Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርከሰላም ማኅበር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ እናቀርባለን

ከሰላም ማኅበር ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪ እናቀርባለን

ቀን:

አዲሱ ዓመት ለእርሶ፣ ለቤተሰብዎ፣ ለሚመሩት ሕዝብና በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሰላም፣ የፍቅርና የነፃነት ዘመን እንዲሆን፣ እርሶም በአዲሱ ዓመት ብቃት ያለዎት መሪ አስተዋይ ልቦና፣ ሰሚ ጆሮ፣ ይቅር ባይና ይቅርታ ጠያቂ እንዲሆኑ ታላቅ ምኞታችን ነው፡፡

በፓርቲዎ ጉባዔ ማብቂያና በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ወቅት ለሕዝባችን ባስተላለፉት መልካም ምኞት፣ አገሪቱ ከገባችበት አጣብቂኝ ለማውጣትና የመፍትሄ አቅጣጫ ለመፈለግ ወረድ ብለው ከባለ ድርሻ አካላት በተለይም ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለመወያየትና በጋራ ለመሥራት ለሕዝባችን በገቡት ቃል መሠረት  ቃሎን ጊዜ ሳይወስዱ ተፈጻሚ እንዲያደርጉ እንጠይቃለን፡፡ ምክንያታችንም ቀናት፣ ሰዓታትና ደቂቃዎች በዘገዩ ቁጥር የዜጎችን አስከፊ ስደት፣ እርስ በርስ የመጣጣል፣ የእንግልትና የእሥራት ችግሮች ስለሚያስተናግዱና የምንገኝበት ወቅትም ጊዜ የማይሰጥ በመሆኑ ነው፡፡

ክቡር መሪያችን፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የወቅቱ አባት ነዎትና ለልማቱ ያለዎት መነቃቃት እሰየሁ የሚያስብል ነው፡፡ ሆኖም ግን ሕልውና ቅድሚያ የሚሰጠው በርቱ አጀንዳ ነው፡፡ በሰላም ማኅበራችን የእውነትን ዓላማ ቀርፀን፣ በእውነት መንገድ ግባችንን የሚጨበጥ፣ የሚተገበርና እውነተኛ ዴሞክራሲ የነገሰበት  ለማድረግ ሕገ መንግሥታችን ላይ የሰፈሩ የዜጎች ተፈጥሮአዊ ሰብአዊ መብቶች ለማስጠበቅና የበለጸገች አገርን ለማምጣት እየሠራን ነው፡፡ የሰላም አማራጭ በጠፋበት ወቅት የአገርና የዜጎች እስትንፋስ በመሆን በቀል ለአንዴና ለመጨረሻም ጊዜ ከኢትዮጵያችን እንዲወገድ፣ ሰላምና ፍቅር በአገራችን እንዲነግስ ዜጎችም ይቅር ባይ ልቦና እንዲኖራቸው ለማድረግ የተመሠረተ የበጎ አድራጎት ማኅበር ነው፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የ41 ዓመታት የኢትዮጵያ የእርስ በርስ ጦርነት አክትሞ ትውልዱ የእኔ የሚላት፣ አባቶች ያቆዩለትን ሉዓላዊት አገር ሳትሸራረፍ ለማስረከብ፣ የበቀል ደዌን በመቅበር ኢትዮጵያውያን አንድ ደም ያለን፣ በአገርም በውጪም የሚገኙ በብሔር፣ በቋንቋ፣ በሃይማኖት፣ በጎሳ፣ በጎጥ፣ በፖለቲካ አመለካከት ሳይነጣጠሉ የሁለት ወገን ጦር ያሰለፈውም አንድ ጥይት ሳይተኩስ የአንድ እናት ልጆች እንደመሆናቸው ለዘለቄታው ሰላም ስንል በሰላም ማኅበር በኩል በምናዘጋጀው የመግባባት፣ የመቻቻል መድረካችን ላይ ተሳታፊ ይሆኑ ዘንድ እንጠይቃለን፡፡ ከሌሎች ባለድርሻ አካላትና በአገር ውስጥ ከሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ በውጪ ከሚገኙ ሌሎች አካላት እንዲሁም በበረሃ ነፍጥ ካነገቡት ጋር በጋራ በመወያየት ኢትዮጵያ አኬልዳማ ሳትሆን በይቅርታ ልብ ችግሮችን አስወገዶ በአንድነት አገርን ለመታደግ በእርስዎ ላይ ሕዝባዊ አደራ  በጫንቃዎ አርፏል፡፡

