Friday, March 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ይድረስ ለሪፖርተርታላቁ ሩጫ ለታላቅ እሴቶች ይሩጥ

ታላቁ ሩጫ ለታላቅ እሴቶች ይሩጥ

ቀን:

ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ በሁለት የተለያዩ የሩጫ ምድቦች በመከፋፈል ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያና ታላቁ ሩጫ የሴቶች ተብሎ ከተለያዩ አገሮች የመጡ ተሳታፊዎች፣ በአገር ውስጥ በተለያየ የሥራ መስክ የተሰማሩ፣ ከተለያዩ የአገሪቷ ክልሎች ተውጣጥተው በብሔር፣ በሃይማኖት፣ በፆታ፣ በዕድሜ ያልተገደቡ ተሳታፊዎች የሚታደሙበት ውድድር ነው፡፡ ዕድሜ ስል ግን ለሕፃናት ተብሎ ዋናው ውድድር ከመካሄዱ በፊት የሚዘጋጀውን ታላቁ ሩጫ ለሕፃናትን ከግምት ሳላስገባ ቀርቼ አይደለም፡፡ በተለያዩ ጊዜያትም እንዲሁ በክልሎች የሚካሄድ ሩጫ ነው፡፡ በሁሉም ክልሎች ስለመሆኑ ግን መረጃው የለኝም፡፡

ለውድድሩ የሚሆነውን ገንዘብም ተሳታፊዎች ከውድድሩ በፊት ቀድመው በመመዝገብ ይከፍላሉ፡፡ በተጨማሪም ድርጅታቸው እንዲተዋወቅላቸው ከሚፈልጉና ከተለያዩ የዕርዳታ ድርጅቶች በሚያገኘው ገቢ ዝግጅቱን ባማረ መልኩ እያካሄደ እዚህ ደርሷል፡፡ ስፖርቱን ብቻ ዓላማ አድርገው የተነሱ ሩዋጮች የሚታደሙበት ይህ ሩጫ፣ እኔ እንደሚገባኝ ዓላማው ለሰዎች ኅብረትን፣ ጤናማ ትውልድ መፍጠርን፣ ኢትዮጵያ በዓለም የምትታወቅበትን ሩጫ በራሷ ሕዝብ አማካይነት ለዓለም ማሳወቅ ነው፡፡  

ለተከታታይ ጊዜያት እየተካሄደ ያለው የሴቶች ታላቁ ሩጫ ዘንድሮ ለ15ተኛ ጊዜ መጋቢት 2 ቀን 2010 ዓ.ም. ተካሂዶ ነበር፡፡  ከእነዚህ ተከታታይ የሩጫ ጊዜያት ውስጥ በሰባቱ ተሳታፌያለሁ፡፡ ግማሹን ሮጫለሁ ማለት ነው፡፡ ዋናው ላነሳው የፈለኩት ሐሳብ፣ ታላቁ ሩጫ የሴቶች የሚል መጠሪያ ይዞ በአዲስ አበባ የሚካሄደው ውድድር ዓላማው ሁሌም ግራ እንደሚጋባኝ ለመግለጽ ነው፡፡ ከዓመት ዓመት ብሳተፍም በአንዱም የተለየ የምለው ሴቶች ላይ የተሠራ ወይም አብዛኛውን ችግር ቀማሽ ናቸው ብዬ በማስበው የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ሴት እናቶቼና እህቶቼ ድረስ በመገኘት የተደረገ ነገር ስለሌም ነው ግራ የሚያጋባኝ፡፡ ተሳታፊዎቹ ተማሪዎች፣ የቤት እመቤቶች፣ የተለያየ ዕውቀትና የሥራ ድርሻ ያላቸው በርካታ ሴቶች ናቸው፡፡

