Saturday, September 30, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርየመንግሥትን ትኩረት ያጣው የሕዝብና የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት

የመንግሥትን ትኩረት ያጣው የሕዝብና የጭነት ትራንስፖርት አገልግሎት

ቀን:

በታደሰ ዓለሙ

አገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በሁለንተናዊ መልኩ እጅግ በፈጣን የዕድገት ጎዳና ላይ ትገኛለች፡፡ ይህም ሀቅ ከአገር ውስጥ እስከ ውጭ ድረስ ይነገራል፡፡ ተጨባጭ እውነታውንም ዓይተው መስክረዋል፡፡ አገራችን በፀጥታዋ ተመራጭ የሆነች፣ በዓለም ደረጃ የቱሪስት መዳረሻ ሆናም መመረጧና ትልልቅ በዓለም አቀፍ ስብሰባዎችን በማስተናገድ በብቃት የተወጣች መሆኑ ማንኛውንም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የሚያኮራና ልባችንን በሐሴት የተሞላ ያደርገዋል፡፡ ሆኖም በትራንስፖርት የሥራ ዘርፍ ስንመለከተው በአየር ትራንስፖርት የአፍሪካ ኩራት የሆነውና በዓለም አቀፍ ደረጃ በአገልግሎት አሰጣጡ በተደራሽነቱ አንቱታን ያተረፈው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ይጠቀሳል፡፡ በባቡር ትራንስፖርትም በአሁኑ ወቅት ከአዲስ አበባ-ጂቡቲ በአዲስ መልክ ተጠናክሮ እየተሠራ ያለውና በአዲስ አበባ ከተማ በቅርቡ ሥራ የሚጀምረው የቀላል ባቡር ግንባታ፣ በሌሎች አካባቢዎችም ወደ ሥራ ለመግባት የመሠረት ድንጋያቸው የተጣሉ በርካታ ፕሮጀክቶች በተጨባጭ ይታያሉ፡፡ በባህር ትራንስፖርትም የዘመናዊ መርከቦች ባለቤት የሆነው የኢትዮጵያ መርከብ ድርጅት የሚሰጠው አገልግሎት ከዕለት ወደ ዕለት እየተሻሻለ የመጣ መሆኑን በተጨባጭ የሚታዩ እውነታዎች አሉ፡፡ በመርከብ ድርጅት ኦፕሬሽን ሥራ ላይ የሚታዩ አንዳንድ የአሠራር ክፍተቶች እንዳሉ ሆኖ፡፡ በትራንስፖርት ዘርፍ አብዛኛው የአገራችን ኅብረተሰብ የሚጠቀምበት የሕዝብና የጭነት ማመላለሻ እንቅስቃሴን ሌሎች ተጓዳኝ አገልግሎቶች ወይም የአገልግሎት አሰጣጡን ስንቃኝ ግን፣ ከላይ ከጠቀስናቸው ተቋማት አንፃር ሲታይ እጅግ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡ በሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ላይ የሚታዩ ችግሮችን በተለያየ ወቅትና ጊዜ ከኅብረተሰቡና ከባለድርሻ አካላት ቢቀርቡም የሚታይ ለውጥ ግን አይታይም፡፡ ችግሮቹ ምንድናቸው በሚል በዝርዝር ስንመለከታቸው፡-

