Thursday, March 23, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
በሕግ አምላክየውርስ ማጣራት በሕጉና በልማዱ መካከል ሲዋልል

የውርስ ማጣራት በሕጉና በልማዱ መካከል ሲዋልል

ቀን:

ይህ ጽሑፍ የሳምንቱ ቀጣይ ክፍል ነው፡፡ ካለፈው ዕትም በመቀጠል የደሴ ከተማ ፍርድ ቤቶችን የውርስ ማጣራት ጉዳይ ይመለከታል፡፡ ጸሐፊው እንደሚያስታውሰው ከአሥር ዓመት በፊት በብዙ የአገራችን ክፍል የውርስ ማጣራት ሥራ በፍርድ ቤቶቻችን በሥራ ላይ አይውልም ነበር፡፡ ወራሾች ከፍርድ ቤት የሚሰጣቸው የወራሽነት የምስክር ወረቀት እከሌ የሟች ልጅ መሆኑን በማረጋገጥ የመጀመሪያ ደረጃ ወራሽ ነው፤ ልጅም ከሌለ የሟች ወላጆች ሁለተኛ ደረጃ ወራሾች ናቸው ወዘተ. የሚል ብቻ ነበር፡፡

የምስክር ወረቀቱ በራሱ ወራሾች በሟች ንብረት ላይ መብት የሚሰጣቸው ተደርጎ ይቆጠር ነበር እንጂ የውርስ ማጣራት ተደርጎ የሚፈፀም ክፍፍል አልነበረም፡፡ የውርስ ጉዳይ ይበዛበት የነበረው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም የውርስ ማጣራቱን ሥራ ራሱ በሕግ አማካሪዎቹ አማካይነት ይሠራ ነበር፡፡ ከፍርድ ቤት የሚመጣውን የወራሽነት የምስክር ወረቀት መሠረት አድርጎ የሕግ አማካሪው ግማሽ ለሚስት፣ ቀሪው ግማሽ ለልጆቹ እኩል ይከፋፈል ወዘተ. በማለት ሟች በባንክ አስቀምጦት ያለፈውን ገንዘብ ያከፋፍል ነበር፡፡ ይህ አሠራር ግን ሕጉን ያልተከተለና ባንኮችን ለችግር ያጋለጠ ነበር፡፡

ሕጉ ሟች እንደሞተ የውርስ መብት እንደሚፈፀም፣ የውርስ ማጣራት መከናወን እንዳለበትና ለወራሾች የሚተላለፈው የጠራ ሀብት ከተለየ በኋላ የውርስ ክፍፍል እንደሚፈፀም ያዛል፡፡ አሠራሩ ግን ይህን የተከተለ ባለመሆኑ ከሕጉ ይልቅ ለልማዱ ያደላ ነበር፡፡ በወራሽነት የምስክር ወረቀት የሚጠቀሙ እንደ ባንክ ያሉ ተቋማትም ያለ ውርስ ማጣራት የሚያከፋፍሉት የውርስ ሀብት ለችግር አጋልጧቸዋል፡፡ በምስክር ወረቀቱ ያልተካተቱ ወራሾች ባንኮችን በመክሰስ ድርሻቸው እንዲከፈላቸው ተደርጓል፡፡ ሟች ወንድ በሆነ ጊዜ በተለይ በአብዛኛው ከጋብቻ ውጭ የተወለዱ ልጆች ዘግይተውም ቢሆን መምጣታቸው አይቀርም፡፡ ሁለተኛ፣ ሦስተኛ ሚስቶች፣ አበዳሪዎች፣ ተጧሪዎች ወዘተ. መብታቸውን በሚጠይቁ ጊዜ ባንኮቹ ጉዳት ላይ የወደቁበት ወቅት ጥቂት አይደለም፡፡ ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ ግን የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አውራ መራሽ የሆነባት የባንክ ኢንዱስትሪ ያለ ውርስ ማጣራት በሟች ስም በባንክ የሚገኝ ገንዘብን ማከፋፈሉን ትቷል፡፡ በባንኮቹ የሥራ መመሪያ ላይ በግልጽ በመቀመጡ ባንኮች ከስጋት ነፃ ሆነዋል፡፡ ለውጡ ከፍርድ ቤቶች ጋር በተከታታይ በተደረጉ የምክክር ጉባዔዎች ፍርድ ቤቶች የውርስ ማጣራት ሪፖርት በአስገዳጅነት እንዲያፀድቁና ለባንኮች እንዲልኩ፣ ባንኮችም በፀደቀው የውርስ ማጣሪያና በፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ መሠረት እንዲፈጽሙ መግባባት ላይ መደረሱን ጸሐፊው ያስታውሳል፡፡

