Tuesday, April 16, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊህልም እንዲፈታ

ህልም እንዲፈታ

ቀን:

ወ/ሮ ቃልኪዳን መሸሻ ይባላሉ፡፡ 37 ዓመታቸው ነው፡፡ ለቤተሰቦቻቸው የበኩር ልጅ ሲሆኑ ተወልደው ያደጉት እዚሁ አዲስ አበባ ነው፡፡ ባለትዳርና የአራት ልጆች እናትም ናቸው፡፡ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን እንዳጠናቀቁ ሴክሬታሪ ሳይንስ ተምረዋል፡፡ የበረራ መስተንግዶን ጨምሮ የተለያዩ ሥልጠናዎችን መከታተልም ችለዋል፡፡ ይህም በተለያዩ መሥሪያ ቤቶች በሙያዎቻቸው ተቀጥረው እንዲያገለግሉ መንገድ ከፍቶላቸዋል፡፡

በኢትዮጵያ አየር መንገድም በመስተንግዶ ሙያ ጥቂት ዓመታት ሠርተዋል፡፡ በተለያዩ ቦታዎች በልዩ ልዩ ሙያዎች ማገልገላቸው እንደጠቀማቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹በቀላሉ ከሰዎች ጋር እንድግባባ አግዞኛል፡፡ በሆስተሲንግ ሙያ ማገልገሌም የውጭውን ዓለም እንዳውቅና በገንዘብም እንዳልቸገር ረድቶኛል፤›› ይላሉ፡፡

ጥረት ከታከለበት ችግር ፈቺ የሆኑ ነገሮችን ለኅብረተሰቡ ማበርከት እንደሚቻል ያምናሉ፡፡ በሥራ አካባቢያቸው ያስተዋሉትን ችግር ለመፍታትም አንድ ብለው ዕርምጃቸውን ጀመሩ፡፡ በአውሮፕላን የውስጥ አካል የሚደረገውን ኢንቲሪየር ዲዛይን ቦታ በሚቆጥብ መልኩ እንዲሁም የአገሪቱን ባህል በሚያስተዋውቅ መልኩ መቀየር ተመኙ፡፡ ቦታ ቆጣቢና ምቹ የሆኑ ወንበሮችን ለገበያ ለማቅረብ ዲዛይኑን ጨርሰው የፓተንት ራይት ከወሰዱ ጥቂት የማይባሉ ጊዜያት አልፈዋል፡፡ ወ/ሮ ቃልኪዳን የመስተንግዶ ሥራቸውን ካቆሙ አራት ዓመታት አስቆጥረዋል፡፡ ‹‹በቂ ጊዜ ኖሮኝ መሥራት እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህም ነው ሥራ ያቆምኩት፤›› ይላሉ፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

ሥራ ማቆማቸው ትክክለኛ ውሳኔ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ እሳቸው እንደሚሉት በእርግጥም ሥራ ማቆምና የውስጣቸውን ጥያቄ መመለስ ነበረባቸው፡፡ ተቀዳሚ ተግባራቸውም ከዚህ ቀደም የጀመሩትን ሥራ ከዳር ማድረስ አልነበረም፡፡ በአንድ ወቅት በገጠራማው የአገሪቱ ክፍል የሚኖሩ ዘመዳቸው ባጋጠማቸው ችግር አዲስ አበባ ወ/ሮ ቃልኪዳን ጋር ይመጣሉ፡፡ በሰባት ወር የተወለደው ሕፃን በቂ እንክብካቤ አላገኘም፡፡ እንደተወለደ ማሞቂያ ክፍል መግባት ነበረበት፡፡ ነገር ግን በአካባቢው የሕፃናት ማሞቂያ አልነበረም፡፡ ስለዚህም ሕፃኑ አስፈላጊውን ሙቀት ሳያገኝ በእናቱ እቅፍ ወደ ቤቱ ገባ፡፡ አጋጣሚው በሕፃኑ ጤና ላይ ወዲያውኑ ያስከተለው የጤና ችግር ባይኖርም ከቀናት በኋላ ችግር አመጣ፡፡ የሕፃኑ ጤና ተቃወሰ፡፡ በሞትና በሕይወት መካከል ሆነ፡፡ ግራ የገባቸው ቤተሰቦቹ ለተሻለ ሕክምና አዲስ አበባ አመጡት፡፡ ነገር ግን ሕይወቱን ማትረፍ አልተቻላቸውም፡፡ ሕፃኑ አረፈ፡፡

