Monday, December 4, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናኢሕአዴግ በአዲስ አበባ አስተዳደር ሹም ሽር እያካሄደ ነው

ኢሕአዴግ በአዲስ አበባ አስተዳደር ሹም ሽር እያካሄደ ነው

ቀን:

የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት አብዛኛዎቹን የክፍላተ ከተሞችና የወረዳ አመራሮች በማንሳት፣ በአዳዲስ አመራሮች እየተካ መሆኑ ታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሁለተኛውን የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ለማሳካት ወረዳዎችና ክፍላተ ከተሞች መመራት ያለባቸው ዲፕሎማና ከዚያ በላይ የትምህርት ደረጃ ባላቸው መሆን አለበት የሚል አዲስ አቋም መያዙ፣ ለሹም ሽሩ ምክንያት መሆኑን ምንጮች ገልጸዋል፡፡

በዚህ መሠረት በአሥሩም ክፍላተ ከተሞችና በሥራቸው በሚገኙ 116 ወረዳዎች የሚገኙ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አመራሮች ተነስተዋል፡፡ በተጨማሪም ሹም ሽሩ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሰፈነውን የመልካም አስተዳደርና የሙሰኝነት ችግር ለመቅረፍ መንግሥት ከያዘው ዕቅድ ጋር የሚያያዝ እንደሆነም ገልጸዋል፡፡

ይህን ችግር ለመቅረፍ በቅድሚያ ይህ ችግር ያለባቸው አመራሮች ተገምግመው እንዲነሱ መደረጉም ተገልጿል፡፡ ለማሳያ ያህል በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ከሚገኙ 12 ወረዳዎች ከዲፕሎማ በታች ያላቸው አመራሮች 70 የሚጠጉ ሲሆን፣ እነዚህ ሁሉ እንደተነሱ ተገልጿል፡፡ በሙስናና በተለያዩ ግድፈቶች ደግሞ 30 አመራሮች እንዲነሱ መደረጉም ተመልክቷል፡፡

በሌሎች ክፍላተ ከተሞችና በሥራቸው በሚገኙ ቀበሌዎችም በተመሳሳይ ከ100 ያላነሱ አመራሮች በእነዚህ ሁለት ምክንያቶች መነሳታቸው ተገልጿል፡፡ ይሁንና ከዲፕሎማ በታች የትምህርት ደረጃ ኖሯቸው አመራር ሲሰጡ የቆዩ አባላት ቅሬታ አቅርበዋል፡፡ ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉት እነዚህ አመራሮች ትምህርት ለመማር ጥያቄ  በሚያቀርቡበት ወቅት መንግሥት ቅድሚያ ሥራችሁን ሥሩ የሚል ምላሽ የሰጣቸው በመሆኑ ትምህርት መማር እንዳልቻሉ አስታውሰው፣ ውሳኔው ፍትሐዊ እንዳልሆነ ጠቁመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ይህንን አለመግባባት ለማስቀረት የውይይት መድረኮች ፈጥሮ እንደነበርም ታውቋል፡፡ በዚህም ያላቸው የትምህርት ደረጃ ዝቅተኛ በመሆኑ የተነሱ አመራሮች የሦስት ወራት ደመወዝ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ሥራዎችን እንዲሠሩ ወይም ዕድሜያቸው ለጡረታ የደረሰው ደግሞ በጡረታ እንዲገለሉ ሐሳብ ቀርቦ፣ ከሞላ ጎደል መግባባት ላይ መደረሱ ተመልክቷል፡፡

ዋነኛው የአዲስ አበባ ከተማ ችግር የመልካም አስተዳደር እጦትና ኪራይ ሰብሳቢነት [ሙስና] እንደሆነ ነዋሪዎች ባገኙት አጋጣሚ ሲገልጹ ቆይተዋል፡፡ ይህ ችግር የ2007 ዓ.ም. የሥራ አፈጻጸም በሚገመገምበት ወቅት በሰፊው ተነስቷል፡፡ በተለይ በመሬት፣ በንግድና በአገልግሎት መስጫ ዘርፎች ላይ ኅብረተሰቡ ከፍተኛ እሮሮ በማቅረብ ላይ ይገኛል፡፡