በዘንድሮ የደሴ ከተማ ቆይታው ፀሐፊው በአንዱ የንግድ ባንክ ቅርንጫፍ በተገኘ ጊዜ ያስተዋለው አሠራር ይህንኑ ሕግ መሠረት ያደረገውን የውርስ ማጣራት ተደርጎ በተሰጠ የፍርድ ቤት ትዕዛዝ ገንዘብን ማከፋፈል ነው፡፡ ይሁን እንጂ የፍርድ ቤቶች አሠራር ወጥነት ይጎድለዋል፡፡ ለባንኮች የሚሠራው የውርስ ማጣራት በሌሎች ንብረቶች በተለይም በማይንቀሳቀስ ንብረት ላይ ሲፈፀም አይታይም፡፡ በደሴ ከተማ የወረዳ ፍርድ ቤት በቀረበ አንድ ጉዳይ መነሻነት ጸሐፊው ለመታዘብ እንደቻለው፣ የውርስ ማጣራት ሥራ አሁንም በሕጉ ላይ በዝርዝር በተቀመጠው መልኩ እየተከናወነ አይደለም፡፡ ጸሐፊው በከተማው ከሚገኙ ጠበቆች እንደተገነዘበው፣ የውርስ ማጣራት ሥራው አሁንም በድፍረትና በስፋት ያልተገባበት፣ከሕጉ ይዘት ባፈነገጠ አሠራር የሚከናወን ነው፡፡ መነሻ የሚሆነን ጉዳይ በማስቀደም የሕጉን ድንጋጌና በአፈጻጸም የሚታዩ ችግሮችን በዚህ ጽሑፍ ለማንሳት እንሞክራለን፡፡

መነሻ ጉዳይ

ሕይወት ሰይድ (ስሟ የተቀየረ) አዲስ አበባ ኗሪ በመሆኗ የአባቷን የውርስ ጉዳይ እንዲያስፈጽሙላት ደሴ ከተማ ለሚገኙ ጠበቃ በወኪሏ በኩል ውክልና ትሰጣለች፡፡ ጠበቃው የወራሽነት የምስክር ወረቀት በደንበኛው ስም ለማቅረብ ሲሄዱ የሟች ሚስትና ቀሪዎቹ ወራሾች የእርሷንም አውጥተውላታል፡፡ ይህን እንጂ በተሳሳተ ስም በመሆኑ፣ ስሙን ከማስቀየር በተጨማሪ ጠበቃው ውርስ እንዲጣራ የሟችን ንብረቶች በመዘርዘር አቀረቡ፡፡ ፍርድ ቤቱም ሌሎቹን ወራሾችና ሚስትን ጠርቶ ያከራክር ዘንድ በተከሳሽነት ጠበቃው ቢዘረዝሩም ፍርድ ቤት አቤቱታው ያለ ተጠሪ ይቅረብ በማለቱ ጠበቃው አቤቱታውን በዚሁ መልክ አቀረቡ፡፡ ፍርድ ቤቱም የውርስ አጣሪ እንዲጠቆሙ አደረገና የውርስ ማጣራቱን ጀመረ፡፡ በውርስ ማጣራቱ ሟች አንድ ሚስትና አራት ልጆች እንዳሉት፣ የባንክ ገንዘብ፣ አክሲዮንና የመኖሪያ ቤት እንዳላቸው ተገለጸ፡፡