በውድድሩ ላይ እንስቶች አዘጋጆችና አትሌቶች መድረኩን በመምራት ከውድድሩ በፊትና ከውድድሩ በኋላ የሚነገሩ ቁንፅል ሐሳቦች ይደመጣሉ፡፡ የለበሱትን የመወዳደሪያ ቲሸርት በተለየ መልኩ ያስዋቡትን በመሸለም፣ በሙዚቃ በማበድ፣ በዕድሜ ትናንሽ የሆኑ የአንደኛና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በሚያስተጋቡት ጩኸት፣ ፎቶ በመነሳት የታጀበ ከመሆኑ በቀር ሌላ የረባ ሚና ሳይኖረው ውድድሩም፣ ዝግጅቱም ያልቃል፡፡ ዘንድሮ ‹‹ከጥቃት ነፃ ሕይወት መብቴ ነው፤›› በሚል መሪ ቃል ነበር ውድድሩ የተካሄደው፡፡ እኔ ግን ይኼን እጠይቃለሁ፡፡ ከተማችን ላይ ከገጠሪቱ ኢትዮጵያ በበለጠ የከፋ ጥቃት አለ ለማለት ባልችልም፣ ሙሉ በሙሉ ግን የለም አልልም፡፡ በርካታ አካላዊና ሥነ ልቦናዊ ጥቃቶች ደርሰው አልፈዋል፡፡ አሁንም እየደረሱ ነው፡፡ ቢያንስ ከተማ ላይ ያለች ሴት በብዙ መልኩ ከገጠሪቱ የተሻለ የመብት ጥበቃም ሆነ ከለላ ልታገኝ ብትችልም ከልዩ ልዩ ጥቃቶች አታመልጥም፡፡

በሴቶች ላይ በርካታ የከፉ ችግሮች ሲኖሩ፣ ያለዕድሜ ጋብቻ፣ ያልተፈለገ እርግዝና፣ በወሊድም ወቅት (የደም መፍሰስ)፣ የጤና ባለሙያዎች ዕገዛ ማጣት፣ የጤና ክብካቤ አለማግኘት፣ የተሻለ ሥራ ዕድል ማጣት፣ የትምህርት ዕድል እንደልብ አለማግኘት፣ የመናገር መብት አለመከበር ከሚደርሱባቸው ችግሮች ውስጥ በጥቂቱ የሚጠቀሱት ናቸው፡፡

በከተማ ያለን ሴቶች የምናገኘውን ዕድል ሁሉ ባይሆንም የተወሰነውን እንኳ የገጠር ነዋሪዎቹ ያገኙ ይሆን? ይህ ካልሆነ መፈክሮችን ብቻ እያሰሙ በየውድድሩ ከዓመት ዓመት መፈክር እያሰሙ ብቻ መዝለቁ እርባና አይኖረውም፡፡ አብዛኞቹ የኢትዮጵያ ሴቶች የአንድ ወይም የሌላ ዓይነት ጥቃት ሰለባዎች ስለመሆናቸው ብቻም ሳይሆን ላልተገባ የባህል ወረራ እየተዳረጉ ስለመሆናቸውና እንዲህ ባለው ዝግጅትም መጤው ባህል እየተበረታታ ስለመሆኑ አዘጋጆቹ አስበውት ያውቁ ይሆን?  

ይኼን እንድል ያስገደደኝ በጥር ወር ‹‹የፍቅረኛሞች ቀን›› የተባለውን ዕለት ከፈረንጆቹ በኮረጁት መሠረት በተለያዩ አካባቢዎች ቀይ ልብስ በመልበስ፣ አበባ በመሰጣጠትና በመገባበዝ ያችን ዕለት ብቻ ፍቅር በፍቅር ሁኑ የተባለ ይመስል ያለ ዕድሜ ገደብ አዲስ አበቤዎች ሲያከብሩት ማየቴ ነው፡፡ ታሪክን፣ ባህልንና ወቅታዊ ሁኔታን ለምሳሌ ዓድዋን ማንሳት ይቻላል፤ መቼ እንደሚከበር፣ ለምን እንደሚከበር ዕውቀቱና መረጃው የሌላቸው በርካታ ሴቶች አሉ እኮ፡፡ ይልቁንም እንዲህ ያለው ነገር ላይ ሐሳቡ ተነስቶ እንድንወያይ ሲጋበዙ የሚጠየፉ ስላሉ ሊሠራበት የሚገባ ነው፡፡ በተገላቢጦሽ ስለውበት መጠበቂያ ዕቃዎች፣ ስለመዝናኛ ሥፍራዎችና ሌላም በሕይወት ውስጥ ምንም ለውጥ በማያመጣ አልባሌ ነገር ውስጥ በመሳተፍ ጊዜያቸውን ማሳለፍን የሚመርጡ በርካቶች ናቸውና ለቁም ነገር ቦታ ይኑረን፡፡ 

