ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ለዓለም የሴቶች እግር ኳስ ዋንጫ ማጣሪያውን እያደረገ የሚገኘው የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን፣ ከቡርኪናፋሶ አቻው ጋር ቅዳሜ መስከረም 22 ቀን 2008 ዓ.ም. ኡጋዱጉ ላይ ይጫወታል፡፡ የዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ቡርኪናፋሶ በነበረባት የውስጥ ችግር ምክንያት የሁለቱ አገሮች የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ላልተወሰነ ጊዜ እንዲራዘም አድርጐ መቆየቱ ይታወሳል፡፡ በዚሁ ምክንያት የኢትዮጵያ ሴቶች ብሔራዊ ቡድን ያለምንም ጨዋታ በዝግጅት ብቻ ከወር በላይ ቆይቷል፡፡
በመጀመሪያው ዙር የካሜሩን አቻውን በደርሶ መልሱ ጨዋታ ከሜዳው ውጪ
0 ለ 0፣ በሜዳው ደግሞ 2 ለ 1 በመርታት ለቅዳሜው ጨዋታ የበቃው የኢትዮጵያ ዕድሜያቸው ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሔራዊ ቡድን፣ ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ የሚገኘውን የቡርኪናፋሶ አቻውን በደርሶ መልስ ጨዋታ ማሸነፍ ከቻለ ከጋናና ከኢኳቶሪያል ጊኒ አሸናፊ ጋር ይገናኛል፡፡ ቡድኑ ሐሙስ መስከረም 20 ቀን 2008 ዓ.ም. ወደ ሥፍራው እንደሚያቀናም ይጠበቃል፡፡