Saturday, April 1, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አሠሪና ሠራተኛ አገናኛ ድረገጾች

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአሁኑ ወቅት በርካታ ማኅበራዊ ድረገጾች የተለያዩ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ለሕዝቡ አቅርበዋል፡፡ በሕዝቡ ዘንድም እየተዘወተሩ ይገኛሉ፡፡ በየጊዜው ተሻሽለው በአዲስ መልክ እየወጡ የሚገኙት ድረገጾቹ ማኅበራዊ ትስስር ከመፍጠራቸውም ባሻገር ዓለምን ወደ አንድ መንደርነት በማሸጋገሩ ረገድም የማይናቅ ሚና ያበረክታሉ፡፡ ብዙዎቹ ድረገጾች የልዩ ልዩ መልዕክት መለዋወጫ ሆነው ሲያገለግሉ የቀሩት መረጃዎችን የሚሰጡ ናቸው፡፡ ግብይት የሚፈጸምባቸውና ‹‹የቪርቹዋል›› ገበያ መድረክ መሆን የጀመሩ ደረገፆችም ተፈጥረዋል፡፡ ከዕለት ወደ ዕለት መሻሻሎችን የሚያሳየው ቴክኖሎጂ ሌሎችም ቁም ነገሮች ይዞ ብቅ ካለ ሰነባብቷል፡፡

ኤቨርጆብስ የተባለው ድረገጽ ከእነዚህ አንዱን ይወክላል፡፡ በሥራ ላይ ከዋለ ቀናት አስቆጥሯል፡፡ በድረገጹ ሥራ ፈላጊዎችና ቀጣሪዎች ይገናኙበታል፡፡ በአፍሪካ በካሜሮን፣ በኮትዲቯር፣ በሴኔጋል፣ በታንዛኒያና በኡጋንዳ አገልግሎቱን ይሰጣል፡፡ ከአፍሪካ ማዶ በካምቦዲያና በባንግላዴሽ ቢሮውን ከፍቶ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል፡፡

ሥራ ቀጣሪዎችና ፈላጊዎችን በቀላሉ የሚያገናኘው ድረገጹ ማክሰኞ፣ መስከረም 12 ቀን 2008 ዓ.ም. በሸራተን አዲስ ሥራ መጀመሩን በይፋ አስታውቋል፡፡ ‹‹አጠቃቀሙ ቀላል ነው፡፡ ከፌስቡክ ጋር ተመሳሳይ ነው፡፡ አንድ ሥራ ፈላጊ ያለውን የትምህርት ደረጃ፣ የሥራ ልምድና ሌሎችም ማስረጃዎች የሚያሳይ የሰነድ (ሲቪ) ገጽ በመክፈት ከቀጣሪዎች ጋር መገናኘት ይችላል፤›› ያሉት ስቴፋኖ ፖሊሚኖ በኢትዮጵያ የኤቨርጆብስ ባልደረባ ናቸው፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ የድረገጹ ዋነኛ ተልዕኮ በአፍሪካ ሥራ ለማግኘት ሲባል በመረጃ ፍለጋ ወቅት የሚደረገውን ከፍተኛ ድካም መቀነስ ነው፡፡ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሥራ ፈላጊዎች በቀላሉ ሥራ እንዲያገኙ መንገዱን ያቀላል የተባለው ድረገጽ፣ ማንኛውም የሥራ ዓይነት ይስተናገዱበታል፡፡ ‹‹ዜሮ ዓመት የሥራ ልምድ ያላቸው የዩኒቨርሲቲ ምሩቃንን ጨምሮ በተለያዩ ተቋማት የኃላፊነት ሥራ ለሚሠሩ ሰዎችም ተስማሚ የሥራ ዘርፎች ይኖሩናል፤›› ብለዋል፡፡

