ከእርግዝና ጀምሮ ሕጻኑ ተወልዶ ሁለት ዓመት እስኪሞላው ድረስ ባሉት የመጀመሪያዎቹ 1000 ቀናት ውስጥ በተመጣጠነ ምግብ እጦት የተነሳ በጨቅላና በታዳጊ ሕፃናት ላይ የሚከሰተውን መቀንጨር ለመከላከል የሚያስችለው የማኅበራዊና የባህሪ ለውጥ ተግባቦት ስትራቴጂ ይፋ ሆነ፡፡ ስትራቴጂው ለመቀንጨር ችግር ፍቱን የሚሆኑ የምግብ ዓይነቶችንና ሥርዓተ ምግብን አካትቷል፡፡
ስትራቴጂው፣ በምግብ አዘገጃጀትና አቅርቦት ሥራ ላይ የቤተሰብ በተለይም የባል የሥራ ድርሻና ኃላፊነት እንዲሁም የማኀበረሰብ ውይይት፣ በሥርዓተ ምግብ ዙሪያ የባህሪ ለውጥ ለማምጣት ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው አመላክቷል፡፡
ነፍሰጡሮች የተመጣጠነ ምግብ ማግኘት አለባቸው፡፡ በተለይ በእርግዝና መጀመሪያና መጨረሻ ወራቶች ተጨማሪ ምግብ (መክሰስ) ያስፈልጋቸዋል፡፡ በስተጨመረሻው የእርግዝና ወራቶች የሚወሰደው መክሰስ ለነፍሰጡሯና ለፅንሱ ጠንካራ መሆን ያግዛል፡፡ በወሊድም ጊዜ በደህና ሁኔታ እንድትገላገል የሚያደርግ ነው፡፡
በእርግዝና ወቅት ከመኝታ በፊት አይረን ፎሊክ አሲድ ወይም የብረት ማዕድን ኪኒን ሊወሰድ ይገባል፡፡ ክኒኑን ከመውሰድ በፊትና ከተወሰደም በኋላ ለአንድ ሰዓት ያህል ሻይና ቡና ከመጠጣት መቆጠብ የሚያስፈልግ ሲሆን፣ ምግብ በሚገባ መብላትና የሕክምና ክትትል ማድረግም ግድ ነው፡፡
ሕፃኑ እንደተወለደ ወዲያው ከእናቲቱ ጡት የሚወጣውን የመጀመሪያ አንገር እንዲጠባ፣ ከዚያም ስድስት ወራት እስኪሞላው ድረስ የእናት ጡት ወተት ብቻ እንዲሰጠው ማድረግ ግድ ይላል፡፡ ከስድስት እስከ ሰባት ወራት ድረስ ከተለያዩ እህሎች ተዘጋጅቶ የቀረበና ቀጠን ያለ ገንፎ ማግኘት ይገባዋል፡፡
ከሰባት እስከ 11 ወራት በቀን ሦስት ጊዜ የተመጣጠነ ምግብ ማለትም አትክልት፣ በቅቤና በዘይት የተሠራ ቀጭን ገንፎ፣ እንዲሁም በቀን አንድ ጊዜ የእንስሳት ተዋፅዖ ሊሰጠው ያስፈልጋል፡፡ ከ12 እስከ 24 ወራት ድረስ ደግሞ በቀን ሦስት ጊዜ ሊመገብ ይገባል፡፡ በእነዚህ ወራት የሚመገባቸውም ዓይነቶች በዘይት ወይም በቅቤ የተዘጋጀ ገንፎ፣ አትክልትና ፍራፍሬ ሲሆኑ የእንስሳት ተዋፅኦ ማለትም እንደ እንቁላል የመሳሰሉ በቀን አንድ ጊዜ ማግኘት ይገባዋል፡፡
ከስድስት ወራት ጀምሮ እስከ 24 ወራት ድረስ ሕፃኑ ከሚመገባቸው ተጨማሪ ምግቦች ባሻገር የእናት ጡት ወተት በምንም መልኩ መለየት እንደሌለበት፣ የሕፃኑ ምግብ ከሌላው ተለይቶ በጥንቃቄና በንፁህ መያዙን፣ ሕፃኑ የቀረበለትን ምግብ ጨርሶ መብላቱን ወይም ማጠናቀቁን ማረጋገጥና ከምግቡ ጋር ውኃ እንዲጠጣ ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡
ቤተሰብ የቤት ውስጥ ልዩ ልዩ ሥራዎችን በማከናወን የወላዷን የሥራ ጫና ማቃለል ይገባዋል፡፡ ይህ ዓይነቱም ሁኔታ ወላዷ በቂ እረፍት እንድታገኝ፤ በጥሩ ሁኔታ እንድትመገብና በቂ ጊዜ ኖሯት ሕጻኑን በደንብ እንድትመግበው የበኩሉን አስተዋጽኦ ያበረክታል፡፡
መስከረም 10 ቀን 2008 ዓ.ም. በተመጣጠነ ምግብ ዙሪያ በተዘጋጀው የግማሽ ቀን አውደ ጥናት ላይ ይፋ የሆነውን ስትራቴጂ ያዘጋጀው የኢትዮጵያ መንግሥት ላወጣው የሥርዓተ ምግብ ስትራቴጂና መርሃ ግብር እውን መሆን የፋይናንስና የቴክኒክ ድጋፍ የሚያደርገው ኢንፖወሪንግ ኒው ጄነሬሽን ቱ ኢምፑሩቭ ኒውትራሽን ኤንድ ኢኮኖሚክ ኦፓርቹኒቲ ፕሮጀክት ነው፡፡
ዶክተር ሀብታሙ ፈቃዱ የፕሮጀክቱ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፣ ፕሮጀክቱ በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች በሚገኙ ልዩ ልዩ ወረዳዎች ውስጥ በጤናና በግብርና ዙሪያ ይሠራል፡፡ ከዚህም ሌላ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ የሥርዓተ ምግብ አካዳሚ የልቀት ማዕከል አቋቁሟል፡፡
ወይዘሪት ዘላለም መኩሪያ በፕሮጀክቱ የማኅበራዊና የባህሪ ለውጥ ተግባቦት ስትራቴጂ ከፍተኛ ዳይሬክተር፣ እናቶች ከፅንስ ጀምሮ በቂና የተመጣጠነ ምግብ ካልተመገቡ ጽንሱ በደንብ አይዳብርም፡፡ የሚወለደው ሕጻን ትክክለኛ የሆነ የአዕምሮና የአካል ዕድገት አያገኝም፡፡ ይህም ሁኔታ መቀንጨርን የሚያስከትል ሲሆን ዕድሜው ከፍ እያለ ሲሄድ ከቁመቱ 11 ሴንቲ ሜትር ይቀንስበታል፡፡ አዕምሮው ባለማደጉና ባለመበልፀጉም ትምህርት ለመቀበል ይቸግረዋል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በአማራ፣ በትግራይ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች በሚገኙ ልዩ ልዩ ወረዳዎች ባለፉት አራት ዓመታት በጤና በተለይም በምግብ ሥርዓትና በግብርና ዙሪያ ባካሄደው እንቅስቃሴ፣ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በተቻ የሆኑ 3.1 ሚሊዮን ሕፃናት፣ ግማሽ ሚሊዮን የሚጠጉ እርጉዞችና የሚያጠቡ እናቶች፣ 3.2 ሚሊዮን የሚሆኑ በወሊድ ዕድሜ ላይ የደረሱ ሴቶች፣ 2.7 ሚሊዮን አባወራዎች ተጠቃሚ እንዳደረጉ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