በእነዚህ ዘርፎች ለተገልጋዮች ተገቢውን አገልግሎት አለመስጠት፣ ተገልጋዮችን ለማስተናገድ ዝግጁ አለመሆን፣ ለሚቀርቡ ቅሬታዎች አፋጣኝ ውሳኔ አለመስጠት፣ ‹‹ጉዳዩ አልታየም›› በማለት ተገልጋዮችን ማጉላላትና ጉቦ መጠየቅ ከሚቀርቡት ቅሬታዎች መካከል ተጠቃሽ ናቸው፡፡

በንግድ በኩል የንግድ ፈቃድ ዕድሳት፣ የንግድ ስያሜ አሰጣጥ፣ የንግድ አድራሻ ማረጋገጫ አሰጣጥ፣ ሕገወጥ ንግድ በሰፊው የሚታዩ ችግሮች ከመሆናቸውም በተጨማሪ፣ በአጠቃላይ የንግድ ሥርዓቱ የተተረማመሰ እንደሆነ ቅሬታ ይቀርባል፡፡

በእነዚህ ሁሉ ችግሮች ሙስና ዋነኛ መገለጫ መሆኑ ከኅብረተሰቡ በሰፊው የሚነሳ ጉዳይ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ይህንን የኅብረተሰብ ሮሮ በመቀበል፣ የራሱን ግምገማ አካሂዶ ችግሩ እንዳለ አምኗል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ከሕዝብ ጋር ተወያይቶ ወደ ተግባር እንደሚገባ ገልጾ ነበር፡፡

ይህንን ችግር ለመፍታት በተካሄዱ ተከታታይ ግምገማዎች ግድፈት እንዳለባቸው የተለዩ አመራሮችን ከክፍላተ ከተሞችም ሆነ ከወረዳዎች ማንሳት ዋነኛ ዕርምጃ ሆኗል፡፡

በዚህ መሠረት ቢያንስ ችግሩ ጎልቶ በሚታይባቸው ክፍላተ ከተሞች ከ30 በላይ አመራሮች፣ በወረዳ ደረጃም በተመሳሳይ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው አመራሮች እንደተነሱ ምንጮች ተናግረዋል፡፡

ይሁንና በአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ባለቤትነት የሚካሄደው ይህ ሹም ሽር ባለፈው ሳምንት መገባደዱን መረጃዎች አመልክተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተወልደ ገብረ ፃድቃን ሥራው እየተካሄደ መሆኑን ለሪፖርተር አረጋግጠው፣ ሥራው ባለመጠናቀቁ መረጃ ለመስጠት እንደማይችሉ ገልጸዋል፡፡

ከዚህ በመቀጠል የአዲስ አበባ ኢሕአዴግ ጽሕፈት ቤት በማዕከል ደረጃ የሚገኙ ቢሮዎችንና ኤጀንሲዎችን የሚመሩ አመራሮች ላይ ሹም ሽሩን እንደሚቀጥልም ተገልጿል፡፡ ሹም ሽሩ በርካታ አመራሮችን ከካቢኔ የሚያስወጣና በምትካቸው አዳዲስ የካቢኔ አባላትን እንደሚሾም ምንጮች ተናግረዋል፡፡

የካቢኔ አባላቱ ሹም ሽር በቅርቡ ለአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት ቀርቦ ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕይወታቸውን በኤድስ ምክንያት ላጡ ሰዎች 35ኛ ዓመት መታሰቢያ

ያለፍንበትን እያስታወስን በቁርጠኝነት ወደፊት እንጓዝ - በኧርቪን ጄ ማሲንጋ (አምባሳደር) በየዓመቱ...

እዚያ ድሮን… እዚህ ድሮን…

በዳንኤል ካሳሁን (ዶ/ር) ተዓምራዊው የማዕበል ቅልበሳ “በሕግ ማስከበር” ዘመቻው “በቃ የተበተነ...

ለፈርጀ ብዙ የማንነት ንቃተ ህሊናችን የሚጠቅሙ ጥቂት ፍሬ ነገሮች

በበቀለ ሹሜ ከጨቅላነት ጅምሮ ያለ የእያንዳንዳችን የሰብዕና አገነባብ ከቤተሰብ እስከ...