Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የንግድ ትርዒት ዋጋ ንረት ተመራጭ ያደረገው ጃንሜዳ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከተማ  በቋሚነት የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮች የሚስተናገዱበት ብቸኛ ሥፍራ አለ ከተባለ የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ዋናው ተጠቃሽ ነው፡፡ ማዕከሉ ግን አንድ የንግድ ትርዒት ዝግጅት ሊያሟላ የሚገባውን ያህል መሠረተ ልማት ይጎድለዋል፡፡ እያደገ ካለው የንግድ ትርዒቶች የዝግጅት ፍላጐት አንፃር በቂ  ሥፍራም የለውም፡፡

አማራጭ ስለሌለ በአዲስ አበባ ከተማ የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮችን ለማካሄድ ሲታሰብ ይህንኑ ብቸኛ ማዕከል መጠቀም ግድ ይላል፡፡ በማዕከሉ በየዓመቱ ከ45 በላይ በተለያዩ ዘርፎች የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮች ይካሄዳሉ፡፡ በተለይ እንደ ዘመን መለወጫ፣ የገናና የፋሲካ በዓላትን ተንተርሰው የሚዘጋጁ የንግድ ትርዒቶች በርካታ ጐብኚዎችና የንግድ ተቋማት የሚሳተፉባቸው እንደሆኑ ይታወቃል፡፡

 በንግድ ትርዒት ዝግጅት ሥራ ላይ የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶችም ከእነዚህ በዓላት ጋር በተገናኘ የንግድ ትርዒቶቻቸውን ለማዘጋጀት በብርቱ ይፎካከራሉ፡፡ ለዚህም ነው ከ15 እስከ 20 ቀናት ማዕከሉን ለመጠቀም የሚካሄደው ጨረታና ዋጋው በየዓመቱ ከልክ በላይ እየጨመረ የመጣው፡፡ ከአሥር ዓመታት በፊት ለአንድ የበዓል ዝግጅት የኤግዚቢሽንና የባዛር ማዕከሉን ለመጠቀም ከአንድ ሚሊዮን ብር ያልበለጠ ዋጋ ይቀርብ ነበር፡፡ በዚህ ወቅት ግን ከአሥር ሚሊዮን ብር በላይ አሻቅቧል፡፡ ከወራት በፊት የ2008 ዓ.ም. የገናና የፋሲካ በዓላትን ለማዘጋጀት በተካሄደው ጨረታ ለፋሲካው ዝግጅት ብቻ ማዕከሉን ለመጠቀም አሸናፊ የሆነው ኩባንያ 12.6 ሚሊዮን ብር ሰጥቷል፡፡ ይህ ዋጋ ምንም ዝርዝር ሐተታ ሳያሻው የንግድ ዝግጅቶች እየጠየቁ ያለው ወጪ በከፍተኛ መጠን እየጨመረ መምጣቱን ጠቋሚ ነው፡፡ ማዕከሉ ከ15 እስከ 20 ቀናት ብቻ ለሚቆየ ዓውደ ርዕይ የሚቀርብለት ዋጋ በእርግጥ ትክክለኛ የገበያ ዋጋ ነው ወይ? የሚለው ጉዳይ በቂ መልስ ይሻል፡፡ የዋጋ ጭማሪው በበዓላት የንግድ ትርዒቶች ላይ ምርቶቻቸውን ለመሸጥና ለማስተዋወቅ የሚሳተፉ ድርጅቶች ላይ ጫና ማሳደሩ አልቀረም፡፡

የኪራይ ዋጋ በጨመረ ቁጥር ጭማሪው በተሳታፊ የንግድ ትርዒቶች ላይ ያርፋል፡፡ እነሱም ለሽያጭ የሚያቀርቡት ሸቀጥ ዋጋ ላይ ይጭኑታል፡፡ በሒደቱ መጨረሻ የዋጋ ንረቱ ሸክም ሸማቹ ላይ ያርፋል፡፡ በንግድ ትርዒቶች ላይ የመሳተፍ ባህል እያደገ በመሆኑ የቱንም ያህል ዋጋ ቢጨምር የኩባንያዎች ቁጥር ግን እንዳልቀነሰ ይነገራል፡፡ እንዲያውም ፍላጐቱና የማዕከሉ የመያዝ አቅም አልጣጣም በማለቱ እንጂ በእነዚህ ሦስት በዓላት ዝግጅት ወቅት የመሳተፍ ዕድል ከሚያገኙት ከ350 እስከ 400 የሚቆጠሩ ድርጅቶች በላይ ይሆን እንደነበርም ይታመናል፡፡ በበዓል ዋዜማ የንግድ ትርዒትና ባዛር ዝግጅት ሲነሳ ሴንቸሪ ፕሮሞሽን ቀዳሚ ሥፍራ ይይዛል፡፡ በተለያዩ የንግድ ትርዒቶችና ባዛር ዝግጅቶች ከ15 ዓመታት በላይ የቆየው ሴንቸሪ ፕሮሞሽን፣ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የበዓላት ዋዜማ የንግድ ትርዒቶችን ቀድሞ በመጀመርም ይጠቀሳል፡፡ ለንግድ ትርዒቶች እየተሰጠ ያለው ዋጋ አሳሳቢ እየሆነ በመምጣቱ ግን አማራጭ የንግድ ትርዒት ማካሄጃ ሥራዎች የግድ ማስፈለጋቸውን እያመለከተ እንደመጣ የሴንቸሪ ፕሮሞሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘውገ ጀማነህ ይገልጻሉ፡፡

ከአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ውጭ አማራጭ የንግድ ትርዒት ማዘጋጃ ሥፍራ ሊኖር ይገባል በሚል እምነት ጃንሜዳን ለዚህ አገልግሎት ለማዋል ኩባንያው ዝግጅት እያደገ ነው፡፡ ሴንቸሪ ፕሮሞሽን በ2008 በጀት ዓመት ስለሚያዘጋጃቸው የንግድ ትርዒቶችና ስለዝግጅቶቹ ይዘት ይፋ ለማድረግ ከአንድ ሳምንት በፊት ባዘጋጀው ፕሮግራም ላይ ይህንኑ አስታውቋል፡፡ የገናና የፋሲካ የንግድ ትርዒቶችን በጃንሜዳ ለማካሄድ ማቀዱንና ለዚህም እየተዘጋጀ እንደሚገኝ ይፋ አድርጓል፡፡ አማራጭ የንግድ ትርዒት ሥፍራው ተደርጎ ስለተመረጠው ጃንሜዳና በጥቅሉ ከንግድ ትርዒት ዝግጅቶች ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ ዳዊት ታዬ አቶ ዘውገ ጀማነህን አነጋግሯል፡፡

ሪፖርተር፡- ለንግድ ትርዒትና ባዛር ዝግጅት ጃንሜዳ መርጣችኋል? ለምን?

አቶ ዘውገ፡- ሴንቸሪ ፕሮሞሽን የአዲስ ዓመት፣ የገና እንዲሁም የፋሲካ በዓላትን ለበርካታ ዓመታት በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ሲያዘጋጅ ቆይቷል፡፡ ለምሳሌ የገና የንግድ ትርዒትና ባዛርን 24 ጊዜ፣ የፋሲካን 23 ጊዜ አዘጋጅቷል፡፡ 25ኛውን የገናና፣ 23ኛውን የፋሲካ የንግድ ትርዒትና ባዛሮችን ደግሞ ከአዲስ አበባ ኢግዚቢሽን ማዕከል ውጭ ለመጀመሪያ ጊዜ በጃንሜዳ ለማካሄድ ወስነናል፡፡ ለዚህም ምክንያት አለን፡፡ በቅርብ የተካሄዱ የበዓላት የንግድ ትርዒቶች ላይ በርካታ ድርጅቶች እየተሳተፉ አለመሆናቸውን ተገንዝበናል፡፡ በብዛት የገቡ መስሎን ነበር፡፡ ነገር ግን ቆየት ብለን ያወቅነው ነገር በንግድ ትርዒቶቹ ላይ ለመሳተፍ አለመቻላቸውን ነው፡፡ ለመሳተፍ ሲሄዱ ለቦታ የሚጠየቁት ዋጋ እየጨመረ በመሄዱ እንዳይሳተፉ አድርጓቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ወደ ጨረታው ተመልሰን ብንገባ እንኳ እየተጠየቀ ባለው ዋጋ ሳቢያ ደንበኞቻችን እኛም ጋር አይመጡም ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ዋጋው የግድ መስተካከል አለበት፡፡ አማራጮችም ሊኖሩ ይገባል ከሚል ነው አማራጭ ፍለጋ የገባነው፡፡

በማዕከሉ ያለው የጨረታ ዋጋ እያደገ ሄዷል፡፡ የ2008 የገናና የፋሲካ በዓል 12.6 ሚሊዮን ብር ሆኗል፡፡ ስለዚህ ይህንን ያህል ዋጋ እየተሰጠ በኤግዚቢሽን ማዕከል ውስጥ መሥራት አስቸጋሪ ነው፡፡ የጨረታ ዋጋው ከመስተካከል ይልቅ እየጨመረ መምጣቱ አሳሳቢ እንዲሆን አድርጐታል፡፡ ለደንበኞቻችንም የሚከብድ ነው፡፡

ስለዚህ አማራጭ መፈለግ ነበረብንና ከስድስት ወራት በላይ ንግድ ትርዒቱን ከማዕከሉ ውጭ ለማዘጋጀት  የሚመች አማራጭ ቦታ ስናፈላልግ ቆይተን ጃንሜዳን ለመጠቀም ወስነናል፡፡ በኤግዚዝበሽን ማዕከል ውስጥ የተሳታፊዎች ቁጥር እየጨመረ ሲመጣ ለመኪና ማቆሚያ ተብሎ የተከለለውን ቦታ ሁሉ ተሳታፊ ኩባንያዎች ምርቶቻቸውን እንዲያስተዋወቁበትና እንዲሸጡበት አድርገን ነበር፡፡ ስለዚህ አማራጭ የንግድ ትርዒት ማዘጋጃ ቦታ ስንፈልግ ከንግድ ትርዒቱ ማሳያ ሥፍራ በተጨማሪ እስከ 500 ተሽከርካሪዎችን ሊይዝ የሚችል መሆን እንዳለበት አቅደን ነበርና ይህንን ፍላጐታችንን ለማሟላትና ለዝግጅቱም ምቹ እንደሆነ ስላመንበት ጃንሜዳን ምርጫችን ሆኗል፡፡ ጃንሜዳ ከመረጥን በኋላ ቦታውን ለመጠቀም በርካታ ድርድሮች ተደርገው በመጨረሻ ላይ ተዋውለን ወደ ዝግጅት ገብተናል፡፡     

ሪፖርተር፡- ጃንሜዳ ሰፊ ነው፡፡ ለንግድ ትርዒቱ ዝግጅት ምን ያህል ቦታ አገኛችሁ?

አቶ ዘውገ፡- የተወሰነውን ቦታ ነው፡፡ በሁለቱ ዋና ዋና የጃንሜዳ መግቢያ በሮች ላይ ያለውን ሥፍራ ለመጠቀም ነው፡፡ በዚያ መሠረት ዲዛይን አድርገን ‹‹ሮድ ማፑንና›› አክቴክቼሪያል ዲዛይን ሠርተን ያቀረብነው ፕሮፖዛላችን ተቀባናይነት አግኝቷል፡፡ ነገር ግን ወደ ጃንሜዳ ለመግባት ከመወሰናችን በፊት ደንበኞቻችን አነጋግረንና በሐሳቡ ተስማምተው ግቡበት ስላሉን ጭምር ነው የመረጥነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል በበዓላት ዋዜማ ለሚዘጋጁ የንግድ ትርዒቶችና ባዛሮች እየተሰጠ ያለው የጨረታ ዋጋ እያደገ መምጣት ዋናው ተፅዕኖ ምንድነው?

አቶ ዘውገ፡- ከዚህ ቀደም የንግድ ትርዒት አዘጋጆች በጨረታ አሸንፈን ዝግጅቱን ስናደርግ የጨረታ ዋጋው የቱንም ያህል ከፍ ቢል በንግድ ትርዒቱ ተሳታፊ ኩባንያዎች ላይ ዋጋ አንጨምርም ነበር፡፡ የጨረታ ዋጋው ከፍ ሲልብን የማዕከሉን ቦታ ዋጋ በስፋት በመጠቀምና ስፖንሰሮች በሚያደርጉት ድጋፍ ጭምር ተሳታፊ ኩባንያዎች ላይ ዋጋ እንዳይጨምር ጥረናል፡፡ የጨረታ ዋጋው ከፍ እያለ መምጣት ሲጠነክር ግን በተሳታፊዎች ላይ የተወሰነ ጭማሪ ተደርጓል፡፡ እሱም በጣም አነስተኛ የሚባል ነው፡፡  ጭማሪው በዛ ከተባለ ከ500 እስከ 1000 ብር አይበልጥም፡፡ አሁን ግን  የመጡት ድርጅቶች ከቀድሞው የበለጠ ዋጋ እየተጠየቁ ነው፡፡ ይህንንም የሚያደርጉት ጨረታውን በከፍተኛ ዋጋ በማሸነፋቸው ነው፡፡ እኛም በአሥር ሚሊዮን ብር ጨረታ አሸንፈው እንዴት ሊያዋጣቸው ይችላል የሚል ሥጋት ነበረን፡፡ ነገሩ ሲታይ ግን ለጨረታው የተሰጠው ዋጋ ወደ ነጋዴው መሻገሩን ነው፡፡ ለምሳሌ እኛ አዘጋጅተን በነበረው የአዲስ ዓመትና የፋሲካ በዓል ዝግጅት አንድ ኩባንያ ከፍተኛ ዋጋ የከፈለው 24 ሺሕ ብር ነበር፡፡ አሁን ግን የማዕከሉ የጨረታ ዋጋ አሥር ሚሊዮን በመድረሱ 24 ሺሕ ብር ይከፈልበት የነበረ ቦታ ከ37 እስከ 40 ሺሕ ብር ገብቷል፡፡  ይህም አንድ ተሳታፊ ኩባንያ ላይ ከዚህ ቀደም ባልታየ ሁኔታ በአንዴ ወደ 15 ሺሕ ብር አካባቢ ጭማሪ እንዲያደርግ ይገደዳል ማለት ነው፡፡ በዚህን ያህል ልዩነት በአንዴ ነጋዴው ላይ ስትጨምርበት ከባድ ነው፡፡ በእርግጥ በዚህም ዋጋ ቢሆን የሚሳተፉ ይኖራሉ፡፡ ነገር ግን እኛ ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ በተለይ በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ እያሳደግን ያመጣናቸውና  በተመጣጣኝ ዋጋ ለኅብረተሰቡ የተለያዩ ምርቶችን ያቀርቡ የነበሩ በርካታ ደንበኞቻችን በዚህን ያህል ደረጃ ዋጋው ሲጨምር ከተሳትፎ ውጭ እየሆኑ መጡ፡፡ በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ባሉት የንግድ ትርዒቶች ላይ ሊገቡ አልቻሉም፡፡ የማይገቡት ደግሞ እኛ ስላላዘጋጀነው አይደለም፡፡ ዋጋው ስለጨመረ ነው፡፡ አሁን እየተሰጠ ባለው ዋጋ እኛ ጨረታውን አሸንፈን ብንገባ ለቦታ የሚደለደለው ዋጋ ከፍተኛ መሆኑ አይቀርም ነበር፡፡ ስለዚህ ዋጋው እንዲህ እየጨመረ በመጣ ቁጥር እኛም ደንበኞቻችንን እያጣን እንሄዳለን፡፡ ስለዚህ ከኤግዚቢሽን ማዕከል ውጭ ተመሳሳይ ሥራ የሚሠራበት ቦታ ለምን አንፈልግም በማለት ጃንሜዳን መርጠናል፡፡

ኤግዚቢሽን ማዕከልም ቢሆን ከ15 ዓመታት በፊት ባዶ ነበር፡፡ በዚያን ወቅት 30 ድርጅቶች ይዘን የንግድ ትርዒት የጀመርነው እኛ ነን፡፡ ከ15 ዓመታት በላይ አብረውን የቆዩ ደንበኞቻችን ሳይቀሩ አማራጭ ቦታ ፈልጉ እያሉ ባሉበት ጊዜ በአማራጩ ቦታ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ከሆኑ ጃንሜዳንም በተመሳሳይ ጥሩ የንግድ ትርዒት ማሳያ ቦታ ማድረግ ይቻላል፡፡

ሪፖርተር፡- በእርግጥ አሁን አማራጭ የንግድ ትርዒት ቦታ ተብሎ የተመረጠውን ጃንሜዳ ለዝግጅቱ ምቹ ነው?

አቶ ዘውገ፡- ቦታው ማዕከል ነው፡፡ ከየትኛውም የከተማው ክፍል መምጣት የሚያስችል ነው፡፡ በርካታ ነዋሪዎች ያሉበትም አካባቢ ነው፡፡ ትላልቅ ዩኒቨርሲቲዎች የሚገኙበት ነው፡፡ ስለዚህ ለጐብኚዎች ምቹ ይሆናል፡፡ ይህ ሆኖ ግን ጐብኚዎችን የበለጠ ለመሳብ በየአቅጣጫው የአውቶብስ አገልግሎት ለማቅረብ አቅደናል፡፡ አሁን ባዘጋጀነው ቦታ እስከ 500 የጐብኚዎች ተሽከርካሪዎችን ማስተናገድ ይቻላል፡፡ ሰፊ የልጆች ማቆያ ቦታ አዘጋጅተናል፡፡ የአምቡላንስ፣ የድንገተኛ አደጋ ተሽከርካሪዎች ማቆሚያ ጭምር እንዲኖረው አድርገን ዲዛይኑን ሠርተናል፡፡

ሪፖርተር፡- በጃንሜዳ ለንግድ ለትርዒቱ ሲባል የምትገነቡት ነገር ይኖራል?

አቶ ዘውገ፡- ግቢው ትልቅ ነው፡፡ እኛ የተፈቀደልን የተወሰነው ክፍል ነው፡፡ ይህንን ክፍል ግን ከሌላው የጃን ሜዳ ክፍል ለመለየት መሃል ላይ ብቻ በቆርቆሮ እንከፍላለን፤ ሌላው ክፍል ግን ዙሪያው ግንብ ነው፡፡ ሁለቱን ዋና ዋና በሮች እንጠቀማለን፡፡

ሪፖርተር፡- ጃንሜዳ ለንግድ ትርዒት የሚሆን ምንም ዓይነት መሠረተ ልማት የሌለው ቦታ ነው፡፡ ቦታውን ለንግድ ትርዒቱ ምቹ ለማድረግ ምን ታደርጋላችሁ?

አቶ ዘውገ፡- ቦታውን ዲዛይን አድርገናል፡፡ ኤግዚቢሽን ማዕከል እንደሚተክሉት ዓይነት ትልልቅ ሳሎኖች ይተከላሉ፡፡ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ባሉት አዳራሾችም እኮ አነስተኛ ተሳታፊዎችን ነው የምንይዘው፡፡ አብዛኛው ከአዳራሽ ውጭ ነው፡፡ ሦስቱ የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን አዳራሾች ግፋ ቢል 160 ተሳታፊዎችን ቢይዙ ነው፡፡ ከአዳራሹ ውጪ ግን ከ300 በላይ ተሳታፊዎች ይይዙታል፡፡ በጃንሜዳም ከአዳራሽ ውጪ ባለው ቦታ በጥሩ ሁኔታ በተሠራ ዲዛይን እናዘጋጅላቸዋለን፡፡ ሌሎች ለዝግጅቱ ምቹነት መሟላት ያለባቸውን ሁሉ እናሟላለን፡፡ የኃይል አቅርቦት ቢቋረጥ እንኳ የራሳችንን ጄኔሬተር ለመጠቀም ተዘጋጅተናል፡፡ በኤግዚቢሽን ማዕከል ግቢ ውስጥ እንደምንገነባው ዓይነት በጃንሜዳ እንገነባለን ማለት ነው፡፡ የምንተክላቸው ሳሎኖች ግን ጊዜያዊ ናቸው፡፡

ሪፖርተር፡- በጃንሜዳ የምታዘጋጁት ኤግዚቢሽን መቼ ይካሄዳል?

አቶ ዘውገ፡- በጃንሜዳ የመጀመሪያውን የንግድ ትርዒት የምናካሂደው ከታኅሳስ 15 እስከ 27 ቀን 2008 ዓ.ም. ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ጃንሜዳን እንዴት አገኛችሁት? ከማን ጋር ተዋዋላችሁ?

አቶ ዘውገ፡- ጃንሜዳ የራሱ አስተዳደር አለው፡፡ የስፖርት ማዕከል የሚባል አለ፡፡ ከእሱ ጋር ተዋዋልን፡፡ እንደማንኛውም ከንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ መውሰድ ያለብንን ፈቃድ ወስደናል፡፡

ሪፖርተር፡- ቦታውን ለመጠቀም ምን ያህል ክፍያ ትፈጽማላችሁ?

አቶ ዘውገ፡- በ1992 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ስንገባ ንግድ ትርዒቱን ለማስለመድ ቦታውን በነፃ ወስደን ነው የሠራነው፡፡ አምስት ዝግጅት ስናዘጋጅ ከሚገኘው ገቢ ከማዕከሉ ጋር ተካፍለን ነው፡፡ እዚህም እንዲህ መሆን ነበረበት፡፡ ነገር ግን ስፖርት ማዕከሉ ገቢ ስለሚፈልግ ከ200 ሺሕ ብር በላይ እንከፍላለን፡፡ በውላችን መሠረትም በየዓመቱ በትንሹ 25 በመቶ እየጨመርን ለመሄድ ነው የተስማማነው፡፡ ኮንትራቱም በየዓመቱ የሚታደስ ሆኖ ለአምስት ዓመት የሚቆይ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ሴንቸሪ ፕሮሞሽን በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የንግድ ትርዒቶችን በመጀመር የሚጠቀስ ነው፡፡ በማዕከሉ ብዙ ሥራ ሲሠራም ቆይቷል፡፡ ከዚህ በኋላ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል አትሠሩም ማለት ነው?

አቶ ዘውገ፡- አይደለም፡፡ ቅድም እንደገለጽኩትም በዚህ ዓመት በኤግዚቢሽን ማዕከሉ የምናዘጋጃቸው የተለያዩ የንግድ ትርዒቶች አሉ፡፡ ከአንድ ሳምንት በፊት የድርጅታችንን የ2008 በጀት ዓመት ዕቅድ በሒልተን ሆቴል ስናስተዋውቅ እንደገለጽነው የጃንሜዳው ዝግጅት በአማራጭ የሚሠራበት ነው፡፡ ከሦስቱ የበዓላት ንግድና ባዛር ዝግጅት ውጪ ጨረታ የማይካሄድባቸውን ሌሎች ኤግዚቢሽኖቻችንን በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ነው የምናካሂደው፡፡ በ2008 በጀት ዓመት ሦስት ወይም አራት የንግድ ትርዒቶችን በኤግዚቢሽን ማዕከል እናካሂዳለን፡፡ ለምሳሌ ከቢጂአይ ኢትዮጵያ ጋር በጥቅምት ወር የምናካሂደው የንግድ ትርዒት አለ፡፡ አቋርጠነው የነበረው የኮንስትራክሽን ኤግዚቢሽናችንንም በኤግዚቢሽን ማዕከል የምናደርገው ነው፡፡ እነዚህ ስፔሻላይዝድ የንግድ ትርዒቶች ስለሆኑ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የምናካሄዳቸው ናቸው፡፡ ስለዚህ በማዕከሉ የምናዘጋጃቸውን ትርዒቶች እንቀጥልባቸዋለን፡፡ ጃንሜዳ መሥራት እንደሚቻል ለማሳየትም ነው እንጂ በኤግዚቢሽን ማዕከል ዋጋዎች ከተስተካከሉ መጫረታችንን ይቀጥላል፡፡

ከዚህ ቀደም ተሳታፊ ደንበኞቻችን እየወጣ ያለው የጨረታ ዋጋ ወደ ተሳፊዎች እንዳይሄድ እየተነጋገርን ሠርተናል፡፡ እነሱ እስከተቀበሉ ድረስ እኛም ሄደናል፡፡ አሁን ግን የሚቻል ስላልሆነ ነው አማራጭ ውስጥ የገባነው፡፡ አሁን እንዳየነው ከአዳራሽ ውጭ ቦታ ይይዙ የነበሩ ድርጅቶች ዋጋው ስለጨመረባቸው አልተሳተፉም፡፡ ስለዚህ በዘርፉ ጀማሪ ሆነን እንደሠራነው ሁሉ አማራጭ ሲፈለግም ከእኛ ይጠበቃል፡፡ ዋጋው ከወረደ እንሳተፋለን፡፡ ከዚህ በፊትም አድርገናል፡፡ ከተስተካከለ ደግሞ በሁለቱም ቦታ ማዘጋጀት ይቻላል፡፡ ጃንሜዳ መግባት ማለት ማዕከሉን ለቀን ወጣን ማለት አይደለም፡፡ እኛ እኮ የጨረታ ዋጋው እያደገ በመምጣቱ ለረዥም ጊዜ መሥራት አለመቻላችንና ዋጋው እያደገ ሲሄድ አማራጭ መፈለጋችን ነው፡፡

 

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች