በከባድ የሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ በተመሠረተባቸው በእነ አቶ መላኩ ፈንታ የክስ መዝገብ የተካተቱትን የልብ ሕክምና ስፔሻሊስት ዶ/ር ፍቅሩ ማሩ ወርዶፋን መንግሥት ትብብር እንዲያደርግላቸው፣ የግል ሆስፒታሎች ማኅበር ጠየቀ፡፡
በማኅበሩ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ሲሳይ ማሩ ጆፋ ፊርማ በቀጥታ ክስ ለመሠረተው ለፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ተጽፎ በግልባጭ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ለፍትሕ ሚኒስቴር፣ ለጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና ለዳያስፖራ ዴስክ እንዲደርስ የተደረገው ደብዳቤ ማኅበሩ ለምን የመንግሥት ትብብር እንደተፈለገ ያብራራል፡፡
ደብዳቤው እንደሚገልጸው፣ በሙስና ወንጀል ክስ ተመሥርቶባቸው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት በመታየት ላይ የሚገኙት ዶ/ር ፍቅሩ፣ በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነውን አዲስ የልብ ሕክምና ማዕከልን የከፈቱ ፈር ቀዳጅ የልብ ሕክምና ባለሙያ ናቸው፡፡
በሆስፒታሉ የተዘጉ የልብ የደም ሥሮች ማየት የሚችል ሕክምና፣ የልብ ምታቸው ለቀነሰ ሕሙማን የልብ ምት ማስተካከል፣ ድንገተኛ የልብ መቆም መከላከል ሕክምናና ሌሎችም በርካታ ከልብ ጋር የሚገናኙ ሕክምናዎች እንደሚሰጡ ማኅበሩ፣ በደብዳቤው ጠቁሟል፡፡
የነፍስ አድን መሣሪያዎች በሰውነታቸው የተገጠመላቸው ታካሚዎች በየሦስት ወራት እየተከታተሉ በሕይወት የመቆየት ተስፋ እንደነበረባቸው የሚገልጸው ማኅበሩ ዶ/ር ፍቅሩ በመታሰራቸው ይሰጥ የነበረው ሕክምና በመቋረጡ የልብ ታካሚዎቹ ለከፋ ችግር እየተጋለጡ መሆኑን አስረድቷል፡፡
ዶ/ር ፍቅሩ ኢትዮጵያውያን ሐኪሞችን ወደ ስዊድን በመላክ የልብ ሕክምና ስፔሻሊስት እንዲሆኑ ማድረጋቸውን ማኅበሩ በደብዳቤው ጠቁሞ፣ ከስዊድን ከሚመጡ ሐኪሞች ጋር በሚደረግ የሕክምና ሒደት ደግሞ የዕውቀት ሽግግርም ይካሄድ የነበረ ቢሆንም፣ እሳቸው በመታሰራቸው መቋረጡን አስረድቷል፡፡
በመሆኑም ዶ/ር ፍቅሩ በመታሰራቸው ምክንያት በእሳቸው ክትትል ይደረግላቸው የነበሩ ሕሙማን ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን፣ በጤና አገልግሎቱም ክፍተት እየተፈጠረ መሆኑን፣ መንግሥት የእሳቸውን አስተዋጽኦ ከግምት ውስጥ በማስገባትና ኅብረተሰቡ የደረሰበትን የሕክምና ዕጦትና መንገላታት ታሳቢ በማድረግ አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርግላቸው ጠይቋል፡፡
ማኅበሩ ለሚመለከታቸው አካላት ደብዳቤ የጻፈው ጳጉሜን 2 ቀን 2007 ዓ.ም. ቢሆንም፣ እስከ መስከረም 18 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ከማናቸውም አካላት ምንም ዓይነት ምላሽ አለማግኘቱ ታውቋል፡፡