የኢሕአዴግ ምክር ቤት በተያዘው ሳምንት ስብሰባውን እንደሚጀምር ተገለጸ፡፡
የገዥው ፓርቲ ኢሕአዴግ አራቱም አባል ድርጅቶች በእኩል የሚወከሉበትና በድምሩ 180 አባላት ያሉት የኢሕአዴግ ምክር ቤት፣ ከፓርቲው ጠቅላላ ጉባዔ ቀጥሎ የሚገኝ አካል ነው፡፡
ምክር ቤቱ ሰሞኑን በሚጀምረው ስብሰባው የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ የ2010 ዓ.ም. ግማሽ ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርትን በማዳመጥ፣ በአፈጻጸሙ ላይ እንደሚወያይ የሪፖርተር ምንጮች ገልጸዋል፡፡፡
የምክር ቤቱ ስብሰባ የሚመራው በድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ መሠረት በግንባሩ ሊቀመንበር በአቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ እንደሚሆንም ምንጮች አስረድተዋል፡፡
ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ለአንድ ሳምንት ያካሄደውን ጉባዔ ማጠናቀቁን የተመለከቱ መረጃዎች እየወጡ ነው፡፡ ሐሙስ መጋቢት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት የግንባሩ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሽፈራው ሽጉጤ፣ የሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴው በታኅሳስ ወር 2010 ዓ.ም. ያሳለፋቸው ውሳኔዎች በተናጠል ብሔራዊ ድርጅቶች እንዴት ተፈጸሙ የሚለውን በጥልቀት መገምገሙን ተናግረዋል፡፡
ስብሰባው የግንባሩን አንድነት ያጠናከረ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ የሪፖርተር ምንጮች እንደሚሉት የግንባሩ አባል ድርጅቶች ባቀረቡት ሪፖርት ላይ ቀናት የፈጀ ውይይት ተደርጓል፡፡
የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሰሞኑን ያደረገውን ግምገማና ሌሎች ኮሚቴዎች የሚያቀርቡትን የውሳኔ ሐሳብ ያጠቃለለ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት፣ ሰሞኑን ለሚሰበሰበው የኢሕአዴግ ምክር ቤት ያቀርባል፡፡
ምክር ቤቱ ሪፖርቱን ካዳመጠ በኋላ በሪፖርቱ ላይ ውይይትና ግምገማ እንደሚያካሂድና ውሳኔ በሚሹ ነጥቦች ላይም ውሳኔዎችን እንደሚያስተላልፍ ይጠበቃል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ የኢሕአዴግ ምክር ቤት የሚከተሉት ሥልጣንና ተግባሮች እንዳሉት በመተዳደሪያ ደንቡ ላይ ተዘርዝሯል፡፡ እነዚህም በምክር ቤቱ አባላት ሁለት ሦስተኛ ድምፅ ዕጩ አባልነትን (የግንባሩ) መፅደቅ፣ የአባልነት ግዴታውን ያላሟላን የግንባሩ አባል ድርጅትን እስከ ግንባሩ ጉባዔ ድረስ ከአባልነት ማገድ (ከአባልነት የሚሰረዘው ግን በጉባዔው ውሳኔ ነው)፣ ጥፋት በፈጸመ የምክር ቤት አባል ላይ በሁለት ሦስተኛ ድምፅ በጊዜያዊነት ከምክር ቤቱ አባልነት ማገድ፣ የግንባሩን ሊቀመንበርና ምክትል ሊቀመንበር መምረጥ ይገኙበታል፡፡
የግንባሩ ሊቀመንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ከሁለቱም ሥልጣናቸው በፈቃዳቸው ለመልቀቅ ጥያቄ ማቅረባቸው የሚታወቅ ሲሆን፣ ምክር ቤቱም በምትካቸው ሊቀመንበር ይመርጣል፡፡