ይህ ሲባል ግን አንዳንዴ የሆነ አጋጣሚን ለበጎ ዓላማ የሚያውሉ መልካም ሴቶች እንዳሉም ማሰብ ይገባል፡፡ የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ለዚህ የሚጠቀሱ ሲሆኑ፣ እንደነሱ በዩኒቨርስቲው የሚማሩ ነገር ግን ለትምህርታቸው የሚረዳቸውን ፎቶ ኮፒ ማስነሻ የሚሆን፣ ያውም ደግሞ ሴቶች በወር አንዴ የፆታ ግዴታ ነውና ለወር አበባ የንፅህና መጠበቂያ (ሞዴስ) መግዣ የሌላቸው በርካታ ተማሪዎችን ለመርዳት ሲሉ በታላቁ ሩጫ ዕለት፣ የቀይ ጽጌረዳ አበባ በመሸጥ ገንዘቡን ችግሩ ለከፋባቸው እህቶቻችን ሲያሰባስቡ ማየት የሚያስመሰግናቸው ታላቅ ተግባር  ነው፡፡

ታዲያ ታላቁ ሩጫ በግምት ከ5,000 እስከ 12,000 የምንደርስ ሴት ተወዳዳሪዎችን ያሰባሰበን በዕውቀታችን፣ በገንዘባችንና በሐሳባችን በገጠሪቱ ኢትዮጵያ የሚገኙ ሴት ሕናቶቻችንና እህቶችን በምንችለው እንድንረዳ ከሆነ፣ አዘጋጁ አካል ዋናውን ድርሻ ወስዶ አለባቸው የሚባለውን ችግር እንድንፈታ የበለጠ እንዲያስተባብረን፣ በወሊድ ወቅት የሚከሰት የሴቶችን ከፍተኛ የደም መፍሰስ ችግር ለመከላከልና፣ ለዚህ የሚረዳውን የደም ልገሳ ዕድል ለማመቻቸት ቢሠሩ ትልቅ አስተዋፅኦ ያደርጋሉ፡፡  በተጨማሪም አዲስ አበባ ውስጥ ብቻ ሳይሆን፣ የታላቁ ሩጫ የሴቶች ውድድርን በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በማስፋፋት ትምህርት ዋናውና ቁልፍ መሣሪያ ስለሆነ፣ ለሴት ልጅ ትምህርት እንዲዳረስ ማድረግ ይገባል በማለት ሐሳቤን እደመድማለሁ፡፡

(ሠብለወንጌል፣ ከቀበና)

***

ገዢ ፓርቲና ተቃዋሚ ፓርቲዎች አፍራሽ ቃላቶች ናቸው

ሚዲያዎች በተለምዶ በምንጠቀምባቸው ቃላቶች ላይ ጥንቃቄ ብናደርግ ይመረጣል፡፡ በተለይም በእነዚህ ሁለት ቃላቶች ማለትም ገዢና ተቃዋሚ ፓርቲ የሚሉት ላይ ብንጠነቀቅ ይበጃል፡፡ ገዢ ፓርቲ የሚለው አባባል ምናልባት በሕገ መንግሥትም ትርጉም ተሰጥቶት ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህ አባባል ትክክል አይመስለኝም፡፡ ፈላጭ ቆራጭ፣ አምባገነን የሚል አንድምታ አለው፡፡ በእኔ አመለካከት ኢሕአዴግ በአገሪቱ ደንብና ሕግ መሠረት በሕዝብ የተመረጠ ሕዝባዊ ወይም ዴሞክራቲክ ፓርቲ እንጂ ንጉሣዊ ወይም ወታደራዊ መንግሥት ስላልሆነ፣ ይህ ቃል አይመጥነውም ባይ ነኝ፡፡ በመሠረታዊነት ዕቃ ይገዛል እንጂ ሰው አይገዛም፡፡ መንግሥት ሕዝብን ያስተዳድራል እንጂ አይገዛም፡፡ ስለዚህ አገር እንዲመራ ወይም እንዲያስተዳድር የተመረጠው ፓርቲ፣ ገዢ ፓርቲ ከመባል መሪ ፓርቲ ቢባል የተሻለ ይመስለኛል፡፡

