Wednesday, February 28, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልድንበር ተሻጋሪ ጥበብ

ድንበር ተሻጋሪ ጥበብ

ቀን:

‹‹ሶልቴር›› አንዲት ግብፃዊት የምትተውንበት ቴአትር ሲሆን፣ አሜሪካ ውስጥ የግብፅ የባህል ሕክምና እየሰጠች የምትኖር ሴት ሕይወት ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ከግብፃዊ ባለቤቷና ሴት ልጇ ጋር ኑሮዋን በአሜሪካ ያደረገችው እንስቷ፣ እ.ኤ.አ. በ2011 ግብፅ ውስጥ ስለተካሄደው አብዮት ትተርካለች፡፡

ለዓመታት በሥልጣን ላይ የቆዩትን የቀድሞው የግብፅ ፕሬዚዳንት ሆስኒ ሙባረክ አስተዳደርን በመቃወም ሠልፍ ስለወጡ የአገሪቱ ዜጎች ስሜት ታስረዳለች፡፡ ዕድሜና ፆታ ሳይለይ ከፍተኛ ንቅናቄ ስለታየበትና የመላው ዓለምን ትኩረት ስለሳበው አብዮት እንዲሁም እ.ኤ.አ. 2001 በአሜሪካ መንታ ሕንፃዎች ላይ ስለደረሰው ጥቃትም ታነሳለች፡፡ ሁለቱን ሁነቶች ዛሬ ዓለም ላይ ከሚስተዋለው ለውጥ ጋር አያይዛም ትተርካለች፡፡ ቴአትሩ በታሒር ስኩዌር የነበረውን ድባብ በቪዲዮ ከማቅረቡ ጎን ለጎን በተለያዩ ግብአቶች የታጀበም ነው፡፡

በግብፃዊቷ ጸሐፊና አዘጋጅ ዳሊያ ባሲዮን የተሰናዳው ‹‹ሶልቴር››፣ መጀመሪያ የታየው እ.ኤ.አ. በ2011 ግብፅ፣ ካይሮ ውስጥ ነበር፡፡ ቴአትሩ በኢራቅና ሞሮኮም የቀረበ ሲሆን፣ ባለፈው ሳምንት ደግሞ በአዲስ አበባ ባህልና ቴአትር አዳራሽ መድረክ ለእይታ በቅቷል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

‹‹ሶልቴር›› ወደ ኢትዮጵያ የመጣው በክሮሲንግ ባውንደሪስ ፌስቲቫልና ኮንፍረንስ አማካይነት ነው፡፡ ዘንድሮ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ የተካሄደው ፌስቲቫሉ፣ ኢትዮጵያን ጨምሮ ከአሥራ አንድ አገሮች የተውጣጡ የሥነ ጥበብ ባለሙያዎችን አሳትፏል፡፡ ከመስከረም 13 እስከ 16 ቀን 2008 ዓ.ም. የዘለቀው ፌስቲቫሉ ከኢትዮጵያ፣ ብሩንዲ፣ ግብፅ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ ዩጋንዳ፣ ኬንያ፣ ሱዳን፣ እስራኤልና አሜሪካ የተውጣጡ ትዕይንቶች ተስተናግደውበታል፡፡ 67 ባለሙያዎች የተሳተፉ ሲሆን፣ 19 ትዕይንቶች በተለያዩ ቴአትር ቤቶች፣ የባህል ማዕከሎችና በጎዳናም ቀርቧል፡፡

ከጎዳና ትዕይንቶቹ መካከል የመክፈቻው እለት በመርካቶ ምንአለሽ ተራ የቀረበው ፐርፎርማንስ ዓርትና ውዝዋዜን ያጣመረው ትርኢት ይጠቀሳል፡፡ ሙዚቀኞችና ገጣሚዎች የተዋሀዱበት ግጥምን በጃዝ ዝግጅት፣ የብርሃኑ ዘሪሁን ኤክስፐርመንታል ቴአትር ‹‹የብርሃን መንገድ›› እና የመዓዛ ወርቁ ‹‹ከሰላምታ ጋር›› ከኢትዮጵያ ትዕይንቶች ጥቂቱ ናቸው፡፡

ከአህጉር አፍሪካ ከተውጣጡቱ፣ የብሩንዲው ‹‹ዲቻየርመንት››፣ የታንዛኒያው ‹‹ቹዋኖ›› የኬንያው ‹‹ፉሞ ሊዮንጎ›› እና የሱዳኑ ‹‹ሲናር ክሩኪብል›› ይጠቀሳሉ፡፡ በእነዚህ የሥነ ጥበብ ሥራዎች የየአገራቸውን ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ገፅታ ያንፀባረቁ ባለሙያዎች ይገኙበታል፡፡ የብሩንዲው ‹‹ዲቻየርመንት›› በአገሪቱ ፓለቲካዊ ቀውስና ማኅበራዊ ውጣ ወረድ ላይ ያተኮረ ነው፡፡ ‹‹ፉሞ ሊዮንጎ›› በብሔራዊ ሙዝየም ግቢ ውስጥ የቀረበ ሲሆን፣ በ9ኛውና በ13ኛው ክፍለ ዘመን አካባቢ አንደኖረ ስለሚነገርለት ፉሞ ሊዮንጎ አኗኗርና አሟሟት ይተርካል፡፡

‹‹የሚስቶቼ ባሎች›› እና ‹‹ፌስ ቡክ›› ከአሜሪካ በመጡ ባለሙያዎች የቀረቡ ናቸው፡፡ በተጨማሪም አናንያ የዳንስ ግሩፕ በተፈጥሮ ሀብትና ሴቶች ላይ ያተኮረ ኮንቴምፓረሪ ዳንስ አቅርበዋል፡፡ ከኢትዮጵያ ከወጣ ዓመታት ባስቆጠረው እሥራኤላዊው ማንደፍሮ ፈረደህ የተዘጋጀው ትዕይንት ደግሞ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር መድረክ ከተስተናገዱ ትዕይንቶች አንዱ ነው፡፡ በፌስቲቫሉ መዝጊያ ባለሙያዎቹ በመስቀል አደባባይ ተገኝተው የደመራ ሥነ ሥርዓትን ታድመዋል፡፡

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲና ጎተ ኢንስቲትዮት በሥነ ጥበብ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ውይይቶች ተካሂደዋል፤ ልዩ ልዩ ጥናታዊ ጽሑፎችም ቀርበዋል፡፡ የፌስቲቫሉ አርቲስቲክ ዳይሬክተር አርቲስት አዜብ ወርቁ፣ ለሪፖርተር እንደተናገረችው፣ በባለሙያዎች መካከል የልምድ ልውውጥ ማካሄድና ጥበባዊ ሥራዎችን መጋራት ከፌስቲቫሉ ዓላማዎች ጥቂቱ ናቸው፡፡

‹‹ከዓላማችን አንዱ የሆነው በሥነ ጥበብ ድንበርን መሻገር ተሳክቷል፤›› የምትለው አርቲስት አዜብ፣ እርስ በእርስ ፖለቲካዊ ውጥረት ውስጥ የሚገኙ አገሮች ያለ ልዩነት የታዩበት ፌስቲቫል እንደሆነ ታስረዳለች፡፡ በሌላ በኩል ከተለመደው የቴአትር ቅርፅ ውጪ ከተዘጋጁ ቴአትሮች ባለሙያዎች ልምድ እንደቀሰሙ  ታምናለች፡፡

እንደ እሷ ገላጻ፣ ከተለያዩ አገሮች የመጡት ባለሙያዎች እንደ ግጥምን በጃዝ ባሉ የኢትዮጵያ ትዕይንቶች ተማርከዋል፡፡ ዘንድሮ ከተሳተፉ አገሮች በተጨማሪ ሌሎችም አገሮች ተካፋይ የመሆን ፍላጎት አሳይተዋል፡፡ ፌስቲቫሉንም ዓመታዊ የማድረግ እቅድ አላቸው፡፡ ስፖንሰር ከማግኘት ጀምሮ ሌሎችም መሰናክሎች ቢገጥሟቸውም፣ ለመደገፍ ፍቃደኛ የሆኑ ተቋሞች በአይነት ድጎማ ማድረጋቸው ነገሮችን እንዳቀለለላቸው ትናገራለች፡፡

አብዛኞቹን ቴአትሮች የመረጡት የአዘጋጅ ኮሚቴው አባላት በሰንዳንስ ፌስቲቫል ላይ ከነበራቸው ቆይታ በመነሳት ሲሆን፣ የቴአትራቸውን ጽሑፍ አስገብተው በአማካሪዎች ተጠቁመው የተካተቱም አሉ፡፡ አርቲስቲክ ዳይሬክተሯ፣ ለኢትዮጵያውያን ተመልካቾች ቢቀርቡ መልካም ይሆናሉ ብለው ያመኑባቸውን ሥራዎችና ባለሙያዎች እንደጋበዙ ገልጻ፣ በሥነ ጥበብ የተቀረጸ ማኅበረሰብ በመፍጠር ረገድ ፌሲቲቫሉ የራሱን አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት አክላለች፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው በቴሌቪዥን የሚተላለፈውን ዜና በመደነቅ እየተመለከቱ አገኟቸው]

እንዲያው የሚደንቅ ነው እኮ። ምኑ? ዜና ተብሎ በቴሌቪዥን የሚተላለፈው ነገር ነዋ፡፡ ምኑ...

በኦሮሚያ የሚፈጸሙ ግድያዎችና የተጠያቂነት መጥፋት

የካቲት 11 ቀን 2016 ዓ.ም. ቢሾፍቱ አቅራቢያ በሚገኘው የዝቋላ...

የኢትዮጵያ መዋዕለ ንዋይ ገበያ ከሚያስፈልገው ካፒታል ውስጥ 90 በመቶውን ሰበሰበ

እስካሁን 15 ባንኮች የመዋዕለ ንዋይ ገበያው ባለድርሻ ሆነዋል የኢትዮጵያ መዋዕለ...

አዲሱ የንብ ባንክ ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር ቢሊዮን ብር ለማሳደግ ማቀዱ ተሰማ

አዲሱ የንብ ኢንተርናሽናል ባንክ የዳይሬክተሮች ቦርድ የባንኩን ካፒታል በአሥር...