Monday, July 15, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አዲስ አበባ በድጋሚ የመዋቅር ለውጥ ልታካሂድ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ12 ዓመት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ መሠረታዊ የመዋቅር ለውጥ ሊያካሄድ ነው፡፡ የከተማ አስተዳደሩን መወቅር እንዲያጠና የተቋቋመው ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት እስከ ግንቦት 2008 ዓ.ም. ድረስ ሥራውን እንዲያጠናቅቅ ኃላፊነት ተሰጥቶታል፡፡

ከተማው አዲስ መዋቅርና የአደረጃጀት ለውጥ እንዲያደርግ ያስፈለገበትን ምክንያት ከንቲባ ድሪባ ኩማ ሲናገሩ፣ የአዲስ አበባ ከተማ በፈጣን ኢኮኖሚ ዕድገት ላይ የሚገኝ በመሆኑ፣ ነገር ግን በከተማው አስተዳደር ፈጣኑን ዕድገት መሸከም የሚችል መዋቅር ባለመኖሩ ነው ብለዋል፡፡

‹‹የአዲስ አበባ አስተዳደር በኢንቨስትመንት፣ በመሠረተ ልማትና በሌሎችም ማኅበራዊ አገልግሎቶች ዕድገት በማስመዝገብ ላይ ይገኛል፡፡ ነገር ግን አሁን ያለው መዋቅር ዕድገቱን መሸከም ብቻ ሳይሆን፣ ከዕድገቱ ጋር እያደገ ላለው የነዋሪዎች ፍላጎት ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚቻል አይደለም፤›› በማለት ከንቲባ ድሪባ የከተማው አስተዳደር መዋቅር እንዲለወጥ ያስፈለገበትን ምክንያት አስረድተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ84 መሥሪያ ቤቶች፣ በአሥር ክፍላተ ከተሞችና በ116 ወረዳዎች የተዋቀረ ነው፡፡ ከ84 መሥሪያ ቤቶች ውስጥ 16 የሚሆኑት የካቢኔ  አባል መሥሪያ ቤቶች ናቸው፡፡

የእነዚህ አካላትን መዋቅር መቀየር የሚያስችል የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተቋቁሟል፡፡ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳድር የአደረጃጀትና የመዋቅር ጥናት ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ሰይፈ ፈቃደ መስከረም 12 ቀን 2008 ዓ.ም. ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱን ለማስተዋወቅ በተጠራው ስብሰባ ላይ እንደገለጹት፣ የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ የከተማውን አስተዳደር መዋቅር በሚገባ ፈትሾ ለረዥም ጊዜ አገልግሎት መስጠት በሚያስችል አደረጃጀት እንዲለወጥ ያደርጋል፡፡

የሰው ኃይሉን በሚመለከትም አቶ ሰይፈ እንዳሉት፣ አሁን ያለው የሰው ኃይል በቁጥር፣ በብቃትና በሥነ ምግባር ያለበት ደረጃ ይመረመራል፡፡ መዋቅራዊ ለውጡ ተግባራዊ ሲደረግም ለሰው ኃይሉም የአቅም ግንባታ ሥልጠና ይሰጣል፡፡ ከዚህ ባለፈም በፕሮፌሽናል ባለሙያዎች መመራት ያለባቸውና በፖለቲካ ተሿሚዎች መመራት ያለባቸው ተቋማት በግልጽ ይለያሉ ተብሏል፡፡

በዶ/ር አርከበ ዕቁባይ ይመራ የነበረው የቀድሞው የአዲስ አበባ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር ከአቶ ዓሊ አብዶ አስተዳደር ሥልጣኑን ሲረከብ አዲስ አበባ ከተማ ከፍተኛ ችግር ውስጥ እንደነበረች አይዘነጋም፡፡ ዶ/ር አርከበ የከተማውን ቁልፍ እንደተረከቡ በ1995 ዓ.ም. ከተማው በታሪኩ ትልቁን የመዋቅር ለውጥ አከናውኗል፡፡

በወቅቱ ባልተማከለ አስተዳደር በአሥር ከፍላተ ከተሞችና በ122 ቀበሌዎች እንድትዋቀር ተደርጓል፡፡ ለበርካታ ሠራተኞች በድጋሚ የሥራ ምደባ የተደረገ ሲሆን፣ አስተዳደሩ አሁን ለያዘው ቅርፅ በወቅቱ የተከናወነው የመዋቅር ለውጥ ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡

በ1997 ዓ.ም. ምርጫ አሸናፊ ቢሆንም ሥልጣን መረከብ ባልቻለው የቀድሞ ቅንጅት ለአንድነትና ዴሞክራሲ ፓርቲ ምትክ ሥልጣን የተሰጠው የባለአደራ አስተዳደር የሥልጣን ዘመን በርካታ ችግሮች እንደተፈጠሩ ይነገራል፡፡

ከዚህ በኋላ ሥልጣኑን ከባለአደራ አስተዳደሩ የተረከበው በአቶ ኩማ ደመቅሳ ይመራ የነበረው አስተዳደር፣ በ2001 ዓ.ም. መሠረታዊ የሥራ ሒደት ለውጥ (ቢፒአር) ላይ ተመሥርቶ የአደረጃጀትና የመዋቅር ለውጥ አድርጓል፡፡

ነገር ግን የተካሄዱት ለውጦች አስተዳደሩ የሚፈለገውን ለውጥ ማምጣት ባለመቻላቸው፣ በ12 ዓመት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ የመዋቅርና የአደረጃጀት ለውጥ ለማድረግ ማስገደዱ እየተገለጸ ነው፡፡

በውይይቱ ወቅት አዲስ አበባ በተከታታይ የመዋቅር ለውጥ ማካሄዷ ጎድቷታል፣ በሠራተኛው ዘንድ የሥራ ዋስትና ችግር ከመፈጠሩም በላይ፣ የተረጋጋ አስተዳደር እንዳይፈጠር አድርጓል የሚሉ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል፡፡

ለዚህ አስተያየት ምላሽ የሰጡት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ አባተ ስጦታው እንዳሉት፣ ያለፉት የመዋቅር ለውጦች አሁን ለተመዘገበው ዕድገት አስተዋፅኦ አላቸው፡፡ ‹‹ክፍላተ ከተሞች ከተፈጠሩ 12 ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ የመዋቅር ማሻሻያ ማድረጉ ተገቢ ነው፡፡ አሁን እያደገ ያለውን ኢኮኖሚ፣ እንዲሁም ከተማውን የወደፊት ዕድገት ታሳቢ ያደረገ መዋቅራዊ ለውጥ የግድ ተግባራዊ ማድረግ አስፈላጊ ነው፤›› በማለት አቶ አባተ አስረድተዋል፡፡

የፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ አምስት መሠረታዊ ዓላማዎችን ይዟል፡፡ የመጀመርያው በከተማ አስተዳደሩ አጠቃላይ ዓላማና ተግባራት ላይ በመመሥረት፣ በሥራ ላይ ያለውን ድርጅታዊ መዋቅርና የሰው ኃይል አጠቃቃም መፈተሽ፣ ሁለተኛ የአስተዳደሩ አስፈጻሚ አካላት የተቀናጀ ሥልጣንና ኃላፊነትን በግልጽ ሊያሳይ የሚችል አደረጃጀትና የድርጀቶችን መዋቅር ማዘጋጀት፣ ሦስተኛ የተዘጋጀውን አደረጃጀትና መዋቅር ሕጋዊነት የሚያሲዙና ተግባራዊነቱንና ውጤታማነቱን ለማረጋገጥ አስፈላጊ የሆኑ የፖሊሲ፣ የሕግና የስታንዳርድ ማዕቀፍ መቅረፅ፣ በአዲሱ አደረጃጀትና መዋቅር መሠረት የተደራጁትን ተቋማት የሰው ኃይል ፍላጎትና የአፈጻጸም እቅድ ማዘጋጀት፣ አምስተኛና የመጨረሻው የአዲሱ አደረጃጀትና መዋቅር ተግባራዊነትና አፈጻጸም ክትትልና ድጋፍ ማድረግ የሚሉት ናቸው፡፡

በ2008 ዓ.ም. ሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ የሚጀመርበት በመሆኑ፣ የከተማው ነዋሪዎች በመልካም አስተዳድር እጦት እየታመሱ በመሆናቸው፣ አዲሱ የመወቅር ለውጥ በፍጥነት ሊተገበር ይገባል ተብሏል፡፡

አቶ አባተ ለዚህ ፕሮጀክት ተግባራዊነት ‹‹ፍጥነት›› ወሳኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ እስከ በጀት ዓመቱ አጋማሽ ጥናቱ እንዲጠናቀቅና ወደ ትግበራ እንዲገባ መመርያ ሰጥተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች