የትምህርት ሚኒስቴር፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበርና የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሬድ ሙዚቃ ትምህርት ቤት ሰላም ኢትዮጵያ ከተሰኘ ግብረ ሰናይ ድርጅት ጋር በጋራ ሲያከናውኑት የነበረው የሙዚቃ ትምህርት እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ እንዲሰጥ የሚጠቁመው የጥናት ሰነድ ይፋ ተደረገ፡፡
ላለፉት አራት ዓመታት ያህል ሲካሄዱ የቆየውን ጥናት ይፋ መደረግ አስመልክቶ መስከረም 11 ቀን 2008 ዓ.ም. በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የስብሰባ አዳራሽ መግለጫ ተሰጥቷል፡፡ መግለጫው የተሰጠው በኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር፣ በትምህርት ሚኒስቴር፣ በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር እንዲሁም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሬድ የሙዚቃ ትምህርት ቤት በተገኙ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ነው፡፡
‹‹የጥናቱ ሰነድ የተዘጋጀው የሙዚቃ ትምህርት እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ብሎም እንደ ዲሲፕሊን (የልኅቀት የእውቀት ዘርፍ) ከቅድመ መደበኛ እስከ ከፍተኛ ትምህርት ድረስ ባለው የአገሪቱ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የተሰጠውን ቦታና ያለበትን ነባራዊ እውነታ ለመገምገምና ችግሮችን ለይቶ ለማውጣት ነው፡፡ የመፍትሔ አቅጣጫ በማመልከት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በተደረገ ምክክር ዳብሮ የተሰናዳ ሰነድ ነው፤›› በማለት የኢትዮጵያ ሙዚቀኞች ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰርፀ ፍሬስብሐት አስረድተዋል፡፡
በጥናት ሰነዱ ውስጥ የሙዚቃ ትምህርት በነባራዊው ሥርዓተ ትምህርት ውስጥ የተሰጠውን ቦታና ተግባራዊነቱን ለማመልከት መሞከሩ የተገለጸ ሲሆን፣ የሁለተኛ ደረጃና የመሰናዶ ትምህርት እርከኑ ከናካቴው ከሥነ ጥበባዊ ትምህርቶች ውጪ መሆኑ በትምህርት ሁለንተናዊነት ላይ ችግር የፈጠረ መሆኑን ጥናቱ ይጠቁማል፡፡
‹‹በከፍተኛ የሙዚቃ ትምህርት ላይ ከኋላ ጀምሮ የተመጣበትና ትኩረት ያልተሰጠው አካሄድ እውነተኛ ችግሩ ጎልቶ የሚታየው ከፍተኛ የሙዚቃ ትምህርት ደረጃ ላይ ሲደረስ ነው፤›› በማለት የችግሩን ጥልቀት የገለጹት አቶ ሰርፀ፣ ‹‹መሠረት ሳይዝ የመጣን ተማሪ በተለምዶ ያልተቋረጠ ልምምድንና የዕለት ተዕለት የክህሎት ማሻሻል ሥራን የሚጠይቅ እንደ ሙዚቃ ባለ ሙያ፣ ወደ ልኅቀት ደረጃ ለማድረስ መሞከሩ ውጤታማ ሊያደርግ አላስቻለም፤›› በማለት ጥናቱ በዝርዝር እንደሚተነትን አክለው ገልጸዋል፡፡
ለተለያዩ አካላት የተለያዩ ጠቀሜታዎችን እንደሚሰጥ የተገለጸለት ይህ የጥናት ሰነድ፣ የሚመለከታቸው አካላት እንዲመክሩበት የተላከ መሆኑም ተገልጿል፡፡
ሰነዱ ከጠቅላይ ሚኒስቴር ጽሕፈት ቤት ጀምሮ ለመንግሥት የፖሊሲ አውጪዎች እንደ ግብዓትነት የሚያገለግል መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፣ ለከፍተኛ የትምህርት ተቋማትና ለመምህራን ማሠልጠኛዎች፣ በየደረጃው ላሉ የትምህርት ጽሕፈት ቤቶች፣ ለባህልና ለሥነ ጥበብ ተቋማት፣ ለሥነ ትምህርት ሊቃውንት፣ በጉዳዩ ላይ ጥናትና ምርምር እያደረጉ ላሉ ድርጅቶች ከፍተኛ ጠቀሜታ እንደሚሰጥ አቶ ሰርፀ አስረድተዋል፡፡