ከአንድ ወር በፊት በአገር ውስጥ ሥራ የጀመረው ኤቨርጆብስ፣ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሥራ ፈላጊዎች መመዝገባቸውም ተነግሯል፡፡ በሥራ ፈላጊነት የተመዘገቡ ሰዎች ነፃ አገልግሎት ሲያገኙ፣ በአንፃሩ ቀጣሪዎች በተዘጋጁላቸው ፓኬጆች መሠረት ለተጠቀሙት የአገልግሎት ክፍያ እንደሚፈጽሙ ስቴፋኖ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ሦስት ፓኬጆች አዘጋጅተናል፡፡ ዲስከቨሪ፣ ፕሮ እና ፕሪሚየም ይባላሉ፡፡ ለቀጣሪዎች የተዘጋጁ ሲሆን ዋጋው እንደየፓኬጆቹ ይለያያል፤›› ብለዋል፡፡

ተቋሞቹ እንደመረጡት ፓኬጅ የተለያዩ አገልግሎቶች ያገኛሉ፡፡ ክፍያውም በዚያው ልክ የተለያየ መጠን ይኖረዋል፡፡ ዲስከቨሪ የአንድ ወር ዕድሜ ያለው ፓኬጅ ሲሆን፣ አንድ የሥራ ማስታወቂያና አሥር የሥሪ ማመልከቻዎችን (ሲቪዎችን) ያሳያል፡፡ ዋጋውም በወር 2,800 ብር ነው፡፡ ፕሮ የተሰኘው ፓኬጅም እንደዚሁ የአንድ ወር ዕድሜ ያለው ቢሆንም ሲቪና የሥራ ማስታወቂያ የማውጣት አቅሙ ግን ከፍ ያለ ነው፡፡ በፓኬጁ አምስት የሥራ ማስታወቂያዎች ማውጣት ይችላል፡፡ እስከ 50 የሚደርሱ ሲቪዎችንም ለመመልከት ያስችላል፡፡ 5,800 ብር ያስከፍላል፡፡ ፕሪሚየም ለተቋሙ የተሻለ መብቶች የሚሰጥ ፓኬጅ ነው፡፡ በወር 17,000 ብር ያስከፍላል፡፡ በሚያወጣቸው የሥራ ማስታወቂያ ቁጥር ላይ ግን ገደብ አልተጣለበትም፡፡ 200 ሲቪዎች የማሳየት አቅምም አለው፡፡ እስካሁን ከመቶ የሚበልጡ ዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ተቋማት የአገልገሎቱ ተጠቃሚ መሆን እንደቻሉ ተገልጿል፡፡

በዕለቱ ድረገጹን በመጠቀም ሥራ ማግኘት የቻሉ ወጣቶችንም ማግኘት ተችሏል፡፡ በጸሎት ዘነበ ትባላለች፡፡ ከዩኒቲ ዩኒቨርሲቲ በኮምፒዩተር ሳይንስ የተመረቀችው ባለፈው ክረምት ነበር፡፡ ሥራ ለማግኘት ብዙም አልተቸገረችም፡፡ በኤቨርጆብስ ድረገጽ አማካይነት ሥራ ለማግኘት የራሷን ገጽ ከፈተች፡፡ ከቀናት በኋላም ራሱ ኤቨርጆብስ በቢሮው የግንኙነት ኃላፊ አድርጐ ቀጠራት፡፡ እንደ እሷ ገለጻ ድረገጹ የበርካታ ሥራ ፈላጊዎችን ችግር ይቀርፋል፡፡ ሥራ በጀመረ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥም በርካታ ሥራ ፈላጊዎች እየተጠቀሙበት ይገኛል፡፡

ሥራ ፈላጊዎች በድረገጹ ለሚወጡ የሥራ ማስታወቂያዎች ሁሉ ሲቪ መላክ ይችላሉ፡፡ ኩባንያው የሚፈልጋቸውን ለይቶ ካወጣ በኋላ ግን በገጻቸው ላይ ያወጡት ሲቪ እውነተኛነት ባስቀመጡት መረጃ መሠረት ይረጋገጣል፡፡ ‹‹የተማሩበት ዩኒቨርሲቲ፣ የሥራ ልምድና የመሳሰሉትን መረጃዎች በገጻቸው ላይ ይሞላሉ፡፡ እኛም በዚህ መሠረት የሲቪውን እውነተኛነት ማንኛውንም መንገድ ተጠቅመን እናረጋግጣለን፤›› ያለችው ከቀናት በፊት የተቋሙ አባል የሆነችው በጸሎት ነች፡፡

