፣ ወደፊት ስለሚካሄዱ ፕሮግራሞችና በሌሎችም ርዕሰ ጉዳዮች ላይ አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- በአሜሪካ ስላለው የልምድ ልውውጥ ፕሮግራም አጀማመር ቢነግሩን? እንዲጀመር ምክንያት የነበሩ ነገሮችስ ምንድን ነበሩ?
ዴቪድ ኬኔዲ፡- በአሜሪካ ታሪክ ውስጥ የልውውጥ ፕሮግራሞች እንዲሁም ፐብሊክ ዲፕሎሚሲ የረጅም ጊዜ ታሪክ አላቸው፡፡ በመደበኛነት የተጀመሩትም ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ነበር፡፡ አሜሪካውያን ከሌሎች የውጭ አገሮች የጋራ እሴቶች ጋር መስተጋብር እንዲፈጥሩ በሚል ዓላማ ነው ፕሮግራሞቹን ለመጀመር ያስቻለው፡፡ ከቀደምት ፕሮግራሞች አንዱ ፉልብራይት የሚባለው ፕሮግራም ሲሆን፣ የተጀመረውም እ.ኤ.አ. በ1946 ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ ኢንተርናሽናል ቪዚተር ሊደርሺፕ ፕሮግራም ነው፡፡ እነዚህ ቀደምት ፕሮግራሞች ሲሆኑ፣ ዓላማ የተደረገውም አሜሪካውያንን ከሌሎች ታዳጊ አገሮች መሪዎች ጋር እንዲተዋወቁ በተለይ ተመራጭ የሚደረገው የውጭ ዜጎች ከሆኑ ወጣቶች ጋር በጋራ እሴቶች ላይ ግንኙነት ወይም ቁርኝት እንዲፈጥሩ ማድረግ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ የሚመስለኝ አሜሪካ ሁልጊዜም ቢሆን በጋራ እሴቶች ዙሪያ የሕዝብ ለሕዝብ የልምድ ልውውጥ ማድረግ ሲበዛ ጠንካራ መሣሪያ እንደሆነ ስለምታምን ነው፡፡ እናንተ የራሳችሁ የቆየ የውጭ ፖሊሲ መሣሪያ አላችሁ፡፡ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ጀምሮ አሜሪካም ቁልፍ የሆኑ የውጭ ፖሊሲ ማዕቀፎች አሏት፡፡ በየጊዜው በርካታ ፕሮግራሞችን እያቀፈና እያስፋፋ የመጣ ነው፡፡ አሁን የባህል ልውውጥ፣ የሙዚቃና የሥነ ጥበብ ልውውጦችን አካቶ ቢመጣም ከመነሻው ሲጀመር ዋና ዓላማው ግን ሰዎችን ማገናኘት ነው፡፡ በመሆኑም በየጊዜው እየተስፋፋ ሊመጣ ችሏል፡፡
ሪፖርተር፡- በቀዝቃዛው ጦርነት ወቅት በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር በተያያዘ የልውውጥ ፕሮግራሙ ጠባይ ምን ይመስል ነበር?
ዴቪድ ኬኔዲ፡- ይህንን ጥያቄ ማምጣትህ ደስ የሚል ነው፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ አንዳንድ ለውጦችን አምጥታለች፡፡ ቀዝቃዛው ጦርነትም ለዚህ ለውጥ ትልቁን ሚና ስለመጫወቱ ምንም ጥርጥር የለውም፡፡ ከመነሻው የልውውጥ ፕሮግራሞች ሲካሄዱ የነበረው በአሜሪካ በምዕራቡ ንፍቀ አካባቢ በሚገኙ አገሮች መካከል ነበር፡፡ ይሁንና እየተስፋፋ ሊመጣ ችሏል፡፡ በቀዝቃዛው የዓለም ጦርነት ወቅት ኮሙዩኒዝም ከምዕራቡ ዓለም ዴሞክራሲ የሐሳቦች ሽኩቻ ላይ ነበር፡፡ የሕዝብ ለሕዝብ ልምድ ልውውጦችና ሐሳቦችን በነፃነት መለዋወጥ በጣም ጠቃሚ ነው፡፡ ምክንያቱም ያኔ ያሰብነውና አሁንም የምናስበው የዴሞክራሲ ሐሳቦች ጠንካራና ለሕዝብም ትክክለኛ ሐሳቦች እንደሆኑ ነው፡፡ በዚያን ጊዜ የአሜሪካ የመረጃ ኤጀንሲ የሚባል ተቋም ነበር፡፡ ይህ ተቋም የባህል ፕሮግራሞችና የትምህርት ጥምረት ቢሆንም የአሜሪካ ድምፅ የተሰኘውን የመረጃ ፕሮግራሞችንም ያካትት ነበር፡፡ አሁን በባህል ልውውጥ ረገድ ትኩረት የምንሰጥበት ጊዜ አይደለም፡፡ ይሁንና በጣም ጠቃሚው የሐሳብ መለዋወጫ መንገድ ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ሥራዬን የጀመርኩት እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ ሲሆን፣ በቀድሞው ሶቪዬት ኅብረት ውስጥ የባህል ልውውጥ ላይ በማተኮር ነው፡፡ ወደ ሶቪዬት ኅብረት በሚደረጉ የባህል ልውውጥ ፕሮግራሞች ላይ እሳተፍ ነበር፡፡ ሥራው ስለአሜሪካ ሕዝብ መናገር ነበር፡፡ ምክንያቱም ይህንን ማድረግ ይገባል ብለን በማመናችን ነው፡፡ ዝግ በነበረው የኮሙዩኒስት ሥርዓት ውስጥ ስለአሜሪካ ማውራት ማለት ጠንካራ መልዕክት ማስተላለፍ ስለነበር ነው፡፡ የምሥሎችና የቃላት ኃይል በጣም ጠቃሚነት ነበራቸው፡፡ አሁንም ቢሆንም በዚህ እናምናለን፡፡
በንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ ስትመጣ ያን ያህል የከረረ የሐሳብ ጦርነት አልነበረም፡፡ ማለቴ በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል በግልጽነት ላይ የተመረኮዘ የሰዎች ልምድ ልውውጥ ይደረግ ነበር፡፡ ስፖርተኞችና መምህራን ይመጡ ነበር፡፡ አሁንም ድረስ በሁለቱ አገሮች መካከል ላለው ትብብርና መልካምነት መሠረቱን የጣለ አስገራሚ የሐሳቦች ልምድ ልውውጥ በዚያ ጊዜ ይካሄድ ነበር፡፡ ደርግ ሲመጣ ተቋርጦ ነበር፡፡ ይሁንና ከዚያ በኋላ ጠንካራ የትምህርት ልውውጥ ፕሮግራሞች ሲካሄዱ ቆይተዋል፡፡ በርካታ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንቶች ትምህርታቸውን በአሜሪካ የልውውጥ ፕሮግራሞች አማካይነት ተከታትለዋል፡፡ የባህል ሰዎች ከሆኑት መካከል በጃዝ ሙዚቃ ታዋቂ የሆነው ዱክ ኤሊንግተን ከሙላቱ አስታጥቄ ጋር ተጫውቷል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግም በጣም ታዋቂ ድምፃውያን ከሆኑት መካከል ‹‹ስዊት ሃኒ ኢን ዘ ሮክ›› የተባለው ቡድን በባህል ልውውጥ መድረኮች ለመሳተፍ መጥቶ ነበር፡፡ በዚህ የሁለቱን አገር ሕዝቦች በሚነካ ሁኔታ ነበር ሲካሄድ የቆየው፡፡ አሜሪካና ኢትዮጵያ ለምዕተ ዓመት ያህል የቆየ የረጅም ጊዜ ግንኙነት ሲኖራቸው የመጀመሪያቹ የልውውጥ መድረኮች የተካሄዱት ግን እ.ኤ.አ. በ1920ዎቹና በ1930ዎቹ ውስጥ ነው፡፡ ከዚህ በተለየ ይዘት ግን በ1950ዎቹም ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ አሁንም ቀጥሏል፡፡
ለምሳሌ የአሁኑ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የአሜሪካ የልውውጥ ፕሮግራም ተሳታፊ ነበሩ፡፡ እንደምናስበው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መልካም ፕሮግራም ነበር፡፡ ይህ እንደጠቀማቸውና መሪዎችም እንዲያውቁንና እንዲረዱን ያስቻለ ፕሮግራም ይመስለኛል፡፡ የልውውጡ አንዱ ዓላማ አንድን ሰው በግድ ማሳመን ሳይሆን አሜሪካን እንዲገነዘብ ማስቻል ነው፡፡ በመሆኑም የኢትዮጵያ መሪዎች ይህንን በተሻለ ተረድተው አንዳችን ከሌላችን ጋር የጋራ መግባባት እንዲኖረን የሚያስችል ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በዚህ ላይ ማስከተል የምፈልገው ጥያቄ ቀደምት ከሆኑት ተሳታፊዎች መካከል ስንመለከት ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝን፣ ፕሮፌሰር መስፍን ወልደ ማርያምንና ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስን የመሳሰሉ ሰዎች እናገኛለን፡፡ እነዚህ ሰዎች የተለያየ የፖለቲካ አመለካከት ያላቸው ናቸው፡፡ የልውውጥ ፕሮግራሙ ምንም ዓይነት የፖለቲካ አመለካከት ቢኖርም ይህንን የማቻቻል ይዘት ያለው ይመስላልና ስለዚህ ምን የሚሉት አለ?
ዴቪድ ኬኔዲ፡- በርካታ የልውውጥ ፕሮግራሞች አሉን፡፡ ከእነዚህ መካከል ደግሞ የተጠቀሱት ግለሰቦች የተሳተፉበትና ‹‹ኢንተርናሽናል ቪዚተር ሊደርሺፕ ፕሮግራም›› አንዱ ነው፡፡ ይህ ዓለም አቀፋዊ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም በወቅቱ የደቡብ ክልል ፕሬዚዳንት የነበሩ ቢሆንም የፕሮግራሙ ጥሩ ጎኑ ግን ገና ሙሉ ለሙሉ መሪ ያልሆኑትን ሰዎች ማሳተፍን ያለመ መሆኑ ነው፡፡ ይሁንና አብዛኞቹ ተሳታፊዎች ወጣቶችና ወደፊት መሪ የመሆን አቅም ያላቸው ናቸው፡፡ ወጣቶቹ የሚመጡት ከባህል መስክ ሊሆን ይችላል፡፡ አሊያም ከጋዜጠኝነት፣ ከሲቪክ ማኅበሰረብ፣ ከፖለቲካ ሲገፋም ከንግድ መስክ ሊሆን ይችላል፡፡ ፕሮግራሙ ጥሩ ነው ከሚያስብሉት አንዱ አብዛኛውን ጊዜ የሚሳተፉት ሰዎች ለትልቅ ቦታና ሥራ ገና በሆኑበት፣ ነገር ግን እያቆጠቆጡ በሚገኙበት ወቅት ላይ ነው፡፡ ተፅዕኖ ፈጣሪ የሆኑ ሰዎችን ልናገኝ እንችላለን፡፡ እኛ ተፅዕኖ እንፈጥርባቸዋለን ማለት ሳይሆን አሜሪካን በተሻለ መረዳት እንዲያውቋት ማድረግ ነው፡፡ በእነዚህ ፕሮግራሞች ሰዎች በሙያ መስካቸው የሚሠሯቸው ሥራዎች ይኖራሉ፡፡ መንግሥታት እንዴት እንደሚንቀሳቀሱ ወይም ማዘጋጃ ቤታዊ (ከተማ አስተዳደሮች) እንዴት እንደሚሠሩ የሚያከናውኗቸው ተግባራት ይኖራሉ፡፡
ከዚህ በተጨማሪ አሜሪካዊ ቤተሰቦችን የመጎብኘት፣ በተለያዩ የአሜሪካ ክፍሎች ያሉ የአሜሪካ ባህላዊ ትዕይንቶች ላይ ሊታደሙ ይችላሉ፡፡ ስለዚህ እነዚህ ሰዎች ወደ አገራቸው ሲመለሱ ስለአሜሪካ የተሻለ ግንዛቤ ይዘው ይመለሳሉ፡፡ የገጠሩና የከተማው አሜሪካ እንዴት እንደሚንቀሳቀስ ይረዳሉ፡፡ እንደማስበው ይህ የውጭ ፖሊሲ መሣሪያ ሲሆን ጠቃሚ ነው ብለን እናምናለን፡፡ ምክንያቱም ሰዎች በተገቢው ደረጃ እንዲያውቁ ለማድረግና የራሳቸውን ውሳኔ እንዲወስኑ ለማስቻል ይጠቅማል፡፡ ሌሎች ለወጣቶችና ለኮሌጅ ተማሪዎችም የሚሰጡ የልውውጥ ፕሮግራሞች እንዳሉን መጥቀስ እፈልጋለሁ፡፡ አንዳንዴ እንደ ልውውጥ ፕሮግራሙ አይሁን እንጂ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎችን የአሜሪካ እንግሊዝኛን እንዲማሩና ስለአሜሪካ እንዲያውቁ ለማድረግ በአንዳንድ ፕሮግራሞች ላይ እናሳትፋቸዋለን፡፡ ለዩኒቨርሲቲ ምሁራን የተዘጋጁና አሜሪካ ሄደው በአሜሪካ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲማሩ የሚረዱ በርካታ ፕሮግራሞችም አሉን፡፡ በጠቅላላው እነዚህ ፕሮግራሞች ሙያቸውን ለማዳበር ለሚፈልጉ ሰዎች የሚሰጡ ናቸው፡፡
ሪፖርተር፡- አብዛኞቹ የልውውጥ ፕሮግራሞች በአመራር፣ በአካዴሚያዊና በባህል ላይ ያተኮሩ ናቸው፡፡ በንግድና መሰል መስኮች ላይ የሚያተኩሩ ፕሮግራሞች አሉ?
ዴቪድ ኬኔዲ፡- ቢዝነስን የተመለከቱ በርካታ ፕሮግራሞች አሉ፡፡ ሆኖም ይህ ተብሎ ተነጥሎ በትኩረት የሚታይ የንግድ ዘርፍ የለም፡፡ ሆኖም ባለፈው ዓመትና ዘንድሮ በኢንተርናሽናል ቪዚቲንግ ሊደርሺፕ ፕሮግራም በኩል ከኢትዮጵያ ኢንተርፕረነርሺፕን በማስፋፋት የተሳተፉ ሰዎች አሉ፡፡ መንግሥታዊ ሥራዎች ላይ ያተኮረ ፕሮግራም ቢሆንም የንግድ ማኅበራትን እንዴት መመሥረት ይቻላል ወይም የንግድ ምክር ቤቶችን እንዴት ማቋቋም እንደሚቻል የሚዳስስ ፕሮግራም ነው፡፡ በቀጥታ ንግድ ተኮር ባለመሆኑ የቢዝነስ ሰዎችን ወደ አሜሪካ መላክ ዓላማው ባይሆንም ጥሩ ጥቅም የሚያስገኝበት ጎን አለው፡፡ ‹‹ማንዴላ ዋሺንግተን›› የተባለው ፕሮግራም አሁንም ድረስ አለ፡፡ ሦስት ክፍሎች አሉት፡፡ አንዱ አስተዳደር ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ሌላኛው ደግሞ በሲቪል ማኅበረሰብ ላይ ያጠነጥናል፡፡ ሦስተኛው በኢኮኖሚክስ ሙያ ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ ስለዚህ እንደ ሥራ ፈጣሪ የሠሩ ሰዎች ወይም ገና ንግድ የጀመሩ ሰዎች የሚሳተፉበት ፕሮግራም ነው፡፡ ንግድ የፕሮግራሙ ጠንካራ አካል ቢሆንም ዋናው መሠረታዊ ክፍል ነው ለማለት ግን አልችልም፡፡ ትኩረቱ በአብዛኛው አስተዳደር ላይ፣ ሲቪክ ማኅበር፣ ትምህርት እንዲሁም ወጣቶች ላይ የሚያተኩር ነው፡፡ እንደምታውቀው በአሜሪካ የግሉ ዘርፍ ላይ ያለን ትኩረት በጣም ጠንካራ ነው፡፡ በመሆኑም ለአሜሪካ መንግሥትም ጠንካራው አጋር ይኼው የግሉ ዘርፍ ስለሆነ፣ ሁሉም የፕሮግራም ይዘቶች የግሉን ዘርፍ ተሳትፎና ተሞክሮ ያካትታሉ፡፡ ይህንን በሚመለከት በኤምባሲያችን የግሉ ዘርፍ ልማትን ለማምጣት የሚሠራ ክፍል አለ፡፡
ሪፖርተር፡- ስለፈንድ እንነጋገር፡፡ ከአሜሪካ ኮንግረስ አባላት የልውውጥ ፕሮግራሙ አስፈላጊነት እንዳከተመ የሚያምኑ አሉ፡፡ ከፈንድ ጋር የተያያዙ ሌሎች ጉዳዮች አሉ ማለት ነው?
ዴቪድ ኬኔዲ፡- በአሜሪካ ሁልጊዜም የፈንድ ችግር ያጋጥመናል፡፡ ሁልጊዜም ስለበጀታችን ለኮንግረስ አቅርበን ማብራራትና እውነታውን ማስረዳት አለብን፡፡ ይህ በሥራ አስፈጻሚውና በኮንግረስ መካከል የሚደረግ በጣም ጠቃሚው ምክክር ነው፡፡ ምክንያቱም እነሱ ናቸው ገንዘቡን የሚሰጡን፡፡ ስለዚህ ስለፕሮግራሞቹ ጠቀሜታና አስፈላጊነት በቋሚነት ማብራራት አለብን፡፡ አንድ ምሳሌ ልስጥህ፡፡ አሜሪካ እስከ ቀዝቃዛው ጦርነት ማክተሚያ በነበሩት በርካታ ዓመታት ውስጥ የባህል ማዕከላት ውስጥ የታቀፉ በርካታ ፕሮግራሞችን በመላው ዓለም ስትተገብር ቆይታለች፡፡ ከሶቪዬት ኅብረት ውድቀት በኋላ ግን ኮንግረሱ ከዚህ በኋላ ምንም ጥቅም የላቸውም ብሎ በማመኑ፣ በአዲስ አበባ የነበረውን ጨምሮ ብዛት ያላቸው ፕሮግራሞች እንዲዘጉ አድርጓል፡፡ ፒያሳ የአሜሪካ ባህል ማዕከል ነበር፡፡ ሆኖም አሁን ያ ተቀይሯል፡፡ ስለአስፈላጊነቱ አብራርተን ኮንግረሱን እንዲህ ያሉ የባህል ማዕከላት ያላቸውን ጠቀሜታ እንዲያምንበት ለማድረግ ተቃርበናል፡፡ በወጣቶች መካከል ትስስር ለመፍጠር መሠረት የሚጥሉ ፕሮግራሞች ናቸው፡፡ አንዱ የሌላውን ባህል ለማየትና ለማወቅ የሚረዱ ናቸው፡፡ በአሁኑ ወቅት ከብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ኤጀንሲ ጋር በመተባበር አዲስ የባህል ማዕከል ለመመሥረት በሒደት ላይ ነን፡፡ ማዕከሉ በተለይ በወጣቶች ላይ በማተኮር ለሕዝብ ክፍት የሚደረግ ሲሆን፣ መረጃዎችንና ጠቃሚ ፕሮግራሞችን ያስተዋውቃል፡፡ ይህም ነገሮች እንዴት እንደሚመጡና እንደሚሄዱ የሚያመላክት ጥሩ ምሳሌ ነው፡፡
ሌላው ምሳሌ ኮንግረስ በፉልብራይት ፕሮግራሞች አስፈላጊነት ላይ ያነሳው ጥያቄ ነው፡፡ በዚህ በዲጂታል ቴክኖሎጂና በኢንተርኔት ዘመን ሰዎች በስካይፕ የፈለጉትን ማድረግ እየቻሉ ለአሥር ወራት በሌላ አገር ቆይተው እንዲመጡ ምሁራንን መላክ ምን ጥቅም አለው የሚል ጥያቄ እየተነሳ ነው፡፡ እንደማስበው የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትና ኋይት ሃውስ በአግባቡ ተሟግተው ፕሮግራሙ እንዲቀጥል ለማድረግ ችለዋል፡፡ እርግጥ የተወሰነ ገንዘብ የዲጂታል ሥርጭቶችን ለመደገፍ ሲባል ከፕሮግራሙ ተቀናሽ ተደርጓል፡፡ ይሁንና አብዛኛው ለዚህ ፕሮግራም ሊቆይ ችሏል፡፡ ኮንግረሱ ጥያቄዎችን መጠየቁ ትክክል ሲሆን፣ እኛም የልውውጥ ፕሮግራሞቹን እሴቶች ማሳየት ግዴታችን ነበር፡፡ ስለዚህ አሁንም የፉልብራይት ፕሮግራምን ጨምሮ በርካታ የልውውጥ ፕሮግራሞች አሉን፡፡ ሆኖም ከዚህ የበለጠ ትልቅ ፕሮግራም መኖር እንዳለበት እናስባለን፡፡ ምክንያቱም ኢትዮጵያ በፍጥነት እየተቀየረች ያለችና የመቶ ሚሊዮን ሕዝቦች አገር በመሆኗ ትልቅ ፕሮግራም በኢትዮጵያ መክፈት የሚያስፈልግበትን ምክንያት ሳናቋርጥ የማስረዳት ሚናችንን መወጣት ይኖርብናል፡፡ ማንዴላ ዋሽንግተን ፕሮግራም ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ለዚህ ነው፡፡ ፕሮግራሙ እንደ ኢትዮጵያ ላለች ትልቅ አገር አስፈላጊነቱን በማስመልከት ለኮንግረስ ለማስረዳት ጠንክረን እየሠራን ነው፡፡ እኛ እንዲህ ባለው ነገር ላይ ስናተኩር ኮንግረሱ ግን ገንዘቡን ሌላ ቦታ ላይ ለማዋል ሁልጊዜም እንዳሰበ ነው፡፡ ለኮንግረስ አባላት ምናልባት ይኼንን ማድረጋቸው ትክክለኛ ተግባር ሊሆን ይችላል፡፡ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የኮንግረስ አባላት እዚህ መጥተው ተዘዋውረው ጎብኝተው ነበር፡፡ ጥሩ ጉብኝት ማድረጋቸውን፣ የእኛንም ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች በሚገባ ተረድተው መመለሳቸውን አውቀናል፡፡
ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ አዲስ የአሜሪካ የባህል ማዕከል ይቋቋማል ብለዋል፡፡ በክልሎችም የማቋቋም ሐሳብ አላችሁ?
