Wednesday, February 28, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

በሁለተኛው ምዕራፍ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር 32 ኪሎ ሜትር መስመር ታቅዷል

ተዛማጅ ፅሁፎች

– ሥራ የጀመረው ባቡር በቀን እስከ 200,000 ብር እያስገኘ ነው

– በዓመት 48 ሜጋ ዋት ኃይል ይፈልጋል

በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ተግባራዊ የሚሆኑ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ሁለተኛ ምዕራፍ ፕሮጀክትቶች ይፋ ሆኑ፡፡ ለሁለተኛው ምዕራፍ 32 ኪሎ ሜትር መስመር ዕቅድ ተይዟል፡፡

ጥናታቸው እየተጠናቀቁ የሚገኙት መስመሮች ከመገናኛ-በኢምፔሪያል ሆቴል በኩል ቦሌ ኤርፖርት፣ በመቀጠልም ወደ ሳሪስ፣ ከሳሪስ በጎፋአድርጎ ለቡ ብሔራዊ የባቡር ጣቢያውን እንደሚቀላቀል፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ኢንጂነር ጌታቸው በትሩ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ሌላኛው በሁለተኛው ምዕራፍ የሚካተተው መስመር ደግሞ ከጊዮርጊስ ምንሊክ አደባባይ በቸርችል ጎዳና ወደ ሜክሲኮ አድርጎ፣ በአፍሪካ ኅብረት ለቡ ብሔራዊ የባቡር ጣቢያ የሚገባ መሆኑን ዶ/ር ጌታቸው ገልጸዋል፡፡ በቀጣይ ምዕራፎች ደግሞ ከአያት ወደ ለገጣፎ፣ ከጦር ኃይሎች ቡራዩ፣ ከጊዮርጊስ ወደ ሽሮሜዳ የማስፋፊያ ፕሮጀክቶች እንደሚኖሩ ጠቁመዋል፡፡

በአጠቃላይ በተለያዩ አምስት ምዕራፎች አዲስ አበባ ውስጥ የባቡር ኔትወርክ ለመፍጠር መታቀዱን፣ ዓላማውም አንድ የባቡር መስመር ውስጥ የገባ ተሳፋሪ የፈለገበት ቦታ በባቡር ማድረስ መሆኑን ዶ/ር ጌታቸው ገልጸዋል፡፡

የባቡር መስመር መዘርጋትና ትራንስፖርቱን ማስፋፋት የመንደላቀቅ ጉዳይ ሳይሆን፣ የግድ የሚያስፈልግ መሆኑን መንግሥትም ጭምር እንዳመነበት ጠቁመዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት እሑድ መስከረም 9 ቀን 2008 ዓ.ም. በከፊል ሥራ የጀመረው የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በየቀኑ እየሰጠ በሚገኘው የትራንስፖርት አገልግሎት፣ በቀን እስከ መቶ አርባ ሺሕ ተሳፋሪዎችን እያጓጓዘ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሏል፡፡

በዚሁ የትራንስፖርት አገልግሎት በየቀኑ በአማካይ እስከ ሁለት መቶ ሺሕ ብር እየሠራ መሆኑንም ዶ/ር ጌታቸው ገልጸዋል፡፡ ይህ ገቢና የማመላለስ አቅም በ12 ባቡሮች ብቻ በሚደረግ ምልልስ መሆኑንም ለማወቅ ተችሏል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ቀላል ባቡር ሙሉ በሙሉ በሁለቱም መስመር አገልግሎት መስጠት ሲጀምር፣ በዓመት እስከ 48 ሜጋ ዋት እንደሚፈጅ የቀላል ባቡሩ ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሔኖክ ቦጋለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በቃሊቲ የሥምሪት ማዕከል ውስጥ ኢትዮጵያውያንና ቻይናውያን ባለሙያዎች የባቡሩን እንቅስቃሴ በቪዲዮ ምሠልና በሲግናል ሲከታተሉ ሪፖርተር ለማስተዋል ችሏል፡፡ በዚህ ማዕከል የባቡሩ መስመር ውስጥ የሚገቡ ሌሎች ተሽከርካሪዎች ወይም እንስሳትና እግረኞች ቢኖሩ ቀድመው ለባቡሩ ሾፌር (ትሬይን ማስተር) ማሳወቅ እንደሚችሉ ለማወቅ ተችሏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በየጣቢያው ያለውን የተሳፋሪ መጠን በመመልከት የባቡር ሥርጭቱን መጨመር መቀነስ እንደሚያስችላቸው ለመገንዘብ ተችሏል፡፡

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አባላትም በዚሁ የሥምሪት ማዕከል ባልደረቦች ሲሆኑ፣ የእነሱ የሥራ ድርሻ ደግሞ የተለያዩ ወንጀሎችንና ዝርፊያዎችን መከታተል ነው፡፡

በእያንዳንዱ ጣቢያ ላይ ያለውን እንቅስቃሴ በሚመለከት የተመለከቱትን ወንጀል፣ ማጭበርበርና የመሳሰሉትን በአካባቢው ላለ የፖሊስ ባልደረባ የመጠቆም ኃላፊነት አለባቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች