Saturday, November 26, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ደካማ መንግሥታዊ ተቋማት ከውጤታማዎቹ ይማሩ!

  ብዙዎቹ መንግሥታዊ ተቋማት ውጤታማ ባለመሆናቸው ምክንያት የአገልግሎት አሰጣጣቸው ደካማና ከዘመኑ ጋር አብሮ የማይሄድ ነው፡፡ በዚህ ድክመታቸው ምክንያት አገልግሎት ፈላጊዎች ይመረራሉ፡፡ እነዚህ ደካማ ተቋማት በተለያዩ ጊዜያት ለለውጥ ይረዳሉ የተባሉ አሠራሮችን ተግባራዊ ለማድረግ ቢሞክሩም አልተሳካላቸውም፡፡ የሚጠበቅባቸውን ቀልጣፋ አገልግሎት በጥራት መስጠት ስላቃታቸው፣ ከውጤታማዎቹ መማር አለባቸው ለማለት ተገደናል፡፡ በተለይ የሕዝቡ ምሬት በየዕለቱ የሚሰማባቸው ደካማ መንግሥታዊ ተቋማት ከውጤታማዎቹ የሚማሩበት ወሳኝ ጊዜ ላይ ናቸው፡፡

  ኢትዮጵያ ውስጥ ውጤታማ ተብለው ከሚጠቀሱ መንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግንባር ቀደም ተጠቃሽ ነው፡፡ አየር መንገዱ ከዚህ በፊት የነበሩበትን ችግሮች በአብዛኛው በመቅረፍ፣ በአሁኑ ጊዜ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአስተማማኝነቱና በአትራፊነቱ ዝናው በስፋት እየተነገረለት ነው፡፡ ከፍተኛ የሆነ ፉክክር ባለበት የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ በርካታ የአፍሪካና የዓለም አየር መንገዶች በኪሳራ ሲዳክሩ፣ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አሁንም በአትራፊነቱ ቀጥሏል፡፡ የመዳረሻዎቹን ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ እጅግ ዘመናዊ የሚባሉ አውሮፕላኖችን በመግዛት ከዘመኑ ጋር እየተራመደ ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃም በበርካታ ሽልማቶች እየተንበሸበሸ ነው፡፡ ከአገሪቱ አልፎም የአፍሪካ መመኪያ ሆኗል፡፡ ይኼንን ዕውነታ ማንም ሊክድ አይችልም፡፡ በተግባርም እየታየ ነው፡፡

  የዚህ ዓይነቱ ውጤታማነት ሚስጥሩ ምንድነው? ብሎ መጠየቅና ለመማር መዘጋጀት የግድ ነው፡፡ አየር መንገዱ ‹‹ራዕይ 2025›› ብሎ የጀመረው የ15 ዓመታት የዕድገት መርሐ ግብር በከፍተኛ የማኔጅመንት ብቃት፣ በሠራተኞች ወደር የሌለው ተሳትፎ፣ በጠንካራ ቁጥጥርና ግምገማ ለዚህ ስኬት አብቅቶታል፡፡ ይህ አርዓያነት ያለው ውጤት የተገኘው በጥናት ላይ የተመሠረተ ዕቅድ፣ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ በተፈተነ አሠራርና ዘመኑን የሚመጥን ተግባራዊ እንቅስቃሴ በሁሉም የሥራ መስኮች ስለተደረገ ነው፡፡ በዚህም መሠረት አፈጻጸሙ ውጤታማ ሲሆን፣ የሚቀርበው ሪፖርትም አሳማኝና ከሐሰት የፀዳ ነው፡፡ ስኬቱም ለዘለቄታዊ ዕድገት አመላካችም ሆኗል፡፡ ይህ ሁሉ የተገኘው አንገት ለአንገት በመያያዝ ፉክክር በሚደረግበት የአቪዬሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ነው፡፡ ሌሎች ስኬቶችንም መግለጽ ይቻላል፡፡

  ኢትዮጵያ ውስጥ እንዲህ ዓይነት ውጤታማ ተቋም እያለ ዕቅዳቸው በጥናት ላይ ያልተመሠረተ፣ የሰው ኃይላቸውንና ሀብታቸውን በወጉ ማቀናጀት የማይችሉ፣ ቁጥጥርና ግምገማ የሚባል ነገር መኖሩን የማያውቁ፣ ውጤታቸው ሲበላሽ በአፈጻጸም የሚያመካኙ፣ ሐሰተኛ ሪፖርት የሚያቀርቡ፣ ለመታረም ዝግጁ ያልሆኑ፣ ከዘመናዊ አሠራር ይልቅ ልማዳዊው የሚቀናቸውና ለዕድገት የማይመቹ ተቋማት ብዙ ናቸው፡፡ በቢፒአርም በውጤት ተኮርም ተሞክረው የትም መድረስ ያልቻሉት እነዚህ ደካማ ተቋማት፣ ዛሬም የሕዝብ እሮሮ ይሰማባቸዋል፡፡ ተነሳሽነት ስለሌላቸውና በመርህ ስለማይመሩ የኋላቀርነት ምልክት ናቸው፡፡

  በተለይ ከግብር ከፋዩ ሕዝብ ጋር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሚገናኙት የምሬት መነሻ ምክንያት የሆኑ መንግሥታዊ ተቋማት ዋናው ችግራቸው ከአመራራቸው ይጀምራል፡፡ አመራሩ ለተሾመበት ቦታ ስለማይመጥን ተቋሙን መምራት ይቸገራል፡፡ ተግባራዊ የማይደረግ የይስሙላ ዕቅድ ያወጣና ማጣፊያው ሲያጥርበት ምክንያት መደርደር ውስጥ ይገባል፡፡ ተገልጋዩ ሕዝብ የመስተንግዶ ችግር ሲያጋጥመው መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ ይደበቃል፡፡ በሥሩ ያሉ ሠራተኞችን የመምራት አቅም ስለሌለው የተቋሙ አገልግሎት የተሳከረ ይሆናል፡፡ ስህተት በስህተት እየታረመ ውድቀት ይከተላል፡፡ ብዙዎቹ ለሕዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ የተቋቋሙ ተቋማት ችግር ይኼ ነው፡፡ ሥራን ከሠራተኛ፣ ሙያን ከሙያተኛ ጋር አገናኝቶ በሠለጠነ መንገድ ከመምራት ይልቅ ማተራመስ የሚታየው ከላይ በተጠቀሰው ምክንያት ነው፡፡

  ሕዝቡ በውኃ ጥም ሲቃጠል፣ በኤሌክትሪክ ኃይል ችግር ሲታመስ፣ በትራንስፖርት እጦት ሲጉላላ፣ በንግድ ፈቃድ ምዝገባና ስያሜ ከላይ ታች ሲል፣ በብቃት ምዘና መከራውን ሲያይ፣ በግንባታ ፈቃድ ሲመረር፣ በመሬት አቅርቦትና አስተዳደር ሲበደል፣ በትራንስፖርትና መገናኛ ሲታሽ፣ በገቢዎችና ጉምሩክ ሲሰቀቅ፣ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች ሲብከነከን፣ በፍርድ ቤቶች ቀጠሮ መከራ ሲያይ፣ በወረዳና በክፍለ ከተማ ፀሐይና ውርጭ ሲፈራረቁበት፣ ወዘተ ማየት የዘወትር ገጠመኝ ነው፡፡ ችግሩ ምንድነው ሲባል፣ የግልጽነትና የተጠያቂነት መርህ አለመኖር በዋነኝነት ይጠቀሳል፡፡ በዚህም ምክንያት የመልካም አስተዳደር ዕጦትና የሙስና መስፋፋት ጎልቶ ይሰማል፡፡ የደካማ ተቋማት አሳዛኝ ትሩፋት ይኼ ነው፡፡

  አገሪቱ ብሎም አፍሪካ የሚመኩበት ታላቅ ምሳሌ የሆነ አየር መንገድ ባለበት አገር ውስጥ፣ በተመሰገነ ተግባራቸውም ሆነ በውጤታማነታቸው ተጠቃሽ የሆኑ ውስን መንግሥታዊ ተቋማት እየታዩ ባሉበት በዚህ ጊዜ ውስጥ፣ ከድክመታቸው ተላቀው ውጤታማ መሆን የሚችሉ በርካታ ተቋማት መፈጠር አለባቸው፡፡ ይኼ ኃላፊነት ደግሞ የመንግሥት ብቻ ነው፡፡ በዘፈቀደ እየተመሩ ምንም ዓይነት እሴት ሳይጨምሩ ሕዝብ በማስመረር ብቻ የሚኖሩ ተቋማት መሠረታዊ ለውጥ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህ ለውጥ የሚመጣው በመፈክር ጋጋታ ሳይሆን፣ በተቀመረ የዕድገት መርሐ ግብር ብቻ ነው፡፡ መርሐ ግብሩ ወርቅ በእሳት እንደሚፈተነው ሁሉ በተግባር ተፈትኖ ውጤት የተገኘበት መሆን አለበት፡፡ ለዚህም ምሳሌ ሊሆኑ የሚችሉ ልምዶች መቀመር ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንን ለማድረግ ደግሞ በትምህርት ዝግጅታቸውም ሆነ በልምዳቸው አንቱ የተባሉ ዜጐችን ተሳትፎ በብዛት ማካተት የግድ ነው፡፡