በሕዝብ ማመላለሻ ዘርፍ በተለይ በትራንስፖርት ባለሥልጣን ቁጥጥር ሥር የሚገኘው በአገር አቋራጭ የትራንስፖርት አገልግሎት የሚሰጡ ኦፕሬተሮች የሥምሪት አገልግሎት ለመስጠት በማኅበር፣ በኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበርና በአክሲዮን ተደራጅተው አገልግሎት ይሰጣሉ፡፡ በአክሲዮን ተደራጅተው ከሚሰጡት ውስጥ ሰላም የሕዝብ ማመላለሻ፣ ስካይ ባስ ትራንስፖርት፣ ሊማሊሞ የሕዝብ ማመላለሻ በአክሲዮን ተደራጅተው ለኅብረተሰቡ የራሳቸውን ታሪፍ ራሳቸው እያወጡ በገበያ መርህ መሠረት የተሻለ ግልጋሎት ለኅብረተሰቡ እየሰጡ መሆኑን የሚታይ ሀቅ ነው፡፡ ይህንን ስንል ከሌሎች በማኅበር ተደራጅተው ከሚሠሩት ኦፕሬተሮች ጋር በማነፃፀር ሲሆን፣ በራሳቸው ብዙ ክፍተቶች የሉባቸውም ማለት አይደለም፡፡ እነዚህም ቢሆኑ የራሳቸው መናኸሪያ በመነሻም ሆነ በመድረሻ ቦታዎች ላይ የሌላቸው መሆኑን ልብ ሊሉ ይገባል፡፡ በአንፃሩ በአዋጅ ቁጥር በ468/97 መሠረት በማኅበር ተደራጅተው የሚገኙ የአገር አቋራጭ ማኅበራት ግን አደረጃጀታቸው የተሻለ ግልጋሎት እንዲሰጡ የሚያግዳቸው በማኅበር ተቀጥረው አመራር የሚሰጡ ከሥራ አስኪያጅ እስከ ታችኛው ሠራተኛ ድረስ የባለሀብቱን ጥቅም ማስከበር ብቻ እንጂ፣ ለኅብረተሰቡ ግልጋሎት እርካታ የሚሰጡት ግምት አነስተኛ ነው፡፡ ይህም ህልውናቸው የተመሠረተው በባለሀብቱ ከሚያገኙት የአገልግሎት ኮሚሽን በመሆኑ ይህ ከተቋረጠ በሥራው ላይ የመቆየት ህልውናቸው አደጋ ውስጥ ሊገባ ስለሚችል ለባለሀብቱ ወገንተኝነት ብቻ የቆሙ ናቸው፡፡ በተጨማሪም በማኅበር አመራር አባልነት የሚመረጡ አካላት ለዘርፉ ሁለንተናዊ ዕድገት ወይም ለኅብረተሰቡ እርካታ እንዲመጣ አበክረው የሚሠሩ ሳይሆኑ፣ ግለኝነት የሚያጠቃቸውና እርስ በርስ ያላቸው የሥራ ግንኙነትም እጅግ በጣም የወረደ መሆኑን በየጊዜው የሚሰሙ እውነታዎች ናቸው፡፡ ስለሆነም ይህንን ዘርፍ የተሻለ ለማድረግና ኅብረተሰቡ የተሻለ የአገልግሎት እርካታ እንዲያገኝ፣ ባለሀብቱም በውድድር መንፈስ እየሠራ የተሻለ ተጠቃሚ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግና መንግሥትም የኅብረተሰቡን እርካታና የባለሀብቱን ተጠቃሚነት እያየ የበኩሉን አስተዋጽኦ ለዘርፉ ዕድገት እንዲያደርግ፣ አሁን ያለው የማኅበራት አደረጃጀት ሙሉ በሙሉ ሊለወጥ ይገባል፡፡ ምክንያቱም ከ1984 ዓ.ም ጀምሮ እየተሠራበት ሆኖ ነገር ግን ምንም የተሻለ አገልግሎት አሰጣጥ ያልታየበት፣ ባለድርሻ አካላትና አገልግሎት ፈላጊው ኅብረተሰብ ያልረካበት፣ ተጠያቂነት የሌለበትና ጥቂቶች ብቻ የበለፀጉበት አደረጃጀት በመሆኑ መንግሥት ይህንን አደረጃጀት ሊፈትሸውና ሊያስተካክለው ይገባል፡፡

በመሠረቱ በማኅበር መደራጀት መብት ቢሆንም የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ትልቁ ሥራው ማኅበራትን መገንባትና ማፍረስ ብቻ መሆን የለበትም፡፡ ከ1984 ዓ.ም. እስከ አሁን ድረስ ስንቶች ፈረሱ? ስንቶችስ ተቋቋሙ? በምን ዓይነት መሥፈርት ተቋቋሙ? የፈረሱት ማኅበራትስ ንብረትና ሀብት የት ደረሰ? ሕጉስ ምን ይላል? ብዙ ጥያቄዎችን የሚያስነሳ፣ ነገር ግን በተጨባጭ መልስ የሌለው እውነት ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት ማኅበራትን የሚያቋቁመው ለኅብረተሰቡ የተሻለ ግልጋሎት ይሰጣሉ ብሎ አልሞና አቅዶ ወይም በመደራጀት መብት ታሳቢ አድርጎ ሳይሆን፣ የራሱን ትክክለኛ ያልሆነ አሠራር የሚነቅፉና የሚተቹ ማኅበራትን ለማዳከምና ደጋፊ ለማብዛት ነው፡፡ ግለሰቦችን በማኅበር ስም ልዩ ተጠቃሚ ለማድረግ ነው የሚሉ አስተያየት ሰጪዎች ይደመጣሉ፡፡ ስለሆነም ማኅበራት አሁን ያላቸው የአደረጃጀት መሥፈርት ተለውጦ ተጠያቂነት ያለባቸው፣ ለኅብረተሰቡ ትክክለኛ አገልግሎት ሊሰጥ የሚያስችል አደረጃጀት ተከትለው እንዲደራጁ መደረግ አለበት፡፡

የአገልግሎት አሰጣጥ

በአገር አቋራጭ የሕዝብ ማመላለሻ ዘርፍ አሁን የሚታየው የአገልግሎት አሰጣጥ ተሽከርካሪዎች በደረጃ ለይቶ የቀለም ቅባቸው የተለያዩ ከመሆን በዘለለ፣ ለኅብረተሰቡ የሚሰጡት ግልጋሎት ተሻሽሏል ለማለት ያስቸግራል፡፡ ለዚህም እንደ አብነት የሚጠቀስ፡-

የሠራተኞች የሥነ ምግባር ሁኔታ

በሕዝብ ማመላለሻ ዘርፍ በማኅበራት ተቀጥረው የሚሠሩ ብዙዎቹ በተሽከርካሪ ላይ የተመደቡ ሠራተኞች የሥነ ምግባር ሁኔታ ሲታይ የደንበኛን ክቡርነት ጠንቅቀው የማያውቁ፣ አገልግሎት ለሚሰጡት ኅብረተሰብ ምንም ከበሬታ የሌላቸው በዕድሜ የሚበልጧቸውን አባቶችና እናቶችን ሳይቀር የሚዘልፉና የሚሰድቡ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ናቸው፡፡    

በመናኸሪያና ከመናኸሪያ አካባቢ የሚገኙ ዕቃ ጫኝና አውራጆች እንደሚሰማውና ብዙ ጊዜ እንደሚነገረው ኅብረተሰቡ እስከ 25 ኪሎ ግራም በነፃ ማስጫንና ማውረድ እንደሚቻል በሚኒ ሚዲያ ቢነገርም፣ ይህንን ተግባራዊ የማያደርጉ እንደፈለጉ ኅብረተሰቡን የሚያስከፍሉ ተቆጣጣሪ አካል የሌላቸው እስከሚመስል ድረስ ኅብረተሰቡን የሚዘርፉ አካላት ያሉበት ተቋም ነው፡፡ እስከ 25 ኪሎ ግራም ድረስ በነፃ አውቶቡሱ ላይ መጫን እንዳለበት ቢነገርም፣ ተግባራዊ የሚያደርጉ ጥቂት አካላት ብቻ እንጂ አብዛኛው በኅብረተሰቡ ላይ የፈለጉትን ሲያስከፍሉ ተመልካችና ሀይ ባይ የሌላቸው ናቸው፡፡ በሕዝባዊ በዓላት በተማሪዎች መግቢያና መውጫ ሰዓት የሚደረግ የሥምሪት ሒደት ኅብረተሰቡን በጋራ ተቀናጅቶ አገልግሎት ከመስጠት ይልቅ፣ ሲስተም ተዘርግቶለት በአግባቡ የማይስተናገድበት፣ ኅብረተሰቡን ለሕገወጦች እንዲጋለጥ እየተዳረገና በጣም የተጋነነ ዋጋ በመክፈል ረጅም መንገድ መጫን ከሚገባው ሰው በላይ በመጫን እንደ ዕቃ በሚኒ ባስ በመታጨቅ የሥጋት ጉዞ እንደሚያደርግ የሚታወቅ ሀቅ ነው፡፡ በመሠረቱ የሕዝብ ክምችት በሚበዛባቸው ወቅታዊ በሆኑ ጊዜያት ኅብረተሰቡ ከገንዘብ ይልቅ ለጊዜ ብዙ ዋጋ እየሰጠ በመሆኑ፣ የተወሰነ ጭማሪ አድርጎ ኅብረተሰቡን በአግባቡ እንዲሸኝ ከማድረግ ይልቅ ማኅበራትም ሆነ አስፈጻሚ አካል ወቅታዊ ምላሽ ለኅብረተሰቡ ስለማይሰጡ ጧት ገብቶ እስከ ማታ ድረስ ትኬት ለማግኘት የሚያጠፋው ጊዜ፣ እንግልት በየጊዜው ሊታረም ያልቻለ ዓበይት ችግር ሆኖ ይታያል፡፡ ልብ ሊባል የሚገባው ኅብረተሰቡ በወቅቱ ካሰበው ቦታ ለመድረስ ሲል በሕገወጦች አላስፈላጊ ክፍያ የሚፈጽም መሆኑን ነው፡፡ ሆኖም መጠነኛ የታሪፍ ማስተካከያ አድርጎ እንዲጓጓዝ ቢደረግ ከኅብረተሰቡ የሚቀርቡ ቅሬታም ሆነ አቤቱታ እንደማይኖር በተጨባጭ የታየ እውነታ ነው፡፡

የመናኸሪያዎች አገልግሎት አሰጣጥ

በአሁኑ ጊዜ በአዲስ አበባ ከተማ በፌደራል ትራንስፖርት ሥር የአገር አቋራጭ አገልግሎት የሚሰጥባቸው መናኸሪያዎች አራት ናቸው፡፡ (አዲስ ከተማ፣ አስኮ፣ ላምበረትና ቃሊቲ መናኸሪያ) የአዲስ ከተማ መናኸሪያ ከተገነባ እጅግ በጣም ረጅም ጊዜ ያደረገና በየጊዜው ዕድሳትም ሆነ ማስፋፊያ ያልተደረገበት፣ አሁን ካለው የኅብረተሰብ ፍላጎት አንፃር የመናኸሪያን ስታንዳርድ ያላሟላ ነው፡፡ የመናኸሪያው ውበትና ፅዳት፣ የመብራትና የደኅንነት፣ የመዝናኛና የእንግዶች ማረፊያ የሌለው፣ በተጨማሪም መፀዳጃ ቤት እንኳን ለመጠቀም የክፍያ ሥርዓት ያለበት እጅግ በጣም ኋላቀር መናኸሪያ ነው፡፡ ከሥምሪት ብዛት አንፃር ተሽከርካሪዎቹን በአግባቡ የመያዝ አቅም የሌለውና የተወሰኑ መስመሮች መንገደኛው ጧት 11 ሰዓት እንዲገኝ ከተደረገ በኋላ እስከ ጧት 3 ሰዓት ድረስ እንኳን ተሽከርካሪው ገብቶ አይስተናገድም፡፡ በእነዚህ መስመሮች ላይ ኅብረሰተቡ በአገር አቋራጭ ከመጠቀም ይልቅ፣ በሕገወጦች እየተጠቀመ ያለበት ሁኔታ ስላለና የትራንስፖርት ባለሥልጣን ይህንን ለመለወጥ ያደረገው ጥረትና እንቅስቃሴ የለም፡፡ መናኸሪያው የትራንስፖርት ባለሥልጣን የመናኸሪያ ስታንዳርድ ብሎ ያወጣውን መሥፈርት የማያሟላ መሆኑን እያወቀ፣ ለማደስም ሆነ ለማስፋፋት ያደረገው ጥረት ባለመኖሩ የችግሮች ሁሉ ችግር ሆኖ ይታያል፡፡ በዚህ ረገድ ትልቁ ተጠያቂ የትራንስፖርት ባለሥልጣን መሆኑ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡

ላምበረትና አስኮ መናኸሪያዎች

ሁለቱ መናኸሪያዎች በአንፃራዊነት ከአዲስ ከተማ መናኸሪያ በፅዳትና በውበት መጠነኛ ለውጥ ቢኖራቸውም፣ የሁለቱም መናኸሪያዎች ስታንዳርድ ወይም መሥፈርት አሟልተው የተሠሩ ባለመሆኑ፣ ለአዲስ አበባ ከተማ ለክፍለ ከተሞች የትራንስፖርት ቢሮ የመንጃ ፈቃድና የተሽከርካሪ ምርመራ ታሳቢ ተደርገው የተሠሩ ናቸው፡፡ ሙሉ በሙሉ መሥፈርቱን የማያሟሉና ኅብረተሰቡ የሚፈልገውን የአገልግሎት አሰጣጥ አሟልተው የተዘጋጁ አይደሉም፡፡ በአጠቃላይ በመናኸሪዎቹ የሚሰጠው አጠቃላይ አገልግሎት ሲታይ እጅግ በጣም ኋላቀርና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈ አይደለም፡፡ የአቅመ ደካሞች፣ የአረጋውያንና የአካል ጉዳተኞችን ታሳቢ ተደርገው ያልተዘጋጁ እንዲሁም ሠራተኛው፣ ባለሀብቱና አስፈጻሚው አካል ተለይቶ የማይታወቅበት ኅብረተሰቡ ቅሬታና አስተያየት ለማቅረብ ችግሩን የሚፈታ ብቻ ሳይሆን፣ የሚያዳምጥ የሌለበት አደረጃጀት ያለበት የሥራ ቦታ ነው፡፡ የትራንስፖርት ባለሥልጣን እጅግ የሆነ ግዙፍ ተቋም ሲሆን፣ በአዋጅ ላይ በተሰጠው ተግባርና ኃላፊነት መሠረት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተነጋግሮ ትኩረት ሰጥቶበት አገሪቱ አሁን የደረሰችበት የዕድገት ደረጃ የሚመጥንና የአገሪቱን ሁለንተናዊ ዕድገትና ዕይታ የሚያመላክት ዘመናዊ የሆነ መናኸሪያ አማካይ በሆነ ቦታ ላይ እንዲሠራ አለማድረጉ ተጠያቂ ያደርገዋል፡፡ ኃላፊነትንም በአግባቡ ያለመወጣት መሆኑን ያሳያል፡፡ በየጊዜው የምንሰማው የአየር ጤና መናኸሪያ በቅርቡ ሥራ ይጀምራል የሚለው የሪፖርት ማሟያ እስካሁን ሥራ አለመጀመሩም ግርምትን የሚጭርና ለኅብረተሰቡ የተሻለ ግልጋሎት እንዳይገኝ ከማድረግና ኃላፊነትን በአግባቡ ያለመወጣት መሆኑን ያሳያል፡፡ በአጠቃላይ የአገር አቋራጭ የትራንስፖርት ዘርፉ ከጥቂት በአክሲዮን ደረጃ ከተደራጁ ማኅበራት ውጪ ያለው የአገልግሎት አሰጣጥ ደረጃውን ያልጠበቀ፣ የኅብረተሰቡን እርካታ ያላመጣ፣ ሲስተም የሌለው፣ በልምድና በዘፈቀደ የሚመራ ተቋም መሆኑን ከሚሰጠው አገልግሎትና አሁን ካለው የመናኸሪያ አደረጃጀት አንፃር የሚታይ ነው፡፡ በክልል ከተሞች እየተሠሩ ያሉት አዳዲስ መናኸሪዎችና ነባሩን በአግባቡ ጠብቆና አዲስ የመያዝ ሁኔታ የፌደራል ትራንስፖርት ባለሥልጣን ትምህርት ሊወስድበት የሚገባ አሠራር ነው፡፡

