– ፕሮፌሽናሎቹ አልተካተቱም
በውድድር ዓመቱ ሁለት አኅጉራዊና የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የሚጠብቀው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን፣ የመጀመሪያውን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከሳኦቶሜና ፕሪንስፔ ጋር መስከረም 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ይጫወታል፡፡ ቡድኑ ለዝግጅት ይረዳው ዘንድ የቦትስዋና አቻውን ለመግጠም ማክሰኞ ወደ ሥፍራው አምርቷል፡፡ ረቡዕ ይጫወታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በቱርክ የሚጫወተውን ዋሊድ አታ፣ ሽመልስ በቀለ፣ ሳላዲን ሰይድ፣ ጌታነህ ከበደና ኡመድ ኡክሪን ሳያካትት ለቦትስዋናው የወዳጅነት ጨዋታ ያመራው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን (ዋሊያዎቹ)፣ መስከረም 30 ቀን 2008 ዓ.ም. በሦስት ቀናት ልዩነት ውስጥ በአዲስ አበባ ስታዲየም የመልሱን ጨዋታ ያደርጋል፡፡ ሁለቱ ቡድኖች አብረው አዲስ አበባ እንደሚገቡም ይጠበቃል፡፡
ዋሊያዎቹ ጋቦን እ.ኤ.አ. በ2017 ለምታስተናግደው የአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ ከሚገኙበት ምድብ ሌሴቶን አሸንፈው፣ ከሲሸልስ ጋር ደግሞ ከሜዳው ውጪ በአቻ ውጤት ተለያይተው በአራት ነጥብ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ይገኛሉ፡፡ ምድቡን አልጄሪያ በስድስት ነጥብ ስትመራ፣ ሲሸልስ በአንድ ነጥብና ሌሴቶ ያለምንም ነጥብ ሦስተኛና አራተኛ ደረጃ ይዘው ይከተላሉ፡፡
በአቶ ዮሐንስ ሳህሌ ዋና አሠልጣኝነት እየተዘጋጁ የሚገኙት ዋሊያዎቹ የሲሸልሱን ውጤት ተከትሎ፣ በተለይም በአሁኑ ወቅት በአልጄሪያ የሚጫወተው ሳላዲን ሰይድ፣ በግብፅ የሚጫወተው ኡመድ ኡክሪና በደቡብ አፍሪካ የሚጨወተው ጌታነህ ከበደ የቡድኑ አባል ሊሆኑ የሚችሉበት ዕድል የጠበበ ስለመሆኑ እየተነገረ ይገኛል፡፡ እንደ ሪፖርተር ታማኝ ምንጮች ከሆነ፣ ሦስቱ ፕሮፌሽናሎች የብሔራዊ ቡድኑ አባል ለመሆን አንድ የመጨረሻ ዕድል ሊኖራቸው የሚችለው፣ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) በሚያወጣቸው የአገሮች የወዳጅነት ጨዋታ ላይ የኢትዮጵያ ቡድን በዚሁ መርሐ ግብር መሠረት ተጫዋቾቹን አካቶ ወቅታዊ አቋማቸው ከተገመገመ በኋላ ነው፡፡ ሽመልስ በቀለና ዋሊድ አታ ግን ከቦትስዋናው የወዳጅነት ጨዋታ ማግሥት ጥሪ ተደርጐላቸው ለሳኦቶሜና ፕሪንስፔ ጨዋታ የቡድኑ አባል ይሆናሉ ተብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያም ሆነ የአፍሪካና የአፍሪካ አገሮች (ቻን) ዋንጫ ማጣሪያ ከፊት ለፊቱ ወሳኝ ግጥሚያዎች እንዳሉበት ቢታወቅም፣ በድኑ ዝግጅት ለማድረግ በሚኖረው ጊዜ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች ተሟልተው አለመገኘት ደግሞ በሌላ በኩል ችግር እየሆነ መምጣቱ እየተነገረ ይገኛል፡፡ ከቦትስዋና ብሔራዊ ቡድን ጋር ይደረጋል ተብሎ ለሚጠበቀው የወዳጅነት ጨዋታ 19 ተጫዋቾች ወደ ሥፍራው አምርተዋል፡፡ ከእነዚህ ተጫዋቾች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ደግሞ ቡድኑን የተቀላቀሉት ባለፈው ቅዳሜ መስከረም 15 ቀን 2008 ዓ.ም. እንደሆነ ይነገራል፡፡