የመኖሪያ ቤቱ ከጋብቻ በፊት የተሠራ መሆኑን አመልካቹ የገለጹ ቢሆንም የውርስ አጣሪዎቹ ሪፖርት ከማድረግ ውጭ በንብረቱ ላይ ማን ምን ያህል ድርሻ እንዳለው ለመወሰን ባለመቻላቸው ለፍርድ ቤቱ መለሱት፡፡ ፍርድ ቤቱም የውርስ አጣሪዎቹን ሪፖርት መሠረት አድርጎ የባንኩ ገንዘብና አክሲዮኑ ለሟች ሚስት ግማሽ፣ ቀሪው ለሌሎቹ ወራሾች እንዲከፋፈል ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ ዋናውን መኖሪያ ቤት በተመለከተ ግን ምንም የተሰጠ ትዕዛዝ የለም፡፡ በመዝገቡ ሦስት ዳኞች የተፈራረቁ ቢሆንም፣ በመኖሪያ ቤቱ ባለመብት የሆኑት ሰዎች የትኞቹ እንደሆኑና ምን ያህል እንደሚገባቸው ሳይወሰን ታለፈ፡፡ ጠበቃው በቤቱ ላይ ምንም ትዕዛዝ አለመስጠቱን በማንሳት ፍርድ ቤቱን በቤቱ ላይ ወራሽ ያላቸውን ድርሻ እንዲወስንላቸው ቢጠይቁም ‹‹ሌላ አዲስ ክስ በሚስት ላይ በማቅረብ ንብረት ይለቀቅልኝ አቤቱታ ማቅረብ ይችላሉ፤›› ተባሉ፡፡ ከዚህ ፍርድ ሒደት ለመገንዘብ እንደሚቻለው የውርስ ማጣራት ሥራን ወደ ሕጉ ለማምጣት ጥረት ቢደረግም አሁንም በሕጉና በልማዱ መካከል እየዋለለ ለመሆኑ አስረጅ ነው፡፡

ሕጉ ስለ ውርስ ማጣራት ምን ይላል?

ውርስ ማጣራት ምን ማለት እንደሆነ የፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 944 ያስረዳል፡፡ ውርስ ማጣራት ማለት የውርስ ተቀባይ እነማን እንደሆኑ መወሰን፣ የውርስ ሀብት ምን መሆኑን መወሰን፣ ለውርሱ የሚከፈለውን ገንዘብ መቀበል፣ ለመክፈል አስገዳጅ የሆነውን ዕዳ መክፈልና ሟቹ በኑዛዜ ስጦታ ላደረገላቸው ሰዎች የተሰጣቸውን መክፈል ነው፡፡ በሕጉ የውርስ አጣሪ የሚሆኑ ሰዎች ተለይተው ተመልክተዋል፡፡ በመርህ ደረጃ ያለ ኑዛዜ ወራሾች የሆኑ ሰዎች ሰውየው ከሞተበት ቀን አንሥቶ ያለ አንዳች ፎርማሊቲ የአጣሪነት መብት ይኖራቸዋል፡፡ ከዚያ ውጭ የውርስ አጣሪ በሟች ኑዛዜ ሊሾም ይችላል፤ ወይም በይገባኛል ባይ ወይም በሕጉ በተመለከቱ ሁኔታዎች የውርስ አጣሪ በፍርድ ቤት ሊሾም ይችላል፡፡

በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 956 እንደተደነገገው የውርስ አጣሪ ሥራዎች አራት ዋና ዋና ተግባሮችን መፈፀም ነው፡፡ አንደኛ ሟች ኑዛዜ ትቶ እንደሆነ መፈለግና በመጨረሻ ውርሱ የሚደርሳቸው ሰዎች እነማን እንደሆኑ ማረጋገጥ ነው፡፡ ሁለተኛ፣ የውርሱን ሀብት ማስተዳደር፤ ሦስተኛ መክፈያቸው የደረሰውን የውርስ ዕዳዎች መክፈል እንዲሁም አራተኛ፣ ሟች በኑዛዜ ያደረጋቸውን ስጦታዎች መክፈልና የኑዛዜውን ቃል ለመፈፀም ማንኛቸውም አስፈላጊ ጥንቃቄዎች ማድረግ ነው፡፡

