– የመጀመሪያው መግባቢያ ሰነድ ዛሬ ይፈረማል
በቢራ ጠመቃ ኢንዱስትሪ ተሳታፊ የሆነው ቢጂአይ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በስሙ መጠራት ይችል ዘንድ፣ ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ጋር መስከረም 19 ቀን 2008 ዓ.ም. በኢሊሊ ሆቴል የመጀመሪያውን የመግባቢያ ሰነድ ይፈራረማል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
ከተመሠረተ ሁለት አሥርታትን ለመድፈን ከጫፍ የደረሰው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እንደተቀሩት አገሮች ውድድሩን ከመዝናኛነት አልፎ አማራጭ የገቢ ምንጭ ለማድረግ ሳይችል ቆይቷል፡፡ ይሁንና ቅርበት ያላቸው የፌዴሬሽን ምንጮች በተለይ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የአገሪቱን እግር ኳስ በበላይነት የሚቆጣጠረው የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን፣ የፕሪሚየር ሊጉን ስያሜ መሸጥ በሚያስችለው ሁኔታ ላይ ከጂአይ ኢትዮጵያ ጋር በሚስጥር ሲደራደር ቆይቶ፣ የመጀመሪያውን የመግባቢያ ሰነድ ለመፈራረም መቃረቡ እየተነገረ ይገኛል፡፡