Wednesday, March 22, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የጃፓን የውጭ ንግድ ተቋም ጽሕፈት ቤቱን እዚህ እንደሚከፍት ይፋ አደረገ

- ማስታወቂያ -

ተዛማጅ ፅሁፎች

በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት (ተመድ) ጉባዔ ላይ የተገናኙት የኢትዮጵያና የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትሮች በውይይታቸው ወቅት፣ የጃፓን የውጭ ንግድ ድርጅት (ጄትሮ) በኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤቱን እንደሚከፍት ይፋ ተደረገ፡፡ ድርጅቱ ለበርካታ ጊዜያት እዚህ ጽሕፈት ቤቱን የመክፈት ፍላጎት እንዳለው ሲገልጽ መቆየቱ ይታወቃል፡፡

የጃፓን ጠቅላይ ሚኒስትር አቤ ሺንዞ አምና በአዲስ አበባ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለ ማርያም ደሳለኝ የጃፓኑ የውጭ ንግድ ድርጅት ጽሕፈት ቤቱን እዚህ ይከፍት ዘንድ ጠይቀው እንደነበር፣ ከጃፓን ኤምባሲ የተገኘው መረጃ ይጠቁማል፡፡ ይህ ተቋም በአዲስ አበባ ጽሕፈት ቤቱን መክፈቱ የጃፓን ኩባንያዎች የኢንቨስትመንት ሥራዎችን ለማከናወን ሲፈልጉ እገዛ ለመስጠት ያለመ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮች በኒውዮርክ በተካሄደው የተመድ ጉባዔ ወቅት እግረ መንገዳቸውን ተገናኝተው መንግሥታዊውን የንግድ ተቋም በአዲስ አበባ ለመክፈት ስምምነት ቢያደርጉም፣ መቼና እንዴት እንደሚከፈት የሚገልጽ ዝርዝር መግለጫ እስካሁን አልወጣም፡፡ ይሁንና ሁለቱ ጠቅላይ ሚኒስትሮቹ በተነጋገሩበት ወቅት የቀረበው መግለጫ እንደሚጠቁመው፣ በሁለቱ አገሮች መካከል የንግድ ትስስርና ኢንቨስትመንት እንዲጠናከር ለማድረግ የሚያስችል ተቋም ቢሆንም፣ በአዲስ አበባ የሚገኘው ኤምባሲ በንግድና ኢንቨስትመንት መስክ ለመሥራት የሚያስችል አደረጃጀት እስካሁን እንደሌለው ታውቋል፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት በአብዛኛው በልማት ትብብር ላይ ያነጣጠረ ሆኖ ቆይቷል፡፡

የሁለቱ መንግሥታት መሪዎች ስምምነት ተግባራዊነቱ ወደፊት የሚታይ ቢሆንም፣ በጃፓናውያንና በኢትጵያውያን ባለሀብቶች መካከል የንግድ ትስስር ለመፍጠር የንግድ ድርጅቱ መከፈት ትልቅ ሚና እንደሚጫወት፣ በቅርበት ጉዳዩን የሚከታተሉ ሰዎች ይገልጻሉ፡፡ ይህ ተቋም በመሪዎቹ በተደረገው ውይይት መሠረት ጽሕፈት ቤቱን የሚከፍት ከሆነ፣ በርካታ የጃፓን ባለሀብቶችን ወደ ኢትዮጵያ ለማምጣት የሚረዳ ድልድይ ተደርጓል፡፡ ከዚህም ባሻገር በተለይ በሁለቱ ወገን በኩል የሚደረጉ የንግድ ልውውጦችን ለማሳደግም ትልቅ ትርጉም እንደሚኖረው ይነገርለታል፡፡

በጠቅላላው ጄትሮ ኢትዮጵያ ውስጥ በሚከፍተው ጽሕፈት ቤት አማካይነት የኢንቨስትመንት ሲምፖዚየሞችን ማካሄድ፣ የጃፓን የንግድ ልዑካንን ወደ ኢትዮጵያ መጋበዝ፣ በኢትዮጵያ በሚካሄዱ ዓለም አቀፍ ዓውደ ርዕዮች ላይ የጃፓን ሳሎን በማዘጋጀት መሳተፍ፣ እንዲሁም ወደ ጃፓን የሚላኩ ምርቶችን ጥራት ለማሻሻል ጃፓናውያን ባለሙያዎችን ወደ ኢትዮጵያ የማምጣት ተግባራትን እንደሚወጣ አስታውቋል፡፡ ይህም ሆኖ በጃፓንና በኢትዮጵያ መካከል ያለው የሁለትዮሽ የንግድ ግንኙነት በእጅጉ ዝቅተኛ ሲሆን፣ በአብዛኛውም ለጃፓን ያደላ ነው፡፡

በኢትዮጵያ እየንተቀሳቀሱ ከሚገኙ በጣት ከሚቆጠሩ የጃፓን ኩባንያዎች መካከል ሚትሱቢሺ የረጅም ጊዜ ቆይታ ያለው ነው፡፡ ማሩቤኒና ኢትዮ-ኒፖን የመሳሳሉት እስከ ደርግ መምጣት ጊዜ በኢትዮጵያ የንግድና የኢንቨስትመንት መስክ ጉልህ ድርሻ የነበራቸው ተቋማት ከነበሩት ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት የቶዮታና የኒሳን ኩባንያዎች የሚያመርቷቸውን ተሽከርካሪዎችን፣ ማሽነሪዎችንና መለዋወጫዎችን የሚያስመጡ የአገር ውስጥ ኩባንያዎች ለዚህ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ ጃፓኖች በአብዛኛው የቡና፣ የአበባና በተወሰነ ደረጃም የቆዳ ምርቶች ግብይት ከኢትዮጵያ ጋር ይፈጽማሉ፡፡

አምና ሥራ የጀመረውና የቆዳ ፋብሪካ በመክፈት ልዩ ልዩ የቆዳ ምርቶችን እዚህ በማምረት ወደ ጃፓን መላክ የጀመረው ሂሮኪ ኩባንያ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያ ውስጥ በጥቂቱም ቢሆን ኢንቨስት ያደረገ የመጀመሪያው ኩባንያ ሆኖ ተመዝግቧል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች