የእንግሊዙ እግር ኳስ ክለብ አርሰናል ከዳሽን ቢራ ጋር ለሦስት ዓመት የሚቆይ ለዳሽን ቢራ ክለብ ቴክኒካዊ ድጋፍ ለማድረግ የአጋርነት ስምምነት ተፈራረመ፡፡
ታላላቅ አሠልጣኞችም ከክለቡ ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ከታዳጊዎች ጀምሮ አስፈላጊውን ሥልጠና በመስጠት እንደሚሠሩ ተገልጿል፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘም የአርሰናል የቀድሞ ተጨዋቾች ወደ ኢትዮጵያ በማምጣት ልምዳቸው እንዲያካፍሉ መንገድ እንደሚፈጥሩም ተመልክቷል፡፡
መስከረም 12 ቀን 2008 ዓ.ም. በተፈረመው ስምምነት በኢንተርኮንቲኔንታል የተፈራረሙት ድርጅቶች በቀጣይ ሦስት ዓመታት ዳሽን ቢራና አርሰናል በቅርበት በመሥራት በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙትን የቢራ ደንበኞችና የአርሰናል ደጋፊዎች የሚያቀራርብ ሊሆን እንደሚችል በመግለጫው ላይ ተገልጿል፡፡
የአርሰናል የእግር ኳስ ክለብ ዋና የንግድ ተጠሪ ቪናይ ሼንካተሻም በመግለጫው ላይ ‹‹አርሰናል እግር ኳስ ክለብ በመላው አፍሪካና ኢትዮጵያ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ደጋፊ እንዳለው ይታወቃል፤›› ብለዋል፡፡
በዚህም መሠረት ለመጀመርያ ጊዜ ከዳሽን ቢራ ጋር እንደዚህ ዓይነት የአጋርነት ስምምነት በመፈራረማችን አስደስቶናል በማለት በመግለጫው ላይ አስታውቀዋል፡፡ በተጨማሪም የዳሽን ቢራ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዴቪሊን ሄን ወርዝ ‹‹በስምምነቱ ዳሽን ቢራም ሆነ አርሰናል እግር ኳስ ክለብ ተጠቃሚ እንደሆነና ኅብረተሰቡም የጋራ ጥቅም እንዲኖረው የሚያስችል ነው፤›› ብለዋል፡፡
በመጨረሻም ስምምነቱ በቀጣይነት በኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን እግር ኳስ ለማሳደግ እንደሚሠራና ሁሉም የኢትዮጵያ እግር ኳስ ክለቦች ከዚህ የአጋርነት ሥራ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተገልጿል፡፡