የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ማገባደጃ የቱሪስቶችን ቁጥር ከአንድ ሚሊዮን በላይ ለማድረስና በዘርፉ የሚገኘውን ገቢም ወደ ስድስት ቢሊዮን ዶላር ለማሳደግ አቅዶ እየሠራ እንደሆነ አስታወቀ፡፡
የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የሕዝብና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ገዛኸኝ አባተ ይህን ያስታወቁት፣ መስከረም 12 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ሶማሌ ዋና ከተማ ጂግጂጋ የሚከበረውን የዘንድሮውን የዓለም የቱሪዝም ቀን አከባበርን አስመልክቶ በሚኒስቴሩ ጋዜጣዊ መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
‹‹በመጀመሪያው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን አንድ ሚሊዮን ቱሪስቶች አገራችንን እንዲጎበኙ ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ ከ774,000 በላይ የሚሆኑ ቱሪስቶች አገሪቱን ጎብኝተዋል፤›› በማለት የገለጹት አቶ ገዛኸኝ፣ ከዚህ በተጨማሪም አገሪቱን ከጎበኙ ቱሪስቶች ሦስት ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ 2.9 ቢሊዮን ዶላር መገኘቱን አክለው አስረድተዋል፡፡
በመጀመሪያው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን የተከናወኑ ተግባራትን ሚኒስቴር በጥልቀት እንደገመገመ ተገልጾ፣ በሁለተኛው የዕድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ መጨረሻ ላይ 1,000,040 ቱሪስቶችን ለማስተናገድ መታቀዱን፣ ከእነዚህ ጎብኚዎችም ከስድስት ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ለማግኘትም መታቀዱንም አቶ ገዛኸኝ አመልክተዋል፡፡
የዘንድሮ የዓለም የቱሪዝም ቀን አከባበር በተመለከተ በዓሉ በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጂግጂጋ ከመስከረም 17 እስከ 23 ቀን 2008 ዓ.ም. በሚቆይ የተለያዩ ዝግጅቶች ተከብሮ እንደሚውል፣ በዝግጅቱ ወቅትም ከተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች የሚመጡ የዘርፉ ባለሙያዎች የሚሳተፉበት ሲምፖዚየም እንደሚካሄድ፣ የቁንጅና ወድድርም የበዓል አከባበሩ አካል እንደሆነ በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ተገልጿል፡፡
የዚህ ዓመት የዓለም የቱሪዝም ቀን መሪ ቃል ‹‹አንድ ቢሊዮን ቱሪስቶች አንድ ቢሊዮን ዕድሎች›› የተሰኘ ነው፡፡ የብሔራዊ በዓሉ መሪ ቃል ግን ‹‹ሚሊዮን ቱሪስቶች ሚሊዮን ዕድሎች›› የሚል እንደሆነ በመግለጫው ወቅት ተገልጿል፡፡ አቶ ገዛኸኝ ‹‹ሚሊዮን ቱሪስቶች ለመሳብ አቅደን እየሠራን ቢሊዮን ቱሪስቶች ማለቱ ተገቢ አይደለም፤›› ብለዋል፡፡
የዓለም የቱሪዝም ቀን በየዓመቱ የሚከበርበትን ምክንያት በተመለከተ አቶ ገዛኸኝ ሲናገሩ፣ ‹‹መንግሥታትና ሕዝቦች ለቱሪዝም ያላቸው ግንዛቤ ይበልጥ እንዲዳብርና ቱሪዝም ለማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ባህላዊና ፖለቲካዊ እሴቶች ጠቃሚነት ያለውን አስተዋጽኦ ማስገነዘብ የመጀመሪያው ዓላማ ነው፤›› ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ቱሪዝም ለአገር ሰላም፣ ለልማት፣ ለሕዝቦች እርስ በርስ መቀራረብ ያለው ፋይዳ ከፍተኛ በመሆኑ፣ የአገር ውስጥ ቱሪዝምን ለማስፋፋት ያለው ድርሻ ትልቅ ነው ብለዋል፡፡ እንዲሁም የዜጎችን የጉብኝት ባህል ማዳበር ሌላው ዓላማ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ቱሪዝም ድርጅት (UNWTO) እ.ኤ.አ. በ1979 በስፔን ቶርሞሊኖስ ባደረገው ሦስተኛ ጠቅላላ ጉባዔ፣ የዓለም የቱሪዝም ቀን እንዲከበር በወሰነው መሠረት እ.ኤ.አ. ከ1980 ጀምሮ በየዓመቱ ሴፕቴምበር 27 በዓለም አቀፍ ደረጃ እየተከበረ ይገኛል፡፡