ሁለተኛው ተቃዋሚ ፓርቲ የሚለው አባባል በአገራችን ያሉትን ተፎካካሪ ፓርቲዎችን ገጽታ ያንፀባርቃል፡፡ ልናስተውለው የሚገባን፣ ኢሕአዴግ ሥልጣን ከመያዙ በፊት የወታደራዊ መንግሥት ተቃዋሚ ነበረ፡፡ የሆነበትም ዋነኛው ምክንያት አገር ሲመራ የነበረው ወታደራዊ መንግሥት በተፈለገው አቅጣጫ አገሪቱን እየመራ እንዳልሆነ ስለተረዳ፣ በድርጊቱ ተቃውመው የተቋቋሙ አገር ወዳድ ቡድኖች ጥምረት የመሠረቱት ነበረ፡፡ እነዚህ አገር ወዳዶች ይህ ነው የማይባል መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡

በዚህ ዘመንም በአገሪቱ ያሉትን ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከዓላማቸው ጥልቀትና ስፋት ልዩነት በቀር የሕዝብ ጉዳይ ተቆርቋሪዎች መሆናቸው ሊዘነጋ አይገባም፡፡ እነዚህ ተቃዋሚ የተባሉ ፓርቲዎች ከዓላማቸውና ከፖለቲካ አመለካከታቸው ልዩነት በቀር መሠረታዊ አወቃቀራቸው በዋናነት ለሕዝብ ጥቅም ትግል ለማካሄድ የተቋቋሙ ናቸው፡፡ አብዛኞቹ ደግሞ ለዚህ ተቆርቋሪነታቸው ይህ ነው የማይባል መስዋዕትነት የከፈሉና አሁንም እየከፈሉ እንዳሉ ብዙዎቻችን የምንገነዘበው ጉዳይ ይመስለኛል፡፡

እንደዚህ ላሉ ተፎካካሪ ወይም ተቆርቋሪ ፓርቲዎች አገር አቀፍ እውቅናና የሕግ ከለላ ሊደረግላቸው ይገባል፡፡ ይህ ብቻ አይበቃም፡፡ ለተመረጠው መሪ ፓርቲ ፍሬያማነት አስተዋፅኦ ስለሚኖራቸውና የራሳቸውን ፓርቲ ደጋፊዎች ሐሳብ ብቻ ይዘው መጓጓዝ በአንድ ዓይን እንደማየት ስለሆነ ቢያንስ በተወሰነ የጊዜ ገደብ ከመሪ ፓርቲ ጋር በመገናኘት ፓርቲውን የመተቸትና ሐሳብ የማጋራት ዕድል ቢሰጣቸው ለአገር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ እንዲያውም ሰሞኑን በአገራችን ለተከሰተው ከፍተኛ ቀውስ ዋነኛው ምክንያት ለነዚህ ተቆርቋሪ ዜጎች ልብ ትርታ ጆሮ አለመስጠት ነው ብል አልተሳሳትኩም፡፡

ስለሆነም በአጠቃላይ ገዢና ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚሉ ቃላቶች የአፍራሽነት አንድምታ ስላላቸው የተሻለ ስያሜ ቢሰጣቸው ይመረጣል፡፡

(ዶ/ር ዱቤ ጡሴ፤ ከአዲስ አበባ)

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ከሚያከብሯቸው አንድ የቀድሞ ጉምቱ ፖለቲከኛ ስልክ ተደውሎላቸው እያወሩ ነው]

አንዳንድ ነገሮች ቢያሳስቡኝ ነው ቀጠሮ ሳልይዝ ላወራህ የፈለኩት ክቡር...

የትግራይ ክልል የሽግግር አስተዳደር ምሥረታና የሰላም ስምምነቱ ሒደት

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ የሽግግር መንግሥት ለመመሥረት ደፋ ቀና እየተባለ...

ጥራዝ ነጠቅነት!

ከሜክሲኮ ወደ ጀሞ እየሄድን ነው፡፡ የተሳፈርንበት አሮጌ ሚኒባስ ታክሲ...