Thursday, November 30, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አንበሳ ባንክ ‹‹ሄሎ ካሽ›› የተሰኘውን የሞባይል ባንክ አሠራር አስተዋወቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከተመሠረተ ዘጠኝ ዓመታትን ያስቆጠረው አንበሳ ኢንተርናሽናል ባንክ፣ ሄሎ ካሽ የተባለውን ወኪል የሞባይል ባንክ አገልግሎት ማክሰኞ፣ መስከረም 12 ቀን 2008 ዓ.ም. በካፒታል ሆቴል በተካሄደ መርሐ ግብር ላይ አስተዋውቋል፡፡ የባንኩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ሰለሞን እንደገለጹት፣ የአንበሳ ባንክ ሄሎ ካሽ ወኪል የሞባይል ባንክ ሥርዓትን ለማስተዋወቅ ‹‹ቤልካሽ›› ከተሰኘው የቴክኖሎጂ ኩባንያ ጋር ላለፉት ሁለት ዓመታት ሲሠራ ቆይቷል፡፡ ዓላማውም እያደገ የመጣውን የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚ ቁጥር መሠረት ያደረገ ዘመናዊ የባንክ አገልግሎትን ማስፋፋት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡

“በኬንያና በደቡብ አፍሪካ የሚታየውን አይነት በተንቀሳቃሽ ስልክ የባንክ ሒሳብ የመክፈት፣ ሒሳብን የማዘዋወርንና ሌሎችንም የባንክ አገልግሎቶችን ማስፋፋት ዓላማችን ነበርን ያሉት አቶ ጌታቸው፣ ወደፊትም የአገሪቱን የቴሌኮም አገልግሎት ዕድገት ተመርኩዘው የሚመጡ አዳዲስ የባንክ ቴክኖሎጂዎችን ለማስተዋወቅ ባንኩ እንደሚሠራ ተናግረዋል፡፡

የሔሎ ካሽ አገልግሎትን ለባንኩ ያቀረበው የቤልካሽ ቴክኖሎጂ ሶሉሽንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቪንስ ዲዎፕ እንደተናገሩት፣ ድርጅታቸው ወደ ኢትዮጵያ ሲመጣ የነበረው የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚ ቁጥር ከስምንት ሚሊዮን የማይበልጥ እንደነበረና በአሁኑ ወቅት ግን የተንቀሳቃሽ ስልክ ተጠቃሚው ቁጥር ከነበረው ከሦስት እጥፍ በላይ መድረሱን በመጠቆም የቴሌኮም ኢንዱስትሪው የመሠረተ ልማት መስፋፋትና ፈጣን ዕድገት ድርጅቱን ለረዥም ጊዜ አገልግሎቱን ለማቅረብ በአገር ውስጥ ለመቆየት እንደሚያስችለው ገልጸዋል፡፡

የአንበሳ ባንክ የአማራጭ ባንኪንግ ክፍል ኃላፊ አቶ አብርሃም ጥላሁን እንዳብራሩት፣ ማንኛውም የተንቀሳቃሽ  ስልክ ተጠቃሚ በአቅራቢያው ባለ የአንበሳ ባንክ የሔሎ ካሽ አገልግሎትን ለመጠቀም የስልክ ቁጥሩን በመስጠትና የምስጢር የይለፍ ቁጥር በማዘጋጀት ምዝገባውን ካጠናቀቀ በኋላ ሒሳብ መክፈትም ሆነ የገንዘብ ዝውውርን በስልኩ ማከናወን ይችላል፡፡ ማንኛውንም ዓይነት የተንቀሳቃሽ ስልክ መጠቀም እንደሚቻልና የቋንቋ ችግር እንዳይኖርም አገልግሎቱን በአማርኛ፣ በኦሮምኛ፣ በሶማሊኛ፣ በትግሪኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች መጠቀም እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡

አንበሳ ባንክ እ.ኤ.አ እስከ ሰኔ 2015 በነበረው ጊዜ ከ6.2 ቢሊዮን ብር የሚገመት ሀብት እንዳካበተ ሲታወቅ፣ በዚያው ዓመት ከ276 ሚሊዮን ብር በላይ ትርፍ ማግኘቱም ተገልጿል፡፡

 

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች