Wednesday, February 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየመስቀል በዓል ባልተገባ መንገድ እንዳይተዋወቅ ጥንቃቄ ያሻል ተባለ

የመስቀል በዓል ባልተገባ መንገድ እንዳይተዋወቅ ጥንቃቄ ያሻል ተባለ

ቀን:

የመስቀል ክብረ በዓል በዓለም አቀፍ የሳይንስና የትምህርት ድርጅት (ዩኔስኮ) መዝገብ ላይ ከሰፈረ ሁለት ዓመት ተቆጥሯል፡፡ በማይዳሰሱ ቅርሶች (ኢንታንጀብል ሔሪቴጅ) ዘርፍ የተመዘገበው የመስቀል አከባበር፣ ቱሪስቶች ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ጥሪ ከሚደረግባቸው ሁነቶችም አንዱ ነው፡፡ የመስቀል ክብረ በዓል መስከረም 16 እና 17 ቀን 2008 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች በደማቅ ሁኔታ ተከብሯል፡፡

በዓሉ በዩኔስኮ መመዝገቡና ቱሪስቶችን እንዲስብ በስፋት መተዋወቁ መልካም ሆኖ ሳለ፣ መስቀልን ከንግድ አንፃር ብቻ መመልከት እንዲሁም ባልተገባ መንገድ ማስተዋወቅ (ኦቨርኮሜርሽያላይዜሽን) ተገቢ እንዳልሆነ የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ባዘጋጀው ውይይት ላይ ተገልጿል፡፡

መስከረም 15 ቀን 2008 ዓ.ም. በመሥሪያ ቤቱ ‹‹የመስቀል ክብረ በዓል ለቱሪዝም ልማት›› በሚል መሪ ቃል በተዘጋጀው ውይይት፣ የመስቀል አከባበር ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን ሳይለቅ ከትውልድ ወደ ትውልድ እንዲሸጋገር ጥንቃቄ እንደሚያሻ ተገልጿል፡፡

መስቀል በዩኔስኮ በተመዘገበበት ወቅት፣ በዓሉ ቱሪስቶችን እንዲስብ ጥቅም ላይ የሚውሉ ማስታወቂያዎችና የበዓሉ አከባበርም ፈር እንዳይለቅ ዩኔስኮም ማሳሰቡን የገለጹት፣ በተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች ያለው የመስቀል አከባበር ላይ ጥናት የሠሩት  አቶ ደመረው ዳኜ ናቸው፡፡ የበዓሉ ገፅታ ለንግድ ዓላማ ተብሎ እንዳይለወጥ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

እንደ አጥኚው ገለጻ፣ አንድ ቅርስ በዩኔስኮ ከተመዘገበ በኋላ የቅርሱ ባለቤት አገር ከሚያደርግለት ጥንቃቄ ባሻገር አላግባብ ጥቅም ላይ እንዳይውል መጠበቅም ያስፈልጋል፡፡ መስቀል በዩኔስኮ መመዝገቡ የቱሪስት ፍሰትን እንደሚጨምር በመግለጽ፣ ወደ አገሪቱ የሚመጡ ቱሪስቶች ስለ በዓሉ አከባበር ትክክለኛ መረጃ ማግኘት እንዳለባቸውም አክለዋል፡፡

ክርስትና ወደ ኢትዮጵያ ከመጣበት ዘመን ጀምሮ የሚከበረው የመስቀል በዓል፣ በተለያየ መንገድ ይዘከራል፡፡ መስቀልን እንደ ዘመን መለወጫ ከሚያከብሩ ብሔረሰቦች መካከል የየምና ወላይታ ብሔረሰብን መጥቀስ ይቻላል፡፡

መስቀልን ከእርቀ ሰላም መውረድ፣ ከቤተሰብ መሰባሰብና አብሮነት ጋር የሚያያይዙ እንደ ጠንባሮና ጉራጌ ያሉ ብሔረሰቦችም ይነሳሉ፡፡ በከተማ ቀመስ አካባቢዎች ደግሞ የአንድ ሰፈር ሰዎች ተሰባስበው ደመራ ሲደምሩ፣ አንዳንድ ሆቴሎችና መዝናኛዎችም ለበዓሉ ልዩ ዝግጅት ሲያሰናዱ ይስተዋላል፡፡

አቶ ደመረው በየስፍራው ያለውን የበዓሉን አከባበር ጠቅሰው፣ ‹‹በዓሉ በቅርስነት ከተመዘገበ በኋላ ያሉት አካሄዶች መፈተሽ አለባቸው፤›› ብለዋል፡፡ የአጥኚውን ሐሳብ  የሚጋሩት የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዮናስ ደስታ በቡኩላቸው፣ የመስቀል በዓል ከንግድ አንፃር ብቻ እንዳይታይ የሚል መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

በዓሉ እሴቱን ጠብቆ መተዋወቅ እንዳለበት፣ ‹‹መስቀል ከአገራዊ በዓልነቱ አልፎ አኅጉራዊና ዓለም አቀፋዊም ነው፤ እሴቱ ሳይበረዝ ቱሪስቶችን በመሳብ ጥቅም ላይ መዋል አለበት፤›› በማለት ገልጸዋል፡፡

የውይይቱ ተካፋይ ከነበሩ ግለሰቦችና የዘርፉ ባለሙያዎች ከቀረቡ አስተያየቶች መካከል በየብሔረሰቡ ያለው አከባበር ትኩረት ሊሰጠው ይገባል የሚለው  ይጠቀሳል፡፡ በበዓሉ ልዩ ዝግጅት ከሚያደርጉ ሆቴሎችና ሌሎችም መዝናኛዎች መካከል ገንዘብ ለማግኘት ብቻ የሚያውሉት እንዳሉ የገለጹም ነበሩ፡፡ ቱሪስቶችን ከመሳብ ባሻገር ከመጡ በኋላ የሚቀርብላቸው መረጃ ወጥና ትክክለኛ እንዲሆን ባለድርሻ አካላት እንዲረባረቡ ያሳሰቡ አስተያየት ሰጪዎችም ነበሩ፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የገጠር መሬት ማሻሻያና የመሬት ባለቤትነት ጥያቄ በኢትዮጵያ

በኢትዮጵያ ከቅርብ ወራት ወዲህ መሬትን በተመለከተ ጠንከር ያሉ የለውጥ...

በፖለቲከኞች እጅ ያለው ቁልፍ

ኢትዮጵያ በተለይ ካለፉት አምስት ዓመታት ወዲህ ሰላሟ መረጋጋት አቅቶታል፡፡...

የኤክሳይስ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ፓርላማው ያፀደቀውን አዋጅ የሚጥሱ ድንጋጌዎችን በማካተቱ እንዳይፀድቅ ተጠየቀ

ሰሞኑን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የኤክሳይስ ታክስ ማሻሻያ...

በፀጥታ ችግር ሳቢያ ከተለያዩ አካባቢዎች ተፈናቅለው አማራ ክልል የገቡ ዜጎች ቁጥር 800 ሺሕ መድረሱ ተነገረ

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል 112 ሺሕ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ...