- ለወጣቶች ከተመደበው አሥር ቢሊዮን ብር ጥቅም ላይ የዋለው 6.4 ቢሊዮን ብር ነው
በኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ ወጣቱ ትውልድ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆን ባለመደረጉ፣ አሁን አገሪቱን ዋጋ እያስከፈለ ነው ሲሉ የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትሩ አቶ ርስቱ ይርዳ ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሩ የስምንት ወራት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርታቸውን ሐሙስ መጋቢት 6 ቀን 2010 ዓ.ም. ለፓርላማ ባቀረቡበት ወቅት፣ ወጣቱ በአገሪቱ የለውጥ ጉዞ ባለቤትና ተጠቃሚ ባለመሆኑ በፖለቲካዊ ጉዳዮችም ንቁ ተሳታፊ እንዳይሆን እንዳደረገው አስረድተዋል በዚህ የተነሳም ዛሬ ዋጋ እያስከፈለ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም በቀጣይ ገዥው ፓርቲና መንግሥት የጀመሩት የሪፎርም ሥራዎች ወጣቶች ንቁ ተሳታፊ በመሆን ለአገራቸው ኃላፊነትን እንዲወስዱ ማድረግ ስለሚገባ፣ የሁሉም አካላት የጋራ ርብርብ እንደሚጠበቅ አስረድተዋል፡፡
የወጣቱን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ መንግሥት አሥር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ማዘጋጀቱን ያስታወሱት ሚኒስትሩ፣ ይህ ፈንድ በሚፈለገው መጠን ሥራ ላይ እየዋለ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡
ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ በአንዳንድ አካባቢዎች አመራሩ በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች በመጠመዱ፣ በሌላ በኩል ደግሞ የአስፈጻሚ አካላት ቅንጅት ማነስና ፈንዱን ለማስተዳደር ከወጣው መመርያ ውጪ ቅድመ ሁኔታዎችን በተለያዩ አካባቢዎች በመቅረባቸው ምክንያት እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
ከተፈቀደው አሥር ቢሊዮን ብር ተዘዋዋሪ ፈንድ ውስጥ አራት ቢሊዮን ብር በ2009 ዓ.ም. መከፋፈሉን ገልጸዋል፡፡ በ2009 ዓ.ም. የተለቀቀው አራት ቢሊዮን ብር በአግባቡ ሥራ ላይ አውለው ተገቢ ሪፖርት ላቀረቡት ለኦሮሚያ፣ ለደቡብ፣ ለአማራ፣ ለቤንሻንጉል ጉምዝ፣ ለሶማሌ፣ ለትግራይ፣ ለሐረር ክልሎችና ለድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ተጨማሪ 2.39 ቢሊዮን ብር በ2010 በጀት ዓመት መለቀቁን አስታውቀዋል፡፡
ከዚህ መረዳት የሚቻለው የኢኮኖሚና የፖለቲካ መዲና የሆነችው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በ2010 ዓ.ም. ለወጣቶች ያገኘው በጀት አለመኖሩን ነው፡፡
የምክር ቤቱ የማኅበራዊ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዚህ የወጣቶች የሥራ ዕድል ፈጠራ ፈንድ ላይ የሚታዩ ችግሮች ተቀርፈው በቅንጅት ፈንዱ ጥቅም ላይ እንዲውል አሳስቧል፡፡