Sunday, May 26, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዓለምየተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባዔን የከፋፈለው የሶሪያ አጀንዳ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጉባዔን የከፋፈለው የሶሪያ አጀንዳ

ቀን:

በሶሪያ የፕሬዚዳንት በሽር አል አሳድን መንግሥት ለመገርሰስ ከአራት ዓመት በፊት የተጠነሰሰው አብዮት መስመሩን ስቶ ሶሪያን በታትኗታል፡፡ ለዜጐቿ ሞትና ስደት ምክንያት ሆኗል፡፡ ለአብዮት የተጠራ የተቃውሞ ሠልፍ አቅጣጫውን ስቶ ለአራት ዓመት ለዘለቀ የእርስ በርስ ጦርነት መነሻ ሆኗል፡፡ በእነዚህ ጊዜያት 250,000 ሶሪያውያን ሲሞቱ፣ አንድ ሚሊዮን ያህል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ አራት ሚሊዮን ከአገራቸው ሲሰደዱ፣ 11 ሚሊዮን ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል፡፡

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በቅርስነት የመዘገባቸውና ያልመዘገባቸው የሶሪያ ቅርሶች ወድመዋል፡፡ መሠረተ ልማቶች ፈራርሰዋል፡፡ አገሪቷን የአሳድ መንግሥት፣ አሸባሪው አይኤስ፣ ሸማቂዎችና ኩርዶችን ጨምሮ ከስምንት ያላነሱ ኃይሎች ተቀራምተዋታል፡፡ በአገር ውስጥ በአል አሳድ መንግሥት ላይ የተነሱ የተለያዩ ኃይሎች፣ የተለያዩ ፍላጐቶቻቸውን በማንፀባረቅ አገሪቷን ለውድመት ሲዳርጉ፣ ከውጭ ያሉት ኃያላን መንግሥታት ደግሞ አገሪቷን ለመታደግ አልቻሉም፡፡ እነሱም በየግል ፍላጐቶቻቸው ተጠልፈው ሶሪያን የጦርነት መናኸሪያ አድርገዋታል፡፡

የሶሪያ አጐራባቾች እንዲሁም ወዳጅ አገሮች ባለፉት አራት ዓመታት ለሶሪያ የፈየዱት ነገር የለም፡፡ በሶሪያ ጉዳይ እርስ በርስም ለመስማማት ተስኗቸዋል፡፡ የእነሱ አለመስማማትና በሶሪያ ላይ ያላቸው የየግል ፍላጐት ደግሞ ለሶሪያ ሌላ ቀውስ ሆኗል፡፡

- Advertisement -

አል አሳድ በአገራቸው ያሉ ሸማቂዎችን ለማጥፋት ከውስጥ ሲዋጉ፣ እሳቸው እንዲወድቁ የሚፈልጉት አገሮች ደግሞ ሸማቂዎችን ያስታጥቃሉ፡፡ በዚህም የሶሪያ ዜጐች ተጐጂ ሆነዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም ለስደት ከአገራቸው የወጡ ሶሪያውያን የባህር ሲሳይ፣ የተረፉትም በተለይ ለአውሮፓ አገሮች ፈተና ሆነዋል፡፡

የሶሪያን ግጭት ለመፍታት በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሆነ በኃያላን አገሮች ሲደረጉ የነበሩ ጥረቶች ከሽፈዋል፡፡ የታየ መፍትሔም የለም፡፡

ኃያላን መንግሥታትም ሆኑ የሶሪያ አጐራባች አገሮች እርስ በርስ እየተወዛገቡ ነው፡፡ ኢራን፣ ሩሲያ፣ የሊባኖስ ሒዝቦላህ ንቅናቄ የአል አሳድን መንግሥት ሲደግፉ ቱርክ፣ ሳዑዲ ዓረቢያና ኳታር አል አሳድን ይቃወማሉ፡፡ አሜሪካ፣ እንግሊዝና ፈረንሣይ አል አሳድን ከሚቃወሙት የሚመደቡ ናቸው፡፡

በሶሪያ ጉዳይ አንድ መሆን ያቃታቸው አገሮች ተቃርኖ ጐልቶ የወጣው ደግሞ፣ በኒው ዮርክ በመካሄድ ላይ ባለው 70ኛው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ነው፡፡

የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ ባን ኪሙን፣ ከ150 በላይ አገር መሪዎች በታደሙበት ጉባዔ ‹‹ሩሲያ፣ አሜሪካ፣ ሳዑዲ ዓረቢያ፣ ቱርክና ኢራን ለሶሪያ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለማፈላለግ ቁልፍ የነበሩ አገሮች ናቸው፡፡ ሆኖም አገሮቹ እርስ በራሳቸው ፍላጐቶቻቸውን አጣጥመው መሄድ ካልቻሉ፣ በሶሪያ ለውጥ ይመጣል ብሎ መጠበቅ ትርጉም አልባ ነው፤›› ማለታቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡

የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን፣ ባን ኪሙን በጠቀሷቸው አገሮች ላይ ግብፅን ጨምረው የሶሪያን ጉዳይ ለመፍታት የሚችል ዓለም አቀፍ ተጠሪ ቡድን ለማቋቋም የሚያስችል ዕቅድ እንደሚያስፈልግ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

አሜሪካና ፈረንሣይ ደግሞ፣ ‹‹አል አሳድ ከሥልጣን መውረድ አለባቸው›› ሲሉ አቋማቸውን አሳውቀዋል፡፡ ሩሲያ ግን የፈረንሣይና የአሜሪካን ሐሳብ ‹‹ትልቅ ስህተት›› ስትል አጣጥላዋለች፡፡ አሸባሪውን አይኤስ ለማጥፋት መንገዱ ከአል አሳድ ጋር መሥራት ብቻ ነው ስትልም ገልጻለች፡፡

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር ለ90 ደቂቃዎች ያህል የተናጠል የጐንዮሽ ውይይት ያደረጉት ቭላድሚር ፑቲን፣ ሩሲያ በአይኤስ ላይ የአየር ጥቃት የሚፈጽመውን ጥምር ኃይል ልትቀላቀል እንደምትችል፣ ይህ የሚሆነው ግን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአየር ጥቃቱን ከደገፈው ብቻ እንደሚሆን አሳውቀዋል፡፡

ሁለቱ መሪዎች በሶሪያ ላለው ቀውስ ፖለቲካዊ መፍትሔ ለማድረግ ቢስማሙም፣ አል አሳድ የሶሪያ የወደፊት ፕሬዚዳንት ይሁኑ ወይም አይሁኑ በሚለው ሐሳብ ላይ ግን መስማማት አልቻሉም፡፡

ከዚሁ ጋር በተያያዘ፣ ሩሲያ ለሶሪያ የጦር መሣሪያ ድጋፍ እያደረገች እንዲሁም የውትድርና ቁሳቁስ ኤክስፐርቶችን እየላከችም ነው፡፡ ይህ ለእስራኤል ሌላ ራስ ምታት ነው፡፡ የሶሪያን መንግሥት የሚረዳው ሒዝቦላህ የእስራኤል ጠላት፣ የሶሪያ መንግሥት ደግሞ ወዳጅ ነው፡፡ ከኢራንና ከሩሲያ ጐን በመሆንም የአል አሳድን መንግሥት ይደግፋል፡፡ የእስራኤል ሥጋት ደግሞ ሩሲያ ወደ ሶሪያ የምትልከው የጦር መሣሪያ ሒዝቦላህ እስራኤልን ለማጥቃት ቢጠቀምበትስ የሚል ነው፡፡

ይህን ሥጋት ይዘው ሰሞኑን ወደ ሞስኮ አቅንተው የነበሩት የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንጃሚን ኔታንያሁ ከፑቲን ጋር መክረዋል፡፡

ኔታንያሁ በሶሪያ ያለው የሩሲያ መከላከያ ኃይል አለመግባባት ተፈጥሮ ከእስራኤል መከላከያ ኃይል ጋር ሊጋጭ ይችላል የሚል ሥጋት አላቸው፡፡ ሩሲያ ደግሞ ይህ አያሰጋትም፡፡ ፑቲን እንደሚሉት፣ ሩሲያ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚኖራት ጣልቃ ገብነት በሙሉ በኃላፊነት የተሞላ ነው፡፡

ኔታንያሁና ፑቲን በክሬምሊን ቤተ መንግሥት የነበራቸውን ውይይት በአዎንታዊ መልኩ እንዳጠናቀቁት ሮይተርስ ዘግቧል፡፡ ሞስኮ በሶሪያ እንዲሁም እስራኤል በጐላን ያላቸውን ወታደራዊ ቅኝት አቀናጅተው ለመሥራትም ተስማምተዋል፡፡

ሮይተርስ ኔታንያሁን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ በእስራኤልና በሩሲያ መከላከያ ኃይል መካከል አለመግባባት እንዳይፈጠር የሚያስችል አሠራር ለመቀየስ ወደ ሞስኮ ያደረጉት ጉዞ የተሳካ ነበር፡፡ ሁለቱ አገሮች አብረው በሚሠሩበት ሁኔታ ላይም ከስምምነት ደርሰዋል፡፡ ሆኖም እንዴት? የሚለው አልተገለጸም፡፡

አሜሪካና ሩሲያ በሶሪያ ጉዳይ ሲመክሩ ከርመዋል፡፡ ኃያላን አገሮች በመካከለኛው ምሥራቅ በሚያደርጉት ፍትጊያ ውስጥ እስራኤል ገለልተኛ ልትሆን አትችልም፡፡ ከሶሪያ ጋር በተያያዘ አሜሪካ የእስራኤልን ፍላጐት ታስጠብቃለች፡፡ ሩሲያ ደግሞ የኢራንን፡፡ በዚህ ሁሉ መሀል ተጐጂ የሆኑት ሶሪያውያን ናቸው፡፡ በመሆኑም የእስራኤልና የሩሲያ፣ የሩሲያና የአሜሪካ ከስምምነት መድረስ ለሶሪያ ሰላም ሊያመጣ ይችላል፡፡ ሆኖም እውን ይሆን ወይ? የሚለው ለኃያላኑ አገሮች ብቻ ሳይሆን ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅትም ሥጋት ነው፡፡ መንግሥታት ፍላጐቶቻቸውን ገታ አድርገው በሶሪያ ምድር እየፈሰሰ ስላለው ደም ማሰብ ካልጀመሩ፣ ሶሪያ የሰላም አየር አትተነፍስም እየተባለ ነው፡፡       

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...