ከጥቂት ወራት በፊት ሁለት ሴቶች ወደ ግሬስ የእናቶችና የሕፃናት ጤና ማዕከል ያመራሉ፡፡ ሁለቱም ሴቶች ነፍሰ ጡር እንደሆኑ የሕክምና ባለሙያዎች ይገልጹላቸዋል፡፡ እርግዝናቸውን ከሌሎች እንስቶች ለየት የሚያደርገው ሁለቱም ሴቶች በማህጸናቸው ሦስት ልጆች መያዛቸው ነበር፡፡
ሁለቱ ሴቶች ባልተለመደ መልኩ በተመሳሳይ ሳምንት ሦስት ሦስት ልጆች ወልደዋል፡፡ ሦስታ (ትሪፕሌት) መውለድ በራሱ አስገራሚ ሲሆን፣ በጥቂት ቀናት ልዩነት ሁለት ሴቶች በአንድ ሆስፒታል ሦስታት መገላገላቸው ደግሞ አጋጣሚውን የተለየ ያደርገዋል፡፡
የማህጸንና ጽንስ ስፔሻሊስትና በግሬስ የእናቶችና የሕፃናት ጤና ማዕከል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር አብዱ ኢብራሂም እንደተናገሩት፣ እናቶቹ ሦስታ እንዳረገዙ በነገሯቸው ቅጽበት አንደኛዋ እናት ስትደናገጥ ሌላኛዋ ደስተኛ ነበረች፡፡ በእርግዝናቸው ወራትም ይኸው ስሜት ይነበብባቸው ነበር፡፡ አንደኛዋ እናት በሥጋት ሌላኛዋ በሙሉ ተስፋ ይጠብቁት የነበረው ቀን ሲደርስ ለቤተሰቦቻቸውም ለሆስፒታሉም አስደሳች ዜና ይዞ መጥቷል፡፡
በሆስፒታሉ የዓመታት ታሪክ ውስጥ በአንድ ሳምንት ሁለት እናቶች ሦስታ ወልደው አያውቁም፡፡ ዶክተሩ እንደሚሉት፣ ሙሉ በሙሉ እርግጠኛ ሆኖ መናገር ባይቻልም፣ መሰል ክስተቶች ዘወትር አያጋጥሙም፡፡ ‹‹ሁለት ሦስታ በሙያው ውስጥ ሁሌ ስለማያጋጥም ሐኪሞችን አስደስቷል፤›› ይላሉ፡፡ ሁለቱም እናቶችና ልጆቻቸው መልካም የሆነ ጤና ላይ መገኘታቸው ደግሞ የበለጠ አስደሳች እንደሆነ ‹‹እናቶቹ በሰላም ተገላግለው ሲሄዱ ማየት ሁላችንንም አስደስቷል፤›› በማለት ያስረዳሉ፡፡
ሦስታ የሚወልዱ እናቶች ጥቂት ከመሆናቸው የተነሳ ሦስት መውለድ እንደ ትንግርት የሚታይበት ጊዜ አለ፡፡ በሦስታ ዙሪያ የተጻፉ ጥናቶች እንደሚያሳዩት፣ በዓለም ላይ ከ8,000 ሴቶች አንዷ ሦስታ የመውለድ ዕድል አላት፡፡ ዶ/ር አብዱ፣ በ14 ዓመታት የሕክምና ቆይታቸው ስድስት ሦስታ አዋልደዋል፡፡ የሦስታ ሕፃናት እርግዝና አንዳንድ የጤና መወሳሰብ የሚፈጠርበት መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ከሦስታ እርግዝና ጋር ተያይዘው የሚመጡ የሚባሉ የጤና መወሳሰቦችን ከግምት በማስገባት ባደጉ አገሮች በተመሳሳይ እርግዝና ያሉ ሴቶች ሐሳብ እንዲለዋወጡባቸው የተዘጋጁ ድረ ገጾች አሉ፡፡ ሦስታ መውለድን ልጅ ማሳደግ ከሚጠይቀው ኢኮኖሚያዊ አቅም አንፃር የሚመለከቱ ሴቶች እንዳሉ ሁሉ፣ ‹‹ከሰጠኸኝማ እንደ ማርታ ሦስት›› የሚለውን ብሂል እየደጋገሙ ሦስት ልጅ በአንዴ መገላገልን የሚመኙም አሉ፡፡
ዶክተሩ እንደሚናገሩት፣ ሦስታ መደበኛ ከሚባለው ወጣ ባለ መንገድ የሚፈጠር እርግዝና ነው፡፡ የመሀንነት ችግር ኖሮባቸው በሕክምና የተረዱ እናቶች ወይም በሕክምና ዕርዳታ የሚያረግዙ እናቶች ላይ ቢስተዋልም በተፈጥሮ የሚከሰትበትም ጊዜ አለ፡፡