የድረገጹ ተጠቃሚ የሆኑ ድርጅቶችም ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ አቶ ኪሩቤል ምንይችል ይባላሉ፡፡ በፀሐይ ኢንሹራንስ ኩባንያ የሰው ኃይል ክፍል ኃላፊ ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ፣ ከዚህ ቀደም ኩባንያው ተጨማሪ የሰው ኃይል ሲያስፈልገው ጋዜጦችንና የተለያዩ የመገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም ማስታወቂያ ለማስነገር ይገደዳል፡፡ በዚህም ብዙ ገንዘብ ለማውጣት ሲገደድ የቆየ ሲሆን፣ ሥራ ፈላጊዎቹ ያስገቡትን ሲቪ መሰብሰብም ሌላ ራስ ምታት ነበር ይላሉ፡፡ ችግሩን እንደሚቀርፍ ባመኑበት የኤቨርጆብስ ድረገጽ መጠቀም ከጀመሩ ወር ሆኗቸዋል፡፡ እስካሁንም ሦስት ሥራ ፈላጊዎችን ማግኘት ችለዋል፡፡

‹‹በድረገጹ ሦስት የሥራ ማስታወቂያዎች አውጥተናል፡፡ የተወሰኑ ሥራ ፈላጊዎችም ቢሮ መጥተው አነጋግረውናል፤›› በማለት አደሱ ድረገጽ በማስታወቂያ ኢንዱስትሪው ውስጥ ከፍተኛ ፉክክር ሊፈጥር እንደሚችል ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባሻገርም አልፎ አልፎ ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ በዝምድናና በትውውቅ የሚደረጉ ቅጥሮችን እንደሚያስቀርም ያምናሉ፡፡

የኢትዮጵያ አሠሪዎች ፌዴሬሽን ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ታደሰ ኢያሱ እንዳሉት፣ ድረገጹ በአገሪቱ የሚታየውን የሥራ አጥነት ችግር ለማቅለል ጥሩ ድልድይ ሊሆን ይችላል፡፡ ‹‹አሠሪና ሠራተኛን የሚያገናኝ ድርጅት እስከሆነ ድረስ እኛም እንደግፈዋለን፤›› ሲሉ እንዲህ ያለው አሠራር እንደሚደገፍ ገልጸዋል፡፡        

በአገሪቱ የሚታየው የሥራ አጦች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ መምጣቱ አያጠራጥርም፡፡ ለዚህም በየጊዜው ወደ ጐረቤት አገሮች የሚሰደዱ ሰዎች ቁጥርና በየሥራ ማስታወቂያው ላይ የሚራኮቱ ተመራቂ ወጣቶችን ማየት በቂ ነው፡፡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱ 72.7 የሚሆነው ሠራተኛ በእርሻ ሥራ የተሰማራ ሲሆን፣ 40 በመቶ የሚሆነው የአገሪቱ ኢኮኖሚ ምንጭም ከዚሁ የሚገኝ ነው፡፡ ከኢንዱስትሪና ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የሚገኘው የሥራ ዕድል ግን ዝቅተኛ ነው፡፡ በአገሪቱ የምርትና የአምራች ተቋማት እጥረት አንዱ ሆኖ፣ የአሠሪና ሠራተኛ አለመገናኘትም አስተዋጽኦ ያደርጋል፡፡

‹‹አገሪቱ ከፍተኛ ለውጥ ላይ ትገኛለች፡፡ ዕድገቷም ብዙዎችን እየሳበ ይገኛል፡፡ ጥቂት የማይባሉ የውጭ ድርጅቶችም ወደ ኢትዮጵያ መጥተው ማምረት ጀምረዋል፡፡ ከፍተኛ የሠራተኛ ፍላጐት እንደሚኖርም እምነታችን ነው፡፡ ለዚህም ነው በኢትዮጵያ መሥራት የጀመርነው፤›› ያሉት ስቴፋኖ ተመሳሳይ ሥራዎች ለአገሪቱ ዕድገት ሚና እንደሚኖራቸው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች