Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

‹­‹ሙስናን መታገስ የማይችል አሠራር ነው ያሰፈነው››

ወ/ሮ ሐና ጥላሁን፣ የእናት ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ

በቅርቡ የእናት ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ በሰብሳቢነት እንዲመሩት ሁለተኛዋን ሴት የቦርድ ሊቀመንበር አድርጎ መርጧል፡፡ የመጀመርያዋም ሆኑ ሁለተኛዋ የባንክ ቦርድ ሊቀመንበር የተሰየሙት በዚሁ እናት ባንክ ነው፡፡ በአገሪቱ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ በዚህ የኃላፊነት ደረጃ ያገለገለ ሴት አልነበረም፡፡ የመጀመርያዋን የቦርድ ሊቀመንበር ተከትለው ሁለተኛዋ የባንኩ ቦርድ ሊቀመንበር መሆን የቻሉት ደግሞ ወ/ሮ ሐና ጥላሁን ናቸው፡፡ ከዚህ ኃላፊነታቸው ቀደም ብሎ ላለፉት ስድስት ዓመታት የእናት ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ ውልደታቸውና ዕድገታቸው ነቀምቴ ነው፡፡ የመጀመርያ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውንም የተከታተሉት በትውልድ ሥፍራቸው ሲሆን፣ የመጀመርያ ዲግሪያቸውን ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በአካውንቲንግ አግኝተዋል፡፡ ከዩኒቨርሲቲ ከወጡ በኋላ ለሁለት ወራት ያህል በከተማ ልማት ሚኒስቴር ሠርተዋል፡፡ በዕርዳታ ማስተባበሪያ ኮሚሽን በስዊድን መንግሥት በሚደገፈው ዲፓርትመንት ውስጥ ሠርተዋል፡፡ ከዚያም በላሊበላ ኮንስትራክሽን፣  ላሊበላ ኮንስትራክሽን ከቻይና ኩባንያ ጋር ተዋህዶ ኖሪላ በሚል ስያሜ ይጠራ በነበረው ኩባንያ ውስጥም በተለያዩ የኃላፊነት መደቦች ተመድበው ሠርተዋል፡፡ ባለትዳርና የሦስት ልጆች እናት የሆኑት ወ/ሮ ሐና በአሁኑ ጊዜ የቤዛ ልኤል የኮንስትራክሽን መሣሪያዎች ማምረቻ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና የሔብሮን ሪዞርት ማኔጂንግ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ ኤችኤም ኢንጂነሪንግ የተባለውን ኩባንያም ከባለቤታቸው ጋር በመመሥረት ወደ ሥራ ማስገባታቸውም የሚጠቀስላቸው ነው፡፡ ወ/ሮ ሐና ራሳቸውን ሲገልጹ ‹‹አርዓያዬ እናቴ ነበረች፤›› ይላሉ፡፡ ‹‹ጓደኛዬም ነበረች፡፡ አብሬያትም ተምሬያለሁ›› በማለት ዛሬ ላሉበት ደረጃ የእናታቸው አሻራ ጉልህ ሥፍራ የሚሰጠው ስለመሆኑ ደጋግመው ይገልጻሉ፡፡ በአዲሱ የኃላፊነት ሥራቸው፣ ስለሕይወት ጉዟቸው፣ ስለሴቶችና እንዲሁም ስለባንክ ኢንዱስትሪው፣ እንዲሁም እናት ባንክ ኢንዱስትሪውን ሲቀላቀል ይዞት በተነሳው ዓላማና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ዳዊት ታዬ ወ/ሮ ሐናን አነጋግሯቸዋል፡፡

ሪፖርተር፡- የቢዝነስ ሥራ ላይ እንዴት ነዎት?

ወ/ሮ ሐና፡- በጣም የሚገርመው ነገር ነጋዴ ነኝ ለማለት ጊዜ ወስዶብኛል፡፡

ሪፖርተር፡- ለምን?

ወ/ሮ ሐና፡-  አሁንም ድረስ ገንዘቤ ጊዜ ነው ብዬ አላስብም፡፡ አንድ ነገር አለኝ ብዬ ነው የምሠራው፡፡

ሪፖርተር፡- የቢዝነስ ፍልስፍናዎ ምንድነው?

ወ/ሮ ሐና፡-  ሥራዎችን ቀለል ማድረግ ነው፡፡ ሥራዎች ትክክለኛ ጥቅም እንዲያስገኙ ማድረግና ሰዎችን ማሠራት መቻል ነው፡፡ ከሙስና የፀዳ አገልግሎት መስጠት ትልቁ ፍልስፍናዬ ነው፡፡ ይህንን በሁሉም ነገር የምተገብረው ነው፡፡ ወደ እናት ባንክም ስገባ ይህንኑ ለመተግበር ነው፡፡ በማንኛውም አቅጣጫ ሙስና ካልጠፋ ማደግ እንደማይቻል የጠነከረ እምነት ስላለኝ፣ ከሙስና የነፃ ሥራ እንዲተገበር አደርጋለሁ፡፡ አንዳንድ ኩባንያዎች በአንድ ጊዜ ሊያድጉ ይችላሉ፡፡ ግን አይቀጥሉም፡፡ ምክንያቱም መሠረታቸው የተበላሸ ነው፡፡ በሃይማኖትም ኢቫንጀሊካን ነኝ፡፡ ይህም የሕይወት መርሔ ነው ብዬ ነው የምወስደው፡፡

ሪፖርተር፡- ከቅጥር ሥራ ወደ ራስዎ ቢዝነስ እንዴት ገቡ?

ወ/ሮ ሐና፡- ከትምህርት ቤት ስወጣ ወጣት ነበርኩ፡፡ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ነው ማሰብ የጀመርኩት፡፡ ከመጀመርያው ተቀጥሮ መሥራትን ወይም መታዘዝን መጥላት ሳይሆን፣ የምፈልገውን በመሥራት በምፈልገው ዓይነት መምራት መፈለግ ነው፡፡ መንግሥታዊ ባልሆነ ድርጅት በምሠራት ወቅት ጥሩ ነበር፡፡ በማኔጅመንትና በነፃነት ደረጃ ጥሩ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ ከገባ በኋላ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሲደክሙ፣ በመከላከያ ሥር ያለው ኮንስትራክሽን ኩባንያ ውስጥ ገባሁ፡፡ ላሊበላ ኮንስትራሽን ይባል ነበር፡፡ በኋላ ኖሪላ ተባለ፡፡ እዚያ እየሠራሁ ኤምኤች ኢንጂነሪንግን ከባለቤቴ ጋር መሠረትን፡፡ በወቅቱ ይህንን ድርጅት የመሠረትነው ቤታችን ውስጥ ነው፡፡ ባለቤቴ ኢንጂነር ነው፡፡ እኔ አካውንታት ብሆንም የማኔጅመንት ክህሎቱ አለኝ፡፡ ኤችኤም ኢንጂነሪንግን በዚህ መንገድ መሥርተን አሁን እያደገ እያደገ መጥቶ ጥሩ ሥራ ይሠራል፡፡

ሪፖርተር፡-  የእርስዎና የእናት ባንክ ግንኙነት እንዴት ተፈጠረ? እንዴት እናት ባንክን ተቀላቅለው ወደዚህ ኃላፊነት ደረጃ ላይ ደረሱ?

ወ/ሮ ሐና፡- እናት ባንክን ለማቋቋም ፕሮሞተሮቹ ለባንኩ ምሥረታ ያግዙናል ያሉዋቸውን በቡድን እያደረጉ ሰብስበው እራት እየጋበዙ ያናግሩ ነበር፡፡ ከባንኩ አደራጆች መካከል ወ/ሮ መዓዛና ወ/ሮ አመለ ትምህርት ቤት አብረን ስለነበርን እነሱ ጋብዘውኝ ተገኘሁ፡፡ ወዲያው ዓላማውን ደግፌ ተቀላቀልኩ፡፡ የባንኩን አክሲዮኖች እንደምገዛ ቃል ገባሁ፡፡ በዚሁ ጉዳይ ስብሰባ ሲጠሩኝም እሳተፍ ነበር፡፡

ሪፖርተር፡- እናት ባንክን ከተቀላቀሉ በኋላ እስካሁን ያለውን ጉዞ እንዴት ይገልጹታል?

ወ/ሮ ሐና፡- ፈታኝ ነው፡፡ 

ሪፖርተር፡- እንዴት?

ወ/ሮ ሐና፡- አንደኛ የፋይናንስ ኢንዱስትሪው አሁን ባለው ሁኔታ የራሱ የሆነ ተግዳሮቶች አሉት፡፡ ሁለተኛ እናት ባንክን ሴቶች ሲመሠርቱት ዋናው ዓላማ ሴቶችን በኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ማጎልበትና ማብቃት ነው፡፡ የፋይናንስ ሥራውን እየሠራ ሴቶቹን ማብቃት ነው፡፡ በኢኮኖሚ ብቁ ካልሆኑ የሚፈለገው ደረጃ ላይ መድረስ አይቻልም፡፡ ግን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የፋይናንሻል ዴስትኔሽን መመርያና ሴቶችን ለማሳደግ የሚደረገው አካሄድ ላይ ሕጉ አይጣጣምም፡፡ መመርያው ስለማይጣጣም ይህንን እያስታረቁ መሄዱ ይፈትናል፡፡ ኢንዱስትሪውም በራሱ ሌላ ተግዳሮቶች ያሉበት ነው፡፡ ሁለተኛ ምሥረታ ላይ እናት ባንክን ማደራጀትና ማዋቀሩ ራሱ ቀላል ሥራ አልነበረም፡፡ ብዙ ፈተና ነበረው፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ወደ ሥራ ተገብቶ ውጤታማ መሆኑ ግን ደስ ያሰኛል፡፡ እኔም የዚህ አካል ነኝ እላለሁ፡፡ 

ሪፖርተር፡- ባለፉት ስድስት ዓመታት የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ አባል ስለነበሩ የእናት ባንክን አጠቃላይ እንቅስቃሴን በደንብ ያውቃሉ፡፡ ስትነሱ ሴቶችን ኢኮኖሚያዊ አቅማቸውን ማጎልበትና ማብቃት የሚለው ዋነኛ አጀንዳ ነበር፡፡ ከዚህ አንፃር ምን ያህል ተራምዳችኋል? ዋነኛ ዓላማችሁ ደግሞ ለሴቶች ብድር እንዲመቻች ማድረግ ነበር፡፡ ሆኖም አሁንም የባንካችሁ የብድር መረጃ ያሳያል እንደሚባለው ከጠቅላላ ከተበዳሪዎቻችሁ ውስጥ ከ70 እስከ 80 በመቶ ወንዶች የሚመሩት ኩባንያዎች ናቸው፡፡ ወይም ወንዶች ናቸው፡፡ ይህ ለምን ሆነ? ሴት ተበዳሪዎችን ለማሳደግ የያዛችሁት ዕቅድ እንዴት ተሳካ ይባላል?

ወ/ሮ ሐና፡- ሞክረናል፡፡ ከኢትዮጵያ አንፃር ስታየው የእናት ባንክ አስተዋጽኦ ‹‹ነጥብ›› ናት፡፡ በፋይናንስ ኢንዱስትሪው ውስጥም ከነጥብ ትንሽ ከፍ ቢል ነው፡፡ የሴት ተበዳሪዎችን ቁጥር ለማሳደግ ምንድነው መደረግ ያለበት? ሴቶቹ የማይበደሩት ኢኮኖሚያዊ አቅም ስለሌላቸው ነው፡፡ ለብድር ማስያዣ የሚሆን ቋሚ ንብረት ስለሌላቸው ነው፡፡ ስለዚህ ትልቁ መፍትሔ ይህንን ክፍተት መድፈን ነው፡፡ ሴቶቹ ያለ ማስያዣ ብድር ማግኘት እንዲችሉ ማድረግ ይገባል፡፡ መመርያው ግን ይህንን አይፈቅድም፡፡ ስለዚህ ዋስትና የሚሰጡንን መፈለግ ነው፡፡ ይህንን ክፍተት ለመድፈን የሚያስችሉ የተለያዩ ጥረቶች አድርገናል፡፡ ለምሳሌ አንዱ የእናት ባንክ ባለአክሲዮኖች ጠቅላላ ጉባዔ በወሰነው መሠረት ከዓመታዊ የባንኩ ትርፍ ውስጥ አምስት በመቶ ለሴቶች ብድር ማስያዣ እንዲውል ፈቅዷል፡፡ ያንንም ፈቅዶና ዋስትና የሚሆነው ገንዘብ እዚህ ቁጭ ብሎ ግን፣ መመርያው የሚያስቀመጣቸው መሥፈርቶች አሉ፡፡ ማስያዣው ቢኖርም ብድሩን ዝም ብለህ አትሰጥም፡፡ ምክንያቱም ገንዘቡ የባለአክሲዮኖች ነው፡፡ መመርያው ያስቀመጣቸውን መሥፈርቶች ማሟላት ደግሞ ሌላው ችግር ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ለዋስትና የሚሆነው ገንዘቡ ቁጭ ብሎ ሴቶቹ ሳይበደሩት ይቀራሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ሴቶች ለሚበደሩት ገንዘብ እንደ ማስያዣ የሚሆን ፈንድ ለማሰባሰብ ቀዳማዊት እመቤት ሮማን ተስፋዬና ሌሎች ሰዎች የተወሰነ ገንዘብ አዋጥተው ነበር፡፡ እንዲህ ባለው መንገድ ፈንድ በማሰባሰብ ሴት ተበዳሪዎችን ለማገዝ የጀመራችሁት እንቅስቃሴ ምን ያህል እገዛ አደረገ?

ወ/ሮ ሐና፡- እሱ እንግዲህ ትንሽ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ እሱን ነው የምልህ፣ የዋስትና ፈንዱ ተገኘ፡፡ በዚህ ፈንድ ቀዳማዊት እመቤትና ሌሎች ሰዎች አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ይህ ብዙ አይደለም ትንሽ ነው፡፡ ባለአክሲዮኖችም ከትርፋቸው ለዚህ ዓላማ እንዲውል የፈቀዱት አምስት በመቶ አለ፡፡ ግን ብዙ አይደለም፡፡ ሴቶቹን እናበቃለን ሲባል ከወደቀ ሌብል ከፍ ብለው መምጣት አለባቸው፡፡ ይኼኛው ግን ትንሽ ነው ከፍ የሚያደርጋቸው፣ የሚያንቀሳቅሳቸው፡፡ ቢዝነሱም ራሱ አሁን ባለው ሁኔታ የራሱ ተግዳሮቶች አሉት፡፡ ቢዝነሱ ውስጥ ተወዳዳሪ ሆኖ ለመቀጠል የራሱ ችግር አለው፡፡ እንዲህም ሆኖ ሴት ተበዳሪዎች ወደ ቢዝነሱ ከመግባታቸው በፊት ብዙ እገዛ ይደረግላቸዋል፡፡ ሥልጠና ይሰጣቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ሆኖ ግን የክፍተቱን ስፋት እንድታየው ያደርገሃል፡፡

ሪፖርተር፡- የምታስቡትን ለማሳካት ከዚህ የተሻለ ሐሳብ ይኖረናል ትላላችሁ? አሁን ደግሞ እርስዎ የቦርዱ ሰብሳቢ ነዎት፡፡ እንደ አንድ የሥራ መሪ ሴቶችን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ ለማድረግ አዲስ ነገር ይዤ እመጣለሁ የሚሉት ነገር አለ?

ወ/ሮ ሐና፡- አሁን ሴቶችን ለማስቻል ማድረግ የሚቻለው በፋይናንስ ብቻ አይደለም መሠራት ያለበት፡፡ እርግጥ ነው ኢኮኖሚያዊ አቅም እንዲኖራቸው ማድረጉ ብዙ እገዛ አለው፡፡ ግን የሰዎችን አስተሳሰብ መለወጥ ይፈልጋል፡፡ የሰዎች አስተሳሰብ ላይ መሥራት የግድ ነው፡፡ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን ባደጉትም አገሮች ላይ ፈተና አለ፡፡ ሴት ሲኮን ለማየት ከወንዶቹ በእጥፍ ነው የሚሠራው፡፡ ቢዝነሱም ውስጥ እንደዚያው ነው፡፡ ኅብረተሰቡ ሴቶችን እንዲያምንና የሴቶችን ቢዝነስ እንዲያበረታታ ለማድረግ ከቤተሰብና ከጓዳ ጀምሮ በሁሉም ቦታ አስተሳሰብ ላይ በጣም መሠራት አለበት፡፡

ሪፖርተር፡- ይኼ የአስተሳሰብ ለውጥ እንዴት ይመጣል?

ወ/ሮ ሐና፡-  እየመጣ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- የአስተሳሰብ ለውጡ እየመጣ ከሆነ እንደ ምሳሌ ልንጠቅሳቸው የሚችሉ ነገሮች አሉ?

ወ/ሮ ሐና፡- የሰዎች አስተሳሰብ መቀየር አለበት ሲባል አንድ እንደ እናንተ ያሉ የሚዲያ ተቋማትንም ይመለከታል፡፡ ብዙ ጊዜ ሚዲያው የሚያወራው፣ ጋዜጦች ላይ የሚጻፈው፣ ሪፖርት የሚደረገው ሁሉ ሴቶች ላይ የደረሰውን በደል ነው፡፡ ይህ አዲሱን ትውልድ አያበረታታውም፡፡ እንዲሰለች ነው የሚያድርገው፡፡ እንደሚባለውም ሰይጣን ደግሞ ሰዎችን እንደ እስረኛ የሚያደርግበት አንዱ የፍርኃት መንገድ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ዘገባ ፍርኃት ነው የሚያበዛባቸው፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ነገር መለወጥ አለበት፡፡ ውጤታማ የሆኑ የተሳካላቸው ብዙ ሴቶች አሉ፡፡ በሳምንት ወይም በሁለት ሳምንት አንዴ ጋዜጦች ይህንን የስኬታማ ሴቶች ዘገባ ማውጣት አለባቸው፡፡ ለምሳሌ ማስታወቂያዎቻችንም እንዲህ ባሉ ነገሮች መቃኘት አለባቸው፡፡ እስካሁን በቴሌቪዥን የምናየው ማስታወቂያ እናት ልጇን አለባብሳ ለአባት ሰጥታ፣ አባት ወደ ትምህርት ቤት ሲሄድ ነው፡፡ ሴቷ ልብስ ስታጥብ ነው የሚያሳየው፡፡ ሰሞኑን አንድ መድረክ ላይ አንዲት ሴት እንዲህ ዓይነት ማስታወቂያን በተመለከተ ስትናገር፣ ቢያንስ ሳሙናውን ስትገዛ እንኳን ብታሳዩ ምናለ ነበር ያለችው፡፡ ስለዚህ እነዚህ ነገሮች ናቸው አሁን ያሉትን ወጣቶች የሚለውጡልን፡፡ በእርግጥ ‹‹ኖ›› ማለትን ማስተማር መቻል አለብን፣ ይኼ አይሆንም መባል አለበት፡፡ የሰዎች አስተሳሰብ መለወጥ አለበት የምንለው ለዚህ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ይህንን ለማድረግ ግን እንደ እናንተ ያሉ ወጥተው ሊታዩ የሚችሉ ሴቶች ኃላፊነት ይኖርባቸዋል፡፡ ይህንን ኃላፊነት ምን ያህል እየተወጣችሁት ነው? በሌላ በኩል ደግሞ እንዲህ ላለው ተግባር እናት ባንክ የተመቸ ነውና ይህንን ኃላፊነት ለመወጣት ምን ታደርጋላችሁ? በተለይ እርስዎ እንደ አመራር በዚህ ረገድ ምን አመጣለሁ ይላሉ?

ወ/ሮ ሐና፡- እንሠራለን ብዬ አስባለሁ፡፡ የበለጠ እየሠራን ሁኔታው ለሴቶች ምቹ እንዲሆን እንጥራለን፡፡ ስብሰባዎቻችን ላይ የምንነጋገራቸው ነገሮች አሉ፡፡ ግን የምንፈልገውን ያህል አልሄድንም፡፡ ጉዳዩ ብዙ ስለሆነ የምንፈልገውን ያህል አልሄድንም፡፡ እንዲያውም አንዳንዱ ላይ የሚያስነደግጥ ነገር ይገጥመናል፡፡ ለምሳሌ አዲሱን ትውልድ እንውሰድ፡፡ የትውልዱ ሴቶች ይማራሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲ ይገባሉ፡፡ ይመረቃሉ፡፡ ከዚያም ያገባሉ፡፡ ሲያገቡ ወደ ኋላ ይመለሳሉ፡፡ የሠራተኛና የመሳሰሉት ችግሮች ስላሉ የቤት ውስጥ ኃላፊነቱን ይወስዳሉ፡፡ የወጣት ትውልዱ ስታትስቲክስ ቢሠራ፣ ብዙ ሴቶች ልጆቻቸውን ለማሳደግ ቤት ይውላሉ፡፡ ልጆቻቸው ካደጉ በኋላ ወደ ሥራ ለመመለስ የሚፈልጉ ብዙ ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ የሥራ ጥንካሬያቸውን ይገላል፡፡ እንዲውም በዚህ ጉዳይ ላይ አንድ ዓውደ ጥናት አዘጋጅተን የራሳችንን ሠራተኞች አሰባስበን ተነጋግረናል፡፡ እዚህ ላይ መሠራት አለበት የሚል ጉዳይ አንስተን ሴቶችን ሥራ ላይ ለማቆየት የሚያስችል ነገር መኖር ስላለበት፣ ሁኔታው አመቺ እንዲሆን ለማድረግ የልጆች ማቆያ መሥሪያ ቤቶች ውስጥ እንዲኖር አድርገናል፡፡ እንዲያውም ከዚያ በኋላ የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች የሕፃናት ማቆያ እንዲያዘጋጁ ሕግ ወጣ፡፡ ይህንን የልጆች ማቆያ ነገር ማፋጠን አለብን፡፡ ወጣቱ ትውልድ ወደ ኋላ እንዳይመለስ ይህ ነገር ወሳኝ ነው፡፡ ይህን ማዘጋጀት ይቻላል፡፡ መወሰን አለባቸው፡፡ እዚህ ላይ አንድ የማስታውሰውን አንድ ጊዜ በሲኤንኤን የቀረበች አንድ ሴት ጉዳይ ላንሳልህ፡፡ እ.ኤ.አ. 2014 ይመስለኛል ህሊና ትባላለች፡፡ የአንድ የትልቅ ኩባንያ ሥራ አስፈጻሚ ነች፡፡ ይቺ ሴት ዘጠኝ ልጅ ወልዳ አሳድጋለች፡፡ ስለዚህ እየሠሩ ማሳደግ ይቻላል፡፡ ሙያቸውን እያሳደጉ መሥራት ይችላሉ፡፡ አሁን ነገሮች እየተለወጡ ሲመጡ አዲስ የሚመጡ ነገሮች አሉ፡፡ አዲሱ ትውልድ ላይ እየታየ ያለ ችግር ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአሁኑ ወቅት ሴቶች መሥራት ይችላሉ የሚለውን ለማሳየት እናት ባንክን ለመመሥረት ሴቶች ያሳዩት ርብርብ ይጠቀሳል፡፡ የእናንተን ስብስብ እንደ ምሳሌ የሚወስዱ አሉ፡፡ ይህ ስብስብ ውጤታማ ሴቶች ያሉበት ነው ከተባለ እናንተ መሰሎችን ለማፍራት ምን ታደርጋላችሁ? ምክንያቱም በሁሉም ቦታ እየተመለከትን ያለነው አንድ ችግር ጠንካራ ባለሙያዎችን ወይም ውጤታማ ሰዎችን ለመተካት የሚያስችሉ አሠራሮች አይታዩም፡፡ አሁን በባንካችሁ ውስጥ ይህ ክፍተት ያለ ይመስላል፡፡   ጠንካራ ሴቶች የመፍጠርና ተተኪ የማፍራቱ ጉዳይ ላይ የሚታየው ክፍተት አያሳስብም?

ወ/ሮ ሐና፡-  እዚህ ላይ ሰፊ ክፍተት አለ ለማለት ይቸግራል፡፡ በተለይ በጽንሰ ሐሳብ ደረጃ በጣም ብዙ አሉ፡፡ ያስደንቅሃል፡፡ እኔ ትልቅም ብሆን ወጣቶች፣ ከእኔ በታች የሆኑ ከእኔም በላይ የሆኑ በተለያዩ ጉዳዮች የማነጋግራቸው ጓደኞች አሉኝ፡፡ አንዳንዶቹን ስታይ በጣም ደፋር ናቸው፡፡ ጠንካራ ሆነው ሊወጡ የሚችሉ ብዙ አሉ፡፡ ላይ ያለው የሸፈነው ነገር ቢኖሩምና ባይታዩም ግን አሉ፡፡

ሪፖርተር፡- ውጤታማ ሴቶችን ከወጣቶች ጋር ለማቀራረብ፣ ባንካችሁ ውስጥ ሴቶችን ለማብቃት፣ ወይም ደግሞ እንደ እናት ባንክ ባሉ ተቋማት እንዲሰባሰቡ ለማድረግ በተለየ የምትሠሩት ነገር አለ?

ወ/ሮ ሐና፡- በዚህ አቅጣጫ በደንብ እየተሠራ ነው፡፡ እናት ባንክ ከሌሎች ባንኮች  በተለየ የሴቶችን ጉዳይ የሚከታተል ራሱን የቻለ ክፍል በዳይሬክተር ደረጃ አለው፡፡ ስለዚህ በዚህ ክፍል ብዙ ሥራዎች እየተሠሩ ነው፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ የአምስት ኪሎ ሜትር ሩጫ ነበር፡፡ እዚህ ላይ እናት ባንክን ብቻ ማስተዋወቅ ብቻ ሳይሆን፣ ሴቶቹ ላይ ለመሥራት ነው፡፡ ስታስበው እኮ እናት ባንክን መመሥረቱ በራሱ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ሁለተኛ በዓለም ላይ ‹‹ፊርለስ ገርልስ›› የሚባል አለ፡፡ ይኼ እንቅስቃሴ በዋናነት አሜሪካ፣ እንግሊዝና የመሳሰሉት አገሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚሠራ ነው፡፡ በዚህ እንቅስቃሴ ሴት ዳይሬክተሮች የሌሉባቸውን 700 ኩባንያዎች በዝርዝር በማውጣትና በማጋለጥ ዘመቻ ተደርጓል፡፡ ይህንን ካላስተካከሉ በሚል 500 ኩባንያዎች ፒቲሽን ተፈራረሙ፡፡ ይህ የሆነው እ.ኤ.አ. በ2017 ነው፡፡ አሁን በ2018 ከእነዚህ ውስጥ 150 ያህሉ ሴት ዳይሬክተሮች አስገብተዋል፡፡ ሌሎቹም ቃል ገብተዋል፡፡ የእንዲህ ዓይነት ሒደቶች መጎልበት ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ እኛም አገር እንዲህ መደረግ አለበት፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ነገር መበረታታቱና ሴቶቹ ወደ አመራር እየመጡ ሲሄዱና ላይ ሲደርሱ፣ አንደኛ ከታች ያሉት አርዓያ ያገኛሉ፡፡ ሁለተኛ ሴቶችን ማብቃት የሚለው በውሳኔ ሰጪነት ላይ ሴቶች እንዲታዩ ማድረግ ነው፡፡ ይኼ በኮታ መሆን የለበትም የሚሉ አሉ፡፡ ልክ ነው በኮታ መሆን የለበትም፡፡ ግን ብቃት ያላቸው ሴቶች አሉ፡፡ ቅድም እንዳልኩህ ሴቶቹ ራሳቸውን ለማሳየት ሁለት እጥፍ መሥራት አለባቸው፡፡ ምክንያቱም ጫና ነው ያለብን፡፡ ስለዚህ ይህንን መዝለል አቃታቸው እንጂ ብቁ የሆኑ ሴቶች የሉም ማለት አይደለም፡፡ በተመሳሳይ እኛም አገር እንዲህ መሆን አለበት፡፡  

ሪፖርተር፡- እንዲህ ባሉ ኩባንያዎች በአመራር ደረጃ ላይ ያሉ ሴቶች ውጤታቸው እንዴት ይታያል?

ወ/ሮ ሐና፡- ስታትስቲክሱ የሚነግረን ነገር አለ፡፡ እጅግ ውጤታማ ሆነዋል፡፡ በአመራር ሰጪነት ላይ ያሉ ሴቶች እያደጉ ነው፡፡ ውጤታቸውም የተሻለ ሆኖ እየተገኘ ነው፡፡ ይኼ እውነት ነው፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስም ብታየው አንድ ሰው አንድ ቀን ሲሰብክ፣ ባሎች ሚስቶቻቸውን ቢሰሙ ክርስቶስ አይሰቀልም ነበር ብሏል፡፡ የጲላጦስ ሚስት ይኼ ሰው ንፁህ ነው ብላው ነበር፡፡ እናንተም ሚስቶቻችሁን ብትሰሙ ብዙ ለውጥ ታመጣላችሁ፡፡ ይኼ እውነት ነው፡፡ ለምሳሌ እኔ ማነች አርዓያሽ ብትለኝ እናቴ ናት፡፡ ምንም ነገር ፊቷ እንዲቆም አትፈልግም፡፡ ኃይለኛ ነች ማለቴ አይደለም፡፡ ኃይለኛ አይደለችም፡፡ በጣም ብልህ ናት፡፡ ግን ማድረግ የማልችለው ነገር የለም ብላ አታስብም፡፡ እኛንም እንደዚያ እንድንሆን ነው የምትነግረን የነበረው፡፡

ሪፖርተር፡- እናት ባንክ እንዳሰባችሁት እየሄደ ነው? አሁን ያለበት አቋምስ ምን ይመስላል?

ወ/ሮ ሐና፡- እናት ባንክ ጥሩ ሁኔታ ላይ ነው ያለው፡፡ ምክንያቱም ዕድገቱ ነው የሚታየው፡፡ ወደ ሥራ ከገባን ስድስት ዓመት ነው፣ ብዙ አይደለም፡፡ ከስድስቱ ውስጥ  የመጀመርያዎቹ ሁለት ዓመታት እንደ መደራጀት ነው፡፡ ይህንን ስድስት ዓመት ብታይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከቀድሞዎቹ ዓመታት የበለጠ ብዙ መመርያዎች ያወጣበት ጊዜ ነው፡፡ ይኼኛውን ነገር ተወጣነው ስንል የሚቀጥለውን ስለሚያወጣ ብዙ ውጥንቅጥ ነገሮች ቢኖሩም፣ በዚህም ውስጥ ሆኖ ዕድገቱ እየቀጠለ ነው፡፡ በባለ አክሲዮኖች ቁጥርና በካፒታልም እያደገ ነው፡፡ የሴት ባአለክሲዮኖችም ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ ማኔጅመንት ላይ ያሉ ሠራተኞችም ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- ከዚህ በኋላ ጉዟችሁ እንዴት ይሆናል?

ወ/ሮ ሐና፡- ከዚህም በኋላም ቢሆን ዕድገቱ ይቀጥላል ብለን ነው የምናስበው፡፡ ሁለተኛ ከሙስና የፀዳ ንፁህ ሥራ እንሠራለን ብለን ነው የምናስበው፡፡ እስካሁን በሥራችን ትክልል አይደለም ተብሎ የመጣልን ነገር የለም፡፡ ምናልባት ጥቃቅን ነገሮች ሊገጥሙን ይችላሉ፡፡ ግን በብዙዎቹ ባንኮች ከሚሰማው አንፃር እኛ ዘንድ የለም፡፡ አሁን አሉ የሚባሉ ጥቃቅን ችግሮች የበለጠ እየተስተካከሉ ይሄዳሉ፣ የተሻለ ዕድገት ይኖራል፡፡

ሪፖርተር፡- ከአንድ ባንክ ጥንካሬ መለኪያዎች አንዱ የተበላሸ ብድር መጠኑ አነስተኛ መሆን ነው፡፡ የእናት ባንክ ከሌሎች ባንኮች የተበላሸ ብድር መጠን አንፃር አነስተኛ ነው፡፡ ይህም እናት ባንክ ጠንቃቃዋ አበዳሪ እስከመባል ተደርሷል፡፡ እንዲህ የሆነበት ምክንያት ምንድነው ብለው ያስባሉ? ምንስ የተለየ ነገር አድርጋችሁ ነው?

ወ/ሮ ሐና፡- አንደኛ እንግዲህ ብዙ የማትጽፈውና የማትናገረው ነገር አለ፡፡ ሌሎቹ ሲያበድሩ ምንድነው የሚያዩት? የሚለው ነገር አለ፡፡ እኛ ጋ ሁሉም ነገር ሥርዓቱ ጠብቆ ነው የሚሄደው፡፡ ቁጥጥር እያደረጉ መሄድ ግድ ነው፡፡ ይህንን እያደረግን ነው አሁን፡፡ እንዲያውም በአዲሱ መመርያ ምክንያት ከብድር አሰጣጡ ጋር በተያያዘ ወደ ታች ወደ ላይ ቢልም ቁጥሩ አለ፡፡ ስለዚህ በጥንቃቄ የመጣ ነው ብዬ ነው የማምነው፡፡ እንደ ሕግ ያስቀመጥነው ነገር ነው፡፡ ሙስናን መታገስ የማይችል አሠራር ነው ያሰፈነው፡፡ ምንም ነገር እናት ባንክ ላይ መሰማት የለበትም፡፡ እንደ እናትነታችንና እንደ ሴትነታችን ትንሽ ችግር ቢመጣ እንዳልሁክ ጥንካሬያችን አይደለም የሚወራው፡፡ ራስን ለማሳየት መስመሩ ላይ መገኘት የግድ ነው፡፡  ከዚህ ውልፊት ብትል ውርጅብኙ ብዙ ነው፡፡ እናት ባንክን ለማቋቋም አደራጆች ሰዎችን በሚያነጋግሩበት ጊዜ ሴቶች ተሰብስበው ምን ሊያመጡ ነው? ነገ ይጣላሉ የሚሉና ብዙ ተመሳሳይ ነገሮች ሲነገሩ ነበር፡፡ ይህንን ለማረጋገጥ ብዙ መንገድ መሄድ ይፈልጋል፡፡

ሪፖርተር፡- ታዳጊ የሚባሉ ባንኮች ይገጥማቸዋል ተብለው ከሚታሰቡ ተግዳሮቶች ውስጥ የባንካቸውን የተከፈለ ካፒታል ሁለት ቢሊዮን ብር ማድረስ ነው፡፡ በእርስዎ የኃላፊነት ዘመን ይህንን ማስፈጸም ይጠበቅብዎታል፡፡ አሁን ያላችሁ የተከፈለ ካፒታል አንድ ቢሊዮን ብር ስለሆነ፣ ወደ ሁለት ቢሊዮን ብር ማሳደግ ፈተና ይሆንባቸዋል እየተባለ ነው፡፡

ወ/ሮ ሐና፡- ይህ ጉዳይ ለሁሉም ባንኮች ትልቅ ተግዳሮት ነው፡፡ ሃያ ዓመት ኢንዱስትሪው ውስጥ የነበረውም እኛም በተመሳሳይ መንገድ ካፒታል አሳድጉ ነው የተባልነው፡፡ እኛም ሃያ ዓመት ብንቆይ ይህንን እናልፈዋለን፡፡ በዚህ ረገድ ብሔራዊ ባንክም ያደረገው ነገር ሚዛናዊ አይደለም፡፡ ሦስት ዓመት የሠራውንም 20 ዓመት የሠራውንም በአንድ ላይ በአንድ ጊዜ ካፒታላችሁ ሁለት  ቢሊዮን ብር መድረስ አለበት የሚለው አግባብ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ነገር ግን ይህንን ካፒታል ለማሟላት ይቻላል ወይ? የሚለው በጣም አስፈርቶን ነበር፡፡ ነገር ግን የፈራነውን ያህል አይደለም፡፡ እየሄደልን ነው፡፡ ከሁለት ቢሊዮን ብር ውስጥ ከግማሽ በላይ አልፈናል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ግን ብሔራዊ ባንክ ሁለት ቢሊዮን ብር ድረሱ ሲል በግልጽ ቁጭ አላደረገውም፡፡ የምጠብቃችሁ እዚህ ደረጃ ላይ ነውና እዚያ ድረሱ የሚል ነው፡፡ ፈተና ነው፡፡ እንደ እናት ባንክ ግን የምንደርስበት ይመስለኛል፡፡

ሪፖርተር፡- እስኪ የአገሪቱን ፋይናንስ እንዴት ይገልጹታል? ተደራሽነቱስ ምን ደረጃ ላይ ነው?

ወ/ሮ ሐና፡- ገና ነው፡፡ አዲስ ነው፡፡ ባለፉት ሁለት ሦስት ዓመታት ዕድገቱ ፈጣን ነው፡፡ በተለይ ከቴክኖሎጂ አጠቃቀም ጋር ስታየው ዕድገቱ ፈጣን ነው፡፡ ጥሩ ነው፡፡ ግን ይህ አዲስ አበባ ላይ ነው የሚሽከረከረው፡፡ ከአዲስ አበባ ውጪ ያለው ሲታይ ገና ነው፡፡

ሪፖርተር፡- እናት ባንክ የስድስት ዓመት ዕድሜ ቢኖረውም፣ የሴቶችን የፋይናንስ ተደራሽነት ለማጎልበት ከአዲስ አበባ ውጪ ያለው እንቅስቃሴያችሁ ምን ይመስላል? ታች ያለችውን ሴት ለመድረስ ምን አድርጋችኋል?

ወ/ሮ ሐና፡- ብዙ ጊዜ እንነጋገርበታለን፡፡ ፈተናው ቴክኖሎጂው ነው፡፡ ኢንተርኔትም የራሱ የሆነ ተግዳሮት አለው፡፡ እኛ እንግዲህ ከዕድሜያችን አንፃር ስናየው ጥሩ መጥተናል፡፡ ምክንያቱም ምርጫ የለንም ግድ ነው፡፡ ቴክኖሎጂ ላይ መሥራት ትልቅ ኢንቨስትመንት ይጠይቃል፡፡ ስለዚህ ይህንን ማድረግ ግድ ስለሆነ እያደረግነው ነው፡፡ መመርያው በሚፈቅደው መሠረት ባንኪንግ ውስጥ ለመግባትም ዝግጅቱ አልቋል፡፡ ይህንን ስንተገብር ትንንሾቹ ዘንድ እንደርሳለን፡፡ እኛ መጀመርያ ጉሊት አካባቢ ያሉ ሴቶችን ለመድረስ በመኪና የሚንቀሳቀስ የባንክ አገልግሎት ለመጀመር ሁሉ ዕቅድ ነበረን፡፡ በእርግጥ ይህንን ማድረግ አለብኝ ብለህ ስትንሳ የጠቀሜታውን ትንታኔ መሥራት ግድ ነው፡፡ ይህንን ስንሠራው የቴክኖሎጂው ውድ መሆንና እዚህ ደግሞ ዝግጁ አለመሆን ብዙ ወጪ ነው የሚያስወጣው፡፡ እንዲህ ያሉ ፈተናዎች ናቸው እንጂ ሐሳቡና ተደራሽ ለመሆን ጥረት ማድረጉ የግድ ነው፡፡  

ሪፖርተር፡- እንደ ችግር የሚያዩትና ሳላሳካ ቀርቻለሁ የሚሉት ነገር አለ?