  የብዙዎቹ ደካማ ተቋማት ትልቁ ችግር የተማረ የሰው ኃይልና ልምድ ያለውን ባለሙያ አለመጠቀም፣ ከዘመኑ ጋር የሚራመድ አሠራር አለመዘርጋት፣ ለተቋማት ግንባታና ለሰው ኃይል ልማት ትኩረት አለመስጠት፣ ለሙስናና ለብልሹ አሠራር የሚያጋልጡ ድርጊቶች መስፋፋት፣ ለግልጽነትና ለተጠያቂነት መርህ ቦታ አለመስጠት፣ በገጠመኝ መመራት፣ ራዕይ አልባነትና የመሳሰሉት ናቸው፡፡ እነዚህን የሕዝብና የአገር ጠንቆችን በማስወገድ ብቁ፣ ተወዳዳሪ፣ ቀልጣፋና ውጤታማ ተቋማትን ለመፍጠር ጥረት ካልተደረገ ከሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ውጤት መጠበቅ አይቻልም፡፡ ምክንያቱም የአንደኛው ዕቅድ አፈጻጸም እነማን ውጤታማ ነበሩ? እነማን በውጤታማዎቹ ውስጥ ተከልለው አልፈዋል? መሰናክል የነበሩትስ የትኞቹ ናቸው? ተብሎ ቢገመገም ውጤቱ ቁልጭ ብሎ ይታያልና፡፡ በደካማ ተቋማት ምክንያት አገሪቱ አሳሯን ማየት የለባትም፡፡

  አሁን ጊዜው የሥራ ነው፡፡ የውድድር ነው፡፡ ለጥራትና እሴት ላላቸው ጉዳዮች ብቻ ትኩረት የሚሰጥበት ነው፡፡ በመሆኑም በአገሪቱ ውስጥ ለዕድገትና ለለውጥ የሚጠቅሙ ምሳሌዎች ስላሉ፣ ከአረጀና ከልማዳዊ አሠራር በመላቀቅ ለተሻለ አገልግሎትና ውጤት መነሳት ይበጃል፡፡ ብዙዎቹ የግል ድርጅቶች ውጤታማ ሆነው የዘለቁት የቆሙለትን ዓላማ በማሳካታቸው ነው፡፡ በኢትዮጵያ ውስጥ በሥራ ላይ ያሉ ባንኮችና የኢንሹራንስ ተቋማት የውጤታማነት ሚስጥር ይኼው ነው፡፡ ያለምንም ድጎማና ድጋፍ አትራፊ ሆነው የሚሠሩት እነዚህ ድርጅቶች ውጤታማ የሆኑበት ሚስጥር ትምህርት መሆን ይችላል፡፡ በዘፈቀደና በልማዳዊ አሠራር የትም መድረስ አይቻልም፡፡ ለዚህም ነው ደካማ የመንግሥት ተቋማት ከውጤታማዎቹ ይማሩ የሚባለው!       

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ሰርጌ ላቭሮቭ ለዲፕሎማቲክ ማኅበረሰቡ በአዲስ አበባ በሰጡት መግለጫ ምዕራባውያንን አጣጣሉ 

  የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ለአፍሪካ አገሮች ላደረጉት...

  በፍላጎት ላይ የተመሠረተ ብሔራዊ አገልግሎት የተካተተበት አዋጅ ለፓርላማ ቀረበ

  የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ወይም የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወጣቶች በፈቃደኝነት...

  ባንኮች በትልልቅ ባለሀብቶችና በከተሞች ላይ ያተኮረ የብድር አቅርቦታቸውን እንዲያርሙ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

  የአገሪቱ ባንኮች ዋነኛ ተግባራቸው የሆነው ብድር የማቅረብ አገልግሎት እንከን...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  የትርፍ መጠኑን በ127 በመቶ ያሳደገው አቢሲኒያ ባንክ ካፒታሉን በ2.5 ቢሊዮን ብር እንዲያድግ ወሰነ

  የአቢሲኒያ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩ  ካፒታል በ2.5 ቢሊዮን ብር...

  አዋሽ ባንክ ካፒታሉን 55 ቢሊዮን ብር ለማድረስ ወሰነ

  የአዋሽ ባንክ ዳይሬክተሮች ቦርድ ዛሬ ህዳር 17 ቀን 2015...

  ከብሔራዊ ባንክ እውቅና ያገኘው ፔይሊንክ አክሲዮን ማህበር ምሥረታውን አካሄደ

  ከገንዘብ ንክኪ ነፃ የሆነ የዲጂታል ክፍያ ሥርዓት ለመተግበር ያቀደው...

  የተወሳሰበው ሰላም የማስፈን ሒደት

  የደቡብ አፍሪካ የሰላም ስምምነት ተፈርሞ ብዙም ሳይዘገይ የኬንያው ቀጣይ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...

  ዘረፋ የሚቆመው በተቋማዊ አሠራር እንጂ በዘመቻ አይደለም!

  ኢትዮጵያ ውስጥ ሌብነት ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ ለያዥ ለገናዥ ሲያስቸግር ከማየት በላይ አሰቃቂ ነገር የለም፡፡ በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች መረን የተለቀቀው ሌብነት አስነዋሪ መሆኑ...

  ሰላም ዘላቂ የሚሆነው ቃል ሲከበር ብቻ ነው!

  እንደ አለመታደል ሆኖ የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት ውስጥ ለሁለት ዓመታት ከተከረመ በኋላ የሰላም መንገድ ተጀምሯል፡፡ በአገር በቀል ሽምግልና ማለቅ የነበረበት ከአገር ውጪ አስጉዞ፣ በባዕዳን...