አቶ መልከቻ ሲዳ በዱከም ከተማ ለ85 ዓመታት ኖረዋል፡፡ ከችግረኛ ቤተሰብ ስለተወለዱ የመማርም ሆነ ጥሩ ሥራ ሠርቶ የመኖር ዕድል አልገጠማቸውም፡፡ በጉብዝናቸው ወራት በአካባቢያቸው በሚገኙ ቅርብ ከተሞች በመዘዋወርና ሰው ቤት ውስጥ በመሥራት አሳልፈዋል፡፡ ዕድሜያቸው እየገፋ ሲመጣ ግን የሚያሠራቸው አላገኙም፡፡
ከማዳበሪያ ገመድ እየገመዱ በከተማው ሐሙስ ሐሙስ ብቻ በሚቆመው ገበያ አንዱን ገመድ በ40 ብር እየሸጡ ኑሯቸውን እንደመሩ ይናገራሉ፡፡ ዛሬ ግን በመድከማቸው ሰው እጅ ላይ ወድቀዋል፡፡
አቶ መልከቻ በደመራ ዕለት ዱከም አሮጌ ገበያ አካባቢ የተገኙት ከበጐ ፈቃደኞች የሚደርሳቸውን 300 ብር ለመውሰድ ነበር፡፡
ከአዲስ አበባ 47 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የምትገኘው ዱከም ብዙዎች የጥሬ ሥጋ አምሮታቸውን የሚወጡባት ናት፡፡ በማኛ ጤፍ (በአደአ ጤፍ) ምርቷም ትታወቃለች፡፡ ከአዲስ አበባ ጂቡቲ ለሚመላለሱ የከባድ መኪና ሾፌሮችም ማረፊያ ናት፡፡ ዛሬ ላይ ደግሞ የኢንዱስትሪ ከተማም እየሆነች ነው፡፡ ቀን ላይ ብዙም ሰው የማይንቀሳቀስባት ዱከም፣ ምሽት 12 ሰዓት ገደማ ሲሆን ትደምቃለች፡፡
በዱከም መስከረም 16 ቀን የ2008 ዓ.ም. የደመራ በዓልን ለማክበር ከዛፍ ቅጠልና ከፅድ የተሠሩ ደመራዎች በየቤቱ ደጃፍ ላይ ቆመዋል፡፡ በማኅበር የተሠሩ ደመራዎች ተቆርጠው በተቀጣጠሉና የኢትዮጵያን ባንዲራ በሚያመላክቱ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ጨርቆች አሸብርቀው ይታያሉ፡፡ ከደመራ በኋላ ለሚኖረው ፌሽታም በሰፊው ዝግጅት ተደርጓል፡፡
ካሱ ፈንታ፣ ጌታቸው ንጉሤ፣ አሸናፊ ዓለምነህና ደምሰው ረጋሳ የተባሉ ወጣቶች ከ11 ዓመት በፊት ደመራን ደምረው፣ ከተበላና ከተጠጣ በኋላ ጨፍረው ለዓመት ያድርሰን ተባብለው ነገር የተለያዩት፡፡ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የደመራን በዓል የበጐ አድራጐት ሥራ የሚሠራበትና ሌሎችን የመርዳት አጋጣሚ የሚፈጠርበት አድርገውታል፡፡ ዘንድሮ የደመራ በዓልን ያከበሩት የድሮ ገበያ በመባል በሚታወቀው ቀቤቻ ቀበሌ ውስጥ ነው፡፡ የድሮ ገበያ ዛሬ በጉሊት ደረጃ ብቻ ነው ያለው፡፡ ደመራ የሚለኮሰው እዚህ ቦታ ላይ ነው፡፡
በትንሽ የጀመሩት የበጐ አድራጐት ሥራ ዛሬ ድፍን የከተማዋን ወጣት በማንቀሳቀስ ከሴቶችና ወጣቶች ማኅበራዊ ጉዳይ ጋር በመተባበር ሰፊ ሥራ መሥራት እንዳስቻላቸው የማኅበሩ ሰብሳቢ ወጣት ካሱ ፈንታ ይናገራል፡፡ ቦታው ላይ ተገኝተን እንደተመለከትነው፣ ወደ ገበያው የሚወስደው መንገድ በትንሽ፣ በትልቅና በመካከለኛ በተሠሩ ደመራዎች ተሞልቷል፡፡ አዛውንቶች ወደስፍራው ያመራሉ፡፡ ወደ እነካሱ ፈንታ ደመራ ለመድረስ የማይችሉ፣ ማኅበሩ ባዘጋጀላቸው ባጃጆች ይመጣሉ፡፡ የበጐ ፈቃደኝነት ትሩፋቱን ለመቋደስ በቦታው ላይ ከ500 ያላነሱ ሰዎች ተገኝተው ነበር፡፡
የማኅበሩ ገንዘብ ያዥ ወጣት ጌታቸው ንጉሤ፣ ከሦስት ወር ቀደም ብሎ ባለሀብቶችንና ወጣቶችን በማደራጀት ከ50 ሺሕ ብር በላይ መሰብሰባቸውን ይናገራል፡፡ በቀጣይ ደግሞ ዕርዳታ በመጠየቅ ሳይሆን በራሳቸው የበጐ አድራጐት ሥራውን የመቀጠል ፍላጐት እንዳላቸው ገልጿል፡፡
በዘንድሮው የደመራ ሥነ ሥርዓት ላይ 23 ለሚሆኑ አቅመ ደካሞች ለእያንዳንዳቸው 300 ብር፣ 30 ለሚሆኑ ብርድ ልብስ፣ 15 ዩኒቨርሲቲ ለሚገቡ ተማሪዎች ሻንጣ፣ እንዲሁም ስምንተኛና አሥረኛ ክፍል ለሆኑ የተለያዩ አጋዥ መጻሕፍትና ደብተር፣ እስክሪፕቶ መስጠታቸውን፤ በመስቀል በዓል ዕለት ደግሞ 600 ለሚሆኑ በልመና ላይ ለተሰማሩ ወገኖችና 34 በገጠርና በከተማ ለሚገኙ እስረኞች የምሳ ግብዣ ማዘጋጀታቸውንም ተናግሯል፡፡
‹‹ይህ የደመራ በዓል የበጐ ፈቃድ አገልግሎት፣ በእኛ ፈቃድ ላይ ብቻ የተመሠረተ ነው፡፡ እኛ ካቆምነው ይቆማል፡፡ የራሳችን የሆነ ቢሮም ሆነ ሰነድ ማስቀመጫ የለንም፡፡ የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ በሚያደርግልን የድጋፍ ደብዳቤ ነው የምንንቀሳቀሰው፡፡ ራሱን ችሎ እንዲቋቋምና ቀጣይነት ያለው እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ የከተማው አስተዳደር ሊተባበረን ይገባል፡፡ ያገኘናትን ብርም ይሁን በዓይነት የተሰጠንን ምንም ሳናስቀር እንገልፃለን፤›› ይላል ካሱ፡፡
በሌላ በኩል በከተማ ውስጥ ያሉ ባለሀብቶችን በማስተባበር ጠንካራ አቅም ፈጥሮ የከተማዋን አቅመ ደካሞች፣ ጧሪ የሌላቸውንና ሥራ አጥ ወጣቶችን ማገዝ ይቻላል የሚል እምነት አለው፡፡
22 የከተማውን ባለሀብቶች በመወከል በዝግጅቱ ላይ የተገኙት አቶ ንጉሤ ሙሉጌታ እንደተናገሩት፣ ለችግረኞች የዋለው ገንዘብ ከባለሀብቶች ቁጥር አንፃር እዚህ ግባ የሚባል ባይሆንም፣ ለወደፊቱ ግን በተጠናከረ ደረጃ የተሻለ እንዲሠራ እንደሚጥሩ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ሌሎች ግለሰቦች አነሰ በዛ ሳይሉ ያላቸውን በማካፈል፣ ሁላችንም ድህነት ላይ መዝመት አለብን፤›› ብለዋል፡፡