ቃሊቲ መናኸሪያ

አንድ መናኸሪያ (በዋና ከተማ የሚገኝ) ቀርቶ ከአንድ የገጠር መንደር ውስጥ ያነሰ በቆርቆሮ የታጠረ ሜዳ ሲሆን፣ በአግባቡ የመፀዳጃ ቤት የሌለው ሜዳ ላይ ለመፀዳዳት የክፍያ ሥርዓት ተዘርግቶለት የሚሠራ ሕገወጥ መናኸሪያ ያስመስለዋል፡፡

ሕገወጥ የሥምሪት እንቅስቃሴ

ሕገወጥ የስምሪት እንቅስቃሴን ስናይ በሕጋዊ መልኩ ሕግና ደንብን አክብረው የሚሠሩ የትራንስፖርት ባለሀብቶችን ያቀጨጨ፣ ጥቂት ሕገወጥ ሥራን የሚሠሩ ሕገወጦችን ያበለፀገ የሥራ ሒደት ነው፡፡ የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤት እንደ መንግሥት ተቋም ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ተቀናጅቶ ሕገወጦችን የማስቆም ተከታትሎም ዕርምጃ የመውሰድ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት ተቋም ቢሆንም፣ ቁርጠኝነት ካለመኖርና ሕገወጦች እንዲጠፉም ካለመፈለግ በመነጨ ከጊዜ ወደ ጊዜ ሕገወጥ ሥምሪት የሚደረግበት ቦታና ሥፍራ እየተበራከተ መጥቷል፡፡ ሥልታቸውንም በመቀያየር ሕጋዊ የሆኑ ባለሀብቶችን ያዳከመ ሥራ የሚሠሩና በተጓዳኝ ከተቆጣጣሪው አካል ለመሸሽ ሲሉ በሌሊትና በከፍተኛ ፍጥነት በመጓጓዝ ለትራፊክ አደጋ ኅብረተሰቡን እያጋለጡ መሆኑ የታወቀ ሀቅ ነው፡፡ ትልቁ ጥያቄ መንግሥት ሕገወጦችን እንዲያቆሙ የማድረግ ትልቅ ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም፣ ይህንን ሥራ እንዲሠራ ኃላፊነት ያለበት የትራንስፖርት ባለሥልጣን በፍፁም ሊሠራው አልቻለም፡፡ ይህ በመሆኑ ሕገወጦች ከጊዜ ወደ ጊዜ ራሳቸውን እያጎለበቱና ሕገወጥ ሥምሪት የሚፈጸምባቸውን ቦታዎች እያስፋፉ ነው፡፡ በሌላ ጎን ሲታይ ኅብረተሰቡ ሕገወጥን ለምን ይፈልጋል ሲባል፣ አሁን ባሉት ማኅበራትና በመንግሥት ራሱ ባቋቋመው መናኸሪያ በሚሰጠው አገልግሎት አሰጣጥ ባለመርካቱና ወደሚሄድበት አቅጣጫ በጊዜ ለመድረስ ስለሚፈልግ፣ በተለይ ሕገወጦች ቤቱ ድረስ ሄደው ስለሚያነሡት መናኸሪያ ሄዶ ከሚጉላላ የትራፊክ አደጋ መኖሩንም እያወቀ በሕገወጦች ይጠቀማል፡፡ ስለሆነም ሕገወጥ የሥምሪት እንቅስቃሴን ለማቆም፡-

የመንግሥት አካላት የተቀናጀ የቁጥጥርና የክትትል ሥርዓት ተከታታይነት ባለው መልኩ ማከናወንና ሕገወጦችን ለማስቆም በቁርጠኝነት መነሳት፣ ባለድርሻ አካላት ከእነሱ የሚጠበቀውንና ደንበኛቸውን ወደ እነርሱ ሙሉ በሙሉ እንዲመጣ የሚያስችሉ ሥራዎችን ለመሥራት ራሳቸውን በአቅም፣ በመዋቅር፣ በአደረጃጀትና በሰው ኃይል ብቁ ሆኖ መገኘት ያስፈልጋል፡፡ አሁን ያሉትን መናኸሪያዎች የአገልግሎት አሰጣጣቸውን በማሻሻል ዕድሳት ማድረግና ዘመናዊ የሆነ አገልግሎት ከመስጠት በተጨማሪም፣ የፌደራል ደረጃን የሚመጥን ዘመናዊ የሆነ መናኸሪያ በመገንባት፣ ማኅበራት የአገልግሎት አሰጣጣቸውን ለማሻሻል ሊረዳቸው የሚችለው አሁን ካሉበት ኋላቀር አደረጃጀት ተላቀው፣ ወደ ንግድ ተቋምነት ለመለወጥ ከፍተኛ ንቅናቄ ሲያደርጉ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

ይህን ማድረግ ካልተቻለ ግን ሕገወጥ ሥምሪቱ ይቆማል ብሎ ማሰብ የዋህነት ነው፡፡ ማቆም ብቻ ሳይሆን ባለድርሻ አካላት አሁን የሚሰጡት የአገልግሎት አሰጣጥ እንዴት መለወጥ አለብን? ኅብረተሰቡ ከእኛ የሚፈልገው ምንድነው? ብለው ቆም ብለው ማሰብ ይጠበቅባቸዋል፡፡ አደራጅ መሥሪያ ቤትም ሕገወጥን ከማቆም ባሻገር ኅብረተሰቡ ከሕገወጦች የሚያገኘውን አገልግሎት ሕጋዊ የሆኑ ባለድርሻ አካላት እንዲሰጡ፣ ማበረታታትና አደረጃጀታቸውን ፈትሾ ጠንካራ ባለድርሻ አካላት እንዲፈጠሩ ማድረግ ይጠበቅበታል፡፡

የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር

የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግር የአገሪቱ ትልቅና ቁልፍ ችግር ነው፡፡ ይህንን ቁልፍ የአገሪቱን ችግር ለመፍታት መንግሥት ቁርጠኝነት ያሳየበትና የሞትና የሽረት ሥራ መሆኑን ያሳወቀበት ወቅት ነው፡፡ የትራንስፖርት ዘርፍ ደግሞ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት እጅግ ሥር የሰደዱና የደነደኑ ችግሮች የሚታይበት ነው፡፡ በትራንስፖርት ባለሥልጣን የሚታዩት የመልካም አስተዳደር ችግሮች አንኳር አንኳር የሆኑትን ለመጥቀስ ያህል፣ የወጡ ሕጎችና ደንቦች በአግባቡ ተፈጻሚነት የማይደረጉና አድሎአዊነት የሠፈነበትና ፍትሐዊ የሆነ ውሳኔ የማይሰጥበት፣ አሁን ያለው የማኅበራት አደረጃጀት ለኅብረተሰቡ የሰጠው ጥቅም አለመኖሩ እየታወቀ አደረጃጀቱን ማሻሻልና መለወጥ እየተቻለ የማይሠራ ግን የማይሞት ተቋም በማድረግ ለግለሰቦች መጠቀሚያ ብቻ እንዲሆን መፈለግ፣ የኅብረተሰቡን ቅሬታ፣ አቤቱታና ገንቢ አስተያየቶች የመቀበል ሥርዓት የሌለውና በድርጊት ያልተደገፈ በወረቀት ላይ ብቻ የሠፈረ ቻርተር በማዘጋጀት ኃላፊነትን እንደተወጡ መቁጠር፣ የሚቀርቡ ሪፖርቶች በዘርፉ ላይ ትልቅ ለውጥ እንደመጣ በማስመሰል በሚዲያ ለመንግሥት በሪፖርት በማቅረብ የዘርፉ ችግሮች ጎልተው እንዳይወጡ መሸፋፈን ይታያል፡፡ ለረጅም ጊዜ የሚወጡ ዕቅዶች በተቀመጠላቸው የጊዜ ገደብ አለመሠራታቸው፣ በዘርፉ ትልቁ ተጠቃሚ የሚሆኑ ሦስተኛ ወገኖች አቅፎ በመያዝ የዘርፉ አጠቃላይ አሠራር እንዲበላሽ ለመልካም አስተዳደርና ለኪራይ ሰብሳቢነት ዋነኛ ተዋናይ የሆኑ ደላሎችን በማደራጀት በቲፎዞነት እንዲያገለግሉና የዘርፉን ኃላፊዎች እንደፈለጉ በሚፈልጉት አቅጣጫ እያሽከረከሩ ያሉበትን ሁኔታ ለማስተካከል ቁርጠኝነት አለመኖር፣ ማኅበራትን መሥፈርቱን ሳያሟሉ በማደራጀትና ለቲፎዞነት እንዲያገለግሉ በማድረግ ትልቅ የሆነ የአገልግሎት አሰጣጥ ተመካክሮና በጋራ ተረዳድቶ እንዳይሠራና በሕገወጥ መልኩ ለሚሠሩ አካላት በሕጋዊ ፈቃድ ሕገወጥ ድርጊት እንዲሠሩ ለማድረግ የሚሠራ ሥራ ነው፡፡ በመሠረቱ ለኅብረተሰቡ የማኅበራት ብዛት ሳይሆን የአገልግሎት አሰጣጡ መሸሻልና ተደራሽነት እንዲኖርለት እንጂ፣ የማኅበራት እንደ አሸን መፍላት የሚሰጠው ጥቅም የለም፡፡ የማኅበራት ብዛት የሚጠቅመው አደራጅ መሥሪያ ቤት ለቲፎዞነት መጠቀሚያ መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡

  • ላይ ላይ በአሁኑ ጊዜ ተጠቃሚ የሚሆኑት ሕገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙ ጥቂት የማኅበር አመራር አካላትና እነርሱን ደግፈው ሕገወጥ ድርጊት ተፈጻሚ የሚያደርጉ አስፈጻሚ አካላት ብቻ ናቸው፡፡ አብዛኛው ባለሀብት በሀብቱ ተጠቃሚ ያልሆነበት፣ በሕጋዊ መንገድ ሠርቶ ለመጠቀም ያልቻለበት፣ በግለሰብ ሀብት ተጠቃሚ የሆኑ ጥቂት ግለሰቦች የከበሩበትና የነገሡበት ዘርፍ ሲሆን፣ ባለሀብቱ በባንክ ዕዳ ለገዛቸው ተሽከርካሪዎች ዕዳውን ለመመለስ አለመቻው እየታየ፣ ይህንን አሠራር እያየ ለማስተካከል ያልፈለገ አስፈጻሚ አካል ያለበት ተቋም ነው፡፡          

ግንኙነትን በተመለከተ

ይህንን ዘርፍ የሚመራው ተቋም አገልግሎትን ከሚሰጠው የኅብረተሰብ ክፍል ጋር ያለበትን ችግር ምን እንደሆነ ነቅሶ ለማውጣትና መፍትሔ ለመስጠት እንዲያስችለው፣ ከኅብረተሰቡ ጋር ምንም ዓይነት የግንኙነት መድረክ ፈጥሮ አያውቅም፡፡ ብዙ ጊዜ እንደሚታየው ጥቂት ባለድርሻ አካላት የተባሉትን በዕውቅና እከሌ ማኅበር እኔን ይደግፋል ከሚል ስሜት በመነጨ ስብሰባ በመጥራት፣ የቀረበውን ሪፖርት አዳምጦ ብቻ እንዲወጣ ይደረጋል፡፡ የባለድርሻን ተሳትፎና ገንቢ ሐሳብ ከመቀበል ይልቅ በጠላትነት መፈረጅ፣ ስለትራንስፖርት አገልግሎት አሰጣጥ ከኅብረተሰቡ በተለያዩ የሚዲያ ተቋማት የሚቀርቡ ትችቶችን፣ ብሶቶችንና ሮሮዎችን አዳምጦ በትክክለኛው ጊዜና ወቅት በሚዲያ ወይም ኅብረተሰቡ ሊያገኛቸው በሚችሉ የመገናኛ ዘዴዎች በመቅረብ መፍትሔ ያለመስጠት ችግር አለ፡፡

  • ወቅት በባለድርሻ አካላት የሚያቀርቡትን ሐሳቦች ለይምሰል ብቻ በመቀበል፣ በተግባር ግን ባለመፈጸም የሚቀርቡትን ሐሳቦች በተሻለ ሐሳብ መመከትና ማሳመን ሲቻል፣ ወይም የተሻለ ሐሰብ ከሆነ ተቀብሎ ወደ መሬት ማውረድ ሲኖርበት፣ ሐሳብን በነፃነት የመግለፅና የመናገርን መብትን በመንፈግ ስድብና ዛቻ ማስፈራራት ይዳረጋል፡፡ ሌላው ባለድርሻ አካል በመሸማቀቅ ሐሳብን እንዳይገልጽ ማድረግ አለ፡፡ የወጡ ሕጎች፣ ደንቦችና መመርያዎች በሁሉም ክልሎች ተፈጻሚ ስለመሆናቸው፣ በአፈጻጸም ወቅት ያጋጠሙ ችግሮችን ነቅሶ በማውጣት የማሻሻል ዕርምጃ ለመውሰድ የመስክ ምልከታ አለማድረግ ይታያል፡፡

የባለሥልጣኑ መሥሪያ ቤትን አሠራሩን እንዲያስተካከል፣ ሕግና ደንብን አክብሮ እንዲሠራ ሁሉንም ባለድርሻ አካላት እኩል ተመልክቶ ፍትሐዊ ውሳኔ እንዲሰጥ በተለያዩ የስብሰባ መድረክ ላይ እየተገኙ ተጨባጭ የሰላ ትችትና ገንቢ የሆነ አስተያትና ሐሳብ የሚያቀርቡ፣ ትክክል አይደለህም ብለው ተጨባጭ እውነታን የሚያቀርቡ አካላት ላይ ሥራ አስኪያጅ ከሆነ እንዲባረር በቦርዱ በኩል ከፍተኛ ግፊት ይደረጋል፡፡ አመራር አካል ከሆነም ከማኅበሩ የአመራር እንዲወርድ የተለያዩ ሥልቶች ይነደፋሉ፡፡ ወይም አባላቱ ከማኅበሩ ወጥተው ወደ ሌላ ማኅበር እንዲገቡ ይህ ካልሆነ ሌላ ማኅበር እንዲያቋቁሙ ይዳረጋል፡፡ ማኅበሩ እንዲዳከምና አቅም እንዳይኖረው ይደረጋል፡፡ ይህ ካልተሳካ ደግሞ ማኅበሩ በሕጋዊ መንገድ ያገኛቸው የነበሩትን ጥቅማ ጥቅሞች እንዳያገኝ በማድረግ፣ አባላቱን በሆነ ባልሆነው በመቅጣት ተማረው ማኅበሩን ለቀው እንዲወጡ ይደረጋል፡፡ በተጓዳኝ የማኅበራት የእርስ በርስ ግንኙነት ተጠናክሮ ወደ ተሻለ አደረጃጀት እንዳይመጡ እርስ በርስ በመከፋፈል፣ ዘርፉ በዚህ በደካማ አደረጃጀት እንዲቀጥልና ያሉ ብልሹ አሠራሮች ትኩረት እንዳያገኙ ይፈልጋሉ፡፡ ስለሆነም በማኅበራትና በአደራጅ አካላት መካከል ያለው ግንኙነት ወጥ ያልሆነና በደጋፊና በተቃዋሚ ጎራ ተከፍሎ የሚታይ አስመስሎታል፡፡

ማጠቃለያ

የትራንስፖርት ዘርፍ ለአገሪቱ ቁልፍ የአገልግሎት ዘርፍ በመሆኑ በጠራ አደረጃጀትና ብቃት፣ የተሻለ ክህሎት ባላቸው አመለካከታቸውና አስተሳሰባቸው በዳበረ አመራርና ባለድርሻ አካላት ሊመራ ይገባዋል፡፡ ስለሆነም በቀጣይ ሁለተኛው የአገሪቱ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ አፈጻጸም ላይ በዘርፉ በኩል የሚጠበቁ የማኅበራት አደረጃጀት ተሻሽሎ፣ የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግሮች ሙሉ በሙሉ ተቀርፈው፣ የሕገወጥ የሥምሪት እንቅስቃሴ በማያዳግም ሁኔታ እንዲቆም ተደርጎ፣ የአደራጁ አካላትና በአዲስ መልክ የሚደራጅ ማኅበራት የእርስ በርስ ግንኙነት ለዘርፉ ዕድገትና ለአገሪቱ ታላቅ ዕቅድ ተፈጻሚነት እጅ ለእጅ ተያይዘው እንዲንቀሳቀሱ፣ የመረጃ አያያዝና የሪፖርት አላላክ ሲስተሙ በተጠናከረ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደገፈና ተዓማኒነት ያለው እንዲሆን ያስፈልጋል፡፡

ባለሀብቱ ለፍቶ ባገኘው ንብረት የበይ ተመልካች ሳይሆን፣ በእርሱ ሀብትና ንብረት ላይ በኮንትራት፣ በመደበኛ መስመርና በሌሎች ከሚያገኘው ገቢ ላይ እየቀነሱ የግል ተጠቃሚ ሆነው ሳይለፉ፣ ሳይደክሙና ሳይወርዱ የበለፀጉ ጥቂት ግለሰቦች ተወግደው፣ ባለሀብቱ በንብረቱ በአግባቡ ተጠቃሚ ሊሆን የሚችልበት የአሠራር ሥርዓት መዘርጋት አለበት፡፡ በአጠቃላይ ባለሀብቱ በሌላ ሦስተኛ ወገን እየተመራ ሳይሆን፣ ወደ ዘርፉ ሲገባ ትክክለኛ መረጃና ተጨባጭ እውነታዎችን አውቆ እንዲገባ ይደረግ፡፡ የትራንስፖርት ተጠቃሚውን ኅብረተሰብ እርካታ በማምጣት ባለሀብቱ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፣ በአኅጉር አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ጥራት፣ ምቾትና ደኅንነቱ የተጠበቀ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት እንዲቻል የሁሉም ፍላጎትና ምኞት በመሆኑ፣ የሚመለከተው የመንግሥት አካል በተቋሙ ላይ ሥር ነቀል ለውጥ በማምጣት ሁለተኛው የዕድገትና ትራስፎርሜሽን እቅድ በተግባር ተተርጉሞ መታየት አለበት፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እየገለጽን፣ ጸሐፊውን በኢሜይል አድራሻቸው [email protected] ማግኘት ይቻላል፡፡

 

 

   

   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...