ዴቪድ ኬኔዲ፡- በኢትዮጵያ እንዲስፋፋ ጠንክረን እየሠራንበት የሚገኝ ተግባር ነው፡፡ ከክልሎች ጋር በትንሹም ቢሆን በአጋርነት እተንቀሳቀስን ነው፡፡ ‹‹አሜሪካን ኮርነር›› እየተባሉ የሚጠሩ ትንንሽ ማዕከላትን በጂማ፣ በባህር ዳር፣ በድሬዳዋና በሐረር ከፍተናል፡፡ ስለአሜሪካ መረጃዎችን መስጠት ከሚችሉ የየአካባቢው ተቋማት፣ አነስተኛ ቤተ መጻሕፍትና ለተማሪዎችም ለሌሎች የኅብረተሰቡ ክፍሎችም የኢንተርኔት አገልግሎት ከሚሰጡ ተቋማት ጋር በአጋርነት የሚሠሩ ማዕከላት ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ የሚከፈተው ዋናውና ትልቁ ማዕከል ይሆናል፡፡ በብሔራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጻሕፍት ውስጥ አገልግሎት መስጠት የጀመረ በአሜሪካ ላይ ያተኮረ አንድ ክፍል አለ፡፡ ይህ ክፍል እንደ አዲስ ሲደራጅ ትልቅና ቀልጣፋ ስለሚሆን የተለያዩ ፕሮግራሞችን ለማከናወን ይረዳል፡፡ ወጣቶችንና ወጣት ባለሙያዎችን በገለጻ፣ በሴሚናር፣ በዓውደ ርዕይ ወይም በፊልሞች ለማሳተፍና መሠረቱን ለመጣል የሚያስችሉ ውይይቶች ሲደረጉ ለነበረው ጥረት ጥሩ ማሣሪያ ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ይህንን ለማድረግ የሚያስችል ማዕከል ስላለን በጥቂት ወራት ውስጥ ሙሉ ለሙሉ እንደገና ተደራጅቶ አገልግሎት ይጀምራል፡፡
ሪፖርተር፡- ሁለቱ አገሮች ካላቸው የቆየ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አኳያ 1‚500 ኢትዮጵያውያን ብቻ በልውውጥ ፕሮግራሞቹ መሳተፋቸውን እንዴት ይገመግሙታል?
ዴቪድ ኬኔዲ፡- የልውውጥ ፕሮግራሞች የ75 ዓመታት ዕድሜ የላቸውም፡፡ በዚያ ላይ በደርግ መንግሥት ወቅት ለአሥር ዓመት ያህል ተቋርጠው እንደነበርም አይዘነጋም፡፡ ከዚህ ባሻገር እስካሁን የተሰጠው የልውውጥ ዕድል በቂ አይደለም፡፡ እየጨመረ እንዲሄድ ለማድረግ የሚያስችሉ ብዙ ዕድሎችም አሉ፡፡ በመስከረም ወር ያደረግነውም ስለልውውጥ ፕሮግራሞች ጠቀሜታ ማብራራት ነው፡፡ በብሔራዊ ሙዚየም ውስጥ የልውውጥ ፕሮግራሞችን በሚመለከት በዓውደ ርዕይ ነበር የጀመርነው፡፡ ኢትዮ-አሜሪካዊው የፊልም ባለሙያ ያሬድ ዘለቀ የሠራውን ‹‹ዳንግሌ›› ወይም ‹‹ላምብ›› የተሰኘ ፊልም ስፖንሰር በማድረግ እንዲታይ አድርገናል፡፡ ፊልሙ በመጪው ዓመት በኦስካር ለውድድር ይቀርባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይህ በጣም ደስ የሚል ነገር ነው፡፡ ይህ እንግዲህ እንዲገነባ የምንፈልገው የልውውጥ ፕሮግራም ማሳያ ነው፡፡ በወሩ መጨረሻም ሌላ ትልቅ ትዕይንት አዘጋጅተናል፡፡ የቀድሞ ተሳታፊዎችን በመጥራት ስለ ፕሮግራሞቹ መጠናከርና ሊያደርጉ ስለሚችሏቸው አስተዋጽኦዎች እንዲገልጹ የሚያስችል መድረክ ይሆናል፡፡ 1‚500 ትንሽ ባይሆንም አገሪቱ ካላት ስፋት አኳያ በቂ ግን አይደለም፡፡ ስለዚህ ከዚህ የበለጠ እናሳድገዋለን፡፡ በዚህ ወር መጨረሻ ሌላ ስለባህል የሚያወሱ ፕሮግራሞችን አሰናድተናል፡፡ የአሜሪካ ዳንስ ቡድን ‹‹ክሮሲንግ ባውንደሪስ ፌስቲቫል›› ከሚለው ፕሮግራም ጋር በተያያዘ እዚህ ይመጣል፡፡ እነዚህ ሁሉ እንግዲህ በአሜሪካና በኢትዮጵያ መካከል ስላለው ጠንካራና ንቁ የባህል ልውውጥ የሚያስረዱ ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ይበልጥ የማደግና የመስፋፋት አቅም ያላቸው በመሆኑ እኛም ይህ ዕውን እንደሚሆን ተስፋ አለን፡፡
ሪፖርተር፡- ወደ ኢትዮጵያ መጥተው የነበሩት ጆን ሮቢንሰን የልውውጥ ፕሮግራሙ አካል ነበሩ?
ዴቪድ ኬኔዲ፡- ጆን ሮቢንሰን ትልቅ ምሳሌ ቢሆኑም የየትኛዎቹም ኦፊሴላዊ የመንግሥት ፕሮግራሞች አካል አይደሉም፡፡ ሆኖም እሳቸው ጥሩ ምሳሌ በመሆን ለብዙዎች አሜሪካውያን መነሳሳትን ያተረፉ፣ የሕዝብ ለሕዝብ ልውውጥ ተግባራት ምን መምሰል እንዳለባቸው አብነት የሚሆኑ ናቸው፡፡ የአሜሪካ መንግሥት የሕዝብ ለሕዝብ ልውውጦችን ያበረታታል፡፡ ጆን ሮቢንሰን ግን በራሳቸው ሐሳብ ተነሳስተው ወደ ኢትዮጵያ የመጡት እ.ኤ.አ. በ1930ዎቹ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ የጣሊያን ፋሺስቶችን በምትዋጋበት ጊዜ የአየር ኃይሏን እንድትገነባ ስለማገዛቸው እንደሚታወቅ እርግጠኛ ነኝ፡፡ ይህ በሕዝብ ለሕዝብ መካከል ስለሚኖረው መስተጋብር የሚያስረዳ ትልቅ ምሳሌ ነው፡፡ ጆን ሮቢንሰን በፈቃደኛነት ኢትዮጵያን ለመደገፍ የመጡና በሁለቱ አገሮች መካከል መተማመን እንዲገነባ፣ ይኼው መተማመንም እስከዛሬ እንዲቀጥል የረዱ ናቸው፡፡ የፎርድ ቤተሰብም እዚህ በመምጣት ትምህርት ቤት የከፈተ የአሜሪካውያን ምሳሌ ነው፡፡ እነዚህ ሁሉ ከመንግሥት ውጪ ባለው መስክ የተከናወኑ ተግባራት ቢሆኑም፣ በመንግሥት ውስጥ ያለነው ሰዎች ተነሳሽነቱን የምንወስደው ግን ከእነዚህ ነው፡፡ ሌሎች በርካታ ሮቢንሰኖችና ፎርዶች ግንኙነታችንን እንደሚያበረቱት ተስፋ አለኝ፡፡