Sunday, April 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ተካሄደ

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ተካሄደ

ቀን:

በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ባለፈው መስከረም 11 እና 13 ቀን 2008 ዓ.ም. በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ፣ ብሔራዊ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ማዕከል ተካሄደ፡፡

ሦስት ሕሙማን የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሲደረግላቸው ሦስት ሰዎች ደግሞ የኩላሊት ልገሳ አድርገዋል፡፡ ልገሳና ተከላ የተደረገላቸውም ሰዎች በአሁኑ ጊዜ በማገገምና በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የኮሌጁ ሕክምና አገልግሎት ምክትል ፕሮቮስት ዶ/ር ብርሃኔ ረዳዒ ገልጸዋል፡፡ ቀጣዩ የንቅለ ተከላ ሕክምና ከስድስት ሳምንት በኋላ ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ ብሔራዊ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ማዕከል ሦስት ሰዓት የፈጀውን ይህን ሕክምና ያከናወነው፣ የኢትዮጵያና የአሜሪካ የኩላሊት ሕክምና ባለሙያዎች ያሉበት ቡድን መሆኑን ዶ/ር ብርሃኔ አስታውቀዋል፡፡

‹‹በአገራችን ያሉትን የኩላሊት ታካሚዎች ተስፋ ያለመልማል ተብለው ከታሰቡት ሕክምናዎች መካከል አንዱና ዋነኛ የሆነው ይህ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ውጤታማ በሆነ መልኩ ተከናውኗል፡፡ ይህ ዓይነቱ ሕክምና በኢትዮጵያ ውስጥ ከአሁን በኋላ እንደ አንድ የሕክምና ሥራ የሚቀጥል መሆኑን ማብሰር እወዳለሁ፤›› ብለዋል፡፡

‹‹አሁን የተጀመው ንቅለ ተከላ ሕክምና መሠረቱን ተክሏል ለማለት እንጂ፣ ችግሩን ሙሉ ለሙሉ እናስወግዳለን ወይም የአገር ውስጥ ፍላጎትን እናሟላለን ማለት እንዳልሆነ ሊታወቅ ይገባል፤›› ሲሉም አክለዋል፡፡

የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ልዩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ዳይሬክተር ጄኔራል ዶ/ር አዲስ ታምሬ በበኩላቸው፣ ይህ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ‹‹በአገሪቱ የሕክምና ታሪክ ውስጥ ፈር ቀዳጅ ነው፤›› ብለዋል፡፡ ከዚህ በኋላ የአገሪቱ አቅም በፈቀደ መጠን በየጊዜው ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም፣ እንዲሁም በከፍተኛ ደረጃ ሕክምና የሚያስፈልጋቸውን በሽታዎች በመለየት በአገራችን ውስጥ በሚገኙ በመንግሥትና በግል ሕክምና ተቋማት እንዲከናወን ለማድረግ መታቀዱንም አስረድተዋል፡፡

በኮሌጁ የኩላሊት ሕክምና ክፍል ኃላፊና ብሔራዊ የኩላሊት ንቅለ ተከላ ሕክምና ማዕከል ቴክኒካል ዳይሬክተር ዶ/ር ሞሚና አህመድ፣ የኩላሊት ንቅለ ተከላ የተደረገላቸው ሦስት ወንዶች ሲሆኑ የለገሱት ደግሞ ሁለት ሴቶችና አንድ ወንድ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ ልገሳው የተከናወነው ለጋሾቹ ተከላ ከተደረገላቸው ጋር ዘመዳሞች መሆናቸው ከተረጋገጠ በኋላ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

እንደ ዶ/ር ሞሚና ገለጻ ከሆነ፣ ኩላሊትን በሕይወት ከሌለና አንጐሉ ከሞተ ሰው አካል ውስጥ ነቅሎ በሌላ ሕሙማን ላይ ተከላ ማድረግ ይቻላል፡፡ ይህ ዓይነቱ አካሄድ ግን የራሱ የሆነ በጣም አስቸጋሪ ሒደትና ኔትወርኪንግ ስለሚፈልግ፣ ማዕከሉም ለዚህ ዝግጁ ስላልሆነ አሁን እየተደረገ ያለው በሕይወት ካለ ሰው የሚወሰድ ንቅለ ተከላ ነው፡፡

‹‹ከንቅለ ተከላ ጋር ተያይዞ ሊፈጠሩ የሚችሉ ሕገወጥ የሰው አካል ዝውውር (ኦርጋን ትራፊኪንግ) የሚባለውንና አላስፈላጊ የሆኑ ግንኙነቶችን ለመቀነስ ሲባል፣ በቀጥታ ዝምድና ወይም በጋብቻ ዝምድና የቀረበውን ልገሳ ነው እየተቀበልን የምንተክለው፤›› ብለዋል፡፡

በኮሌጁ የቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስትና የኩላሊት ንቅለ ተከላ ፌሎው ዶ/ር እንግዳ አበበ፣ ‹‹አካላቸውን ለሌላ ሰው ሕይወት እንዲሆን መለገስ የፈቀዱ ሰዎች እንደ ብሔራዊ ጀግና ይቆጠራሉ፡፡ ምክንያቱም ሕይወት ለማዳን የራስን አካል ከመስጠት በላይ የሰው ልጅ ለሌላው ሊያደርግ የሚችል ትልቅ ነገር ስለሌለ ነው፤›› ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኦቲዝምን ለመቋቋም በጥምረት የቆሙት ማዕከላት

ከኦቲዝም ጋር የሚወለዱ ልጆች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ...

አወዛጋቢው የወልቃይት ጉዳይ

የአማራና ትግራይ ክልሎችን እያወዛገበ ያለው የወልቃይት ጉዳይ ዳግም እየተነሳ...

ተጠባቂው የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የውድድር መለኪያ የሆነው የሞባይል ገንዘብ ዝውውር በኢትዮጵያ

የሞባይል ገንዘብ ዝውውር የሞባይል ስልክን በመጠቀም ሊገኙ የሚችሉ የፋይናንስ...

የአማራና ደቡብ ክልሎች ለሠራተኛ ደመወዝ መክፈል መቸገራቸውን የፓርላማ አባላት ተናገሩ

በአማራና በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልሎች የሚገኙ የመንግሥት ተቋማት...