አጋጣሚው በቅርብ ቤተዛመዳቸው ቢከሰትም በተለያዩ ሁኔታዎች መሰል ክስተቶችን አይተዋል፡፡ ‹‹በሥራ ላይ እያለሁ ወላድ ሴቶች ያጋጥሙኛል ዕርዳታ እንዲያገኙም ሆስፒታል እወስዳቸው ነበር፡፡ በዚያም የነበረውን የማሞቂያ ችግር በቅርበት እመለከት ነበር፤›› በማለት የችግሩ መደራረብ መፍትሔ እንዲያበጁለት ይገፋፋቸው እንደጀመር ይናገራሉ፡፡

በቅርበት የሚያውቋቸውን የሕክምና ባለሙያዎችም በአገሪቱ ስላለው የጨቅላ ሕፃናት ማሞቂያ ያማክሩ ጀመር፡፡ በሰበሰቡት መረጃ መሠረትም የማሞቂያ ማሽኖች በአገር ውስጥ ከጥቃቅን የጥገና አገልግሎት ባለፈ እንደማይመረት ተረዱ፡፡ አጋጣሚውም በቀላሉ በአካባቢያቸው ከሚያገኙት ግብአት ማሞቂያ ለመሥራት አስገደዳቸው፡፡ ማኅበራዊ ድረገጾችን በመጠቀም የሌሎች አገሮችን ተሞክሮዎች ማየትና አሠራራቸውን ማጥናት ጀመሩ፡፡ የተወሰኑትን ግብአቶች በአገር ውስጥ ከሚገኙ ዕቃዎች በማድረግ የቀረውን ከባህር ማዶ በማስመጣት ንድፉን መሥራት ጀመሩ፡፡ ጋቢ፣ የሕፃናት መታቀፊያ፣ የሙቀት መስጫ መሣሪያዎችን በመጠቀም ኤሌክትሪክ በሌለባቸው አካባቢዎች በውኃ ኃይልና በፀሐይ ብርሃን እንዲሠራ አድርገው ንድፉን ሠሩ፡፡

‹‹አንድን ነገር ለመሥራት ሐሳብ ብቻ ዋጋ የለውም፡፡ ተንቀሳቅሶ ባለሙያዎችን ማናገር ማስተቸትና መሥራት ያስፈልጋል፤›› የሚሉት ወ/ሮ ቃልኪዳን ሪች ፎር ቼንጅ በተባለ የማኅበረሰቡን ችግር የሚፈቱ ሐሳቦችና ፈጠራዎች ወደ ትግበራ እንዲገቡ ድጋፍ ከሚሰጥ ተቋም ጋር አብረው መሥራት ከጀመሩ ወራት ተቆጥረዋል፡፡ ተቋሙ የኅብረተሰቡን ችግሮች የሚፈቱ ሐሳቦች በማወዳደር የላቀ ሚና ያላቸውን ለይቶ በማውጣት በተግባር እንዲለወጡ ልዩ ልዩ ድጋፎች ይሰጣል፡፡ ወ/ሮ ቃልኪዳንም ድጋፍ ከተሰጣቸው መካከል ናቸው፡፡

አቶ ዮሐንስ መኩሪያም እንዲሁ ከሃያዎቹ ተወዳዳሪዎች አንዱ ናቸው፡፡ ተወልደው ያደጉት ደብረ ዘይት ከተማ ነው፡፡ በአዳማ ዩኒቨርሲቲ ማኑፋክቸሪንግ ቴክኖሎጂ ተምረዋል፡፡ በንፋስ ስልክ ቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ የማሽን ቴክኖሎጂ መምህር ናቸው፡፡ የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውንም በመከታተል ላይ ይገኛሉ፡፡

‹‹በአገራችን ልብስ ማጠብ አሰልቺና አድካሚ ነገር ነው፡፡ አልፎ አልፎ ማጠቢያ ማሽኖችን በመጠቀም የሚወጣውን ጉልበት ለመቀነስ ቢሞከርም የኤሌክትሪክ ኃይል በማይደርስበት ቦታ መጠቀም አይቻልም፡፡ ከዋጋው ውድነት አንፃርም ብዙዎች አይደፍሩትም፤›› የሚሉት አቶ ዮናስ ችግሩን መቅረፍ የሚችል በፔዳል የሚሠራ የልብስ ማጠቢያ ማሽን ለኅብረተሰቡ ለማቅረብ ንድፉን ጨርሰዋል፡፡ አገር ውስጥ የሚገኙ ግብአቶችን በመጠቀም የሚሠራ ሲሆን፣ የብዙኃኑን አቅም ያማከለ ዋጋ እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡ በተለያየ መጠን እንደሚዘጋጅ የጠቆሙት አቶ ዮናስ ከ0.5 ኪሎ ግራም እስከ 12 ኪሎ ግራም የማጠብ አቅም ያላቸውን ማሽኖች ዲዛይን አድርገው እንደጨረሱ ተናግረዋል፡፡

ዋጋውም ኪስ የማይጐዳና የብዙኃኑን አቅም ያማከለ ሲሆን፣ ተደራጅተው የልብስ ማጠብ አገልግሎት ለሚሰጡ ወጣቶችና ሴቶች በረጅም ጊዜ በሚከፈል ብድር እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡ እንደ አቶ ዮናስ ገለጻ ማሽኑ የተገነባው ሌሎች ተጨማሪ አገልግሎቶች መስጠት እንዲችል ታስቦ ነው፡፡ ውኃ የማጣራት፣ በእርሻ ላይም በፓምፐርነት እንዲሁም፣ ለቤት ግልጋሎት የሚውል ኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጨት እንዲችል አድርገው ሠርተውታል፡፡ ከዚህ ቀደምም የተለያዩ አነስተኛ ማሽኖችን የሠሩ ሲሆን፣ ከሃያዎቹ መካከል መገኘታቸው ንድፉ በተግባር እንዲውልና ለኅብረተሰቡ እንዲደርስ እንደሚያግዛቸው ተናግረዋል፡፡

አቶ ኢብራሂም ማማ የሪች ፎር ቼንጅ በኢትዮጵያ ዳይሬክተር ናቸው፡፡ እንደ እሳቸው ገለጻ ፕሮግራሙ የኅብረተሰቡን ችግር የሚቀርፉ ፈጠራዎችን ማውጣት ሲሆን፣ በኢትዮጵያ መንቀሳቀስ ከጀመረ አምስት ወራት አስቆጥሯል፡፡ በዋናነት መርሐ ግብሩ እናቶችና ሕፃናት ላይ ያተኮረም ነው፡፡ የፈጠራ ሥራዎቹን ለማውጣት በደተረጉ ጥረቶች እስከ 500 የሚሆኑ ፈጣሪዎችን ለመድረስ ተችሏል፡፡ ይሁን እንጂ ከ200 የሚበልጥ ማመልከቻ ማግኘት አልተቻለም፡፡

‹‹የቀረቡት ሐሳቦች በሙሉ በሚያስብል ደረጃ ጥሩ ነበሩ፤›› የሚሉት አቶ ኢብራሂም የግድ 40 ንድፈ ሐሳቦች መውጣት ስለነበረባቸው የመጀመሪያ ማጣሪያ እንደተደረገ ይናገራሉ፡፡ በተለያዩ ጊዜያት በተሰጡ ሥልጠናዎችም 20 የሚሆኑ ፈጠራዎች ተመርጠው ቀርተዋል፡፡ ፈጠራው ለማኅበረሰቡ የሚሰጠው አስተዋጽኦ፣ ቀጣይነቱ፣ ችግር መቅረፍ መቻሉ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ ማደግ መቻሉና የባለቤቱ ሐሳብ የማመንጨት አቅምና ቆራጥነት ሃያዎቹ የተመረጡበት መሥፈርት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ የተለያዩ ሙያዊ እገዛዎችና የገንዘብ ድጋፎች እንደሚደረግላቸው የተናገሩት አቶ ኢብራሂም በመጨረሻው ውድድር ከአንድ እስከ ሦስት ለሚወጡ የፈጠራ ሥራዎች ለኢንቨስትመንት እንዲጠቅማቸው 400,000 ብር የገንዘብ ሽልማትና ቋሚ ባለሙያ ተመድቦላቸው ወደ ሥራ እንደሚገቡ ተናግረዋል፡፡       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...