ከሕጉ ድንጋጌዎች ለመረዳት እንደሚቻለው፣ የውርስ ማጣራት ዋና ዓላማ ባለቤቱ በመሞቱ ምክንያት በቤተሰቦቹ ዙሪያ በሚፈጠር ያለመረጋጋትና የአስተዳደር ችግር ባጋጣሚው የውርስ ሀብት በየአቅጣጫው እንዳይባክንና የሟች ሀብት በአግባቡ ተጠብቆ በሕጉ ለሚገባቸው ወራሾች እንዲተላለፍላቸው ለማድረግ፤ የሟች ገንዘብ ጠያቂዎችን ጥቅም ለማስጠበቅ ጭምር ነው፡፡ ከዚህ አንፃር ዳኞች የውርስ ማጣራት ጥያቄ ሲቀርብላቸው እነዚህ የሕጉን ዓላማዎች ለማስፈፀም የሚያስችል አካሄድ ሊከተሉ ይገባል፡፡ ዳኞች በተጠየቁ ጊዜ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 950 እና 951 መሠረት ውርስ አጣሪ መመደብ፣ የውርስ አጣሪውን ተግባርና ኃላፊነት በጥንቃቄ መምራትና መቆጣጠር፣ ተገቢውን ሪፖርት መቀበልና ማጽደቅ ከዳኞች የሚጠበቅ ድርሻ ነው፡፡ በዚህ ጽሑፍ እንደመነሻነት የተመለከትነውን ጉዳይ ከመረመርነው ሕጉ ካስቀመጠው፣ ሰበር ሰሚ ችሎቱም ከፈረዳቸው ገዥ ፍርዶች የሚጣረስ፣ ከሕጉ ይልቅ ልማድን የተከተለ አሠራር የዳበረ መሆኑን እንረዳለን፡፡

በጉዳዩ ላይ የቀረበ ምልከታ

የደሴ ወረዳ ፍርድ ቤት የውርስ ማጣራት አቤቱታ ቀርቦለት ከተከተላቸው ሥርዓቶችና ከሰጣቸው ውሳኔዎች ውስጥ የተወሰኑ ነጥቦች ምልከታ ይፈልጋሉ፡፡ የመጀመሪያው ጠበቃው የሟች ሚስትንና ሌሎች ወራሾችን በተከሳሽነት በማካተት ያቀረበውን አቤቱታ ውድቅ በማድረግ አቤቱታው ያለ ተጠሪ እንዲቀርብ ማድረጉ ነው፡፡ ሁለተኛው በውርስ ማጣራት ሒደት የውርስ አጣሪዎቹን በመምራትና በመቆጣጠር ረገድ ፍርድ ቤቱ የነበረው ሚና ነው፡፡ አጣሪዎቹ ሚስትንና ወራሾቹን ለይተዋል፡፡ ንብረቶቹን ዘርዝረዋል ነገር ግን በመኖሪያ ቤቱ ላይ ያቀረቡት ማጣሪያ አከራካሪ ከሆነ ፍርድ ቤት በራሱ ጉዳዩን በመያዝ ሊመረምረው ይገባ ነበር፡፡ ሦስተኛው ፍርድ ቤቱ ለአመልካች መፍትሔ በሚል የጠቆመው ሐሳብ ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ አመልካች በሟች የውርስ ንብረት (የመኖሪያ ቤቱ) ላይ ያላትን ድርሻ ከመወሰን ይልቅ በመኖሪያ ቤቱ ላይ ያላትን ‹‹መብት›› በሌላ ክስ እንድታስከብር መምከሩ ነው፡፡

የውርስ ይጣራልኝ አቤቱታ ይዘት

በጽሑፉ መነሻነት እንደተመለከተው ፍርድ ቤቶች የውርስ ይጣራልኝ አቤቱታ ሲቀርብ ንብረቱን የያዘው ወይም ሌላኛውን ወራሽ በተከሳሽነት የሚያቀርብ ክስ እንደማይቀበሉ ነው፡፡ ይህ ሕጉን የተከተለ አይደለም፡፡ ማንኛውም ሰው ከውርስ ማጣራቱ ጋር አግባብነት አለው ብሎ ከሳሽ (መብት ጠያቂው) ባመለከተ ጊዜ የተጠቀሱት ሰዎች በተከሳሽ ዘንግ ሊሰየሙ እንደሚችሉ ግልጽ ነው፡፡ የፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ ቁጥር 36 እንደሚደነግገው ከሳሹ የሚያነሱት የሕግና የፍሬ ነገር ጭብጦች ሁሉንም ተከሳሾች የሚመለከቱ ከሆነ ወይም ከንብረት ማስለቀቅና መረከብ ጋር በተያያዘ በንብረቱ ላይ የሰፈሩ ሰዎችን ወይም ከሳሽ መብቱን ማግኘት የሚገባው ከየትኛው ተከሳሽ ላይ እንደሆነ ለይቶ ለማወቅ ካልቻለ፣ ተከሳሾችን አጣምሮ ማቅረብ መብቱ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ሚስት በንብረቱ ላይ መብት አለኝ ስለምትልና ንብረቱንም በይዞታ ሥር ስላደረገች፣ ሌሎቹም ወራሾች በንብረቱ ላይ የሚመለከታቸው በመሆኑ፣ በውርስ ማጣራቱ ሥራ ላይ ተሳታፊ ሊሆኑ ይገባል፡፡

ሰበር ሰሚ ችሎት የሰጠው ፍርድም ከዚህ ሐሳብ ጋር የተጣጣመ ነው፡፡ ችሎቱ በሰበር መዝገብ ቁጥር 46726 ታህሳስ 13 ቀን 2003 ዓ.ም. በሰጠው ፍርድ ንብረቱን በይዞታው ያደረገ ሰው ወይም ወራሽ በውርስ ማጣራት ሥራ ተከሳሽ ሆኖ ሊቀርብ እንደሚገባው ነው፡፡ የሟች ወራሾች ንብረቱ በይዞታው ሥር የሚገኘውንና የሟች ባል ስለመሆኑ የተጠረጠረውን ሰው ንብረት እንዲጣራላቸው ባቀረቡት አቤቱታ ላይ በተከሳሽነት ያስጠሩታል፡፡ ሰውየውም መጥሪያ ደርሶት በሰጠው መልስ ከከሳሾች እናት ጋር የጋብቻ ግንኙነት የለኝም፡፡ አብረን በጋራ ያፈራነው ንብረት የለም፣ ወራሾች እኔን በመክሰስ የሚጣራላቸው ንብረት የለም የሚል ተቃውሞ ያነሳል፡፡

የስር ፍርድ ቤት ከሳሾች የሟች እናታቸው ልጆች እስከሆኑ ድረስ የተጠሪ ሚስት ብትሆንም ባትሆንም የአውራሻቸውን ውርስ የመጠየቅ መብት አላቸው በማለት የሟች የውርስ ሀብት ይጣራ በማለት ወስኗል፡፡ ይግባኝ የቀረበለት ከፍተኛ ፍርድ ቤቱም ይግባኙ የመጨረሻ ፍርድ ሳይሰጥ ነው በማለት ውድቅ ስላደረገው ተከሳሽ አቤቱታውን ለሰበር ያቀርባል፡፡ ሰበር ችሎቱ ተከሳሽ በውርስ ይጣራልኝ ክሱ በተከሳሽነት መቅረቡ ትክክል መሆኑን በመግለጽ የውርስ ማጣራቱ ሪፖርት ከመቀጠሉ በፊት ግን በተከሳሽና በሟች መካከል ያለው ግንኙነት ላይ የስር ፍርድ ቤቶች ሊያከራክሩ እንደሚገባ ገዥ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ ሰበር ችሎቱ በፍርድ ሀተታው ‹‹አንድ ሰው በሞተ ጊዜ ትቶት የሄደውን ንብረት መካፈል የሚችሉት በሕጉ አግባብ ወራሾች እንደመሆናቸው የውርስ ሀብቱን ይዞ በሚገኝ ሰው ላይ ክስ በማቅረብ ሀብቱን ሊያገኙ እንደሚችሉ ይታወቃል፡፡

ውርስ ከመጣራቱ በፊት መከፋፈል ባልተቻለ ጊዜም ወራሾቹ ወይም ከወራሾቹ አንዱ ውርስ ይጣራ ዘንድ እንዲታዘዝላቸው ለፍርድ ቤት አቤቱታ ማቅረብ እንደሚችሉ በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 942 እንዲሁም ቀጥለው ካሉት ድንጋጌዎች እንገነዘባለን፡፡ ውርሱ እንዲጣራ ሲጠየቅም ተከሳሽ መሆን ያለበት የውርሱን ሀብት በያዘ ወይም ወራሽ በሆነው ሰው ላይ ነው፡፡›› በማለት የሕጉን መንፈስ በግልጽ ተንትኗል፡፡

በደሴ ወረዳ ፍርድ ቤት በዳኞች በተያዘው አቋም ግን በውርስ ይጣራልኝ ክስ ተከሳሽ ሆኖ የሚቀርብ ወገን ሊኖር አይገባም፡፡ ይህ አቋም ሕጉን ያልተከተለና የውርስ ማጣራቱን ሥራ የሚያሰናክል ነው፡፡ የውርስ አጣሪው ንብረቱን የያዘችውን ሚስትና ሌሎቹን ወራሾች ለመጠየቅና መብታቸውን ለመለየት እንዲችሉም በተከሳሽነት መቅረባቸው ጠቃሚ ነበር፡፡

በውርስ ማጣራት የፍርድ ቤትና የውርስ አጣሪው ሚና

በደሴ ወረዳ ፍርድ ቤት በተከናወነው የውርስ ማጣራት ሥራ አከራካሪ የነበረው የሟች መኖሪያ ቤት ነው፡፡ የውርስ አጣሪው በአመልካች አቤቱታ ንብረቱ ከጋብቻ በፊት የተፈራና የሟች የግል ሀብት መሆኑን ገልጻለች፡፡ በውርስ ማጣራት ሒደቱ ደግሞ ሚስት የጋብቻውን በሞት መፍረስ ተከትሎ የጋራ ባለሀብት እንደሆነች አረጋግጦ፣ ፍርዱን በውርስ ማጣሪያው ሪፖርት አያይዟል፡፡ ከዚህ አንፃር የውርስ አጣሪው በሕግ የተሰጠውን ተግባር በአግባቡ ፈጽሟል፡፡ ውርስ አጣሪው በሕግ የተጣለበት ግዴታ ወራሾቹን መለየት፣ የውርስ ሀብቱን መወሰን፣ ዕዳ ካለ ማጣራትና የኑዛዜ ተጠቃሚ ካለ መክፈል ነው፡፡

በውርስ ሀብቱ ላይ የባለሀብትነት ክርክር (የወራሾች ብቻ ነው ወይስ ሚስትም ይገባታል) የሚለውን መብት የመወሰን ድርሻ የውርስ አጣሪው ሳይሆን የፍርድ ቤቱ ነበር፡፡ ፍርድ ቤቱ ሚስትንና ሌሎች ወራሾችን አስጠርቶ በቤቱ ላይ ያለውን የባለመብትነት ክርክር ማስቀጠል ነበረበት፡፡ ፍርድ ቤቱ ግን ሚስት ቀድሞውኑ የክሱ አካል እንዳትሆን ያደረገ ሲሆን፣ በተጨባጭ ከንብረቱ ክርክር ጋር በተያያዘ አስፈላጊ በሆነችበትም ጊዜ ሳያስጠራትና መብቱን ሳይወስን መዘገቡን መዝጋቱ ትልቅ ስህተት ነው፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎት በሰጠው ገዥ ፍርድ የውርስ አጣሪው አከራካሪ በሆኑ የውርስ ሀብቶች ላይ ማስረጃዎቹን ሰምቶ ማስረጃው ምን እንደሚያስረዳ ሪፖርት ላይ በማስፈር እንዲጣራ ላዘዘው ፍርድ ቤት ማቅረብ እንጂ የውርስ ሀብት መሆኑን የመወሰን ሥልጣን የለውም፡፡

በሰበር መዝገብ ቁጥር 66727 ሐምሌ 29 ቀን 2003 ዓ.ም. የሰጠውን የሰበር ፍርድ ይመለከቷል፡፡ በዚህ ፍርድ ሰበር ችሎቱ ‹‹የባለቤትነት ክርክር በውርስ ማጣራት ሒደት ከተነሣ ጉዳዩ መታየት ያለበትና እልባት ሊያገኝ የሚገባው በመደበኛው ፍርድ ቤት በፍትሐ ብሔር ሥነ ሥርዓት ሕግ መሠረት ተገቢው ጭብጥ ተይዞ የግራ ቀኙ ማስረጃዎች ተሰምተው ሊሆን ይገባል፤›› በማለት ግልጽ ፍርድ ሰጥቷል፡፡ በተያዘው ጉዳይም የመኖሪያ ቤቱ የሟች የግል ሀብት ነው ወይስ የሟችና የሚስታቸው የጋራ ሀብት የሚለው ጭብጥ በመነሳቱ፣ ፍርድ ቤቱ የውርስ አጣሪውን ሪፖርት መነሻ አድርጎ ለጭብጡ እልባት ሊሰጥ ይገባ ነበር፡፡ ይህን አለማድረጉ ሕጉን ያልተከተለና ለልማድ የወገነ ነው፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ ተመሳሳይ ፍርድ በሰበር መዝገብ ቁጥር 25869 ሰኔ 19 ቀን 2000 ዓ.ም. የሰጠ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ሰበር ሰሚ ችሎቱ የሰጣቸው እነዚህ ሁለት ጠቃሚ ፍርዶችን ማንኛውንም ፍርድ ቤት (የደሴ ወረዳ ፍርድ ቤትን ጨምሮ) የሚያስገድዱ መሆናቸውን ለሚገነዘብ ሰው የፍርድ ቤቱ ስህተት መግዘፉን ያስተውላል፡፡

የንብረት ይለቀቅልኝ ክስ አማራጭ

የደሴ ወረዳ ፍርድ ቤት  ወራሽ በውርስ ሀብቱ ላይ ያለውን ድርሻ ሳይወስን መዝገቡን ዘግቶ የንብረት ይለቀቅልኝ ክስ እንዲያቀርቡ መምራቱ ሕጉን ያልተከተለ ነው፡፡ ሲጀመር በፍትሐ ብሔር ሕግ ቁጥር 996 መሠረት ፍርድ ቤቱ ወራሽ በውርስ ሀብቱ ላይ ያለውን ድርሻ የሚገልጽ የምስክር ወረቀት የመስጠት ግዴታውን ቸል ብሎታል፡፡ ፍርድ ቤቱ የውርስ ማጣራት በአግባቡ መከናወኑን አረጋግጦ በመኖሪያ ቤቱ ላይ አመልካች ያላቸውን ድርሻ አላመለከተም፡፡ ሲቀጥል የንብረት ይልቀቅልኝ ክስ ለማቅረብ ወራሾች መጀመሪያ በመኖሪያ ቤቱ ላይ ድርሻ እንዳላቸው ሊመለከት ይገባ ነበር፡፡ ንብረቱን በያዙት ሚስት ላይ ይለቀቅልኝ የሚል ክስ ወራሽ ሊያቀርብ በንብረቱ ላይ ጥቅም የለውም፣ ክስ ለማቅረብ አይችልም የሚል ጠንካራ ተቃውሞ ይቀርብበታል፡፡ ከዚያ በተጨማሪ ወራሽ በመኖሪያ ቤቱ ላይ ያለው የድርሻ መጠን ባልታወቀበት ሁኔታ በድርሻው መጠን ዳኝነት ከፍሎ መብት የሚጠይቅበት ሁኔታ አይኖርም፡፡ ከዚህ አንፃር የደሴ ወረዳ ፍርድ ቤት ከሕጉ ይልቅ ልማዱን መርጦ የውርስ ማጣራቱን በአግባቡ አለማከናወኑ ኃላፊነትን መሸሽ ነው፡፡

እንደማጠቃለያ

የውርስ ይጣራልኝ አቤቱታ በደሴ ወረዳ ፍርድ ቤት የሚከናወንበት አካሄድ ሕጉን ያልተከተለና የወራሾችን መብት የጠበቀ አይደለም፡፡ ወራሾች የውርስ ይጣራልኝ አቤቱታ ሲያቀርቡ ንብረቱን የያዘ ሰው፣ ሚስትን ወይም ሌላ ወራሽን ተከሳሽ አድርገው ማቅረብ ይችላሉ፡፡ በንብረት ላይ የባለቤትነት ጥያቄ ከተነሳም ፍርድ ቤቱ አከራክሮ ውሳኔ ይሰጣል፡፡ እነዚህን ነጥቦች ባለማወቅ ወይም በተሳሳተ ግንዛቤ ሳቢያ አለመተግበር ፍርድ ቤቱ ከሕግ ይልቅ ልማድን ለመምረጡ ዐቢይ ማሳያ ነው፡፡ የሰበር ሰሚ ፍርዶች በማንኛውም ደረጃ የሚገኝን የክልልም ሆነ የፌዴራል ፍርድ ቤትን የሚገዛ እንደመሆኑ፣ ፍርዶቹን ወደ ጎን ማለት የሕግ ተጠያቂነትን ያስከትላል፡፡ የደሴ ወረዳ ፍርድ ቤት አስተዳደር በውርስ ማጣራት ላይ ያለውን አሠራር ሕጉንና የሰበር ፍርድን መሠረት አድርጎ ካላስተካከለው በሕግና በልማድ መካከል መዋለሉ ይቀጥላል፡፡  ለሕጉ አለመወገን ለዳኝነት አካሉ ሕገ መንግሥታዊ አይሆንም፡፡ ልማድንም ያለ ሕግ መሠረት ለማስፈጸም የሚያስችል የሕግ መሰረት አይኖርም፡፡   

ከአዘጋጁ፡– ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...