የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ዋና ጸሐፊ ሚስተር ባን ኪሙን በዘላቂ ትራንስፖርት ጉዳዮች የሚያማክራቸውን ከፍተኛ አማካሪ ቡድን በጋራ እንዲመሩ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ተወልደ ገብረ ማርያምን መረጡ፡፡
የባን ኪሙን አማካሪ ቡድን ለመጪዎቹ ሦስት ዓመታት የሚያገለግል ሲሆን፣ በዘላቂ ትራንስፖርት ጉዳዮች ላይ የፖሊሲ ምክረ ሐሳቦች ያቀርባል፣ ዓለም አቀፍ መልዕክቶች ያስተላልፋል፡፡ አማካሪ ቡድኑ ከመንግሥታት፣ ከትራንስፖርት ዘርፍ፣ ከንግድ ተቋማት፣ ከገንዘብ ተቋማት፣ ከሲቪል ማኅበረሰብና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር አብሮ ይሠራል፡፡ ቡድኑ በመንግሥታት መካከል የተቀናጀ የትራንስፖርት ዘርፍ አሠራር እንዲኖር ይጥራል፡፡ እ.ኤ.አ. 2015 በኋላ ለሚቀረፀው የልማት አጀንዳ ምክረ ሐሳቦች እንደሚያቀርብ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አቶ ተወልደ ከሚስተር ባን ኪሙን ጋር በመሆን ቡድኑን በጋራ ይመራሉ፡፡ በቡድኑ ውስጥ ከሲቪል ማኅበረሰብ፣ ከግሉ ዘርፍና ከመንግሥታት የተውጣጡ ታዋቂ ግለሰቦች እንደሚገኙበት ለማወቅ ተችሏል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ የአቶ ተወልደ አማካሪ ቡድኑን እንዲመሩ መመረጥ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለአፍሪካ የአየር ትራንስፖርት ዕድገት ላደረገው አስተዋጽኦ ዕውቅና መስጠት መሆኑን ገልጿል፡፡
አቶ ተወልደ ባን ኪሙን ለኢትዮጵያ አየር መንገድ የሰጡት ዕውቅና እንዳስደሰታቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይህን ታላቅ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ከተመድ ዋና ጸሐፊ ሚስተር ባን ኪሙን በማግኘታችን ታላቅ ደስታ ተሰምቶናል፤›› ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ አረንጓዴ አካባቢ ለመፍጠር የሚተጋ ኩባንያ መሆኑን ጠቅሰው፣ የካርቦን ልቀትን ለመቆጣጠር ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ አዳዲስ አውሮፕላኖችን እንደሚገዛ አስረድተዋል፡፡ የባን ኪሙን አማካሪ ቡድንን እንዲያገለግሉ መመረጣቸው፣ ቀጣይነት ያለው የትራንስፖርት ዘርፍ ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት ለማገዝ የበኩላቸውን ሚና ለመጫወት ዕድል እንደሚፈጥርላቸው ገልጸዋል፡፡
አቶ ተወልደ በወጣትነት ዕድሜያቸው እ.ኤ.አ. 1985 በኢትዮጵያ አየር መንገድ በሽያጭ ሠራተኝነት የተቀጠሩ ሲሆን፣ ዕውቀትና ልምዳቸውን በማሳደግ በተለያዩ ኃላፊነት ቦታዎች አገልግለዋል፡፡ የህንድና የደቡብ እስያ፣ የሳዑዲ ዓረቢያ፣ የሰሜን አሜሪካ ቀጣና ኃላፊ፣ እንዲሁም ቺፍ ኦፕሬቲንግ ኦፊሰር ሆነው አገልግለዋል፡፡ እ.ኤ.አ. ከጥር 2011 ጀምሮ የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሆነው በማገልገል ላይ ይገኛሉ፡፡
አቶ ተወልደ የዓለም አቀፍ አየር ትራንስፖርት ማኅበር ገዢዎች ቦርድ አባል ሲሆኑ፣ የአፍሪካ አየር መንገዶች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ናቸው፡፡ በተጨማሪም የኢትዮ ቴሌኮም፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽንና የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ቦርድ አባል ሲሆኑ፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ድርጅት የቦርድ ሊቀመንበር ናቸው፡፡