ለብሔራዊ ቡድኑ አራት ተጫዋቾችን ያስመረጠው የደደቢት እግር ኳስ ክለብ ለብሔራዊ ቡድን ያስመረጣቸውን ተጫዋቾች በጊዜ ካላኩት ክለቦች በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳል፡፡ ክለቡ ምክንያት ያላቸውን ከአሥራ አምስት ቀን በፊት ለብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ማሳወቁን ይፋ አድርጓል፡፡ ክለቡ ምክንያት ብሎ ከገለጻቸው ውስጥ የፊፋ አባል አገር የሆነ ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችን ለዝግጅት ሲጠራ፣ እንዴትና በምን አግባብ መሆን እንዳለበት ባስቀመጠው መመርያ መሠረት ለወዳጅነት ጨዋታ ከሆነ አራት ቀን፣ ለወሳኝ አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ጨዋታ ከሆነ ደግሞ ለአንድ ሳምንት ክለቦች ለብሔራዊ ቡድን የተመረጡ ተጫዋቾቻቸውን መልቀቅ እንደሚገባቸው ያስገድዳል፡፡ የደደቢት እግር ኳስ ክለብም ተጫዋቾቹን የሚለቀው ይህንኑ የፊፋን መመርያ መነሻ አድርጐ እንደሆነ ነው ቀደም ብሎ ይፋ ያደረገው፡፡
ጉዳዩን በሚመለከት ሪፖርተር ያነጋገራቸው የብሔራዊ ፌዴሬሽኑ የሕዝብ ግንኙነት ባለሙያ አቶ ወንድምኩን አላዩ በበኩላቸው፣ ክፍተቱ የተፈጠረው በመመርያ ምክንያት መሆኑን ተናግረዋል፡፡ መመርያው ፊፋ ለዓመታት ሲጠቀምበት የቆየ ከመሆኑ አኳያ፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንደ አባል አገር ፌዴሬሽንነቱ በመመርያው ያገኘውን ክፍተት እንዲታረም ማድረግ አይችልም ነበር ወይ? ለሚለው ጥያቄ ኃላፊው በሰጡት ምላሽ፣ ‹‹በአጠቃላይ መመርያው በውድድር ጊዜና ውድድር በሌለበት ጊዜ ተብሎ በዝርዝር መቀመጥ ሲገባው ያ አልሆነም፤›› ብለው ዝርዝሩን ከመናገር ተቆጥበዋል፡፡
ማንነታቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉና ለተቋሙ ቅርበት ያላቸው ወገኖች በበኩላቸው፣ የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ችግሮች ከመፈጠራቸው በፊት ችግር በሚያስከትሉ ጉዳዮች ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር መክሮ የተሻለውን መንገድ ከመሻት ይልቅ ችግሩ ሲፈጠር ምክንያት መደርደር ያውቅበታል ይላሉ፡፡ ለዚህ ትልቁ ማሳያ የሚሆነው ደግሞ የደደቢት እግር ኳስ ክለብ የብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾችን መቼና በምን አግባብ መልቀቅ እንዳለበት አሳማኝ ምክንያት አቅርቦ ለፌዴሬሽኑ በደብዳቤ ሲያሳውቅ፣ ብሔራዊ ፌዴሬሽኑ ደግሞ ክለቡ ባለድርሻ እንደ መሆኑ መጠን ቅሬታውን ተቀብሎ አለመግባባቱን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት መሞከር ነበረበት በማለት፣ የፌዴሬሽኑን የማያሳምን ምክንያትና የአሠራር ሥርዓቱን ዝርክርክነት ይተቻሉ፡፡