ለ41 ዓመታት ለዴሞክራሲ ሰማዕትነት በከፈሉት ወገኖቻችን፣ በሰቀቀን ውስጥ ባሉት ዜጎቻችን፣ ችግሮች ቢከሰቱ እንኳ መላወስ በማይችሉት የዕድሜ ባለፀጋ አዛውንቶቻችን፣ በአልጋ ተይዘው በሚገኙ ሕሙማን፣ በነፍሰ ጡሮችና በመጫቶች፣ በሕፃናት ልጆቻችን ስም ከሕዝባዊ የአመፅ እንቅስቃሴ ወይም ከእርስ በእርስ ጦርነት እንዲታደጉን፣ ከፈጣሪ በታችም እርስዎ በጎ ምላሽ እንደሚሰጡ በማመን ከዚህ በታች የተዘረዘሩት ሕገ መንግሥታዊ መብቶች እንዲያከብሩ እንጠይቃለን፡፡

  1. የሥልጣን ባለቤት የሆነውን ሰፊውን ሕዝብ በማክበር በባለቤትነት በየአካባቢው የግጭት ችግሮችን ማስወገድ እንዲቻል ከአገር ሽማግሌዎችና ከሃይማኖት አባቶች ጋር መንግሥት ተባብሮን በጋራ እንድንሠራ ዕድል እንዲሰጠን እንጠይቃለን፡፡
  2. ከተቀናቃኝ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ለውይይት በምጠራው መድረክ ላይ እንዲገኙልን በጎ ምላሽዎን እንጠይቃለን፡፡
  3. የህሊና እስረኞችን ለመፍታት መልካም ጅማሬዎን አሟጠው ይተግበሩ፤ ይፈጸሙ፡፡
  4. የሃይማኖት ተቋማትና የሙያ ማኅበራት ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው እንዲጠበቅ እንጠይቃለን፡፡
  5. የፍትህ አካሎችና አስፈጻሚ መለዮ ለባሾች የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ መብት እንዲያስከብሩ፤ ገለልተኛ እንዲሆኑ እንጠይቃለን፡፡
  6. ለሽምግልና የቆመው የሰላም ማኅበር አባላት ፋሲሊቲዎች እንዲሟሉልንና የሕግ ከለላ እንዲደረግልን እንጠይቃለን፡፡
  7. የሰላም ማኅበር ተወካዮች ከፓርቲ ተወካዮች ጋር ለመወያየት በጎ ምላሽ እንዲሰጡን እንጠይቃለን፡፡

ከላይ ለዘረዘርናቸው በቁርጠኛ የአገርና የወገን አለኝታ መሪነትዎ ሳያቅማሙ ጊዜ ሳይሰጡም፣ ፈጣን ምላሽ ለሕዝባችን እንደሚያስደምጡ በማመን በአክብሮት አገርና ወገንን የመታደግ የሕልውና ጥሪያችንን አናቀርባለን፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር››

(የሰላም አምባሳደር ፋንታሁን ብርሃኑ፣ የሰላም ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ)

  •  

የአዲስ አበባ አስተዳደር የፕሮጀክት ሠራተኞችን መብት ሊያጤነው ይገባል

በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ዕውቅና ከተሰጣቸው መብቶች አንዱ ማኅበራዊ ዋስትና ነው፡፡ በአገራችን ነባራዊ ሁኔታ የማኅበራዊ ዋስትና የሚሰጠው በጡረታ አበልና ዳረጎት መልክ ነው፡፡ ይኼ ተግባራዊ የሚሆነው በመንግሥትና፣ በግል ተቋማት ተቀጥረው አገልግሎት ለሚያበረክቱና የጡረታ መዋጮ የመክፈል ግዴታ ባለባቸው አሠሪዎችና ሠራተኞች ላይ ነው፡፡

