Tuesday, November 29, 2022
ሌሎች ዓምዶች
  - Advertisment -
  - Advertisment -

  ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ይገምገሙ!

  ኢትዮጵያ ውስጥ ወጣቶችን የማብቃት ከፍተኛ ኃላፊነት ያለባቸው ብዙዎቹ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ በሚፈለጉበት ደረጃ ላይ ሊገኙ ባለመቻላቸው ምክንያት መገምገም ይኖርባቸዋል፡፡ ብዙዎቹ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከተቋቋሙበት ዓላማ አንፃር በብቃት ተግባራቸውን እየተወጡ ነው? ወይስ በደመነፍስ ነው የሚንቀሳቀሱት? ተቀብለው የሚያስተምሯቸውን ወጣቶች እንዴት ነው እየቀረፁ ያሉት? ራሳቸውስ እንዴት ነው የሚመሩት? በአካባቢያቸው ከሚኖረው ኅብረተሰብ ጋር ያላቸው መስተጋብር ምን ይመስላል? ከሙስናና ከብልሹ አሠራር የፀዱ ናቸው? አካዴሚያዊ የምርምር ሥራዎችን በብቃት ያካሂዳሉ? አካዴሚያዊ ነፃነት አላቸው? ለጥራት የሚሰጡት ትኩረት እንዴት ነው? ብዙ ጥያቄዎች ማንሳት ይቻላል፡፡

  እንደሚታወቀው ያለንበት ወቅት የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ወጣቶች ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን የሚቀላቀሉበት ነው፡፡ እነዚህ ወጣቶች በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ዕውቀትን ሲቀስሙ አቅም በፈቀደ መጠን የተመቸ መኝታ፣ ምግብ፣ የፅዳት አገልግሎትና የትምህርት ቁሳቁሶችን ማግኘት አለባቸው፡፡ በተጨማሪም ደኅንነታቸው ተጠብቆ ከማናቸውም አደጋ ከሚያመጡ ተግባራት መጠበቅ አለባቸው፡፡ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማቱ ለወጣቶቹ የዕውቀት መቅሰሚያ ብቻ ሳይሆኑ፣ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ከሚመጡ አቻዎቻቸው ጋር በሰላምና በፍቅር የሚቆዩባቸው የኢትዮጵያ ትንሿ አምሳያ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ ወጣቶቹን ከማናቸውም ዓይነት አላስፈላጊ ተግባራት በማራቅ፣ ለጠብና ለጥላቻ በር የሚከፍቱ ተገቢ ያልሆኑ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ መከላከል አለባቸው፡፡ በዚህም ያሉበት ደረጃ መገምገም አለበት፡፡

  በአሁኑ ጊዜ ብዙዎቹ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት በርካታ የትምህርት ክፍሎችን ከፍተው የዕውቀት ገበያ ለመሆን ቢጣጣሩም፣ በርካታ ችግሮችን በውስጣቸው ተሸክመው ይጓዛሉ፡፡ በመጀመሪያ የትምህርት ተቋማቱ ዙሪያቸውን የከበቡዋቸው የጫትና የሺሻ ቤቶች፣ የመጠጥ ግሮሰሪዎችና የቁማር መጫወቻዎች ተጠቃሽ ናቸው፡፡ እነዚህ ወጣቱን ትውልድ በአደገኛ ሁኔታ በመመረዝ ላይ ያሉ የንግድ ተቋማት ለምን ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ እንዲወገዱ አይደረግም? ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚማሩ ወጣቶችን ዒላማ አድርገው የተከፈቱ እነዚህ ሕገወጥ ድርጅቶች ዝም የመባላቸው ሚስጥር፣ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቱን አመራሮች ጭምር ያስጠረጥራል፡፡ በዚህ ምክንያት መገምገም አለባቸው፡፡

  ሌላው ችግር ሙስናና ብልሹ አሠራር ናቸው፡፡ በፌዴራል ዋና ኦዲተር መሥሪያ ቤት ሁሌም ሪፖርት ከሚደረግባቸው መንግሥታዊ ተቋማት መካከል ተጠቃሾቹ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ናቸው፡፡ በግንባታ፣ በምርምርና በመሳሰሉት ወጪዎች ሒሳብ ማወራረድ አለመቻላቸውና ሙስና የሚሸቱ በርካታ ሕገወጥ ግዢዎችና ኮንትራቶች መፈጸማቸው በተደጋጋሚ ሪፖርት ተደርጓል፡፡ በሠራተኛ ቅጥር፣ ምደባ፣ ሹመት፣ ዝውውርና ስኮላርሺፕ ላይ የሚታዩ ዓይን ያወጡ አሳዛኝ ድርጊቶችም የብዙዎች ቅሬታ መነሻ ምክንያት ናቸው፡፡ በእንዲህ ዓይነት የዘቀጠ ተግባር ውስጥ የተሰማሩ የትምህርት ተቋማት እንዴት ትውልዱን ይቀርፃሉ? ይኼም በሚገባ መገምገም አለበት፡፡

  ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት የመልካም አስተዳደር አርዓያ መሆን ሲገባቸው፣ በተቃራኒው ብዙዎቹ ለተማሪዎቻቸው፣ ለመምህራኖቻቸውና ለድጋፍ ሰጪ ሠራተኞቻቸው ያላቸው አመለካከት የተዛባ ነው፡፡ አመራሮቻቸው የቡድንተኝነት ሰለባ ይሆኑና ሰዎችን በዘራቸው፣ በሃይማኖታቸው፣ በፖለቲካ አመለካከታቸውም ሆነ በፆታቸው ምክንያት በደል ያደርሱባቸዋል፡፡ በተለይ በአካባቢ ልጅነትና በጥቅም ግንኙነት ላይ የተመሠረተው ቡድንተኝነት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ገጽታ እያበላሸው ከመሆኑም በላይ፣ ከቁጥጥር ውጪ እየሆነ ብዙዎችን እየጎዳ ነው፡፡ የመማር ማስተማሩን ሒደትም እያደናቀፈ ነው፡፡ ይህ ዓይነቱ አደገኛ አካሄድ በጊዜ ካልታረመ ለአገር ጭምር አደጋ ነው፡፡ ይኼም ከሥር ከመሠረቱ ይገምገም፡፡

  በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ውስጥ ያለው ሌላው ትልቁ ችግር ጥራት ነው፡፡ በጥራት መጓደል ምክንያት የምትጎዳው አገር ናት፡፡ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ሚና በዕውቀት ላይ የተመሠረተ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ዕድገት ማስመዝገብ ቢሆንም፣ የብዙዎቹ ጥራት መጓደል አነጋጋሪ ከሆነ ቆይቷል፡፡ በጥናትና በምርምር በመታገዝ፣ የመምህራንን አቅም በማጎልበት፣ ከዘመኑ ጋር የማራመድ ቴክኖሎጂ ሽግግር በማከናወን፣ የትምህርት ዘርፎችን ከገበያው ጋር በማስተሳሰርና አገር በቀል ነባር ዕውቀቶችን በማካተት ጥራትን ለማምጣት ሙከራ ቢደረግም አመርቂ አይደለም፡፡ ሙሉ ጊዜንና ጉልበትን በመሰዋት ለጥራት ከመትጋት ይልቅ፣ ጊዜያዊ ነገሮች ላይ መሯሯጥ ስለሚበዛ የሚገኘው ውጤት ደካማ ነው፡፡ የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅዶችን አውጥታ ለምትጣጣር አገር አይመጥንም፡፡ ለአገርና ለሕዝብ ጥቅም ሲባል ግን ይህ የጥራት ጉዳይ ከፍተኛ ግምገማ ሊካሄድበት ይገባል፡፡

  ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከአካባቢያቸው ማኅበረሰብ ጋር ያላቸው ትስስር በሚገባ መፈተሽ አለበት፡፡ አገሪቱ ከድህነት ለመውጣት በምታደርገው ጥረት ውስጥ ተቋማቱም ማኅበራዊ ኃላፊነት ስላለባቸው ከማኅበረሰቡ፣ ከንግድ ኅብረተሰቡ፣ ከአርሶ አደሮች ወይም ከአርብቶ አደሮችና ከወጣቶች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ምን ይሠራሉ? የምርምር ውጤቶቻቸው ማኅበረሰቡ ዘንድ ይደርሳሉ? በተጨባጭ የተገኙ ውጤቶች አሉ? በዚህ በኩል ከተባራሪ ወሬ ያለፈ ሥራ ስለሌለ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ አንድ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ከማስተማር ባለፈ በተጨባጭ ለአካባቢው ማኅበረሰብ ብሎም ለአገሪቱ የሚጠቅም አስተዋጽኦ ማበርከት አለበት፡፡ የትምህርት ተቋማቱ በትምህርት፣ በምርምርና በትብብር ሥራዎች በአካባቢያቸው ምን እያከናወኑ እንደሆነ መገምገም አለበት፡፡

  ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ለአካዴሚያዊ ነፃነት በግንባር ቀደምትነት መቆም አለባቸው፡፡ ተማሪዎች፣ መምህራንና ሠራተኞች ሐሳባቸውን በነፃነት የመግለጽ መብታቸውን ተጠቅመው ለአገር የሚያበረክቱት አስተዋጽኦ መደገፍ አለበት፡፡ የተለየ አመለካከት ስላላቸው ብቻ መገለል የለባቸውም፡፡ መታፈን የለባቸውም፡፡ ዕድገትና ጥቅማ ጥቅም መነፈግ የለባቸውም፡፡ ከትምህርትም ሆነ ከሥራ መባረር የለባቸውም፡፡ አንድ መምህር በማስተማር ወቅትም ሆነ ሐሳቡን በሚያስተላልፍበት ጊዜ እነ እከሌን ያስደስታል፣ እነ እከሌን ያስቀይማል ተብሎ ነፃነቱ ሊገፈፍ አይገባም፡፡ ይልቁንም የትምህርት ተቋማት ከፖለቲካ ወገንተኝነት በተቻለ መጠን ፀድተውና ጠቀሜታ ከሌላቸው አወዛጋቢ ከሆኑ ጉዳዮች ታቅበው፣ ለዕውቀትና ለምርምር የሚጋብዙ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮችን በነፃነት ማንሸራሸር አለባቸው፡፡ ተማሪዎች፣ መምህራንና ሌሎች ሠራተኞች አላስፈላጊ በሆኑ ባህሪያቸውና በብቃታቸው ሊመዘኑ ይገባል እንጂ፣ በአመለካከታቸው ምክንያት ለመባረር፣ ለመታሰር ወይም ጥቅማቸውን ለማጣት መዳረግ የለባቸውም፡፡ ይህም ብርቱ ግምገማ ያስፈልገዋል፡፡

  በአጠቃላይ ሲታይ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ዜጎች በነፃነት የሚንቀሳቀሱባቸው፣ ለአገር ጠቃሚ የሆኑ ጉዳዮች የሚከናወኑባቸው፣ ወጣቱ ትውልድ የሚቀረፅባቸው፣ ጥራት ያለው ትምህርት የሚሰጥባቸውና መሰል ተግባራት የሚከናወኑባቸው የልቀት ማዕከላት ሊሆኑ ይገባል፡፡ ግልጽነት፣ ኃላፊነትና ተጠያቂነት የሌለባቸውና ማንም እንደፈለገ የሚፈነጭባቸው ከሆኑ ግን ከጠቀሜታቸው ይልቅ ጉዳታቸው ይብሳል፡፡ ትውልዱን ከመቅረፅ ይልቅ እንዲደነዝዝ የሚፈቅዱ ከሆነ መኖራቸው አይፈለግም፡፡ ምንም እንኳ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳዩ የመጡ ከፍተኛ ትምህርት ተቋማት እየታዩ ቢሆንም፣ በአመዛኙ ግን ጠንካራ ግምገማ የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ በአንዳንድ የትምህርት ተቋማት ውስጥ የሚታዩ ዘረኝነት፣ ቡድንተኝነት፣ ሙስና፣ ሕገወጥ አሠራሮችና ለመማር ማስተማር ሒደቱ ፈታኝ የሆኑ ድርጊቶች ከሥር መሠረታቸው ሊናዱ ይገባል፡፡ ለአገሪቱም ሆነ ለሕዝብ አይጠቅሙምና፡፡ በዚህም ምክንያት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መገምገም አለባቸው፡፡

  በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

  ‹‹ከገበሬው እስከ ሸማቹ ያለውን የንግድ ቅብብሎሽ አመቻቻለሁ›› ያለው ፐርፐዝ ብላክ ውጥኑ ከምን ደረሰ?

  ከመቼውም ጊዜ በላይ በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ በተደጋጋሚ የሚሰማ አንድ...

  ከመሬት ለአራሹ ወደ ደላላ የዞረው የመሬት ፖለቲካ

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ለመጀመርያ ጊዜ...

  ኢትዮጵያ በብድርና ዕርዳታ የምታገኘው ገንዘብ ለታለመለት ዓላማ እንዲውል ፓርላማው አሳሰበ

  በብድር የተገኘ ገንዘብ በሥልጠናና ውሎ አበል መልክ እንዳይባክን ተጠየቀ የሕዝብ...
  - Advertisment -

  ትኩስ ፅሁፎች

  በችግር የተተበተበው የሲሚንቶ አቅርቦት

  ሲሚንቶን እንደ ግብዓት ተጠቅሞ ቤት ማደስ፣ መገንባት፣ የመቃብር ሐውልት...

  ‹‹የናይል ዓባይ መንፈስ›› በሜልቦርን

  አውስትራሊያ ስሟ ሲነሳ ቀድሞ የሚመጣው በተለይ በቀደመው ዘመን የባህር...

  ‹‹ልብሴን ለእህቴ››

  ለሰው ልጅ መኖር መሠረታዊ ፍላጎት ተብለው ከተዘረዘሩት ውስጥ ልብስ...

  የአዲስ አበባ ትምህርት ቤቶች የምርመራ ውጤት እስከምን?

  በፍቅር አበበ የትምህርት ጥራትን፣ ውጤታማነትንና ሥነ ምግባርን ማረጋገጥ ዓላማ አድርጎ...

  ከመሬት ለአራሹ ወደ ደላላ የዞረው የመሬት ፖለቲካ

  ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) በአንድ ወቅት ለመጀመርያ ጊዜ...
  spot_img

  ተዛማጅ ፅሁፎች

  መንግሥት ለአገር የሚጠቅሙ ምክረ ሐሳቦችን ያዳምጥ!

  በሕዝብ ድምፅ የተመረጠ መንግሥት ለሕዝብ የሚጠቅሙ ሐሳቦችን የማዳመጥ ኃላፊነት አለበት፡፡ ሥራውን ሲያከናውንም በግልጽነት፣ በተጠያቂነትና በኃላፊነት መርህ መመራት ይኖርበታል፡፡ እያንዳንዱ ዕርምጃው በሕግ ከተሰጠው ኃላፊነት አኳያ...

  የሰላም ስምምነቱ ተግባራዊ ይደረግ!

  የሰላም ስምምነቱ ‹‹ታጥቦ ጭቃ›› ሊሆን የሚችልባቸው ምልክቶች እየተስተዋሉ ነው፡፡ ሚሊዮኖችን ለዕልቂት፣ ለመፈናቀል፣ ለከፍተኛ ሰብዓዊ መብት ጥሰትና መሰል ሰቆቃዎች የዳረገው አውዳሚ ጦርነት በፕሪቶሪያው ስምምነት መሠረት...

  ዘረፋ የሚቆመው በተቋማዊ አሠራር እንጂ በዘመቻ አይደለም!

  ኢትዮጵያ ውስጥ ሌብነት ከመንግሥት አቅም በላይ ሆኖ ለያዥ ለገናዥ ሲያስቸግር ከማየት በላይ አሰቃቂ ነገር የለም፡፡ በፌዴራል፣ በክልሎችና በከተማ አስተዳደሮች መረን የተለቀቀው ሌብነት አስነዋሪ መሆኑ...