ወ/ሮ ሐና፡- እንደዚህ ዓይነት ሐሳብ የለኝም፡፡ በተፈጥሮዬ ያበላሸሁትንም ሆነ ያሳለፍኩትን ነገር እኔ ትክክል ነው ብዬ የምወስደው፡፡ በዚህ ሁሉ ዕድሜዬ የተሳሳኩት ነገር የለም ልል አልችልም፡፡ ግን በዚያ ጊዜ ትክክል ነኝ ብዬ ነው የማምነው፡፡ በዚያ ጊዜ ሳላስብ ድንገት የምወስነው ነገር አልነበረም፡፡ በጊዜው ለወሰንኩት ግን ትክክል ነኝ፡፡ አሁን ወደ ኋላ ተመልሼ አልፀፀትም፡፡ በዚያ ጊዜ ትክክል ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ቁጭ ብዬ ትክልል የማይመስለው ነገር በወቅቱ ትክክል ነገር ብዬ ነውና የምወስደው ፈተና ብዬ የምገልጸው ነገር የለኝም፡፡ ምናልባት ዕድለኛ ሆኜ ሊሆን ይችላል፡፡ የምችለውን እሠራለሁ፡፡   

ሪፖርተር፡- በሴትነትዎ ምክንያት የደረሰብዎ ጥቃት ወይም የተጫንዎ ነገር አለ?

ወ/ሮ ሐና፡- አለ፡፡ ግን እንደነገርኩህ እናቴ ከምትነግረኝ አንድም ቀን ራሴን ዝቅ አድርጌ አላውቅም፡፡ ተፅዕኖም ቢደርስብኝ እኔ ሳልሆን እነሱ ናቸው ትክክል ያልሆኑት ብዬ ነው የምወስደው፡፡ ፈተናውማ ሁል ጊዜ አለ፡፡ ራስህን ለማሳየት እጥፍ የምትሄደው መንገድ አለ፡፡ ይህንንም አድርገህ ተቀባይነት የማታገኝበት ጊዜ አለ፡፡ በዚህ ረገድ የተለየ ሴት መሆን አልችልም፡፡ ተመሳሳይ ማኅበረሰብ ውስጥ ነው ያለሁት፡፡ ሁለተኛ በማኔጅመንት ደረጃ ብዙ ጊዜ ስለሠራሁኝ ሁልጊዜ አንድ ወይም ሁለት ሴት ነው የምትገኘው በምናደርጋቸው ስብሰባዎች፡፡ ሁልጊዜ ሴት ሲሆን ጠንቃቃ መሆን ይፈልጋል፡፡ ይህንን እያሰብኩ ነው የኖርኩት፡፡ ሁልጊዜ ሴት ስትሆን ሰው ከሚያስበው አንድ ተጨማሪ ሐሳብ ይኖራል፡፡

ሪፖርተር፡- ከሥራ ውጪ በተለየ የሚሠሩት ምንድነው? በተለይ ቤት ውስጥ?

ወ/ሮ ሐና፡- የአትክልት ሥፍራና ምግብ መሥራት እፈልጋለሁ፡፡ ደስ ይለኛል፡፡ አስቤበት ምግብ የምሠራበት ጊዜ አለ፡፡ ይህንንም መሥራት ስላልቻሉ ቤት ማስተዳደር አልችልም፣ ቤት የሚጠብቅብኝን ኃላፊነት አልተወጣሁም ብለው ሴቶች እንዲያስቡ አልፈልግም፡፡ አሁን ያለው ትውልድ ላይ ያለው ችግር ይኼ ነው፡፡ ማናችንም ፍፁም አይደለንም፡፡ ቤት ውስጥ ባለው ነገርም ፍፁም መሆን አይጠበቅብንም፡፡ ማንም ቢሆን በልቶ መኖር ስላለበት ያበስላል፡፡ ምርጫ የለም፡፡ ያለበለዚያ ካልበላህ መኖር አይቻልም፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የማስተላልፈው መልዕክት የንብረት ማስመለስ ረቂቅ አዋጅ ያለበቂ ምክክርና ውይይት እንዳይፀድቅ ነው›› አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም፣  የሕግ ባለሙያ

አቶ ፊሊጶስ ዓይናለም በዳኝነትና በጥብቅና ሙያ ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል፡፡ ከአምስተርዳም ዩኒቨርሲቲ በሕገ መንግሥትና አስተዳደር ሁለተኛ ዲግሪያቸውን አግኝተዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ  ጠበቆች ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ...

‹‹ከ400 ዓመት በፊት በአውሮፓ የኢትዮጵያ ጥናት እንዲመሠረት ምክንያት ለሆኑት ለአባ ጎርጎርዮስ ምን አደረግንላቸው?›› ሰብስቤ ደምሰው (ፕሮፌሰር)፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የተፈጥሮ ሳይንስ ኮሌጅ የዕፀዋት...

ዘንድሮ ጀርመን በኢትዮጵያዊው አባ ጎርጎርዮስ ግእዝና አማርኛ፣ የኢትዮጵያን ታሪክና መልክዓ ምድር ጠንቅቆ የተማረው የታላቁን ምሁር ሂዮብ ሉዶልፍ 400ኛ የልደት በዓልን እያከበረች ትገኛለች፡፡ በ1616 ዓ.ም....

‹‹ፍትሕና ዳኝነትን በግልጽ መሸቀጫ ያደረጉ ጠበቆችም ሆኑ ደላሎች መፍትሔ ሊፈለግላቸው ይገባል›› አቶ አበባው አበበ፣ የሕግ ባለሙያ

በሙያቸው ጠበቃ የሆኑት አቶ አበባው አበበ በሕግ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ሕጉ ምን ይላል የሚል የሬዲዮ ፕሮግራም አዘጋጅ ናቸው፡፡ በሕግ መምህርነት፣ በዓቃቤ ሕግነት፣ እንዲሁም ከ2005...