የመንግሥትና የግል መሥሪያ ቤቶችና ድርጅቶች ከሠራተኞቻቸው እንዲሁም ከራሳቸው ሊያዋጡ የሚገባውን የጡረታ መዋጮ በመሰብሰብ ለግል ወይም ለመንግሥት ማኅበራዊ ዋስትና ተቋማት ገቢ የሚያደርጉበት አሠራር ተዘርግቷል፡፡ ሠራተኞቻቸው በዕድሜ፣ በሞት ወይም በሌላ ምክንያት ሥራ መሥራት ሳይችሉ ሲቀሩ የሚከፈላቸው ጡረታና ሌሎች ክፍያዎች በሕግና በደንብ ተለይተው ሥራ ላይ መዋል ከጀመሩ ዓመታት  አልፈዋል፡፡

የአዲስ አበባ አስተዳደር ግን ይህንን መብት ወደ ጎን በማለት በፕሮጀክት በሚያደራጃቸው ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች የጡረታ ባለመብት እንዳይሆኑ እገዳ ያደርግባቸዋል፡፡ በመሆኑም የተቋማቱም ሆነ የሠራተኛው የጡረታ መዋጮ አይሰበሰብም፡፡ ይኼ የሠራተኛውን የማኅበራዊ ዋስትና መብት ያጣብባል፡፡ ሠራተኛው በኮንትራት ከዓመት በላይ ተቀጥሮ በተከታታይ ይሠራል፡፡ ጡረታ ዕድሜው ቢደርስ ወይም ቢሞት ‹‹የኮንትራት ሠራተኛ›› በመሆኑ የሚከፈለው ክፍያ ስለማይኖር በራሱና በቤተሰቡ ላይ ችግር ይፈጠርበታል፡፡ በሌላ አባባል የማበራዊ ዋስትናው አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡

በመሆኑም የሕገ መንግሥቱን፣ የመንግሥት ሠራተኞች የጡረታ አዋጅን፣ ኢትዮጵያ የተቀበለቻቸው ዓለም አቀፍ ስምምነቶችና መርሆዎችን ግምት ውስጥ በማስገባት፣ እንዲሁም በግል ድርጅቶች ሳይቀር ከ45 ቀናት በላይ የተቀጠሩ ሠራተኞች የጡረታ መዋጮ በመክፈል በሚያገኙት ማኅበራዊ ዋስትና መብት በፕሮጀክት ለተቀጠርነውም እንዲከበር በማድረግ የተዛባ አሠራሩን ሊያስተካከል ይገባል እንላለን፡፡

(አበበ አሰበ፣ ከፕሮጀክት ሠራተኞች)

*****

ሁሉም እንደየአቅሙ ይፅዳ

አንድ ሰው ለራሱ የጠላውንና የሚቀፈውን ቆሻሻ ሲያስወግድ በሌላው ላይ የሚያስከትለውን ጉዳት መገንዘብ አዋቂነት ነው፡፡ ከተሞች እየሰፉ የገጠሬው ነዋሪ በተለይም ወጣቱ ከየትውልድ ሥፍራው እየተሰደደ በአቅራቢያው ወደሚገኘው ከተማ ሥራ ፍለጋ እየፈለሰ ነው፡፡ አብዛኛው የገጠር ወጣት ወደ አዲስ አበባ እየመጣ ሕንፃ በሚሠራበትና በሌላው የቀን ሥራ መሥሪያ አካባቢ የሚሰማራ ሲሆን፣ ማታ ማታ በጋራ ተከራይቶ ወደ ሚኖርበትና መፀዳጃ ወደ ሌለው መጠለያ ይከተታል፡፡ በመሆኑም ጠዋት ወፍ ሳይንጫጫ፣ ማታ ማታ ጨለማን ተገን በማድረግ በየሜዳው ይፀዳዳል፡፡ ይኼ ግን ለየአካባቢው ነዋሪ የጤና ጠንቅ ሆኖ ይታያል፡፡

ሁኔታው የተፈጠረው በአብዛኛው የአዲስ አበባ ክፍለ ከተሞች ውስጥ በሚታየው የመፀዳጃ ቤት ችግር መሆኑን የተለመከቱ ግብረሰናይ ድርጅቶች የጋራ መፀዳጃዎችን በየሥፍራው አሠርተው ለሚመለከታቸው ቢያስረክቡም የፅዳቱን ሁኔታ በቅርብ የሚከታተል ባለመኖሩ እየተበላሹ በቤቱቹ ውስጥ መፀዳዳት አልተቻለም፡፡ በመሆኑም በተሠሩት ቤቶች ዙሪያ ያለውን ሁኔታ መመልከትና የጤና ጠንቅነቱን መገንዘብ ይቻላል፡፡

በአዲስ አበባ እንደዛሬው የቆርቆሮ ቤቶች ሳይበረከቱ የፎቁም ጋጋታ ሳይመጣ፣ በ1945 ዓ.ም. እንኳ እያንዳንዱ ነዋሪ በየጓሮው ሽንት ቤት ቆፍሮ ጥልቅም ባይሆን የቤቱን ጥራጊ የሚያከማችበት ጉድጓድ ማዘጋጀት ግዴታው እንደነበር እናስታውሳለን፡፡ ማንም ሰው ባገኘበት ሥፍራ ውኃ ሽንት ሳይቀር መፀዳዳት አጥብቆ የተከለከለ ነበር፡፡ ይህንን የሚያስፈጽሙትም በትከሻቸውና በደረታቸው ላይ የፅዳት ዘበኛ የሚል የደንብ ልብስ ለብሰው በከተማው የሚዘዋወሩ ሠራተኞች ነበሩ፡፡ በየቤቱ የተመደበው የሽንት ቤት ጉድጓድና የቆሻሻ ማከማቻ ጉድጓድ የሌለበት ቤት ካገኙ ሕግ ይከበር ስለነበር ያገኙትን ሰው አስገድደው ወደ ፅዳት ቢሮ በመውሰድ የሽንትን አጸያፊነት ለማሳወቅ ሽንት የፈሰሰበት ክፍል ውስጥ አቆይተውና መክረው ይለቁ ነበር፡፡

በየመንገዱና በየአጥሩ ጥግ ሽንት መሽናት አጥብቆ የተከለከለ ስለነበር ሲፀዳዳ የተገኘውን ሰው የፅዳት ዘበኛው ሕጋዊ የሆነና ማኅተም የተደረገበት ደረሰኝ ከመሥሪያ ቤቱ ይሰጣቸው ነበር፡፡ አጥፊውን ለመቀጫ በወቅቱ ከአሥር ሳንቲም ያልበለጠ ገንዘብ ወዲያውኑ ይከፈል ነበር፡፡ ጥፋተኛው ላለመክፈል ካንገራገረም አስገድደው ወደ ፅዳት ቢሮ ይወስዱትና የሽታን አስከፊነት እንስኪያንገሸግሸው ያሳዩት ነበር፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ እንደዚህ ዓይነት የፅዳት ቢሮዎች በየሥፍራው እንደነበሩ የሚታወቅ ሲሆን፣ ከእነዚህ ውስጥ በየጊዜው በብዛት ሰው ሰፍሮበት በነበረው ከአራት ኪሎ እስከ ፍልውኃ ባለው አካባቢ የሚያገለግል የፅዳት ቢሮ በአሁኑ ወቅት ከዘውዲቱ ሆስፒታል ወደ መከላከያ ሲኬድ በሚገኘው ሥፍራ ላይ ይገኝ ነበር፡፡

ታዲያ በምን እንደሆነ ሳይታወቅ ቢሮው ተዘግቶ የከተማውን ፅዳት ሁኔታ የሚቆጣጠር ሠራተኛም ስለጠፋ ከተማችን ከዕለት ወደ ዕለት ፅዳቷ በሚያሳዝን ሁኔታ ላይ ይገኛልና እባካችሁ በሌሎች መሳቂያና መሳለቂያ እንዳንሆን እንጠንቀቅ፡፡ ጤና ለሁሉም ነውና ያለ ነጋሪና ያለ ተቆጪ፣ ያለአስገዳጅ ሁላችንም ስለፅዳት እናስብ፡፡ የሚመለከተውም መንግሥታዊ አካል ጠበቅ፣ ቆንጠጥ ያለ ዕርምጃ እንዲወስድና የ2007 ዓ.ም. ወቀሳና ውርጅብኙን እንደ ትምህርት ወስዶ እያንዳንዱ ወረዳ እንዲነቃቃና እኔ እበልጥ እኔ እሻል፣ በሚል መንፈሳዊ ቅናት በ2008 ዓ.ም. የአዲስ አበባችን መልክና ገፅታ እንዲለወጥ በጋራ እንሥራ፡፡

(አካሉ መሸሻ ይግለጡ፣ ከአዲስ አበባ) 

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...